የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መስከረም 2018
ከመስከረም 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 1-2
“ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምሩን ፈጸመ”
(ዮሐንስ 2:1-3) በሦስተኛውም ቀን በገሊላ በምትገኘው በቃና የሠርግ ድግስ ነበር፤ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። 2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ ተጠርተው ነበር። 3 የወይን ጠጁ እያለቀ ሲሄድ የኢየሱስ እናት “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው።
ክርስቶስ—የአምላክ ኃይል
3 ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምሩን የፈጸመው በገሊላ በምትገኘው በቃና በተከናወነ የሠርግ ድግስ ላይ ነው። በድግሱ ላይ ከተጠበቀው በላይ ብዙ እንግዶች መጥተው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የወይን ጠጅ አለቀ። ከተጠሩት እንግዶች መካከል የኢየሱስ እናት ማርያም ትገኝበታለች። ማርያም ስለ ልጇ በተነገሩት ትንቢቶች ላይ ለዓመታት ስታሰላስል እንደቆየች ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ልጇ ‘የልዑሉ አምላክ ልጅ’ ተብሎ እንደሚጠራ ታውቃለች። (ሉቃስ 1:30-32፤ 2:52) ማርያም፣ ኢየሱስ ለሰዎች እስካሁን ያላሳየው ኃይል እንዳለው ተማምና ይሆን? ያም ሆነ ይህ ማርያምና ኢየሱስ ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እንዳዘኑላቸውና ከእፍረት ሊታደጓቸው እንደፈለጉ አሳይተዋል። ተጋቢዎቹ ለእንግዶች ጥሩ መስተንግዶ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ኢየሱስ ያውቃል። በመሆኑም 380 ሊትር የሚሆነውን ውኃ በተአምር ወደ ‘ጥሩ የወይን ጠጅ’ ለወጠው። (ዮሐንስ 2:3, 6-11ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ተአምር የመፈጸም ግዴታ ነበረበት? በፍጹም። ይህን ያደረገው ለሰዎች ስለሚያስብና ለጋስ የሆነውን በሰማይ ያለውን አባቱን ምሳሌ ስለተከተለ ነው።
(ዮሐንስ 2:4-11) ኢየሱስ ግን “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል? ሰዓቴ ገና አልደረሰም” አላት። 5 እናቱም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። 6 የአይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት በሚያዘው መሠረት እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት የፈሳሽ መለኪያዎች የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት የውኃ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር። 7 ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። እነሱም እስከ አፋቸው ድረስ ሞሏቸው። 8 ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” አላቸው። እነሱም ወስደው ሰጡት። 9 የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ 10 እንዲህ አለው፦ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል።” 11 ኢየሱስ ከምልክቶቹ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ተአምር በገሊላ በምትገኘው በቃና ፈጸመ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእሱ አመኑ።
ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያ ተአምር
ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያው ተአምር ይህ ነው። አዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲያዩ በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ተጠናከረ። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከእናቱና ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ከገሊላ ባሕር በስተ ሰሜን ምዕራብ ወደምትገኘው ቅፍርናሆም የተባለች ከተማ ተጓዘ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 1:1) በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር፤ ቃልም አምላክ ነበር።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 1:1
ቃል፦ ወይም “ሎጎስ።” ግሪክኛው፣ ሆ ሎጎስ። እዚህ ላይ የገባው የማዕረግ ስም ሆኖ ነው፤ በዮሐ 1:14 ላይ እና በራእይ 19:13 ላይም ተሠርቶበታል። ዮሐንስ ይህ የማዕረግ ስም የተሰጠው ለኢየሱስ እንደሆነ ገልጿል። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር በነበረበት ወቅት፣ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድራዊ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜና በሰማይ ከፍ ያለ ቦታ ከተሰጠው በኋላ በዚህ የማዕረግ ስም ተጠርቷል። ኢየሱስ፣ አምላክ ለሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታቱና ለሰው ልጆች መረጃ እንዲሁም መመሪያ የሚያስተላልፍበት ቃል ወይም ቃል አቀባይ ሆኖ አገልግሏል። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ይሖዋ በቃል ማለትም ቃል አቀባዩ በሆነው መልአክ አማካኝነት የሰው ልጆችን ያነጋግር እንደነበር ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—ዘፍ 16:7-11፤ 22:11፤ 31:11፤ ዘፀ 3:2-5፤ መሳ 2:1-4፤ 6:11, 12፤ 13:3
ጋር፦ ቃል በቃል “አቅራቢያ።” ፕሮስ የሚለው የግሪክኛው መስተዋድድ በዚህ አገባቡ አጠገብ መሆንንና መቀራረብን ያመለክታል። በተጨማሪም ሁለት የተለያዩ አካላትን የሚያመለክት ሲሆን በዚህ ጥቅስ ላይ ቃልንና ብቸኛ የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ቃልም አምላክ ነበር፦ ወይም “ቃልም መለኮት [ወይም “እንደ አምላክ ያለ”] ነበር።” ዮሐንስ እዚህ ላይ የተናገረው ሐሳብ ‘የቃልን’ (ግሪክኛው፣ ሆ ሎጎስ፤ በዚህ ጥቅስ ሥር የሚገኘውን ቃል የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት) ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይ የሚገልጽ ነው። ቃል “አምላክ፤ እንደ አምላክ ያለ፤ መለኮት፤ መለኮታዊ አካል” ተብሎ የተጠራው አምላክ ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር የተጠቀመበት የበኩር ልጁ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉ የላቀ ቦታ ስላለው ነው። በርካታ ተርጓሚዎች “ቃልም አምላክ [God] ነበር” ብለው በመተርጎም ኢየሱስን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል አድርገውታል። ሆኖም ዮሐንስ “ቃል” ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል ነው ማለቱ እንዳልነበር የሚያሳዩ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ “ቃልም አምላክ ነበር” ከሚለው ዓረፍተ ነገር በፊትም ሆነ በኋላ ያሉት ዓረፍተ ነገሮች ቃል “ከአምላክ ጋር” እንደነበር ይገልጻሉ። በተጨማሪም ቴኦስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በቁጥር 1 እና 2 ላይ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። በመጀመሪያውና በሦስተኛው ላይ ቴኦስ ከሚለው ቃል በፊት የግሪክኛው ጽሑፍ ጠቃሽ አመልካች የሚጨምር ሲሆን በሁለተኛው ላይ ግን ጠቃሽ አመልካች አይጨምርም። በርካታ ምሁራን ከሁለተኛው ቴኦስ በፊት ጠቃሽ አመልካች አለመኖሩ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር እንደሆነ ይስማማሉ። በዚህ አገባብ፣ ጠቃሽ አመልካች ሲጨመር ቴኦስ የሚለው ቃል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ያመለክታል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሰዋስዋዊ አወቃቀር፣ ጠቃሽ አመልካች ካልተጨመረ ቴኦስ ባሕርይን ማለትም ‘የቃልን’ ባሕርይ የሚያመለክት ቃል ይሆናል። በመሆኑም በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በፈረንሳይኛ የሚገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ከአዲስ ዓለም ትርጉም ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይኸውም ቃል “አምላክ [a god]፤ መለኮት፤ መለኮታዊ አካል፤ መለኮታዊ፤ እንደ አምላክ ያለ” እንደሆነ በሚገልጽ መንገድ ተርጉመውታል። የኮፕቲክ ቋንቋ ቀበሌኛዎች በሆኑት የሳሂዲክና የቦሄሪክ ቋንቋዎች የተዘጋጁት የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ትርጉሞችም (በሦስተኛውና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጁ እንደሆኑ ይገመታል) በዮሐ 1:1 ላይ፣ የመጀመሪያውን ቴኦስ የተረጎሙት ከሁለተኛው ቴኦስ በተለየ መንገድ ሲሆን ይህም በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ያለውን አተረጓጎም የሚደግፍ ነው። እነዚህ አተረጓጎሞች “ቃል” ከአምላክ ጋር ተመሳሳይ ባሕርይ እንዳለው ጎላ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው እንጂ ከአባቱ ማለትም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል እንደሆነ የሚያሳዩ አይደሉም። ከዚህ ጥቅስ ጋር በሚስማማ መልኩ ቆላ 2:9 “መለኮታዊው ባሕርይ በተሟላ ሁኔታ” በክርስቶስ ውስጥ እንደሚኖር ይናገራል። በተጨማሪም 2ጴጥ 1:4 እንደሚለው ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙት ተባባሪ ወራሾችም ጭምር “ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች” ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ፣ ቴኦስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “አምላክ” ተብለው የሚተረጎሙትና “ኃያል የሆነው፤ ብርቱ የሆነው” የሚል መሠረታዊ ትርጉም እንደሚያስተላልፉ የሚታመኑት ኤል እና ኤሎሂም የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት አቻ ሆኖ ተሠርቶበታል። እነዚህ የዕብራይስጥ ቃላት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ፣ ከሌሎች አማልክትና ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ተሠርቶባቸዋል። ቃል “አምላክ (a god)” ወይም “ኃያል የሆነው” መባሉ መሲሑ “ኃያል አምላክ” (“ሁሉን ቻይ አምላክ” አይደለም) ተብሎ እንደሚጠራና ተገዢዎቹ የመሆን መብት ላገኙ ሁሉ “የዘላለም አባት” እንደሚሆን ከሚናገረው ከኢሳ 9:6 ትንቢት ጋር ይስማማል። ደግሞም ይህ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርገው የአባቱ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት” ነው።—ኢሳ 9:7
(ዮሐንስ 1:29) በማግስቱ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 1:29
የአምላክ በግ፦ ኢየሱስ ከተጠመቀና በዲያብሎስ ተፈትኖ ከተመለሰ በኋላ መጥምቁ ዮሐንስ “የአምላክ በግ” በማለት አስተዋውቆታል። ይህ አገላለጽ የሚገኘው እዚህና ዮሐ 1:36 ላይ ብቻ ነው። (ተጨማሪ መረጃ ሀ7ን ተመልከት።) ኢየሱስ ከበግ ጋር መመሳሰሉ ተገቢ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች ኃጢአተኛ መሆናቸውን አምነው እንደተቀበሉ ለማሳየትና ወደ አምላክ ለመቅረብ በጎችን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ እንደነበር የሚናገሩ በርካታ ዘገባዎች አሉ። ይህም ኢየሱስ ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን ለሰው ልጆች አሳልፎ በመስጠት ለሚከፍለው መሥዋዕት ጥላ ሆኖ አገልግሏል። “የአምላክ በግ” የሚለው አገላለጽ በመንፈስ መሪነት በተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተጠቀሱ ሐሳቦችን የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። መጥምቁ ዮሐንስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ የነበረ እንደመሆኑ መጠን “የአምላክ በግ” የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመው የሚከተሉትን ነገሮች በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፦ አብርሃም በልጁ በይስሐቅ ምትክ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን አውራ በግ (ዘፍ 22:13)፣ በግብፅ ባርነት የነበሩት እስራኤላውያን መዳን ለማግኘት ሲሉ ያረዱትን የፋሲካ በግ (ዘፀ 12:1-13) ወይም በኢየሩሳሌም ባለው የአምላክ መሠዊያ ላይ ጠዋትና ማታ ይቀርብ የነበረውን ተባዕት የበግ ጠቦት (ዘፀ 29:38-42)። በተጨማሪም ዮሐንስ፣ የይሖዋ አገልጋይ “እንደ በግ ለመታረድ [እንደሚነዳ]” የሚገልጸውን የኢሳይያስን ትንቢት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (ኢሳ 52:13፤ 53:5, 7, 11) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ኢየሱስን “የፋሲካችን በግ” በማለት ጠርቶታል። (1ቆሮ 5:7) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም” ስለሆነው ስለ ክርስቶስ “ውድ ደም” ተናግሯል። (1ጴጥ 1:19) ከዚህም ሌላ ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከ25 ጊዜ በላይ “በጉ” ተብሎ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተገልጿል።—አንዳንድ ምሳሌዎች፦ ራእይ 5:8፤ 6:1፤ 7:9፤ 12:11፤ 13:8፤ 14:1፤ 15:3፤ 17:14፤ 19:7፤ 21:9፤ 22:1
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 1:1-18) በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር፤ ቃልም አምላክ ነበር። 2 እሱም በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር ነበር። 3 ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ በኩል ነው፤ ያለእሱ ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም። 4 በእሱ አማካኝነት ሕይወት ወደ ሕልውና መጥቷል፤ ይህ ሕይወት ደግሞ የሰው ብርሃን ነበር። 5 ብርሃኑም በጨለማ እየበራ ነው፤ ጨለማውም አላሸነፈውም። 6 ከአምላክ የተላከ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም ዮሐንስ ይባላል። 7 ይህ ሰው ስለ ብርሃኑ ይመሠክር ዘንድ ምሥክር ሆኖ መጣ፤ ይህን ያደረገው ሁሉም ዓይነት ሰዎች በእሱ በኩል እንዲያምኑ ነው። 8 ያ ብርሃን እሱ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ እሱ የመጣው ስለ ብርሃኑ ሊመሠክር ነው። 9 ለሁሉም ዓይነት ሰው ብርሃን የሚሰጠው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር። 10 እሱም በዓለም ነበረ፤ ዓለምም ወደ ሕልውና የመጣው በእሱ በኩል ነው፤ ሆኖም ዓለም አላወቀውም። 11 ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። 12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ስላመኑ የአምላክ ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው። 13 እነሱም የተወለዱት ከአምላክ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አይደለም። 14 ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ኖረ፤ አንድያ ልጅ ከአባቱ እንደሚያገኘው ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ እሱም መለኮታዊ ሞገስንና እውነትን ተሞልቶ ነበር። 15 (ዮሐንስ ስለ እሱ መሥክሯል፤ እንዲያውም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “‘ከእኔ ኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ብዬ የተናገርኩት ስለ እሱ ነው።”) 16 ከእሱ የጸጋ ሙላት የተነሳ ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። 17 ምክንያቱም ሕጉ የተሰጠው በሙሴ በኩል ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን የመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። 18 በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም፤ ስለ እሱ የገለጸልን ከአብ ጎን ያለውና አምላክ የሆነው አንድያ ልጁ ነው።
ከመስከረም 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 3-4
“ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት መሠከረ”
(ዮሐንስ 4:6, 7) ደግሞም በዚያ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም ከጉዞው የተነሳ ደክሞት ስለነበር በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። 7 አንዲት የሰማርያ ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 4:6
ደክሞት ስለነበር፦ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ኢየሱስ ‘እንደደከመው’ የተገለጸው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ሰዓቱ ከቀኑ 6፡00 ገደማ ሲሆን ኢየሱስ በዚያን ዕለት ጠዋት በይሁዳ ከሚገኘው የዮርዳኖስ ሸለቆ ተነስቶ በሰማርያ እስካለው ሲካር ድረስ 900 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ከፍታ ያለውን አቀበት ተጉዞ ነበር።—ዮሐ 4:3-5፤ ተጨማሪ መረጃ ሀ7ን ተመልከት።
(ዮሐንስ 4:21-24) ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት ይመጣል። 22 እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ፤ እኛ ግን መዳን የሚጀምረው ከአይሁዳውያን ስለሆነ የምናውቀውን እናመልካለን። 23 ይሁንና እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው። 24 አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።”
(ዮሐንስ 4:39-41) ሴትየዋ “ያደረግኩትን ሁሉ ነገረኝ” ብላ ስለመሠከረች ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእሱ አመኑ። 40 ሳምራውያኑም ወደ እሱ በመጡ ጊዜ አብሯቸው እንዲቆይ ለመኑት፤ እሱም በዚያ ሁለት ቀን ቆየ። 41 በመሆኑም ሌሎች ብዙ ሰዎች ከተናገረው ቃል የተነሳ አመኑ፤
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 3:29) ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት። ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 3:29
የሙሽራው ጓደኛ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሙሽራው የቅርብ ወዳጅ የሙሽራው ሕጋዊ ወኪል ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ የሠርጉን ዝግጅት ከማድረግ ጋር በተያያዘ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ሙሽራውንና ሙሽራይቱን ያጣመራቸው እሱ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በሠርጉ ዕለት አጃቢዎች ድግሱ ወደተደገሰበት ቤት ማለትም ወደ ሙሽራው ወይም ወደ አባቱ ቤት ይሄዳሉ። የሙሽራው ጓደኛ በዚህ ድግስ ላይ ሙሽራው ከሙሽራይቱ ጋር ሲነጋገር ሲሰማ ኃላፊነቱን በተሳካ ሁኔታ እንደተወጣ ስለሚሰማው በሙሽራው ድምፅ ይደሰታል። መጥምቁ ዮሐንስ ራሱን ‘ከሙሽራው ጓደኛ’ ጋር አመሳስሏል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሙሽራው ኢየሱስ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በቡድን ደረጃ ደግሞ ምሳሌያዊቷን ሙሽራ ያመለክታሉ። መጥምቁ ዮሐንስ ‘የሙሽራይቱ’ ክፍል የሚሆኑትን የመጀመሪያዎቹን አባላት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማስተዋወቅ ለመሲሑ መንገድ አዘጋጅቷል። (ዮሐ 1:29, 35፤ 2ቆሮ 11:2፤ ኤፌ 5:22-27፤ ራእይ 21:2, 9) “የሙሽራው ጓደኛ” ሙሽራውንና ሙሽራይቱን በተሳካ ሁኔታ በማስተዋወቅ ዓላማውን ዳር ካደረሰ በኋላ የሚጫወተው የተለየ ሚና አይኖርም። በተመሳሳይም ዮሐንስ ከኢየሱስ አንጻር ስላለው ቦታ ሲገልጽ “እሱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ እኔ ግን እየቀነስኩ መሄድ አለብኝ” ብሏል።—ዮሐ 3:30
(ዮሐንስ 4:10) ኢየሱስም መልሶ “የአምላክን ነፃ ስጦታ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም የሕይወት ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 4:10
ሕያው ውኃ፦ ይህ የግሪክኛ አገላለጽ ቃል በቃል ወራጅ ውኃን፣ የምንጭ ውኃን ወይም ጉድጓድ ውስጥ የተጠራቀመን የምንጭ ውኃ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይህ አገላለጽ ከታቆረ የጉድጓድ ውኃ የተለየ ነው። ዘሌ 14:5 ላይ “ወራጅ ውኃ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ ቃል በቃል “ሕያው ውኃ” የሚል ትርጉም አለው። በኤር 2:13 እና 17:13 ላይ ይሖዋ “የሕያው ውኃ” ማለትም ሕይወት ሰጪ የሆነው ምሳሌያዊ ውኃ “ምንጭ” እንደሆነ ተገልጿል። ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር “ሕያው ውኃ” የሚለውን አገላለጽ የተጠቀመበት በምሳሌያዊ መንገድ ቢሆንም ሴትየዋ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ቃል በቃል ተረድታው እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።—ዮሐ 4:11
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 4:1-15) ጌታ፣ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ደቀ መዛሙርት እያፈራና እያጠመቀ መሆኑን ፈሪሳውያን እንደሰሙ ባወቀ ጊዜ፣ 2 (እርግጥ ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም) 3 ይሁዳን ለቆ እንደገና ወደ ገሊላ ሄደ። 4 ሆኖም በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት። 5 ስለሆነም ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው መሬት አጠገብ ወዳለችው ሲካር ወደተባለች የሰማርያ ከተማ መጣ። 6 ደግሞም በዚያ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም ከጉዞው የተነሳ ደክሞት ስለነበር በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር። 7 አንዲት የሰማርያ ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት። 8 (ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማዋ ሄደው ነበር።) 9 ሳምራዊቷም “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” አለችው። (ይህን ያለችው አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ስላልነበራቸው ነው።) 10 ኢየሱስም መልሶ “የአምላክን ነፃ ስጦታ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም የሕይወት ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። 11 እሷም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ውኃ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጉድጓዱ ደግሞ ጥልቅ ነው። ታዲያ ይህን የሕይወት ውኃ ከየት ታገኛለህ? 12 አንተ ይህን የውኃ ጉድጓድ ከሰጠን እንዲሁም ከልጆቹና ከከብቶቹ ጋር ከዚህ ጉድጓድ ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህ?” 13 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል። 14 እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ፈጽሞ አይጠማም፤ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።” 15 ሴትየዋም “ጌታዬ፣ እንዳልጠማም ሆነ ውኃ ለመቅዳት ወደዚህ ቦታ እንዳልመላለስ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው።
ከመስከረም 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 5-6
“በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስታችሁ ኢየሱስን ተከተሉ”
(ዮሐንስ 6:9-11) “አምስት የገብስ ዳቦና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ አንድ ትንሽ ልጅ እዚህ አለ። ይህ ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይበቃል?” 10 ኢየሱስም “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ። በስፍራው ብዙ ሣር ስለነበር ሰዎቹ በዚያ ተቀመጡ፤ ወንዶቹም 5,000 ያህል ነበሩ። 11 ኢየሱስ ዳቦዎቹን ወስዶ ካመሰገነ በኋላ በዚያ ለተቀመጡት ሰዎች አከፋፈለ፤ ትናንሾቹን ዓሣዎችም ልክ እንደዚሁ አደለ፤ እነሱም የሚፈልጉትን ያህል ወሰዱ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 6:10
ሰዎቹ በዚያ ተቀመጡ፤ ወንዶቹም 5,000 ያህል ነበሩ፦ ስለዚህ ተአምር በሚናገረው ዘገባ ላይ “ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ” የሚለውን መግለጫ የሚጨምረው የማቴዎስ ዘገባ ብቻ ነው። (ማቴ 14:21) ተአምራዊ በሆነ መንገድ ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ከ15,000 በላይ ሊሆን ይችላል።
(ዮሐንስ 6:14) ሰዎቹም ኢየሱስ የፈጸመውን ተአምራዊ ምልክት ባዩ ጊዜ “ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረለት ነቢይ በእርግጥ ይህ ነው” አሉ።
(ዮሐንስ 6:24) ሕዝቡ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን ባወቁ ጊዜ በጀልባዎቻቸው ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 6:14
ትንቢት የተነገረለት ነቢይ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን በዘዳ 18:15, 18 ላይ የተጠቀሰው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ መሲሕ ሆኖ እንደሚገለጥ ይጠብቁ ነበር። ወደ ዓለም እንደሚመጣ የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ፣ በተስፋ ይጠበቅ የነበረውን የመሲሑን መገለጥ የሚያመለክት ይመስላል። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኙትን ክንውኖች የዘገበው ዮሐንስ ብቻ ነው።
(ዮሐንስ 6:25-27) ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ “ረቢ፣ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት። 26 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የምትፈልጉኝ ተአምራዊ ምልክት ስላያችሁ ሳይሆን ዳቦ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው። 27 ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ፤ ምክንያቱም አብ ይኸውም አምላክ ራሱ እሱን እንደተቀበለው አሳይቷል።”
(ዮሐንስ 6:54) ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ፤
(ዮሐንስ 6:60) ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን ሲሰሙ “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።
(ዮሐንስ 6:66-69) ከዚህም የተነሳ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ። 67 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን “እናንተም መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 68 ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። 69 አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 6:27, 54
ለሚጠፋ ምግብ . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ፦ ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች እሱንና ደቀ መዛሙርቱን የሚከተሏቸው ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ብቻ እንደሆነ ተረድቶ ነበር። ሰብዓዊ ምግብ ሰዎች በየዕለቱ በሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ሲሆን ከአምላክ ቃል የሚገኘው “ምግብ” ግን ለዘላለም በሕይወት መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። ኢየሱስ ሕዝቡን “የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ” እንዲሠሩ ማለትም መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጥረት እንዲያደርጉና በሚማሩት ነገር ላይ እምነት እንዲያሳድሩ አበረታቷቸዋል።—ማቴ 4:4፤ 5:3፤ ዮሐ 6:28-39
ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ፦ በዙሪያው ያለው ሐሳብ እንደሚጠቁመው የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት የሚለው አገላለጽ በእሱ ላይ እምነት ማሳደርን የሚያመለክት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። (ዮሐ 6:35, 40) ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በ32 ዓ.ም. ነበር፤ በመሆኑም ከአንድ ዓመት በኋላ ስለሚያቋቁመው የጌታ ራት እየተናገረ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ይህን የተናገረው “የአይሁዳውያን በዓል የሆነው ፋሲካ” ከመከበሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለነበር (ዮሐ 6:4) አድማጮቹ በቅርቡ ስለሚከበረው በዓልና እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው በወጡበት ምሽት የበጉ ደም ሕይወታቸውን በማዳን ረገድ ስለተጫወተው ሚና አስበው መሆን አለበት። (ዘፀ 12:24-27) ኢየሱስ ልክ እንደ በጉ ደም ሁሉ የእሱም ደም ደቀ መዛሙርቱ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጎላ አድርጎ መናገሩ ነበር።
በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለን
13 የሆነ ሆኖ ሰዎቹ ኢየሱስን ለመከተል ቆርጠው ስለነበር ዮሐንስ እንደገለጸው “ከባሕሩ ማዶ” አገኙት። ኢየሱስን ለማንገሥ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸው እያወቁ ለምን ተከተሉት? ብዙዎቹ ይሖዋ በሙሴ ዘመን በምድረ በዳ ስላደረጋቸው ቁሳዊ ዝግጅቶች በቀጥታ በመናገር አመለካከታቸው ሥጋዊ እንደሆነ አሳይተዋል። ኢየሱስ ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል የፈለጉ ይመስላል። ኢየሱስ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ መሆኑን በማስተዋሉ አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት መንፈሳዊ እውነት ያስተምራቸው ጀመር። (ዮሐንስ 6:17, 24, 25, 30, 31, 35-40) አንዳንዶቹ ግን በተለይ የሚከተለውን ምሳሌ ሲነግራቸው አጉረመረሙ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”—ዮሐ. 6:53, 54
14 ብዙውን ጊዜ የኢየሱስ ምሳሌዎች ሰዎች በእርግጥ ከአምላክ ጋር ለመሄድ መፈለግ አለመፈለጋቸውን እንዲያሳዩ የሚያደርጉ ነበሩ። ይህም ምሳሌ ከዚህ የተለየ ዓላማ አልነበረውም። በመሆኑም ተቃውሞ አስነስቷል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ ‘ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?’ አሉ።” ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት መንፈሳዊ ትርጉም ለመረዳት እንዲሞክሩ ሲያበረታታቸው እንዲህ አለ:- “መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው።” አብዛኞቹ ሰዎች ግን ለመስማት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ዘገባው እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።”—ዮሐ. 6:60, 63, 66
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 6:44) የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 6:44
ካልሳበው፦ “መሳብ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ዓሣ የያዘን መረብ ከመጎተት ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ቢሆንም (ዮሐ 21:6, 11) አምላክ ሰዎችን ያለፍላጎታቸው ወደ ራሱ እንደሚጎትታቸው አያመለክትም። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ይሖዋ በጥንት ጊዜ ለነበሩ ሕዝቦቹ “በታማኝ ፍቅር ወደ እኔ ሳብኩሽ” በማለት የተናገረውን በኤር 31:3 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም እዚህ ቦታ ላይ ተመሳሳይ የግሪክኛ ግስ ይጠቀማል።) ዮሐ 12:32 ኢየሱስም በተመሳሳይ መንገድ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስብ ይናገራል። ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት እንደሰጣቸው ይጠቁማሉ። እያንዳንዱ ሰው ይሖዋን ከማገልገል ጋር በተያያዘ የራሱን ምርጫ ማድረግ ይችላል። (ዘዳ 30:19, 20) አምላክ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች በደግነት ወደ ራሱ ይስባቸዋል። (መዝ 11:5፤ ምሳሌ 21:2፤ ሥራ 13:48) ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው መልእክትና በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ነው። በዮሐ 6:45 ላይ የተጠቀሰው ከኢሳ 54:13 ላይ የተወሰደው ትንቢት የሚናገረው አብ ስለሳባቸው ሰዎች ነው።—ከዮሐ 6:65 ጋር አወዳድር።
(ዮሐንስ 6:64) ነገር ግን ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ያለው የማያምኑት እነማን እንደሆኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ከመጀመሪያው ያውቅ ስለነበረ ነው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 6:64
ኢየሱስ . . . ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው . . . ያውቅ ስለነበረ፦ ኢየሱስ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ እየተናገረ ነበር። ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ አባቱ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12-16) በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ይሁዳ ለአምላክ ታማኝ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት ትንቢቶች በመነሳት የቅርብ ወዳጁ አሳልፎ እንደሚሰጠው ያውቅ ነበር። (መዝ 41:9፤ 109:8፤ ዮሐ 13:18, 19) ኢየሱስ ልብንና ሐሳብን ማንበብ ስለሚችል ይሁዳ መጥፎ ጎዳና መከተል ሲጀምር ለውጡን ማስተዋል ችሎ ነበር። (ማቴ 9:4) አምላክ ነገሮችን አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን በመጠቀም ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ከሃዲ እንደሚሆን አውቆ ነበር። ሆኖም ይህን ክህደት የሚፈጽመው ይሁዳ እንዲሆን አስቀድሞ ተወስኖበታል ብሎ ማሰብ ከአምላክ ባሕርይም ሆነ ከዚህ በፊት ነገሮችን ካከናወነበት መንገድ ጋር ይጋጫል።
ከመጀመሪያው፦ ይህ አገላለጽ ይሁዳ የተወለደበትን ወይም ኢየሱስ ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ ካደረ በኋላ እሱን ሐዋርያ አድርጎ የመረጠበትን ጊዜ የሚያመለክት አይደለም። (ሉቃስ 6:12-16) ከዚህ ይልቅ በይሁዳ ልብ ውስጥ የአታላይነት ባሕርይ ማቆጥቆጥ የጀመረበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው፤ ኢየሱስ ይህን ወዲያውኑ ማስተዋል ችሎ ነበር። (ዮሐ 2:24, 25፤ ራእይ 1:1፤ 2:23) ይህም ይሁዳ ክህደቱን የፈጸመው ድንገት ተነስቶ ሳይሆን አስቀድሞ አስቦበትና አቅዶበት እንደሆነ ያሳያል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “መጀመሪያ” (ግሪክኛው፣ አርክሄ) የሚለው ቃል ትርጉም አንጻራዊ ሲሆን እንደየአገባቡ የተለያየ መልእክት ያስተላልፋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2ጴጥ 3:4 ላይ “መጀመሪያ” የሚለው ቃል የፍጥረትን መጀመሪያ ያመለክታል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ቃሉ ይበልጥ አጠር ያለን ጊዜ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ጴጥሮስ “መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደወረደው ሁሉ [በአሕዛብም] ላይ ወረደ” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 2:1-4) እዚህ ላይ ጴጥሮስ፣ ስለተወለደበት ወይም ሐዋርያ እንዲሆን ስለተመረጠበት ጊዜ እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ለአንድ የተለየ ዓላማ መፍሰስ ‘ስለጀመረበት’ ጊዜ ማለትም ስለ 33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ ዕለት እየተናገረ ነበር። (ሥራ 2:1-4) “መጀመሪያ” የሚለው ቃል እንደየአገባቡ የተለያየ ትርጉም ሊያስተላልፍ እንደሚችል የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን በሉቃስ 1:2፤ በዮሐ 15:27 እና በ1ዮሐ 2:7 ላይ መመልከት ይቻላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 6:41-59) ከዚያም አይሁዳውያን “ከሰማይ የወረደው ምግብ እኔ ነኝ” በማለቱ በኢየሱስ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር። 42 ደግሞም “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለም? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለም እንዴ? ታዲያ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?” አሉ። 43 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ። 44 የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ። 45 ነቢያት በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ‘ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፏል። ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46 ከአምላክ ዘንድ ከመጣው በስተቀር አብን ያየ አንድም ሰው የለም፤ እሱ አብን አይቶታል። 47 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። 48 “ሕይወት የሚያስገኘው ምግብ እኔ ነኝ። 49 አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። 50 ከሰማይ የወረደውን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን አይሞትም። 51 ከሰማይ የወረደው ሕያው ምግብ እኔ ነኝ። ከዚህ ምግብ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል፤ ምግቡ ደግሞ ለዓለም ሕይወት ስል የምሰጠው ሥጋዬ ነው።” 52 አይሁዳውያንም “ይህ ሰው እንዴት ሥጋውን እንድንበላ ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። 53 በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በመጨረሻውም ቀን ከሞት አስነሳዋለሁ፤ 55 ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56 ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ ከእኔ ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እኔም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረኛል። 57 ሕያው የሆነው አብ እንደላከኝና እኔም ከእሱ የተነሳ በሕይወት እንደምኖር ሁሉ የእኔን ሥጋ የሚበላም ከእኔ የተነሳ በሕይወት ይኖራል። 58 ከሰማይ የወረደው ምግብ ይህ ነው። ይህም አባቶቻችሁ በበሉበት ጊዜ እንደነበረው አይደለም፤ እነሱ ቢበሉም እንኳ ሞተዋል። ይህን ምግብ የሚበላ ሁሉ ግን ለዘላለም ይኖራል።” 59 ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኩራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።
ከመስከረም 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 7-8
“ኢየሱስ አባቱ እንዲከበር አድርጓል”
(ዮሐንስ 7:15-18) አይሁዳውያንም በጣም ተገርመው “ይህ ሰው ትምህርት ቤት ገብቶ ሳይማር ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዴት እንዲህ ሊያውቅ ቻለ?” አሉ። 16 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው። 17 ማንም የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልግ ከሆነ ይህ ትምህርት ከአምላክ የመጣ ይሁን ከራሴ ለይቶ ያውቃል። 18 ከራሱ አመንጭቶ የሚናገር ሁሉ ራሱ እንዲከበር ይፈልጋል፤ የላከው እንዲከበር የሚፈልግ ሁሉ ግን እሱ እውነተኛ ነው፤ በእሱም ዘንድ ዓመፅ የለም።
“ተብሎ ተጽፏል”
5 ኢየሱስ የሚናገረው መልእክት ምንጭ ማን እንደሆነ ሰዎች እንዲያውቁ ይፈልግ ነበር። “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) በሌላ ጊዜ ደግሞ ‘በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር አላደርግም፤ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ ነው’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:28) በተጨማሪም “የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም፤ ሆኖም ሥራውን እየሠራ ያለው ከእኔ ጋር አንድነት ያለው አብ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:10) ኢየሱስ ከላይ የተናገራቸው ሐሳቦች እውነት መሆናቸውን የሚያሳየው አንዱ ማስረጃ በጽሑፍ ከሰፈረው የአምላክ ቃል በተደጋጋሚ ጊዜ መጥቀሱ ነው።
6 በጽሑፍ የሰፈሩትን ኢየሱስ የተናገራቸውን ሐሳቦች በጥልቀት ስንመረምር እነዚህ ሐሳቦች ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ አሊያም በተዘዋዋሪ የተጠቀሱ መሆናቸውን እንረዳለን። እንዲሁ ስናስበው ይህ ምንም የሚያስገርም እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። እንዲያውም ኢየሱስ ሲያስተምርና ሲሰብክ በቆየበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ከነበሩት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት በሙሉ ለምን አልጠቀሰም ብለህ ታስብ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እንደዚያ አድርጎም ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች መካከል በጽሑፍ የሰፈሩት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን አትዘንጋ። (ዮሐንስ 21:25) እንዲያውም ኢየሱስ የተናገራቸውን በጽሑፍ የሰፈሩ ሐሳቦች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አንብበህ ልትጨርስ ትችላለህ። እስቲ አሁን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ማስረጃ እየጠቀስክ ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ ማብራራት ትችል እንደሆነ አስብ! ደግሞም ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ ጥቅልሎቹን በቅርብ ማግኘት አይችልም ነበር። የታወቀውን የተራራ ስብከቱን ባቀረበበት ወቅት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በጣም ብዙ ጊዜ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጠቅሷል፤ ሁሉንም የጠቀሰው በአእምሮው በማስታወስ ነው!
(ዮሐንስ 7:28, 29) ከዚያም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “እኔ ማን እንደሆንኩም ሆነ ከየት እንደመጣሁ ታውቃላችሁ። የመጣሁትም በራሴ ተነሳስቼ አይደለም፤ ሆኖም የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ እናንተም አታውቁትም። 29 እኔ ግን የእሱ ተወካይ ሆኜ የመጣሁ ስለሆንኩ አውቀዋለሁ፤ የላከኝም እሱ ነው።”
(ዮሐንስ 8:29) እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”
የዓለምን መንፈስ ሳይሆን የአምላክን መንፈስ ተቀበሉ
19 ይሖዋን በሙሉ ልባችሁ ታዘዙ። ኢየሱስ ምንጊዜም የሚያደርገው አባቱን የሚያስደስተውን ነገር ነበር። በአንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ፣ አንድን ጉዳይ ሊይዝ ያሰበበት መንገድ አባቱ ከሚፈልገው የተለየ ነበር። ያም ሆኖ ለአባቱ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ምንም ሳያመነታ በሙሉ ልብ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 22:42) ‘አምላክን መታዘዝ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እታዘዘዋለሁ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። አምላክን መታዘዝ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ከመሆኑም ሌላ በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚሰጠን እሱ በመሆኑ በሙሉ ልብ ልንታዘዘው ይገባል። (መዝ. 95:6, 7) መታዘዝን በምንም ነገር መተካት አንችልም። ካልታዘዝን የአምላክን ሞገስ ማግኘት አንችልም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 7:8-10) እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ እኔ ግን ገና ጊዜዬ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም።” 9 ይህን ከነገራቸው በኋላ በገሊላ ቆየ። 10 ሆኖም ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደዚያው ሄደ።
እውነቱን መናገር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል? በአንድ ወቅት፣ ደቀ መዛሙርቱ ያልሆኑ ሰዎች “ከዚህ ወደ ይሁዳ ሂድ” በማለት ስለ ጉዞው ሐሳብ ሰጥተውት ነበር። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? “እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም” በማለት ወደ ኢየሩሳሌም እንደማይሄድ ገለጸላቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ ለበዓሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ። ታዲያ እንደዚያ ብሎ የመለሰላቸው ለምን ነበር? እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የት እንደሚሄድ የማወቅ መብት አልነበራቸውም። ስለዚህ ኢየሱስ ውሸት ባይናገርም ሰዎቹ በእርሱም ሆነ በተከታዮቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ሲል የተሟላ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል። ይህን በማለቱ አልዋሸም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ እርሱ ሲጽፍ “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም” ብሏል።—ዮሐንስ 7:1-13፤ 1 ጴጥሮስ 2:22
(ዮሐንስ 8:58) ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” አላቸው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 8:58
እኔ ነበርኩ፦ ኢየሱስን ይቃወሙት የነበሩት አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ “አብርሃምን አይቼዋለሁ” ብሎ በመናገሩ ሊወግሩት ፈልገው ነበር፤ ምክንያቱም እነሱ እንዳሉት ኢየሱስ “ገና 50 ዓመት እንኳ [አልሞላውም]።” (ዮሐ 8:57) ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምላሽ የሰጠው፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት በሰማይ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር እንደነበር ለማመልከት ነው። አንዳንዶች ይህ ጥቅስ ኢየሱስ ከአምላክ ጋር አንድ እንደሆነ እንደሚጠቁም ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች እዚህ ላይ የገባው ኢጎ ኤይሚ (በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “እኔ ነኝ” ተብሎ ተተርጉሟል) የሚለው የግሪክኛ አገላለጽ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ የሚገኘውን የዘፀ 3:14ን አተረጓጎም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቅስ እንደሆነና ሁለቱም ጥቅሶች በተመሳሳይ መንገድ ሊተረጎሙ እንደሚገባ ይከራከራሉ። ሆኖም እዚህ ላይ ኤይሚ በሚለው የግሪክኛ ግስ የተገለጸው ድርጊት “አብርሃም ከመወለዱ በፊት” የጀመረና በዚያ ጊዜም መከናወኑን የቀጠለ ድርጊት ነው። በመሆኑም “እኔ ነኝ” ተብሎ ከመተርጎም ይልቅ “እኔ ነበርኩ” ተብሎ መተርጎሙ ተገቢ ነው፤ ደግሞም በርካታ ጥንታዊና ዘመናዊ ትርጉሞች “እኔ ነበርኩ” ከሚለው አገላለጽ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አተረጓጎም ተጠቅመዋል። እንዲያውም በዮሐ 15:27 ላይ በሚገኘው ኢየሱስ “ከመጀመሪያ አንስቶ ከእኔ ጋር ነበራችሁ” በማለት በተናገረው ሐሳብ ላይ ኤይሚ የሚለው የግሪክኛ ግስ በተመሳሳይ መንገድ ተሠርቶበታል። አብዛኞቹ ትርጉሞች ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አገላለጽ መጠቀማቸው ኤይሚ የሚለው ቃል “ነበርኩ” ተብሎ እንደየአገባቡ መተርጎሙ ከሰዋስው አንጻር ምንም ስህተት እንደሌለው ያሳያል። (የግሪክኛው ግስ በዚህ መንገድ የተተረጎመባቸው ሌሎች ጥቅሶች፦ ሉቃስ 2:48፤ 13:7፤ 15:29፤ ዮሐ 1:9፤ 5:6፤ 14:9፤ ሥራ 15:21፤ 2ቆሮ 12:19፤ 1ዮሐ 3:8) በተጨማሪም በዮሐ 8:54, 55 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ማብራሪያ ከአባቱ ጋር አንድ አካል እንደሆነ ማመልከቱ እንዳልነበር ይጠቁማል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 8:31-47) ከዚያም ኢየሱስ በእሱ ላመኑት አይሁዳውያን እንዲህ አለ፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32 እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።” 33 እነሱም መልሰው “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም። ታዲያ አንተ ‘ነፃ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት። 34 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው። 35 ደግሞም ባሪያ በጌታው ቤት ለዘለቄታው አይኖርም፤ ልጅ ከሆነ ግን ሁልጊዜ ይኖራል። 36 ስለዚህ ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ። 37 የአብርሃም ዘር እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ሆኖም ቃሌ በእናንተ ውስጥ ሥር ስለማይሰድ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38 እኔ ከአባቴ ጋር ሳለሁ ያየሁትን ነገር እናገራለሁ፤ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ነገር ታደርጋላችሁ።” 39 እነሱም መልሰው “አባታችን አብርሃም ነው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ ኖሮ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር። 40 እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41 እናንተ እየሠራችሁ ያላችሁት የአባታችሁን ሥራ ነው።” እነሱም “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ እኛ አንድ አባት አለን፤ እሱም አምላክ ነው” አሉት። 42 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ ስለሆነ በወደዳችሁኝ ነበር። እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም። 43 እየተናገርኩት ያለው ነገር የማይገባችሁ ለምንድን ነው? ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው። 44 እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ። እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል። 45 በሌላ በኩል ግን እኔ እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም። 46 ከመካከላችሁ እኔን ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ በማስረጃ ሊወነጅለኝ የሚችል ማን ነው? የምናገረው እውነት ከሆነ ደግሞ የማታምኑኝ ለምንድን ነው? 47 ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል። እናንተ ግን ከአምላክ ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”