ወደ ኋላ አትበሉ—ፕሮግራማችን የተጣበበ ቢሆንም ሁኔታችንን ማመቻቸት
1. አንዳንዶች ጥናት ከመምራት ወደ ኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?
1 አንዳንዶች ፕሮግራማቸው የተጣበበ በመሆኑ ጥናት ከመምራት ወደ ኋላ ይላሉ። ጥናት መምራት ጊዜ እንደሚጠይቅ አይካድም። ለጥናቱ መዘጋጀት፣ ጥናቱን መምራትና ተማሪው ለመንፈሳዊ እድገቱ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን እንዲወጣ መርዳት ጊዜ ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ያሉ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ሲል ነፍሱን ጭምር ለእነሱ እንዳካፈለ ገልጿል። (1 ተሰ. 2:7, 8) ታዲያ ፕሮግራማችን የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ጥናት መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጊዜያችንን የምንጠቀምበትን መንገድ የሚነካው እንዴት ነው?
2 አምልኮ ጊዜ ይጠይቃል፦ አምልኮን ማከናወን ጊዜ እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ለምሳሌ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በአገልግሎት ለመካፈል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እንዲሁም ለመጸለይ ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። አንድ ባለትዳር ፕሮግራሙ የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ከትዳር ጓደኛው ጋር ለመሆን የሚያስችለውን ጊዜ ለመመደብ በደስታ ፈቃደኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ታዲያ ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ እሱን ለማምለክ የሚያስችል ጊዜ ‘ለመግዛት’ ይበልጥ በደስታ ፈቃደኞች እንድንሆን ሊያነሳሳን አይገባም? (ኤፌ. 5:15-17፤ 1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ እንደተናገረው ከዋነኞቹ የአምልኳችን ክፍሎች አንዱ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ እውነታ ላይ ማሰላሰላችን ጥናት የመምራት ኃላፊነት ከመቀበል ወደ ኋላ እንዳንል ያደርገናል።
3. አንዳንድ ሁኔታዎች የአገልግሎት ፕሮግራማችንን ቢያስተጓጉሉብንም ጥናቶቻችንን በአግባቡ መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?
3 ፕሮግራማችን በሰብዓዊ ሥራ፣ ሥር በሰደደ የጤና ችግር ወይም በቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት ምክንያት ቢስተጓጎልስ? አልፎ አልፎ ካሉበት አካባቢ ርቀው የሚሄዱ አንዳንድ አስፋፊዎች በስልክ ወይም በኢንተርኔት ቪዲዮ አማካኝነት ጥናት ይመራሉ። ሥር በሰደደ የጤና ችግር ምክንያት ፕሮግራማቸው የተቃወሰባቸው አስፋፊዎች ደግሞ ጥናቶቻቸው ቤታቸው ድረስ እንዲመጡ ዝግጅት አድርገዋል። ሌሎች እነሱ በማይኖሩበት ጊዜ፣ ኃላፊነት የሚሰማው አስፋፊ ተክቷቸው ጥናታቸውን እንዲመራ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ምን በረከቶችን ያስገኛል?
4 ጳውሎስ ሌሎች እውነትን እንዲማሩ ለማድረግ ሲል ጊዜውንና ጉልበቱን መስጠቱ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። (ሥራ 20:35) በተሰሎንቄ በነበረበት ጊዜ ስለረዳቸው ሰዎች ቆም ብሎ ሲያስብ ይሖዋን ለማመስገን ተነሳስቷል። (1 ተሰ. 1:2) አዎን፣ የተጣበበ ፕሮግራም ያለን መሆኑ ጥናት ከመምራት ወደ ኋላ እንድንል የማያደርገን ከሆነ ከአገልግሎታችን የምናገኘው ደስታና እርካታ ይጨምራል።