የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ታኅሣሥ 2016
ከታኅሣሥ 5-11
it-2 761 አን. 3
እርቅ
እርቅ ለማግኘት ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች። ሕጉ የተጣሰበትና እየተጣሰበት ያለው ወገን እንዲሁም የተበደለው አምላክ ነው፤ በመሆኑም ከአምላክ ጋር መታረቅ የሚያስፈልጋቸው የሰው ልጆች ናቸው እንጂ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር መታረቅ አያስፈልገውም። (መዝ 51:1-4) አምላክ ከሰው ልጆች ጋር መደራደርም ሆነ የጽድቅ አቋሙን መለወጥ፣ ማረም ወይም ማሻሻል አያስፈልገውም። (ኢሳ 55:6-11፤ ሚል 3:6፤ ከያዕ 1:17 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም ለእርቅ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለድርድር የሚቀርቡ ወይም ለጥያቄ ክፍት የሆኑ አሊያም በስምምነት ሊለወጡ የሚችሉ አይደሉም። (ከኢዮብ 40:1, 2, 6-8፤ ኢሳ 40:13, 14 ጋር አወዳድር።) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኢሳይያስ 1:18ን “ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር” ብለው ተርጉመውታል (1954 ትርጉም)፤ ይሁን እንጂ ይበልጥ ተገቢ የሆነውና ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ጋር የሚስማማው አተረጓጎም “‘ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ’ ይላል ይሖዋ” የሚለው ነው። ለተፈጠረው አለመግባባት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሆኑት ሰዎች ናቸው እንጂ አምላክ አይደለም።—ከሕዝ 18:25, 29-32 ጋር አወዳድር።
ከታኅሣሥ 12-18
it-1 1219
ኢሳይያስ
ሌላኛው የኢሳይያስ ልጅ ስም የወጣለት ከመፀነሱ በፊት ነው፤ ስሙ በጽላት ላይ የተጻፈ ሲሆን ታማኝ የሆኑ ምሥክሮች ማረጋገጫ ሰጥተውበታል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ልጁ እስኪወለድ ድረስ ጉዳዩ በሚስጥር ተይዞ ነበር፤ ልጁ ከተወለደ በኋላ ምሥክሮቹ መጥተው ነቢዩ ስለ ልጁ መወለድ አስቀድሞ ትንቢት እንደተናገረ ይመሠክራሉ፤ ይህም ጉዳዩ ትንቢታዊ ትርጉም እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው። አምላክ ለልጁ ያወጣለት ስም ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ የሚል ሲሆን ትርጉሙም “ወደ ምርኮው ፈጥኖ መሄድ፣ ወደ ብዝበዛው ፈጥኖ መምጣት” የሚል ነው። ልጁ “አባዬ!” እና “እማዬ!” ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት ሶርያና አሥሩ የእስራኤል ነገድ በይሁዳ ላይ ያሴሩት ሴራ ይከሽፋል።—ኢሳ 8:1-4
ትንቢቱ ይሁዳ በቅርቡ እፎይታ እንደምታገኝ ይገልጻል፤ ደግሞም የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሄ በይሁዳ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ የአሦር ሠራዊት ጣልቃ በመግባት እንዲከሽፍ ሲያደርግ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። አሦራውያን ደማስቆን የተቆጣጠሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ማለትም በ740 ዓ.ዓ. የእስራኤልን መንግሥት በዝብዘዋል እንዲሁም አጥፍተዋል፤ በዚህ መንገድ የልጁ ስም የያዘው ትንቢታዊ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርገዋል። (2ነገ 16:5-9፤ 17:1-6) ንጉሥ አካዝ ግን በይሖዋ ከመታመን ይልቅ ለአሦር ንጉሥ ጉቦ በመስጠት ከሶርያና ከእስራኤል ጥቃት ለማምለጥ ሞክሯል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ አሦራውያን በይሁዳ ላይ ትልቅ ስጋት እንዲፈጥሩ ፈቅዷል፤ እንዲያውም ኢሳይያስ ባስጠነቀቀው መሠረት አሦራውያን እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ዘልቀው ገብተዋል።—ኢሳ 7:17-20