የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሐምሌ 2018
ከሐምሌ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 6-7
“በልግስና ስፈሩ”
(ሉቃስ 6:37) “በተጨማሪም በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ ፈጽሞ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትኮንኑ፤ እናንተም ፈጽሞ አትኮነኑም። ምንጊዜም ሌሎችን ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅር ትባላላችሁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 6:37
ምንጊዜም ሌሎችን ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅር ትባላላችሁ፦ ወይም “ምንጊዜም ሌሎችን በነፃ ልቀቁ፤ እናንተም በነፃ ትለቀቃላችሁ።” “ይቅር ማለት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ቃል በቃል “ነፃ ማውጣት፤ ማሰናበት፤ ነፃ መልቀቅ (ለምሳሌ እስረኛን)” የሚል ትርጉም አለው። እዚህ ጥቅስ ላይ በገባበት መንገድ፣ ከመፍረድና ከመኮነን ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ድርጊት የፈጸመን ሰውም እንኳ ነፃ መልቀቅን ወይም ይቅር ማለትን ያመለክታል።
መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ
13 ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ [“መፍረድ ተዉ፣” NW]” በማለት እንደተናገረ የማቴዎስ ወንጌል ይገልጻል። (ማቴ. 7:1) ሉቃስ እንደጻፈው ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አትፍረዱ [“መፍረዳችሁን ተዉ፣” NW]፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ።” (ሉቃስ 6:37) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎችን መሠረት በማድረግ በሌሎች ላይ ደግነት በጎደለው መንገድ ይፈርዱ ነበር። ኢየሱስን ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል እንዲህ የሚያደርጉ ካሉ ‘መፍረዳቸውን በመተው’ የሌሎችን ድክመት ‘ይቅር ማለት’ ነበረባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሐዋርያው ጳውሎስም ይቅር ማለትን በተመለከተ ተመሳሳይ ምክር ሰጥቷል።
14 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይቅር ባዮች መሆናቸው ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። ኢየሱስ “በምትፈርዱበትም ዐይነት ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል” ብሏል። (ማቴ. 7:2) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የምንዘራውን እናጭዳለን።—ገላ. 6:7
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 6:38
ስጡ፦ ወይም “መስጠታችሁን ቀጥሉ።” “መስጠት” ተብሎ ሊተረጎም የሚችለው እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ቀጣይ የሆነ ድርጊትን ያመለክታል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 6:38
በእቅፋችሁ፦ ወይም “በደረታችሁ።” የግሪክኛው ቃል በዚህ አገባቡ ሰፊ የሆነ መደረቢያ በመቀነት ሲታሰር ከመቀነቱ በላይ የሚተርፈውን እጥፋት ያመለክታል። በጥንት ዘመን የነበሩ ነጋዴዎች አንድ ገበያተኛ የገዛቸውን ነገሮች በዚህ እጥፋት ውስጥ የመሙላት ልማድ ነበራቸው፤ ‘ሰፍሮ በእቅፍ መስጠት’ የሚለው አገላለጽ ይህን ልማድ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 6:12, 13) በዚያው ሰሞን ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ። 13 በነጋ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ ከመካከላቸው 12 ሰዎች መረጠ፤ ሐዋርያት ብሎም ሰየማቸው፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦
እውነተኛ መንፈሳዊነት—እንዴት ልታገኘው ትችላለህ?
ኢየሱስ በአብዛኛው ረዘም ላለ ጊዜ ይጸልይ ነበር። (ዮሐንስ 17:1-26) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያቱ የሚሆኑትን 12 ሰዎች ከመምረጡ በፊት “ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ” የሚል ዘገባ እናገኛለን። (ሉቃስ 6:12) መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች የግድ ሌሊቱን ሙሉ ባይጸልዩም የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። በሕይወታቸው ውስጥ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት፣ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊነታቸውን ሊያሻሽል የሚችል ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳቸው ስለሚፈልጉ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ወደ አምላክ ይጸልያሉ።
(ሉቃስ 7:35) የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ተረጋግጧል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 7:35
በልጆቿ፦ ወይም “በውጤቷ።” እዚህ ላይ ጥበብ ልጆች እንዳሏት ተደርጋ በሰውኛ ዘይቤ ተገልጻለች። ተመሳሳይ ሐሳብ የያዘው የማቴ 11:19 ዘገባ ጥበብ “ሥራ” እንዳላት ይገልጻል። የጥበብ ልጆች ወይም ሥራዎች ማለትም መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ ያከናወኗቸው ነገሮች በእነሱ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች ሐሰት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ‘ማስረጃውን ማለትም የግለሰቡን የጽድቅ ሥራዎችና ምግባሩን ብትመለከቱ የተሰነዘረበት ክስ ሐሰት መሆኑን መገንዘብ ትችላላችሁ’ እያለ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 7:36-50) ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ደጋግሞ ለመነው። ስለሆነም ኢየሱስ ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37 እነሆም፣ በከተማው ውስጥ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ አንዲት ሴት ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት እየበላ መሆኑን በሰማች ጊዜ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች። 38 እሷም ከበስተ ኋላ እግሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር፤ ከዚያም በፀጉሯ አበሰችው። በተጨማሪም እግሩን እየሳመች ዘይቱን ቀባችው። 39 የጋበዘው ፈሪሳዊም ይህን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ ቢሆን ኖሮ የምትነካው ማን መሆኗንና ምን ዓይነት ሴት እንደሆነች ይኸውም ኃጢአተኛ መሆኗን ባወቀ ነበር” ብሎ በልቡ አሰበ። 40 ኢየሱስ ግን መልሶ “ስምዖን፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እሱም “መምህር፣ እሺ ንገረኝ” አለው። 41 “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ 500 ሌላው ደግሞ 50 ዲናር ተበድረው ነበር። 42 ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው ዕዳቸውን ሙሉ በሙሉ ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ ሰዎች አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?” 43 ስምዖንም መልሶ “ብዙ ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” አለው። እሱም “በትክክል ፈርደሃል” አለው። 44 ከዚያም ወደ ሴቲቱ ዞር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያታለህ? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ይሁንና አንተ ለእግሬ ውኃ አልሰጠኸኝም። ይህች ሴት ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ አበሰች። 45 አንተ አልሳምከኝም፤ ይህች ሴት ግን ከገባሁበት ሰዓት አንስቶ እግሬን መሳሟን አላቋረጠችም። 46 አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ ይህች ሴት ግን እግሬን ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ቀባች። 47 ስለዚህ እልሃለሁ፣ ኃጢአቷ ብዙ ቢሆንም ይቅር ተብሎላታል፤ ምክንያቱም ታላቅ ፍቅር አሳይታለች። በትንሹ ይቅር የተባለ ግን የሚያሳየውም ፍቅር አነስተኛ ነው።” 48 ከዚያም ሴትየዋን “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” አላት። 49 በማዕድ አብረውት የተቀመጡት በልባቸው “ኃጢአትን እንኳ ይቅር የሚል ይህ ሰው ማን ነው?” ይሉ ጀመር። 50 ኢየሱስ ግን ሴትየዋን “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
ከሐምሌ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 8-9
“የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?”
(ሉቃስ 9:57, 58) በመንገድ እየተጓዙም ሳሉ አንድ ሰው “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። 58 ኢየሱስ ግን “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” አለው።
it-2-E 494
ጎጆ
ከጸሐፍት አንዱ ወደ ኢየሱስ መጥቶ “መምህር፣ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” ባለው ጊዜ ኢየሱስ “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” በማለት መልሶለታል። (ማቴ 8:19, 20፤ ሉቃስ 9:57, 58) እዚህ ላይ ኢየሱስ ሰውየው ተከታዩ መሆን የሚፈልግ ከሆነ እንደ አብዛኞቹ ሰዎች የተደላደለና የተመቻቸ ሕይወት የመምራት ሐሳቡን ትቶ ሙሉ እምነቱን በይሖዋ ላይ መጣል እንዳለበት እየጠቆመው ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው የጸሎት ናሙና ላይ የሚገኘው “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን” የሚለው ሐሳብም ሆነ “ከእናንተ መካከል ያለውን ንብረት ሁሉ የማይሰናበት ፈጽሞ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” በማለት የተናገረው ሐሳብ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ያንጸባርቃል።—ማቴ 6:11፤ ሉቃስ 14:33
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 9:59, 60
አባቴን እንድቀብር፦ ይህ አገላለጽ በዚያ ወቅት የሰውየው አባት እንደሞቱና ሰውየው የአባቱን የቀብር ሥነ ሥርዓት ብቻ አስፈጽሞ ለመምጣት እየጠየቀ እንዳለ የሚጠቁም አይመስልም። ምክንያቱም እንዲህ ቢሆን ኖሮ ሰውየው እዚያ ከኢየሱስ ጋር እየተነጋገረ ይገኛል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ባሕል አንድ የቤተሰብ አባል ከሞተ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸመው ወዲያውኑ እንዲያውም በአብዛኛው በዚያኑ ቀን ነው። በመሆኑም የሰውየው አባት ሞተው ሳይሆን ታመው ወይም በዕድሜ ገፍተው ሊሆን ይችላል። ደግሞም ኢየሱስ ሰውየውን የታመሙና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን አባቱን ብቻቸውን ትቶ እንዲመጣ እንደማይጠይቀው የታወቀ ነው፤ ስለዚህ እንዲህ ያለውን አስፈላጊ ኃላፊነት የሚወጡ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሳይኖሩ አይቀሩም። (ማር 7:9-13) በተዘዋዋሪ መንገድ ሰውየው ‘ተከታይህ እሆናለሁ፤ ሆኖም አባቴ በሕይወት እስካለ ድረስ እንዲህ ማድረግ አልችልም። አባቴ ሞቶ ቀብሬ እስክመጣ ድረስ ታገሠኝ’ ያለ ያህል ነበር። በኢየሱስ አመለካከት ግን ይህ ሰው ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሕይወቱ ውስጥ ማስቀደም የሚችልበትን አጋጣሚ ወደጎን ገሸሽ እያደረገ ነበር።—ሉቃስ 9:60, 62
ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፦ ለሉቃስ 9:59 በተዘጋጀው ለጥናት የሚረዳ መረጃ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ያነጋገረው ሰው አባት፣ ሞተው ሳይሆን ታመው ወይም በዕድሜ ገፍተው መሆን አለበት። በመሆኑም ኢየሱስ ሰውየውን ‘በመንፈሳዊ የሞቱት ሰዎች ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው’ እያለው እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ በሌላ አነጋገር አባቱ ሞቶ እስኪቀበር ድረስ ሊንከባከቡት የሚችሉ ሌሎች ዘመዶች ስላሉ ሰውየው ውሳኔ ለማድረግ እስከዚያ ጊዜ ድረስ መጠበቅ እንደማያስፈልገው እየነገረው ነው። ይህ ሰው ኢየሱስን መከተሉ በአምላክ ፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ ሙታን ከሚታዩት ሰዎች ጎራ ወጥቶ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዝ እንዲጀምር ያስችለዋል። ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ አንድ ሰው በመንፈሳዊ ሕያው ሆኖ መቀጠል ከፈለገ በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን መንግሥት ማስቀደምና ስለዚህ መንግሥት በስፋት ማወጅ እንዳለበት ያሳያል።
(ሉቃስ 9:61, 62) አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፣ እኔ እከተልሃለሁ፤ በመጀመሪያ ግን ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። 62 ኢየሱስም “ዕርፍ ጨብጦ በኋላው ያሉትን ነገሮች የሚመለከት ሰው ለአምላክ መንግሥት የሚገባ አይደለም” አለው።
nwtsty ሚዲያ
ማረስ
አብዛኛውን ጊዜ እርሻ የሚታረሰው በመከር ወቅት ማለትም በበጋ ወራት የነበረው ፀሐይ ያደረቀው አፈር በዝናብ ከለሰለሰ በኋላ ነው። (ተጨማሪ መረጃ ለ15ን ተመልከት።) አንዳንዱ ማረሻ ከሹል እንጨት የተሠራ ሲሆን ጫፉ ላይ ብረት ሊደረግበት ይችላል፤ እንጨቱ ከሞፈሩ ጋር ከተያያዘ በኋላ በአንድ ወይም በሁለት እንስሳ ይጎተታል። መሬቱ ከታረሰ በኋላ ዘር ይዘራል። በስፋት ይታወቅ የነበረው የእርሻ ሥራ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ በምሳሌነት ተሠርቶበታል። (መሳ 14:18፤ ኢሳ 2:4፤ ኤር 4:3፤ ሚክ 4:3) ኢየሱስ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን ለማስረዳት ከግብርና ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ብዙ ጊዜ እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ በሙሉ ልብ የእሱ ደቀ መዝሙር የመሆንን አስፈላጊነት ለማጉላት እርሻ በሚታረስበት ወቅት የሚከናወንን አንድ ሥራ ጠቅሷል። (ሉቃስ 9:62) እያረሰ ያለ አንድ ገበሬ ከሥራው ትኩረቱ ከተከፋፈለ ቀጥ ያለ ትልም ሊያወጣ አይችልም። በተመሳሳይም አንድ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ትኩረቱ የሚከፋፈል ወይም ኃላፊነቶቹን ከመወጣት ዞር የሚል ከሆነ ለአምላክ መንግሥት የተገባ አይሆንም።
ይሖዋን በፍጹም ልባችሁ ማገልገላችሁን ቀጥሉ
11 ኢየሱስ ከሰጠው ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን እስቲ ምሳሌውን ሰፋ አድርገን እንመልከት። በእርሻው ላይ ተቀጥሮ የሚሠራው ሰው መሬቱን በማረስ ተግባር ተጠምዷል። ይሁንና ይህ ግለሰብ መሬቱን እያረሰ ሳለ ቤተሰቡ፣ ወዳጆቹ፣ ምግቡ፣ ሙዚቃውና ደስታው ወደ አእምሮው ይመጣሉ፤ እንዲሁም በፀሐይ ከመንቃቃት ጥላ ሥር አረፍ ማለት ያምረዋል። ይህ ሠራተኛ ለተወሰነ ጊዜ ካረሰ በኋላ እነዚህን ነገሮች የማግኘት ምኞቱ እያየለ በመሄዱ “በኋላው ያሉትን ነገሮች” ለማየት ይዞራል። ዘሩ እስኪዘራ ድረስ ገና ብዙ ሥራ ቢቀረውም ሐሳቡ በመከፋፈሉ ሥራው ተበድሏል። የእርሻው ባለቤት ሠራተኛው ተግባሩን በጽናት አለማከናወኑን ሲመለከት እንደሚያዝን የታወቀ ነው።
12 እስቲ አሁን ምሳሌውን በዘመናችን ከሚከሰት ሁኔታ ጋር እናነጻጽረው። ገበሬው በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ጥሩ ተሳትፎ የሚያደርግ ሆኖም መንፈሳዊ አደጋ ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ክርስቲያን ሊያመለክት ይችላል። ለንጽጽር እንዲያመቸን በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግን አንድ ወንድም ወደ አእምሯችን እናምጣ። ይህ ወንድም በስብሰባዎች ላይ የሚገኝ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት የሚካፈል ቢሆንም ማራኪ መስለው ስለሚታዩት ዓለም ስለሚያቀርባቸው አንዳንድ ነገሮች ማሰቡን ማቆም አልቻለም፤ በመሆኑም በልቡ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ይመኛል። ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሎቱን ሲያከናውን ከቆየ በኋላ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች የማግኘት ጉጉቱ በጣም እያየለ ስለሚሄድ “በኋላው ያሉትን ነገሮች” ለማየት ይዞራል። በአገልግሎቱ የሚያከናውነው ገና ብዙ ሥራ ቢኖርም ‘የሕይወትን ቃል አጥብቆ መያዙን’ አልቀጠለም፤ በዚህም የተነሳ ከቲኦክራሲያዊው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚያከናውነው ሥራ ይበደላል። (ፊልጵ. 2:16) “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” የሆነው ይሖዋ ከሠራተኞቹ አንዱ ሥራውን በጽናት እንዳላከናወነ ሲመለከት እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 10:2
13 ከምሳሌው የምናገኘው ትምህርት ግልጽ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች እንደመገኘትና በአገልግሎት እንደመካፈል ባሉ ጠቃሚና አስደሳች እንቅስቃሴዎች አዘውትረን መካፈላችን የሚያስመሰግን ነው። ይሁንና ይሖዋን በፍጹም ልብ ማገልገል ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። (2 ዜና 25:1, 2, 27) አንድ ክርስቲያን በልቡ ውስጥ ‘በኋላው ላሉ ነገሮች’ ማለትም ዓለም ለሚያቀርባቸው አንዳንድ ነገሮች ፍቅር ማሳደሩን ከቀጠለ በአምላክ ፊት ያለውን ጥሩ አቋም የማጣት አደጋ ያጋጥመዋል። (ሉቃስ 17:32) ‘ለአምላክ መንግሥት የምንገባ’ ሰዎች መሆን የምንችለው “ክፉ የሆነውን ነገር” ከልባችን የምንጸየፍ እንዲሁም “ጥሩ የሆነውን ነገር” አጥብቀን የምንይዝ ከሆነ ብቻ ነው። (ሮም 12:9፤ ሉቃስ 9:62) እንግዲያው ሁላችንም፣ የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው ማንኛውም ነገሮች ምንም ያህል ጠቃሚ ወይም አስደሳች መስለው ቢታዩንም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ ልብ ከማከናወን ወደኋላ እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም።—2 ቆሮ. 11:14፤ ፊልጵስዩስ 3:13, 14ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 8:3
ያገለግሏቸው ነበር፦ ወይም “ይደግፏቸው (የሚያስፈልጋቸውን ያደርጉላቸው) ነበር።” ዲያኮኔኦ የሚለው የግሪክኛው ቃል ምግብ ይዞ በመሄድ፣ በማብሰል፣ በማቅረብና የመሳሰሉትን ነገሮች በማድረግ የሌሎችን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላትን ሊያመለክት ይችላል። በሉቃስ 10:40 (“በብዙ ሥራ ተጠምዳ”)፤ በሉቃስ 12:37 (“ያስተናግዳቸዋል”)፤ በሉቃስ 17:8 (“አገልግለኝ”) እና በሥራ 6:2 (“ምግብ ለማከፋፈል”) ላይ ቃሉ በዚሁ መንገድ የተሠራበት ቢሆንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ለአንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ የሚቀርቡ ሌሎች አገልግሎቶች ሁሉ ሊያመለክት ይችላል። ይህ ጥቅስ በቁጥር 2 እና 3 ላይ የተጠቀሱት ሴቶች ለኢየሱስና ለደቀ መዛሙርቱ ድጋፍ በማድረግ አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የረዷቸው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። እነዚህ ሴቶች እንዲህ በማድረግ አምላክን ያከበሩ ሲሆን አምላክም የልግስና ተግባራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቆይና መጪው ትውልድ ሁሉ እንዲያነበው በማድረግ አድናቆቱን አሳይቷል። (ምሳሌ 19:17፤ ዕብ 6:10) ይኸው የግሪክኛ ቃል በማቴ 27:55፤ ማር 15:41 ላይም ከሴቶች ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል።
(ሉቃስ 9:49, 50) ዮሐንስም “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ይሁንና ከእኛ ጋር ሆኖ አንተን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። 50 ኢየሱስ ግን “የማይቃወማችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ስለሆነ አትከልክሉት” አለው።
የሉቃስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
9:49, 50—ኢየሱስ፣ በዚህ ዘገባ ላይ የተጠቀሰው ግለሰብ እሱን ተከትሎት ባይሄድም አጋንንት እንዳያስወጣ ያልከለከለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ግለሰቡን ያላስቆመው በወቅቱ የክርስቲያን ጉባኤ ስላልተቋቋመ ነበር። በመሆኑም ግለሰቡ በኢየሱስ ስም ለማመንም ሆነ አጋንንት ለማስወጣት ቃል በቃል ኢየሱስን ተከትሎ መሄድ አይጠበቅበትም ነበር።—ማር. 9:38-40
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 8:1-15) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ተጓዘ። አሥራ ሁለቱም ከእሱ ጋር ነበሩ፤ 2 በተጨማሪም ከክፉ መናፍስትና ከበሽታ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፦ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ 3 የሄሮድስ ቤት አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሴቶች የነበሩ ሲሆን በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር። 4 ኢየሱስም የየከተማው ሕዝብ ተከትሎት በመጣ ጊዜና እጅግ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ወቅት እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ 5 “አንድ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወድቀው ተረጋገጡ፤ የሰማይ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው። 6 አንዳንዶቹ ዓለት ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ እርጥበት ስላላገኙ ደረቁ። 7 ሌሎቹ ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ አብሯቸው ያደገውም እሾህ አነቃቸው። 8 ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወደቁ፤ ከበቀሉም በኋላ 100 እጥፍ አፈሩ።” ይህን ከተናገረ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። 9 ደቀ መዛሙርቱ ግን የዚህን ምሳሌ ትርጉም ጠየቁት። 10 እሱም እንዲህ አለ፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥሮች የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ ለቀሩት ግን በምሳሌ እነግራቸዋለሁ፤ ይኸውም እያዩ እንዳያስተውሉ እንዲሁም እየሰሙ ትርጉሙን እንዳይረዱ ነው። 11 እንግዲህ የምሳሌው ትርጉም ይህ ነው፦ ዘሩ የአምላክ ቃል ነው። 12 በመንገድ ዳር የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ከዚያ በኋላ ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። 13 በዓለት ላይ የወደቁት ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ ነገር ግን ሥር የላቸውም። ለጊዜው አምነው ቢቀበሉም በፈተና ወቅት ይወድቃሉ። 14 በእሾህ መካከል የወደቁት ቃሉን የሰሙ ናቸው፤ ሆኖም በዚህ ዓለም የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ሥጋዊ ደስታ ትኩረታቸው ተከፋፍሎ ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ፤ ለፍሬም አይበቁም። 15 በጥሩ አፈር ላይ የወደቁት ደግሞ ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በውስጣቸው በማኖር በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
ከሐምሌ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 10-11
“የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ”
(ሉቃስ 10:29-32) ሰውየው ግን ጻድቅ መሆኑን ለማሳየት ፈልጎ ኢየሱስን “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው። 30 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በዘራፊዎች እጅ ወደቀ፤ እነሱም ከገፈፉትና ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ሄዱ። 31 እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲወርድ ሰውየውን አየውና ራቅ ብሎ አልፎት ሄደ። 32 በተመሳሳይም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና ገለል ብሎ አልፎት ሄደ።
nwtsty ሚዲያ
ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚወስደው መንገድ
በዚህ አጭር ቪዲዮ ላይ የሚታየው መንገድ (1) በጥንት ዘመን የነበረውን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ የሚወስደውን ጎዳና ተከትሎ የሚሄድ ሳይሆን አይቀርም። ይህ መንገድ የይሁዳን ምድረ በዳ አቋርጦ ያልፍ ነበር። የጥንቱ መንገድ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ያለው ሲሆን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ቁልቁል እየተጠማዘዘ ይወርዳል፤ በሁለቱ ቦታዎች መካከል ያለው የከፍታ ልዩነት 1,000 ሜትር ገደማ ይሆናል። በዚህ ጭር ያለ ምድረ በዳ ውስጥ ብዙ ዘራፊዎች ከመኖራቸው የተነሳ መንገደኞችን የሚጠብቁ ወታደሮች ማስፈር አስፈልጎ ነበር። የሮም ግዛት የነበረችው ኢያሪኮ (2) የምትገኘው በይሁዳ ምድረ በዳ ጫፍ ላይ ነበር። የቀድሞዋ ኢያሪኮ (3) ደግሞ የሮማውያን ከተማ ከሆነችው ኢያሪኮ 2 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ትገኝ ነበር።
“ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”
14 ሁለተኛ፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሚናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ምሳሌውን መናገር ጀመረ፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።” (ሉቃስ 10:30) ኢየሱስ መልእክቱን ለማስጨበጥ በምሳሌው ውስጥ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ” የሚወስደውን መንገድ መጠቀም የፈለገው ሆን ብሎ ነው። ይህን ምሳሌ የተናገረው ከኢየሩሳሌም እጅግም በማትርቀው በይሁዳ ሆኖ ነው። ስለዚህም አድማጮቹ መንገዱን ጥሩ አድርገው የሚያውቁት መሆን አለበት። ይህ መንገድ በተለይ ለብቻው ለሚጓዝ ሰው በጣም አደገኛ ነው። መንገዱ ጠመዝማዛ በመሆኑ አድብተው ለሚዘርፉ ወንበዴዎች የተመቻቸ ነበር።
15 ኢየሱስ “ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ” ብሎ መናገሩ ሌላም ትኩረት የሚስብ ነገር አለው። በታሪኩ መሠረት በመጀመሪያ አንድ ካህን ቀጥሎም አንድ ሌዋዊ በዚያ መንገድ ያለፉ ሲሆን አንዳቸውም ቢሆኑ ጉዳት ለደረሰበት ሰው የእርዳታ እጃቸውን አልዘረጉም። (ሉቃስ 10:31, 32) ካህናት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሲሆን ሌዋውያን ደግሞ በሥራ ያግዟቸው ነበር። በኢያሪኮና በኢየሩሳሌም መካከል ያለው ርቀት 23 ኪሎ ሜትር ብቻ በመሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሥራ በማይኖራቸው ጊዜ ኢያሪኮ ይቀመጡ ነበር። በዚህም የተነሳ በዚያ መንገድ ላይ ካህን ወይም ሌዋዊ ሲያልፍ ማየት የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ካህኑም ሆነ ሌዋዊው የተነሱት ‘ከኢየሩሳሌም’ እንደሆነ ልብ በል። ስለሆነም ከቤተ መቅደሱ እየተመለሱ ነበር። በመሆኑም ‘ጉዳት የደረሰበትን ሰው ሳይረዱት የቀሩት የሞተ መስሏቸው ነው፤ ሬሳ መንካት ደግሞ ስለሚያረክስ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሰጡትን አገልግሎት ለጊዜውም ቢሆን ያስተጓጉልባቸው ነበር’ በማለት እነዚህ ሰዎች ላሳዩት ግዴለሽነት ማንም ማስተባበያ ማቅረብ አይችልም። (ዘሌዋውያን 21:1, 2፤ ዘኍልቍ 19:11, 16) ኢየሱስ ምሳሌውን የሚናገረው አድማጮቹ ከሚያውቁት ነገር ተነስቶ እንደነበር ይህ በግልጽ አያሳይምን?
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 10:33, 34
አንድ ሳምራዊ፦ በጥቅሉ ሲታይ አይሁዳውያን ሳምራውያንን ይንቋቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖራቸው አይፈልጉም ነበር። (ዮሐ 4:9) እንዲያውም አንዳንድ አይሁዳውያን “ሳምራዊ” የሚለውን አገላለጽ ንቀትንና ትችትን ለማሳየት ይጠቀሙበት ነበር። (ዮሐ 8:48) ሚሽና የተባለው የአይሁዳውያን ጽሑፍ አንድ ረቢ “የሳምራውያንን ዳቦ የሚበላ ሰው የአሳማ ሥጋ ከሚበላ ሰው ተለይቶ አይታይም” በማለት እንደተናገረ ይገልጻል። (ሼቢት 8:10) በርካታ አይሁዳውያን አንድ ሳምራዊ የሚሰጠውን ምሥክርነትም ሆነ የሚያቀርበውን አገልግሎት አይቀበሉም ነበር። ኢየሱስ አይሁዳውያን የነበራቸውን እንዲህ ያለውን የንቀት አመለካከት ያውቅ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ የደጉ ሳምራዊ ምሳሌ ተብሎ በሚጠራው በዚህ ምሳሌ አማካኝነት ጠንካራ ትምህርት አስተላልፏል።
በቁስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ በጨርቅ አሰረለት፦ እዚህ ላይ ሐኪሙ ሉቃስ ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ በጥንቃቄ የመዘገበ ሲሆን የሰውየው ቁስል የታከመበትን መንገድ በተመለከተ ያሰፈረው ዘገባ በዚያን ዘመን ቁስልን ለማከም ይሠራበት ከነበረው ዘዴ ጋር ይስማማል። ዘይትም ሆነ የወይን ጠጅ ማንም ሰው በቀላሉ ሊያገኛቸው የሚችላቸው ቁስልን ለማከም የሚያገለግሉ ነገሮች ነበሩ። ዘይት ቁስልን ለማለዘብ ወይም እንዳይደርቅ ለማድረግ ጥቅም ላይ ይውል ነበር (ከኢሳ 1:6 ጋር አወዳድር)፤ የወይን ጠጅ ደግሞ ቁስልን ለማጠብ የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ በተወሰነ መጠን በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን የመግደል ኃይል አለው። በተጨማሪም ሉቃስ ቁስሉ በጨርቅ እንደታሰረ ገልጿል፤ እንዲህ መደረጉ ቁስሉ እንዳይባባስ ይረዳል።
የእንግዶች ማረፊያ፦ የግሪክኛው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ለማንም ክፍት የሆነ ወይም ማንም የሚስተናገድበት ቦታ” የሚል ነው። መንገደኞችም ሆኑ እንስሶቻቸው እንዲህ ባሉ ቦታዎች ማረፊያ ማግኘት ይችሉ ነበር። የእንግዶች ማረፊያ ቤቱ ባለቤት ለመንገደኞች መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን የሚያቀርብ ሲሆን በዚያ ላረፉ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተጨማሪ ገንዘብ ተከፍሎት እንክብካቤ ያደርግ ነበር።
(ሉቃስ 10:36, 37) ታዲያ ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” 37 እሱም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” አለ። ከዚያም ኢየሱስ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
አንድ ሳምራዊ መልካም ባልንጀራ ሆኖ ተገኘ
ትክክል የሆነውን ነገር ከልቡ የሚሠራ ሰው የአምላክን ሕግ መታዘዝ ብቻ ሳይሆን ባሕርያቱንም መኮረጅ እንዳለበት የኢየሱስ ምሳሌ ያሳያል። (ኤፌሶን 5:1) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም’ በማለት ይገልጽልናል። (ሥራ 10:34) በዚህ ረገድ አምላክን እየመሰልን ነውን? ኢየሱስ የተናገረው ስሜት የሚነካ ምሳሌ ለሰዎች የምናሳየው ወዳጃዊ ስሜት ብሔራዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ድንበሮችን አልፎ መሄድ እንዳለበት ያሳያል። በእርግጥም ክርስቲያኖች ከእነሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማኅበራዊ ኑሮ፣ ዘር ወይም ብሔር ላላቸው እንዲሁም ለእምነት ጓደኞቻቸው ብቻ ሳይሆን “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።—ገላትያ 6:10
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 10:18
ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ፦ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የሰይጣንን ከሰማይ መባረር ልክ እንደተፈጸመ አድርጎ ትንቢት መናገሩ ነበር። ራእይ 12:7-9 በሰማይ ስለተደረገው ጦርነት የሚናገር ሲሆን የሰይጣንን መባረር ከመሲሐዊው መንግሥት መወለድ ጋር አያይዞ ገልጾታል። እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደፊት በሚካሄደው ጦርነት ላይ መሸነፋቸው እንደማይቀር በእርግጠኝነት መናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም አምላክ ፍጽምና ለጎደላቸው ለእነዚያ 70 ደቀ መዛሙርት እንኳ አጋንንትን የማስወጣት ኃይል ሰጥቷቸዋል።—ሉቃስ 10:17
የሉቃስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
10:18—ኢየሱስ ለ70ዎቹ ደቀ መዛሙርት “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” ያላቸው ምን ለመግለጽ ፈልጎ ነው? ኢየሱስ፣ ሰይጣን ከሰማይ እንደተባረረ መግለጹ አልነበረም። ሰይጣን ከሰማይ የተባረረው ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። (ራእይ 12:1-10) ኢየሱስ እንዲህ ያለበትን ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ወደፊት የሚከናወነውን ነገር እንደተፈጸመ አድርጎ የተናገረው፣ ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ የማይቀር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ለመግለጽ ሳይሆን አይቀርም።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 11:5-9
ወዳጄ ሆይ፣ እባክህ ሦስት ዳቦ አበድረኝ፦ ከዚህ ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው በመካከለኛው ምሥራቅ ባሕል እንግዳ ተቀባይነት ከፍ ተደርጎ የሚታይ ኃላፊነት ሲሆን በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ይህን ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው እንግዳ የመጣበት ድንገት እኩለ ሌሊት ላይ ነው፤ እንግዳው በዚህ ሰዓት እንደደረሰ መገለጹ በወቅቱ አንድ ተጓዥ በጉዞ ላይ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። እንግዳው የመጣው አጉል ሰዓት ላይ ቢሆንም ሰውየው ለእንግዳው የሆነ የሚበላ ነገር ማቅረብ እንዳለበት ተሰምቶታል። እንዲያውም በዚያ ሰዓት ጎረቤቱን በማስቸገር ምግብ እንዲያበድረው እስከመጠየቅ ደርሷል።
ባክህ አታስቸግረኝ፦ በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ጎረቤት እንዲህ ያለ ምላሽ የሰጠው መርዳት ስላልፈለገ ሳይሆን በዚያ ሰዓት ተኝቶ ስለነበር ነው። በወቅቱ የነበሩት ቤቶች በተለይም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች አብዛኛውን ጊዜ አንድ ትልቅ ክፍል ብቻ ያላቸው ነበሩ። የቤተሰቡ ራስ ከመኝታው መነሳቱ እንቅልፍ የወሰዳቸውን ልጆች ጨምሮ መላውን ቤተሰብ መረበሹ አይቀርም።
ውትወታው፦ እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል ቀጥታ ሲተረጎም “ሥርዓት አልበኝነት” ወይም “እፍረተ ቢስነት” ሊባል ይችላል። በዚህ አገባቡ ግን አንድን ነገር ለማግኘት በተደጋጋሚ መጠየቅን ወይም መወትወትን ያመለክታል። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው እፍረት ተሰምቶት የሚፈልገውን ነገር በተደጋጋሚ ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱም በሚጸልዩበት ጊዜ ልክ እንደዚህ ሰው የሚፈልጉትን ነገር ደጋግመው መጠየቅ እንዳለባቸው እያስተማራቸው ነበር።—ሉቃስ 11:9, 10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 10:1-16) ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች 70 ሰዎችን ሾመ፤ እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ከተማና ቦታ ሁሉ ቀድመውት እንዲሄዱም ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። 2 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። 3 እንግዲህ ሂዱ! እነሆ፣ በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ። 4 የገንዘብ ኮሮጆ ወይም የምግብ ከረጢት ወይም ትርፍ ጫማ አትያዙ፤ በመንገድም ላይ ቆማችሁ ከማንም ጋር ሰላምታ አትለዋወጡ። 5 ወደ ማንኛውም ቤት ስትገቡ በቅድሚያ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ። 6 በዚያም ሰላም ወዳድ ሰው ካለ ሰላማችሁ ያርፍበታል። ሰላም ወዳድ ሰው ከሌለ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። 7 ለሠራተኛ ደሞዙ ስለሚገባው ያቀረቡላችሁን ነገር እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያው ቤት ቆዩ። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ። 8 “በተጨማሪም ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ 9 እንዲሁም በዚያ ያሉትን በሽተኞች ፈውሱ፤ ደግሞም ‘የአምላክ መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቧል’ በሏቸው። 10 ሆኖም ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ካልተቀበሏችሁ ወደ አውራ ጎዳናዎች ወጥታችሁ እንዲህ በሉ፦ 11 ‘በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን አቧራ እንኳ ሳይቀር አራግፈንላችሁ እንሄዳለን። ይሁንና የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እወቁ።’ 12 እላችኋለሁ፦ በዚያ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። 13 “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ማቅ ለብሰውና አመድ ላይ ተቀምጠው ንስሐ በገቡ ነበር። 14 ስለዚህ በፍርድ ወቅት ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 15 አንቺም ቅፍርናሆም ወደ ሰማይ ከፍ የምትዪ ይመስልሻል? በፍጹም! ወደ መቃብር ትወርጃለሽ! 16 “እናንተን የሚሰማ ሁሉ እኔንም ይሰማል። እናንተን የማይቀበል ሁሉ ደግሞ እኔንም አይቀበልም። ከዚህም በላይ እኔን የማይቀበል ሁሉ የላከኝንም አይቀበልም።”
ከሐምሌ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 12-13
“እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 12:6
ድንቢጦች፦ ስትሮውቲዮን የሚለው የግሪክኛ ቃል ትንሽነትን የሚያመለክት ቅጥያ የተጨመረበት ሲሆን የትኛውንም አነስተኛ ወፍ ለመግለጽ ያገለግላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ለምግብነት ከሚሸጡ ወፎች መካከል ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን ድንቢጦችን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 12:7
የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል፦ በሰው ጭንቅላት ላይ ያለው ፀጉር በአማካይ ከ100,000 በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ጥቃቅን ነገሮች እንኳ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑ ለእያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳያል።
(ሉቃስ 12:7) የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል። አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።
“ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን” የሚችል ነገር የለም
4 በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።” (ማቴዎስ 10:29-31) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን ትርጉም እንደነበራቸው ተመልከት።
5 አንድ ሰው ድንቢጥ የሚገዛበት ምን ምክንያት አለ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። በኢየሱስ ዘመን ለምግብነት ይሸጡ ከነበሩት ወፎች ሁሉ በጣም ርካሿ ድንቢጥ ነበረች። አንድ ሰው በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ባላት አምስት ሳንቲም ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል እንደነበረ ልብ በል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በኋላ እንደገለጸው አንድ ሰው አሥር ሳንቲም ካወጣ አራት ሳይሆን አምስት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር። አምስተኛዋ ወፍ ምንም ዋጋ እንደሌለው ነገር በምርቃት መልክ የምትሰጥ ናት። እነዚህ ፍጥረታት በሰዎች ፊት ዋጋ አይኖራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ፈጣሪ ለእነዚህ ፍጥረታት ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ኢየሱስ “ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ [በምርቃት መልክ የምትሰጠው እንኳ ሳትቀር] በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 12:6, 7) ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት እንችላለን። ይሖዋ ለአንዲት ድንቢጥ እንኳ ይህን ያህል ግምት የሚሰጥ ከሆነ ሰውንማ ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት መገመት አያዳግትም! ኢየሱስ እንደገለጸው ይሖዋ ስለ እኛ እያንዳንዷን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። የራሳችን ፀጉር እንኳ ሳይቀር የተቆጠረ ነው!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 13:24
ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ፦ ወይም “ከፍተኛ ትግል ማድረጋችሁን ቀጥሉ።” ኢየሱስ የሰጠው ማሳሰቢያ በጠባቡ በር ለመግባት በሙሉ ነፍስ መጋደል እንደሚያስፈልግ ያጎላል። የተለያዩ የማመሣከሪያ ጽሑፎች እዚህ ላይ የገባው አገላለጽ “አቅማችሁ የቻለውን ሁሉ አድርጉ፤ ያለ የሌለ ኃይላችሁን ተጠቀሙ” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይጠቁማሉ። አጎኒዞማይ የሚለው የግሪክኛ ግስ ብዙውን ጊዜ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማመልከት ከሚሠራበት አጎን ከሚለው የግሪክኛ ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። በዕብ 12:1 ላይ አጎን የሚለው ቃል ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ምሳሌያዊ የሕይወት “ሩጫ” ለማመልከት ተሠርቶበታል። ጠቅለል ባለ ሁኔታ ‘ትግልን’ (ፊልጵ 1:30፤ ቆላ 2:1) ወይም ‘ገድልን’ (1ጢሞ 6:12፤ 2ጢሞ 4:7) ለማመልከት የተሠራበት ጊዜም አለ። ሉቃስ 13:24 ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ግስ በተለያየ አገባቡ፣ ‘በውድድር መሳተፍ’ (1ቆሮ 9:25)፣ ‘ብርቱ ጥረት ማድረግ’ (1ጢሞ 4:10) እና ‘መጋደል’ (1ጢሞ 6:12) ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ አገላለጽ ከስፖርታዊ ውድድሮች ጋር በተያያዘ የሚሠራበት አገላለጽ ከመሆኑ አንጻር አንዳንዶች ኢየሱስ ልክ አንድ አትሌት ሽልማቱን ለማግኘት ያለ የሌለ ኃይሉን እንደሚጠቀም ሁሉ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ተጋድሎ እንዲያደርጉ እያበረታታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 13:33
ሊገደል ስለማይችል፦ ወይም “መገደሉ የማይታሰብ ነገር ስለሆነ።” መሲሑ በኢየሩሳሌም እንደሚገደል በቀጥታ የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ባይኖርም በዳን 9:24-26 ላይ ካለው ሐሳብ በመነሳት እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻል ይሆናል። በተጨማሪም አይሁዳውያኑ አንድን ነቢይ በተለይም መሲሑን ከገደሉ እንዲህ የሚያደርጉት በኢየሩሳሌም ውስጥ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነገር ነው። ሰባ አንድ አባላት ያሉት የሳንሄድሪን ከፍተኛ ሸንጎ የሚሰበሰበው ኢየሩሳሌም ውስጥ ስለሆነ አንድ ሰው ሐሰተኛ ነቢይ ነው ተብሎ ከተከሰሰ ጉዳዩ የሚታየው እዚያው ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ቋሚ የሆኑት መሥዋዕቶች ለአምላክ የሚቀርቡትና የፋሲካው በግ የሚታረደው በኢየሩሳሌም መሆኑን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። በኋላ እንደታየው ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በትክክል ተፈጽመዋል። ኢየሱስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ቀርቦ ወንጀለኛ እንደሆነ የተፈረደበት ኢየሩሳሌም ውስጥ ነው። ‘የፋሲካ በግ’ ሆኖ የሞተውም እዚያው ኢየሩሳሌም ከከተማዋ ቅጥር ውጭ ነው።—1ቆሮ 5:7
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 12:22-40) ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንበላለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ። 23 ሕይወት ከምግብ ሰውነትም ከልብስ የላቀ ዋጋ አለውና። 24 ቁራዎችን ተመልከቱ፦ አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም? 25 ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል? 26 ታዲያ እንዲህ ያለውን ትንሽ ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ ስለ ሌሎች ነገሮች ለምን ትጨነቃላችሁ? 27 እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፦ አይለፉም ወይም አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ያን ያህል ክብር የነበረው ሰለሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዷ አላጌጠም። 28 አምላክ ዛሬ ያለውንና ነገ ወደ ምድጃ የሚጣለውን በሜዳ ያለ ተክል እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ! 29 ስለዚህ ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር ከልክ በላይ አታስቡ፤ እንዲሁም አትጨነቁ፤ 30 እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዓለም ያሉ ሰዎች አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው፤ ይሁንና አባታችሁ እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። 31 ይልቁንስ ዘወትር መንግሥቱን ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል። 32 “አንተ ትንሽ መንጋ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗልና። 33 ያላችሁን ንብረት ሸጣችሁ ምጽዋት ስጡ። የማያረጁ የገንዘብ ኮሮጆዎች አዘጋጁ፤ አዎ፣ ሌባ በማይደርስበት፣ ብልም ሊበላው በማይችልበት በሰማያት ለራሳችሁ የማያልቅ ውድ ሀብት አከማቹ። 34 ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናልና። 35 “ወገባችሁን ታጠቁ፤ መብራታችሁንም አብሩ፤ 36 ጌታቸው ከሠርግ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶ በሩን ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት እንደተዘጋጁ ዓይነት ሰዎች ሁኑ። 37 ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው ሲጠባበቁ የሚያገኛቸው ባሪያዎች ደስተኞች ናቸው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታቸው ለሥራ ካሸረጠና በማዕድ እንዲቀመጡ ካደረገ በኋላ ቆሞ ያስተናግዳቸዋል። 38 በሁለተኛው ክፍለ ሌሊትም ይምጣ በሦስተኛው፣ ዝግጁ ሆነው ሲጠብቁ ካገኛቸው ደስተኞች ናቸው! 39 ነገር ግን ይህን እወቁ፤ አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር። 40 እናንተም የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ።”
ከሐምሌ 30–ነሐሴ 5
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 14-16
“የኮብላዩ ልጅ ምሳሌ”
(ሉቃስ 15:11-16) ከዚያም እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12 ታናሽየውም ልጅ አባቱን ‘አባቴ ሆይ፣ ከንብረትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። በመሆኑም አባትየው ንብረቱን ለልጆቹ አካፈላቸው። 13 ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሽየው ልጅ ያለውን ነገር ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ፤ በዚያም ልቅ የሆነ ሕይወት በመኖር ንብረቱን አባከነ። 14 ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር በሙሉ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ በዚህ ጊዜ ችግር ላይ ወደቀ። 15 ከችግሩም የተነሳ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ሄዶ የሙጥኝ አለ፤ ሰውየውም አሳማ እንዲጠብቅለት ወደ ሜዳ ላከው። 16 እሱም አሳማዎቹ የሚመገቡትን ምግብ በልቶ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን የሚሰጠው አልነበረም።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 15:11-16
አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፦ ስለ አባካኙ ልጅ (“ኮብላዩ ልጅ” ተብሎም ይታወቃል) የሚናገረው ምሳሌ አንዳንድ ለየት ያሉ ገጽታዎች አሉት። ኢየሱስ ከተናገራቸው ረጅም ምሳሌዎች መካከል አንዱ ነው። የዚህ ምሳሌ አንዱ ጉልህ ገጽታ ቤተሰባዊ ትስስር ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው። ኢየሱስ የጠቀሳቸው አብዛኞቹ ምሳሌዎች እንደ ዘር ወይም የአፈር ዓይነቶች ባሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች ላይ ያተኮሩ አሊያም በአንድ ጌታና በባሪያዎቹ መካከል ስላለው ያን ያህል ቅርበት የማይንጸባረቅበት ግንኙነት የሚናገሩ ናቸው። (ማቴ 13:18-30፤ 25:14-30፤ ሉቃስ 19:12-27) በዚህ ምሳሌ ላይ ግን ኢየሱስ በአንድ አባትና በልጆቹ መካከል ያለውን የቀረበ ግንኙነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህን ምሳሌ ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ደግና አፍቃሪ አባት አይኖራቸው ይሆናል። ይህ ምሳሌ በሰማይ ያለው አባታችን ከእሱ ጎን ጸንተው ለሚቆሙም ሆነ ለተወሰነ ጊዜ ባዝነው ለሚመለሱ ምድራዊ ልጆቹ ያለውን ጥልቅ ርኅራኄና ፍቅር ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።
ታናሽየው ልጅ፦ በሙሴ ሕግ መሠረት የበኩር ልጅ እጥፍ ድርሻ ይሰጠው ነበር። (ዘዳ 21:17) በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው አባት ሌሎች ልጆች ከሌሉትና ታላቅየው ልጅ የበኩር ልጅ ከሆነ የታናሽየው ልጅ ድርሻ ከታላቁ ልጅ በግማሽ ያነሰ ይሆናል ማለት ነው።
አባከነ፦ እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “መበተን (በተለያዩ አቅጣጫዎች)” የሚል ነው። (ሉቃስ 1:51፤ ሥራ 5:37) በዚህ አገባቡ ገንዘብን ያለአግባብ መበተንን፣ በማይረባ ነገር ማጥፋትን ያመለክታል።
ልቅ የሆነ ሕይወት፦ ወይም “ብኩን (የንዝህላልነት፤ የልቅነት) ሕይወት።” ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው የግሪክኛ ቃል ኤፌ 5:18፤ ቲቶ 1:6፤ 1ጴጥ 4:4 ላይ ተመሳሳይ ትርጉም ለማስተላለፍ ተሠርቶበታል። የግሪክኛው ቃል አባካኝነት የሚንጸባረቅበትን አኗኗርም ሊያመለክት ስለሚችል አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የአባካኝነት ሕይወት” የሚለውን አገላለጽ ይጠቀማሉ።
አሳማ እንዲጠብቅለት፦ በሙሴ ሕግ መሠረት አሳማዎች ርኩስ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። በመሆኑም አሳማዎችን መጠበቅ ለአንድ አይሁዳዊ ክብር የሚነካና ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ሥራ ነው።—ዘሌ 11:7, 8
አሳማዎቹ የሚመገቡትን ምግብ፦ እዚህ ላይ የተጠቀሰው የምግብ ዓይነት በዛሬው ጊዜም ለፈረሶች፣ ለከብቶችና ለአሳማዎች ምግብ ሆኖ ያገለግላል። ይህ ወጣት አሳማዎች የሚመገቡትን ምግብ እንኳ ለመመገብ እንደፈለገ መገለጹ ወጣቱ ምን ያህል የተዋረደ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያመለክታል።—ለሉቃስ 15:15 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
(ሉቃስ 15:17-24) “ወደ ልቦናው ሲመለስ ግን እንዲህ አለ፦ ‘ስንቶቹ የአባቴ ቅጥር ሠራተኞች ምግብ ተርፏቸው እኔ እዚህ በረሃብ ልሞት ነው! 18 ተነስቼ ወደ አባቴ በመሄድ እንዲህ እለዋለሁ፦ “አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። 19 ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም። ከቅጥር ሠራተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።”’ 20 ስለዚህ ተነስቶ ወደ አባቱ ሄደ። ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው። 21 ከዚያም ልጁ ‘አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው። 22 አባትየው ግን ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ቶሎ በሉ! ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጥታችሁ አልብሱት፤ ለእጁ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት። 23 የሰባውንም ጥጃ አምጥታችሁ እረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት። 24 ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል። ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 15:17-24
በአንተ ላይ፦ ወይም “በአንተ ፊት።” ኢኖፒኦን የሚለው የግሪክኛው መስተዋድድ ቃል በቃል “ፊት ለፊት፤ በእይታ ውስጥ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ በ1ሳሙ 20:1 ላይ በተመሳሳይ መንገድ ተሠርቶበታል። በዚህ ጥቅስ ላይ ዳዊት ዮናታንን “አባትህ ሕይወቴን ለማጥፋት የሚፈልገው በእሱ ላይ ምን ኃጢአት ሠርቼ ነው?” በማለት ጠይቆታል።
ከቅጥር ሠራተኞችህ፦ ታናሽየው ልጅ ወደ ቤት ሲመለስ አባቱ እንደ ልጁ አድርጎ ሳይሆን ከቅጥር ሠራተኞቹ እንደ አንዱ አድርጎ እንዲቀበለው ለመጠየቅ አስቦ ነበር። አንድ የቅጥር ሠራተኛ ከባለቤቱ ጋር አብሮ እንደሚኖር ባሪያ የባለቤቱ ንብረት ተደርጎ አይታሰብም፤ ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው ለአንድ ቀን ብቻ እንዲያገለግል የሚቀጠር ሠራተኛ ነው።—ማቴ 20:1, 2, 8
ሳመው፦ እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል ፊሌኦ የሚለውን ግስ ከፍተኛ ደረጃ የሚያመለክት አገላለጽ እንደሆነ ይታመናል፤ አንዳንድ ጊዜ ‘መሳም’ (ማቴ 26:48፤ ማር 14:44፤ ሉቃስ 22:47) ተብሎ የተተረጎመ ቢሆንም በአብዛኛው ‘መውደድ’ (ዮሐ 5:20፤ 11:3፤ 16:27) የሚል ትርጉም ለማስተላለፍ ተሠርቶበታል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አባት እንዲህ ባለ ፍቅር የሚንጸባረቅበት መንገድ ልጁን ሰላም ማለቱ ንስሐ የገባውን ልጁን መልሶ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ያሳያል።
ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፦ አንዳንድ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች ከዚህ ሐሳብ በኋላ “ከቅጥር ሠራተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ” የሚለውን ዓረፍተ ነገር የሚጨምሩ ቢሆንም የተለያዩ ጥንታዊና ከፍተኛ ተአማኒነት ያላቸው ቅጂዎች ይህን ዓረፍተ ነገር አይጨምሩም። አንዳንድ ምሁራን ይህ ሐሳብ የተጨመረው ጥቅሱ ከሉቃስ 15:19 ጋር እንዲመሳሰል ለማድረግ ሲባል እንደሆነ ይናገራሉ።
ልብስ . . . ቀለበት . . . ጫማ፦ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ልብስ እንዲሁ ተራ ልብስ ሳይሆን ምርጥ የሆነ ምናልባትም ለተከበረ እንግዳ የሚሰጥ በጌጣጌጥ የተንቆጠቆጠ ልብስ ሳይሆን አይቀርም። ልጁ ቀለበት የተደረገለት መሆኑ አባትየው በሞገስ ዓይን እንዳየውና በፍቅር እንደተቀበለው የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ለተመለሰው ልጁ ክብር፣ ማዕረግና ከፍ ያለ ቦታ እንደሰጠው ይጠቁማል። አብዛኛውን ጊዜ ባሪያዎች ቀለበትና ጫማ አያደርጉም። በመሆኑም አባትየው ለልጁ ቀለበትና ጫማ እንዲደረግለት ማዘዙ ልጁን ሙሉ በሙሉ የቤተሰቡ አባል አድርጎ መልሶ እንደተቀበለው በግልጽ ያሳያል።
(ሉቃስ 15:25-32) “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በእርሻ ቦታ ነበር፤ ተመልሶ መጥቶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ። 26 ስለዚህ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው። 27 አገልጋዩም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደህና ስለመጣም አባትህ የሰባውን ጥጃ አርዶለታል’ አለው። 28 እሱ ግን ተቆጣ፤ ወደ ቤት ለመግባትም አሻፈረኝ አለ። ከዚያም አባቱ ወጥቶ ይለምነው ጀመር። 29 እሱም መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፣ እኔ ስንት ዓመት ሙሉ እንደ ባሪያ ሳገለግልህ ኖርኩ፤ መቼም ቢሆን ከትእዛዝህ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ አንተ ግን ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም። 30 ሆኖም ሀብትህን ከዝሙት አዳሪዎች ጋር ያወደመው ይህ ልጅህ ገና ከመምጣቱ የሰባውን ጥጃ አረድክለት።’ 31 በዚህ ጊዜ አባቱ እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ደግሞም የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። 32 ሆኖም ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል። ስለዚህ ልንደሰትና ሐሴት ልናደርግ ይገባል።’”
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 14:26) “ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱን፣ እናቱን፣ ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን ሌላው ቀርቶ የገዛ ራሱን ሕይወት እንኳ የማይጠላ ከሆነ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 14:26
የማይጠላ፦ “መጥላት” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። በአንድ ሰው ላይ የሚጎዳ ነገር ወደመፈጸም የሚያመራን ከክፋት የመነጨ ጥላቻ ሊያመለክት ይችላል። አሊያም ከአንድ ሰው ወይም ነገር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ከመፍጠር እንድንቆጠብ የሚያደርግን ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት ሊያመለክት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ሰው ወይም ነገር አሳንሶ መውደድን ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ ሊያን ‘እንደጠላትና’ ራሔልን እንደወደዳት ሲገልጽ ያዕቆብ ሊያን ከራሔል አሳንሶ እንደወደዳት መጠቆሙ ነው፤ (ዘፍ 29:31 ግርጌ፤ ዘዳ 21:15 ግርጌ) በሌሎች ጥንታዊ የአይሁዳውያን ጽሑፎችም ላይ ይህ አገላለጽ በዚህ መንገድ ተሠርቶበታል። በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ ለቤተሰቦቻቸውም ሆነ ለራሳቸው የጥላቻ ስሜት ሊኖራቸው እንደሚገባ መናገሩ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይህ ከሌሎቹ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ጋር ይጋጫል። (ማር 12:29-31፤ ኤፌ 5:28, 29, 33) “የማይጠላ” የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ “አሳንሶ የማይወድ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።
(ሉቃስ 16:10-13) በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ያልሆነ ሰው ደግሞ በብዙ ነገርም ታማኝ አይሆንም። 11 ስለዚህ በዓመፅ ሀብት ታማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ እውነተኛውን ሀብት ማን በአደራ ይሰጣችኋል? 12 የሌላ ሰው በሆነው ነገር ታማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ ለእናንተ የታሰበውን ማን ይሰጣችኋል? 13 ለሁለት ጌቶች ባሪያ መሆን የሚችል አገልጋይ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድ ጊዜ ባሪያ መሆን አትችሉም።”
እውነተኛ የሆነውን ሀብት መፈለግ
7 ሉቃስ 16:10-13ን አንብብ። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው መጋቢ ወዳጆችን ያፈራው ለግል ጥቅሙ ሲል ነው። ኢየሱስ በሰማይ ወዳጆች እንዲያፈሩ ተከታዮቹን ሲያሳስባቸው ግን ይህን በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንዲያደርጉት ማበረታታቱ አልነበረም። ኢየሱስ ከተናገረው ምሳሌ ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ላይ፣ “በዓመፅ ሀብት” መጠቀም ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ጋር ተያይዞ ተገልጿል። ኢየሱስ ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ፣ ያለንን የዓመፅ ሀብት ለአምላክ ‘ታማኝ መሆናችንን’ በሚያሳይ መንገድ ልንጠቀምበት የሚገባ መሆኑን ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
8 ከቁሳዊ ንብረታችን ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ በገንዘብ መደገፍ ነው። (ማቴ. 24:14) በሕንድ የምትኖር አንዲት ትንሽ ልጅ፣ በአነስተኛ ሣጥን ውስጥ ሳንቲም ማጠራቀም ጀመረች፤ ይህች ልጅ ገንዘቡን መጫወቻ ለመግዛት እንኳ አላዋለችውም። ሣጥኑ ሲሞላላት ገንዘቡን በሙሉ አውጥታ ለስብከቱ ሥራ እንዲውል መዋጮ አደረገችው። በዚያው በሕንድ የሚኖር የኮኮናት እርሻ ያለው ወንድም ደግሞ ለማላያላም የርቀት የትርጉም ቢሮ ብዛት ያለው ኮኮናት ይሰጣል፤ ምክንያቱም የርቀት የትርጉም ቢሮው ኮኮናት መግዛት ያስፈልገዋል፤ በመሆኑም ኮኮናት በመሸጥ የሚተዳደረው ይህ ወንድም፣ ለቢሮው ገንዘብ ከሚሰጥ ይልቅ ኮኮናቱን ቢሰጥ እንደሚሻል ተሰምቶታል። ይህ አርቆ አሳቢነት ነው። በተመሳሳይም በግሪክ የሚኖሩ ወንድሞች የወይራ ዘይት፣ አይብ እና ሌሎች ምግቦችን ለቤቴል ቤተሰብ አዘውትረው ይሰጣሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 14:1-14) በሌላ ወቅት ኢየሱስ በአንድ የሰንበት ቀን ከፈሪሳውያን መሪዎች ወደ አንዱ ቤት ምግብ ሊበላ በገባ ጊዜ በቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 2 በዚያም ሰውነት የሚያሳብጥ በሽታ የያዘው አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር። 3 ኢየሱስም ሕግ አዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው። 4 እነሱ ግን ዝም አሉ። በዚህ ጊዜ በሰውየው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሰውና አሰናበተው። 5 ከዚያም “ከእናንተ መካከል ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ቢወድቅ ወዲያውኑ ጎትቶ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። 6 እነሱም ለዚህ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም። 7 ኢየሱስ የተጋበዙት ሰዎች ለራሳቸው የክብር ቦታ ሲመርጡ ተመልክቶ እንዲህ ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው፦ 8 “አንድ ሰው ወደ ሠርግ ሲጠራህ በክብር ቦታ አትቀመጥ። ምናልባት ከአንተ የበለጠ የተከበረ ሰው ተጠርቶ ሊሆን ይችላል። 9 በመሆኑም ሁለታችሁንም የጋበዘው ሰው መጥቶ ‘ቦታውን ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ እያፈርክ ወደ ዝቅተኛው ቦታ ትሄዳለህ። 10 አንተ ግን ስትጋበዝ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጋበዘህም ሰው ሲመጣ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ይልሃል። በዚህ ጊዜ አብረውህ በተጋበዙት ሰዎች ሁሉ ፊት ክብር ታገኛለህ። 11 ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋልና፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።” 12 ቀጥሎ ደግሞ የጋበዘውን ሰው እንዲህ አለው፦ “የምሳ ወይም የራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ጓደኞችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ሀብታም ጎረቤቶችህን አትጥራ። አለዚያ እነሱም ሊጋብዙህና ብድር ሊመልሱልህ ይችላሉ። 13 ሆኖም ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ 14 ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ። ምክንያቱም በጻድቃን ትንሣኤ ብድራት ይመለስልሃል።”