የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ነሐሴ 2018
ከነሐሴ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 17-18
“አመስጋኝ ሁኑ”
(ሉቃስ 17:11-14) ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ሳለ በሰማርያና በገሊላ መካከል አለፈ። 12 ወደ አንድ መንደር እየገባም ሳለ የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥር ሰዎች አዩት፤ እነሱም በርቀት ቆሙ። 13 ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ “ኢየሱስ፣ መምህር፣ ምሕረት አድርግልን!” አሉ። 14 እሱም ባያቸው ጊዜ “ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። ከዚያም እየሄዱ ሳሉ ነጹ።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 17:12, 14
የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥር ሰዎች፦ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው ይገኙ ወይም አብረው በቡድን ይኖሩ የነበረ ሲሆን ይህም እርስ በርስ ለመረዳዳት ያስችላቸዋል። (2ነገ 7:3-5) የአምላክ ሕግ የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ተገልለው እንዲኖሩ ያዝዝ ነበር። በተጨማሪም የሥጋ ደዌ ያለበት አንድ ሰው “ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!” እያለ በመጮኽ ሌሎች ወደ እሱ እንዳይቀርቡ ማስጠንቀቅ ነበረበት። (ዘሌ 13:45, 46) እዚህ ላይ የተጠቀሱት የሥጋ ደዌ የያዛቸው ሰዎች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ወደ ኢየሱስ ሳይጠጉ በርቀት ቆመው ነበር።—ከቃላት መፍቻው ላይ “የሥጋ ደዌ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፦ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በሕጉ ሥር ስለነበር የአሮን የክህነት አገልግሎት እንደሚሠራ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ከሥጋ ደዌ የፈወሳቸውን ሰዎች ሄደው ራሳቸውን ለካህን እንዲያሳዩ አዟቸዋል። (ማቴ 8:4፤ ማር 1:44) በሙሴ ሕግ መሠረት የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ከበሽታው መንጻቱን ካህኑ ማረጋገጥ ነበረበት። በተጨማሪም ከበሽታው የነጻው ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ በመሄድ ሕጉ የሚያዝዘውን መባ ማቅረብ ነበረበት።—ዘሌ 14:2-32
(ሉቃስ 17:15, 16) ከእነሱ አንዱ እንደተፈወሰ ባየ ጊዜ አምላክን በታላቅ ድምፅ እያመሰገነ ተመለሰ። 16 ኢየሱስ እግር ላይ ተደፍቶም አመሰገነው። ሰውየውም ሳምራዊ ነበር።
(ሉቃስ 17:17, 18) ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “የነጹት አሥሩም አይደሉም እንዴ? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? 18 ከዚህ ከባዕድ አገር ሰው በስተቀር አምላክን ለማመስገን የተመለሰ ሌላ አንድም ሰው የለም?”
አመስጋኝ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
ኢየሱስ፣ ዘጠኙ ሰዎች ምስጋናቸውን ሳይገልጹ መቅረታቸውን ችላ ብሎ አልፎት ይሆን? ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ ‘የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በስተቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?’”—ሉቃስ 17:17, 18
የሥጋ ደዌ ይዟቸው የነበሩት የተቀሩት ዘጠኝ ሰዎች ዓመጸኞች አልነበሩም። ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳላቸው በግልጽ የተናገሩ ሲሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ራሳቸውን ለካህናት ማሳየትን ጨምሮ ኢየሱስ የሰጣቸውን መመሪያዎች በፈቃደኝነት ታዘዋል። ኢየሱስ ላደረገላቸው መልካም ነገር ጥልቅ አድናቆት እንደነበራቸው ግልጽ ቢሆንም አመስጋኝነታቸውን ሳይገልጹ ቀርተዋል። ይህ ድርጊታቸው ክርስቶስን አሳዝኖታል። እኛስ? አንድ ሰው መልካም ነገር ሲያደርግልን ምስጋናችንን ለመግለጽ ወይም አድናቆታችንን የሚያሳይ ነገር ለማድረግ ፈጣኖች ነን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 17:7-10) “ከእናንተ መካከል አራሽ ወይም እረኛ የሆነ ባሪያ ያለው ሰው ቢኖር፣ ባሪያው ከእርሻ ሲመለስ ‘ቶሎ ናና ወደ ማዕድ ቅረብ’ ይለዋል? 8 ከዚህ ይልቅ ‘ራቴን አዘጋጅልኝ፤ በልቼና ጠጥቼ እስክጨርስም ድረስ አሸርጠህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ መብላትና መጠጣት ትችላለህ’ አይለውም? 9 ባሪያው የተሰጠውን ሥራ በማከናወኑ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋል? 10 በተመሳሳይ እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 17:10
ምንም የማንጠቅም፦ ቃል በቃል “ከንቱ፤ ዋጋ ቢስ።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የሰጠው ባሪያዎቹ ወይም ደቀ መዛሙርቱ ራሳቸውን ከንቱ ወይም ዋጋ ቢስ እንደሆኑ አድርገው ሊቆጥሩ እንደሚገባ ለማስተማር አይደለም። ከአገባቡ መረዳት እንደሚቻለው “ምንም የማንጠቅም” የሚለው አገላለጽ ባሪያዎቹ ለራሳቸው የተጋነነ አመለካከት ሊኖራቸው እንደማይገባ ማለትም ለየት ያለ ምስጋና ወይም ውዳሴ እንደሚገባቸው አድርገው ማሰብ እንደሌለባቸው ያመለክታል። አንዳንድ ምሁራን ይህ አገላለጽ በዚህ አገባቡ “ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጠን የማይገባ ተራ ባሪያዎች ነን” የሚል ትርጉም የሚያስተላልፍ ግነታዊ ዘይቤ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
(ሉቃስ 18:8) እላችኋለሁ፣ በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል። ሆኖም የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እምነት ያገኝ ይሆን?”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 18:8
እምነት፦ ወይም “እንዲህ ያለ እምነት።” ግሪክኛው “እምነት” ከሚለው ቃል በፊት ጠቃሽ አመልካች የሚጨምር መሆኑ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በጥቅሉ ስለ እምነት ሳይሆን በምሳሌው ላይ የተጠቀሰችው መበለት ስላሳየችው ዓይነት እምነት እንደሆነ ያመለክታል። (ሉቃስ 18:1-8) ይህም ጸሎት ባለው ኃይል ላይ እምነት ማሳደርን እንዲሁም አምላክ ለመረጣቸው ፍትሕን እንደሚያመጣ ማመንን ይጨምራል። ኢየሱስ ስለ እምነት ላነሳው ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ ያለፈው ደቀ መዛሙርቱ እምነታቸው ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እንዲያስቡበት ስለፈለገ ሳይሆን አይቀርም። ቀደም ሲል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ተናግሮ ስለነበር ስለ ጸሎትና ስለ እምነት የሚገልጸውን ይህን ምሳሌ መጥቀሱ ተገቢ ነው።—ሉቃስ 17:22-37
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 18:24-43) ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ምንኛ አስቸጋሪ ነው! 25 እንዲያውም ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” 26 ይህን የሰሙ ሰዎች “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። 27 እሱም “በሰዎች ዘንድ የማይቻል፣ በአምላክ ዘንድ ይቻላል” አለ። 28 ጴጥሮስ ግን “እነሆ፣ እኛ ያለንን ነገር ትተን ተከትለንሃል” አለ። 29 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለአምላክ መንግሥት ሲል ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ወንድሞችን ወይም ወላጆችን ወይም ልጆችን የተወ ሁሉ፣ 30 አሁን በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።” 31 ከዚያም አሥራ ሁለቱን ገለል አድርጎ በመውሰድ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ! ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰውን ልጅ በተመለከተም በነቢያት የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ይፈጸማሉ። 32 ለምሳሌ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል እንዲሁም ይተፉበታል። 33 ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፤ በሦስተኛው ቀን ግን ይነሳል።” 34 ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ መካከል አንዱንም አልተረዱም፤ የተናገረው ቃል ተሰውሮባቸው ነበርና፤ የተባለውም ነገር አልገባቸውም። 35 ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ እየተቃረበ ሳለ አንድ ዓይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 36 ዓይነ ስውሩም ብዙ ሕዝብ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ይጠይቅ ጀመር። 37 ሰዎቹም “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው!” ብለው ነገሩት። 38 በዚህ ጊዜ “ኢየሱስ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” ሲል ጮኸ። 39 ከፊት ከፊት የሚሄዱትም ሰዎች ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እሱ ግን “የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ምሕረት አድርግልኝ!” እያለ ይበልጥ መጮኹን ቀጠለ። 40 ኢየሱስም ቆመና ሰውየውን ወደ እሱ እንዲያመጡት አዘዘ። ሰውየው ወደ እሱ በቀረበ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ 41 “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” እሱም “ጌታ ሆይ፣ የዓይኔን ብርሃን መልስልኝ” አለው። 42 ስለዚህ ኢየሱስ “የዓይንህ ብርሃን ይመለስልህ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። 43 ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም ይከተለው ጀመር። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ አምላክን አወደሱ።
ከነሐሴ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 19-20
“ከአሥሩ ምናን ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?”
(ሉቃስ 19:12, 13) ስለዚህ እንዲህ አለ፦ “አንድ መስፍን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ተነሳ። 13 ከባሪያዎቹ መካከል አሥሩን ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና ‘እስክመጣ ድረስ ነግዱበት’ አላቸው።
ስለ አሥሩ ምናን የተናገረው ምሳሌ
ኢየሱስ “አንድ መስፍን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ተነሳ” በማለት ምሳሌውን ጀመረ። (ሉቃስ 19:12) እንዲህ ዓይነቱ ጉዞ ጊዜ ይወስዳል። ወደ “ሩቅ አገር” ይኸውም ወደ ሰማይ የተጓዘው “መስፍን” ኢየሱስ እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል፤ በዚያም አባቱ ንጉሣዊ ሥልጣን ይሰጠዋል።
በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው “መስፍን” ከመሄዱ በፊት አሥር ባሪያዎች ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው አንድ የብር ምናን ከሰጣቸው በኋላ “እስክመጣ ድረስ ነግዱበት” አላቸው። (ሉቃስ 19:13) የብር ምናን ውድ ዋጋ ያለው ገንዘብ ነው። የእርሻ ሠራተኛ የሆነ ሰው፣ አንድ ምናን እንዲከፈለው ከሦስት ወር በላይ መሥራት አለበት።
ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ደቀ መዛሙርቱን ከመከር ሠራተኞች ጋር አመሳስሏቸዋል፤ በመሆኑም በምሳሌው ላይ የተጠቀሱት አሥር ባሪያዎች እነሱን እንደሚያመለክቱ አስተውለው መሆን አለበት። (ማቴዎስ 9:35-38) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ቃል በቃል አዝመራ ሰብስበው እንዲያመጡ አልጠየቃቸውም። አዝመራው የሚያመለክተው በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ የሚኖራቸውን ሌሎች ደቀ መዛሙርት ነው። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ጊዜና ጉልበት አልፎ ተርፎም ጥሪታቸውን በሙሉ በመጠቀም ተጨማሪ የመንግሥቱ ወራሾችን ያፈራሉ።
(ሉቃስ 19:16-19) በመሆኑም የመጀመሪያው ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው። 17 ጌታው ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩ ባሪያ! በጣም አነስተኛ በሆነው ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በአሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። 18 ሁለተኛው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አምስት ምናን አስገኝቷል’ አለ። 19 ይሄኛውንም ‘አንተም በአምስት ከተሞች ላይ ተሹመሃል’ አለው።
ስለ አሥሩ ምናን የተናገረው ምሳሌ
ደቀ መዛሙርቱ፣ የተሰጣቸውን ንብረት አቅማቸው በፈቀደ መጠን ተጠቅመው ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት እንዳፈሩት ባሪያዎች እንደሆኑ ከተሰማቸው ኢየሱስ እንደሚደሰትባቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። እንዲህ ያለ ትጋት በማሳየታቸው ኢየሱስ እንደሚሸልማቸውም መተማመን ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ሁሉም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ሁኔታ፣ አጋጣሚ ወይም ችሎታ የላቸውም። ያም ቢሆን “ንጉሣዊ ሥልጣኑን” የተቀበለው ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በታማኝነት የሚያደርጉትን ጥረት የሚመለከት ከመሆኑም ሌላ ይባርካቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20
(ሉቃስ 19:20-24) ሆኖም ሌላኛው መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‘ጌታዬ፣ በጨርቅ ጠቅልዬ የደበቅኩት ምናንህ ይኸውልህ። 21 ይህን ያደረግኩት ጨካኝ ሰው ስለሆንክ ፈርቼህ ነው፤ አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ሰው ነህ።’ 22 ጌታውም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ። ያላስቀመጥኩትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትንም የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንኩ ታውቅ ኖሯል ማለት ነው? 23 ታዲያ ገንዘቤን ለምን ለገንዘብ ለዋጮች አልሰጠህም? እንደዚህ አድርገህ ቢሆን ኖሮ ስመጣ ከነወለዱ እወስደው ነበር።’ 24 “ከዚያም በዚያ ቆመው የነበሩትን ሰዎች ‘ምናኑን ውሰዱበትና አሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው።
ስለ አሥሩ ምናን የተናገረው ምሳሌ
ይህ ባሪያ የጌታውን መንግሥት ሀብት ለመጨመር ጥረት ስላላደረገ ያለውን አጥቷል። ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት ላይ መግዛት የሚጀምርበትን ጊዜ እየጠበቁ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ስለዚህ ባሪያ ከተናገረው ሐሳብ አንጻር፣ እነሱም ትጉ ካልሆኑ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸው ሳይገባቸው አይቀርም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 19:43) ምክንያቱም ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት በዙሪያሽ ቅጥር ቀጥረው አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 19:43
በሾለ እንጨት . . . ቅጥር፦ ወይም “አጥር።” ካራክስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ቃሉ “አንድን አካባቢ ለመከለል የሚያገለግል ሹል አጣና ወይም ምሰሶ፤ እንጨት” እንዲሁም “በእንጨት የታጠረ ወታደራዊ ይዞታ፤ አጥር” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። በቲቶ የሚመራው የሮም ሠራዊት በ70 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ዙሪያ የከበባ ግድግዳ ወይም አጥር ሲገነባ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ቲቶ ይህን አጥር የገነባው አይሁዳውያኑ እንዳይሸሹ ለመከላከል፣ እጅ እንዲሰጡ ለመገፋፋትና ምግብ አጥተው ሲቸገሩ እንዲገዙለት ለማድረግ ሲል ነበር። የሮም ወታደሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ ለሚሠሩት አጥር የሚሆን እንጨት ለማግኘት በገጠራማዎቹ አካባቢዎች ያሉትን ዛፎች ሁሉ ጨፍጭፈው ነበር።
(ሉቃስ 20:38) እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 20:38
በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና፦ ወይም “ከእሱ አመለካከት አንጻር ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።” መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የራቁ ሰዎች በሕይወት ቢኖሩም እንኳ ከአምላክ አመለካከት አንጻር ሙታን እንደሆኑ ይናገራል። (ኤፌ 2:1፤ 1ጢሞ 5:6) በተመሳሳይ ሁኔታ የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ ከአምላክ አመለካከት አንጻር አሁንም ሕያዋን ናቸው፤ ምክንያቱም አምላክ እነሱን ለማስነሳት ያለው ዓላማ መፈጸሙ እንደማይቀር የተረጋገጠ ነው።—ሮም 4:16, 17
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 19:11-27) እነሱም እነዚህን ነገሮች እየሰሙ ሳሉ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ ይህን የተናገረው ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የአምላክ መንግሥት ወዲያውኑ የሚገለጥ ስለመሰላቸው ነው። 12 ስለዚህ እንዲህ አለ፦ “አንድ መስፍን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ተነሳ። 13 ከባሪያዎቹ መካከል አሥሩን ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና ‘እስክመጣ ድረስ ነግዱበት’ አላቸው። 14 የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ስለነበር እሱ ከሄደ በኋላ ‘ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው እንዲነግሩላቸው መልእክተኞች ላኩ። 15 “ከጊዜ በኋላ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ሲመጣ ገንዘብ የሰጣቸው ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው። 16 በመሆኑም የመጀመሪያው ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው። 17 ጌታው ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩ ባሪያ! በጣም አነስተኛ በሆነው ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በአሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው። 18 ሁለተኛው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አምስት ምናን አስገኝቷል’ አለ። 19 ይሄኛውንም ‘አንተም በአምስት ከተሞች ላይ ተሹመሃል’ አለው። 20 ሆኖም ሌላኛው መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‘ጌታዬ፣ በጨርቅ ጠቅልዬ የደበቅኩት ምናንህ ይኸውልህ። 21 ይህን ያደረግኩት ጨካኝ ሰው ስለሆንክ ፈርቼህ ነው፤ አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ሰው ነህ።’ 22 ጌታውም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ። ያላስቀመጥኩትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትንም የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንኩ ታውቅ ኖሯል ማለት ነው? 23 ታዲያ ገንዘቤን ለምን ለገንዘብ ለዋጮች አልሰጠህም? እንደዚህ አድርገህ ቢሆን ኖሮ ስመጣ ከነወለዱ እወስደው ነበር።’ 24 “ከዚያም በዚያ ቆመው የነበሩትን ሰዎች ‘ምናኑን ውሰዱበትና አሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው። 25 እነሱ ግን ‘ጌታ ሆይ፣ እሱ እኮ አሥር ምናን አለው’ አሉት። እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ 26 ‘እላችኋለሁ፣ ላለው ሁሉ ተጨማሪ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ላይ ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 27 በተጨማሪም በእነሱ ላይ እንድነግሥ ያልፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ግደሏቸው።’”
ከነሐሴ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 21-22
“መዳናችሁ እየቀረበ ነው”
(ሉቃስ 21:25) “እንዲሁም በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ከባሕሩ ድምፅና ነውጥ የተነሳ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ።
የአምላክ መንግሥት ጠላቶቹን ያጠፋል
9 በሰማይ አካላት ላይ የሚታይ ምልክት። ኢየሱስ “ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ” በማለት ተናግሯል። ሰዎች ብርሃን ወይም መመሪያ ለማግኘት ወደ ሃይማኖት መሪዎች ዘወር ማለታቸው እንደሚያከትም ግልጽ ነው። በዚህ ትንቢት ላይ ኢየሱስ፣ በሰማይ እንግዳ ነገሮች እንደሚታዩም መግለጹ ይሆን? ሊሆን ይችላል። (ኢሳ. 13:9-11፤ ኢዩ. 2:1, 30, 31) ሰዎች እነዚህን ነገሮች ሲመለከቱ ምን ይሰማቸው ይሆን? “የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 21:25፤ ሶፎ. 1:17) ‘ከነገሥታት’ እስከ “ባሪያዎች” ያሉ የአምላክ መንግሥት ጠላቶች “ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።” እንዲሁም መሸሸጊያ ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ይሁን እንጂ ከንጉሣችን ቁጣ ለማምለጥ የሚያስችላቸው መደበቂያ አያገኙም።—ሉቃስ 21:26፤ 23:30፤ ራእይ 6:15-17
(ሉቃስ 21:26) የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።
(ሉቃስ 21:27, 28) ከዚያም የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28 ሆኖም እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።”
“እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ”!
17 “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው’ . . . እንላለን።” (ዕብራውያን 13:6ን አንብብ።) ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን፣ በይሖዋ መታመናችን ድፍረት እንድናገኝ ያስችለናል። ይህ ዓይነቱ ድፍረት ደግሞ አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። እንዲህ ያለው አዎንታዊ አመለካከት በወንድማማች ፍቅራችን ላይ ሲደመር የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማነጽና ለማበረታታት ያስችለናል። (1 ተሰ. 5:14, 15) በታላቁ መከራ ወቅት ዓለም ጭንቅ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ መዳናችን እንደቀረበ ስለምናውቅ “ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን።—ሉቃስ 21:25-28
‘መዳናችሁ እየቀረበ ነው’!
13 ፍየሎቹ “ወደ ዘላለም ጥፋት” እንደሚሄዱ ሲገነዘቡ ምን ያደርጋሉ? “በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።” (ማቴ. 24:30) ይሁንና የክርስቶስ ወንድሞችና ታማኝ አጋሮቻቸው በዚያ ወቅት ምን ይሰማቸዋል? በይሖዋ አምላክና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ስለሚተማመኑ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ ያደርጋሉ፦ “እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።” (ሉቃስ 21:28) በእርግጥም መዳን እንደምናገኝ ስለምንተማመን ብሩህ አመለካከት ይኖረናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 21:33) ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ሉቃስ 21:33
ሰማይና ምድር ያልፋሉ፦ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሰማይና ምድር ለዘላለም እንደሚኖሩ ይናገራሉ። (ዘፍ 9:16፤ መዝ 104:5፤ መክ 1:4) በመሆኑም ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ፣ ሊሆን የማይችለው ነገር ሆኖ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እሱ የተናገራቸው ቃላት መፈጸማቸው እንደማይቀር የሚያሳይ ግነታዊ ዘይቤ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። (ከማቴ 5:18 ጋር አወዳድር።) ሆኖም እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰማይና ምድር በራእይ 21:1 ላይ “የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር” ተብለው የተጠቀሱትን ምሳሌያዊ ሰማይና ምድር የሚያመለክቱም ሊሆኑ ይችላሉ።
ቃሌ . . . ፈጽሞ አያልፍም፦ ወይም “ቃሌ በምንም ዓይነት አያልፍም።” በግሪክኛው ግስ ላይ ሁለት አፍራሽ ቃላት መጨመራቸው የተጠቀሰው ሐሳብ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር እንደሆነ ያሳያል፤ ይህም የኢየሱስ ቃል በምንም ዓይነት እንደማያልፍ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
(ሉቃስ 22:28-30) “ይሁን እንጂ እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል፤ 29 አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ 30 ይኸውም በመንግሥቴ ከማዕዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ እንዲሁም በዙፋን ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እንድትፈርዱ ነው።
“የመንግሥት ካህናት” ትሆናላችሁ
15 ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ በኋላ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፤ ይህ ቃል ኪዳን ብዙ ጊዜ የመንግሥት ቃል ኪዳን ተብሎ ይጠራል። (ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።) ይሖዋ ከሌሎች ጋር ከገባቸው ቃል ኪዳኖች በተለየ ይህ ቃል ኪዳን የተደረገው በኢየሱስና በቅቡዓን ተከታዮቹ መካከል ነው። ኢየሱስ “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ” ብሎ ሲናገር ይሖዋ “በመልከጼዴቅ ሥርዓት መሠረት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” በማለት ከእሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እየጠቀሰ መሆን አለበት።—ዕብ. 5:5, 6
16 ታማኝ የሆኑት 11ዱ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ‘በፈተናዎቹ ከጎኑ ሳይለዩ ቆይተዋል።’ የመንግሥቱ ቃል ኪዳን፣ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚሆኑ እንዲሁም በዙፋኖች ላይ ተቀምጠው ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙና ካህናት ሆነው እንደሚያገለግሉ አረጋግጦላቸዋል። ይሁንና ይህን መብት የሚያገኙት 11ዱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም። ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ ብሎታል፦ “እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥኩ ሁሉ ድል የሚነሳውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።” (ራእይ 3:21) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው የመንግሥቱ ቃል ኪዳን የተደረገው በኢየሱስና በ144,000ዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:4) ይህ ቃል ኪዳን ቅቡዓኑ ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ለመግዛት የሚያስችላቸው ሕጋዊ መሠረት ጥሏል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከአንድ ትልቅ ቤተሰብ የመጣች ሙሽራ በመግዛት ላይ ካለ ንጉሥ ጋር ትዳር እንደምትመሠርት አድርገን እናስብ፤ ሙሽራዋ ንጉሡን ካገባች በኋላ ከእሱ ጋር የመግዛት ሥልጣን ይኖራታል። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የክርስቶስ “ሙሽራ” እንዲሁም ለክርስቶስ የታጩ “ንጽሕት ድንግል” እንደሆኑ ተደርገው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተገልጸዋል።—ራእይ 19:7, 8፤ 21:9፤ 2 ቆሮ. 11:2
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 22:35-53) በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ያለገንዘብ ኮሮጆ፣ ያለምግብ ከረጢትና ያለትርፍ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጎደለባችሁ ነገር ነበር?” እነሱም “ምንም አልጎደለብንም” አሉ። 36 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “አሁን ግን የገንዘብ ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ የምግብ ከረጢት ያለውም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለው ደግሞ መደረቢያውን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። 37 ይህን የምላችሁ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ መፈጸም ስላለበት ነው። ስለ እኔ የተነገረው ነገር ፍጻሜውን እያገኘ ነውና።” 38 እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ይኸው ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት። እሱም “በቂ ነው” አላቸው። 39 ከዚያ ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 40 እዚያም በደረሱ ጊዜ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው። 41 እሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ከእነሱ በመራቅ ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ፤ 42 እንዲህም አለ፦ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” 43 ከዚያም አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። 44 ሆኖም በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ፤ ላቡም መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም ሆኖ ነበር። 45 ከጸለየም በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲሄድ ከሐዘን የተነሳ ደክሟቸው ስለነበር ሲያንቀላፉ አገኛቸው። 46 እሱም “ለምን ትተኛላችሁ? ተነሱ፤ ደግሞም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው። 47 ገና እየተናገረ ሳለ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። 48 ኢየሱስ ግን “ይሁዳ፣ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህ?” አለው። 49 በዙሪያው የነበሩትም አዝማሚያውን ሲያዩ “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸው?” አሉት። 50 እንዲያውም ከመካከላቸው አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው። 51 ኢየሱስ ግን መልሶ “ተዉ!” አለ። ጆሮውንም ዳሶ ፈወሰው። 52 ከዚያም ኢየሱስ እሱን ለመያዝ የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደሱን ሹሞችና ሽማግሌዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ መጣችሁ? 53 በየዕለቱ በቤተ መቅደስ አብሬያችሁ ሳለሁ እኔን ለመያዝ እጃችሁን አላነሳችሁብኝም። ይሁንና ይህ የእናንተ ሰዓትና ጨለማ የሚነግሥበት ሰዓት ነው።”
ከነሐሴ 27–መስከረም 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሉቃስ 23-24
“ይቅር ለማለት ዝግጁ ሁኑ”
(ሉቃስ 23:34) ኢየሱስም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ይል ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ልብሶቹን ለመከፋፈል ዕጣ ተጣጣሉ።
‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
16 ኢየሱስ “ይቅር ባይ” በመሆንም የአባቱን ፍቅር ፍጹም በሆነ ሁኔታ አንጸባርቋል። (መዝሙር 86:5) ተሰቅሎ እያለም እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን አሳይቷል። እጆቹና እግሮቹ በምስማር ተቸንክረው ክብርን በሚነካ ሁኔታ እንዲሞት በተደረገበት ወቅት የተናገረው ቃል ምን ነበር? ይሖዋ የሰቀሉትን ሰዎች እንዲቀስፍለት ተማጽኗል? በፍጹም፤ እንዲያውም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል አባቱን ለምኗል።—ሉቃስ 23:34
(ሉቃስ 23:43) እሱም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።
አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይላል?
ይሖዋ የሚያየው ግለሰቡ ኃጢአት መሥራቱን ብቻ ሳይሆን የሚያሳየውን ዝንባሌ ጭምር ነው። (ኢሳይያስ 1:16-19) ከኢየሱስ አጠገብ ተሰቅለው የነበሩትን ሁለት ወንጀለኞች ለአንድ አፍታ ለማሰብ ሞክር። አንደኛው ሰው “እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው [ኢየሱስ] ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም” በማለት ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ሁለቱም ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል። የዚህ ወንጀለኛ አነጋገር ስለ ኢየሱስ የሚያውቀው ነገር እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን ይህ እውቀቱ በዝንባሌው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳስከተለ አያጠራጥርም። ኢየሱስን “በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ብሎ መማጸኑ በእርግጥም ግለሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳመጣ ያሳያል። ክርስቶስ ልባዊ ለሆነው ለዚህ ልመና ምን ምላሽ ሰጠ? “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።—ሉቃስ 23:41-43
እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ቆም ብለህ አስብ፦ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሞት እንደሚገባው አምኖ ለተቀበለው ሰው የተናገረው ሐሳብ መሐሪ መሆኑን ያንጸባርቃል። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ከዚህ በመነሳት፣ ሰዎች ከዚህ ቀደም የፈጸሙት ነገር ምንም ይሁን ምን እውነተኛ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ኢየሱስም ሆነ አባቱ ይሖዋ ርኅራኄ እንደሚያሳዩአቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 4:7
(ሉቃስ 24:34) እነሱም “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” ይሉ ነበር።
‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’
17 ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ያሳየው ምሕረት ይቅር ባይ መሆኑን የሚያሳይ ልብ የሚነካ ምሳሌ ነው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ከልብ ይወደው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኒሳን 14 በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የመጨረሻ ምሽት ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ” ሲል ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጴጥሮስ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው በመናገር ሦስት ጊዜ ካደው! መጽሐፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስን በካደበት ወቅት የሆነውን ሁኔታ ሲገልጽ “ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው” ይላል። ጴጥሮስ በሠራው ከባድ ኃጢአት ቅስሙ በመሰበሩ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።” በዚያው ዕለት ኢየሱስ ሲሞት ሐዋርያው ‘ጌታዬ ይቅር ብሎኝ ይሆን?’ ብሎ ማሰቡ አይቀርም።—ሉቃስ 22:33, 61, 62
18 ጴጥሮስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ አላስፈለገውም። ኢየሱስ ኒሳን 16 ጠዋት ከሞት የተነሳ ሲሆን የዚያኑ ዕለት ለጴጥሮስ በግል ተገልጦለታል። (ሉቃስ 24:33, 34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:4-8) ኢየሱስ ሽምጥጥ አድርጎ ለካደው ሐዋርያ እንዲህ ያለ ትኩረት የሰጠው ለምንድን ነው? ንስሐ ለገባው ሐዋርያ ማለትም ለጴጥሮስ ያለው ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት እንዳልቀነሰ ሊያረጋግጥለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን ከማጽናናት በተጨማሪ ሌላም ያደረገው ነገር አለ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሉቃስ 23:31) ዛፉ እርጥብ ሆኖ ሳለ እንዲህ ካደረጉ በደረቀ ጊዜማ ምን ይከሰት ይሆን?”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ሉቃስ 23:31
ዛፉ እርጥብ ሆኖ ሳለ . . . በደረቀ ጊዜ፦ ኢየሱስ ስለ አይሁድ ብሔር እየተናገረ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ በአይሁድ ብሔር መካከል ስለነበርና በኢየሱስ የሚያምኑ የተወሰኑ አይሁዳውያን ስለነበሩ ብሔሩ ጥቂት እርጥበት እንደቀረው በመጠውለግ ላይ ያለ ዛፍ ነበር። ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ የሚገደል ከመሆኑም ሌላ ታማኝ የሆኑ አይሁዳውያን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ይሆናሉ። (ሮም 2:28, 29፤ ገላ 6:16) በዚያን ጊዜ የእስራኤል ብሔር በመንፈሳዊ ሙሉ በሙሉ በመሞት ልክ እንደደረቀ ዛፍ ይሆናል።—ማቴ 21:43
(ሉቃስ 23:33) የራስ ቅል ወደተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስን በዚያ ከወንጀለኞቹ ጋር በእንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ወንጀለኞቹም አንዱ በቀኙ ሌላው ደግሞ በግራው ተሰቅለው ነበር።
nwtsty ሚዲያ
ምስማር የተመታበት የእግር አጥንት
ይህ፣ 11.5 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ምስማር የተመታበት የሰው እግር አጥንት ነው። (mwb17.12 5ን ተመልከት።) ፎቶግራፉ ተመሳስሎ የተሠራውን አጥንት ያሳያል። ዋናው አጥንት የተገኘው በ1968 በሰሜናዊ ኢየሩሳሌም በተደረገ ቁፋሮ ወቅት ሲሆን እግሩ ላይ ምስማር የተመታበት ይህ ሰው በሮማውያን ዘመን እንደኖረ ይገመታል። ይህ አጥንት፣ ሮማውያን ወንጀለኞችን በእንጨት ላይ ለመቸንከር ምስማር ይጠቀሙ እንደነበር የሚያሳይ አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃ ነው። ሮማውያን ወታደሮች ኢየሱስ ክርስቶስን በእንጨት ላይ ለመቸንከር የተጠቀሙት እንዲህ ዓይነት ምስማር ሳይሆን አይቀርም። ይህ አጥንት የተገኘው በአንድ የድንጋይ ሣጥን ውስጥ ነው። በዚያ ዘመን፣ የሞተ ሰው በድን ከበሰበሰ በኋላ አፅሙ ተሰብስቦ እንዲህ ባለው የድንጋይ ሣጥን ውስጥ ይቀመጥ ነበር። ይህ ምስማር የተመታበት አጥንት በዚህ የድንጋይ ሣጥን ውስጥ መገኘቱ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የተገደለ ሰው ሊቀበር እንደሚችል ይጠቁማል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሉቃስ 23:1-16) ስለዚህ በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተነስተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት። 2 ከዚያም እንዲህ እያሉ ይከሱት ጀመር፦ “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አግኝተነዋል።” 3 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም መልሶ “አንተው ራስህ እኮ እየተናገርከው ነው” አለው። 4 ከዚያም ጲላጦስ ለካህናት አለቆቹና ለሕዝቡ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ። 5 እነሱ ግን “በመላው ይሁዳ፣ ከገሊላ አንስቶ እስከዚህ ድረስ እያስተማረ ሕዝቡን ይቀሰቅሳል” በማለት አጥብቀው ተናገሩ። 6 ጲላጦስ ይህን ሲሰማ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ። 7 ከሄሮድስ ግዛት የመጣ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ሄሮድስ ላከው። 8 ሄሮድስ ኢየሱስን ሲያየው በጣም ደስ አለው። ስለ እሱ ብዙ ነገር ሰምቶ ስለነበር ለረጅም ጊዜ እሱን ለማየት ይፈልግ ነበር፤ አንዳንድ ተአምራት ሲፈጽም ለማየትም ተስፋ ያደርግ ነበር። 9 በመሆኑም ብዙ ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤ እሱ ግን ምንም መልስ አልሰጠውም። 10 ይሁን እንጂ የካህናት አለቆቹና ጸሐፍት በተደጋጋሚ እየተነሱ አጥብቀው ይከሱት ነበር። 11 ከዚያም ሄሮድስ ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ አቃለለው፤ እንዲሁም ያማረ ልብስ አልብሶ ካፌዘበት በኋላ መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው። 12 በዚያን ዕለት ሄሮድስና ጲላጦስ ወዳጆች ሆኑ፤ ከዚያ በፊት በመካከላቸው ጠላትነት ነበር። 13 ከዚያም ጲላጦስ የካህናት አለቆቹን፣ ገዢዎቹንና ሕዝቡን በአንድነት ጠርቶ 14 እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁት ሕዝቡን ለዓመፅ ያነሳሳል ብላችሁ ነበር። ይኸው በፊታችሁ መረመርኩት፤ ሆኖም በእሱ ላይ ያቀረባችሁትን ክስ የሚደግፍ ምንም ነገር አላገኘሁም። 15 ሄሮድስም ቢሆን ምንም ጥፋት ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶ ልኮታል፤ በመሆኑም ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም። 16 ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”