የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥቅምት 2018
ከጥቅምት 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 9-10
“ኢየሱስ ለበጎቹ ያስባል”
(ዮሐንስ 10:1-3) “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው። 2 በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው። 3 በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል።
(ዮሐንስ 10:11) እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።
(ዮሐንስ 10:14) እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ። በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤
nwtsty ሚዲያ
ጉረኖ
ጉረኖ፣ በጎችን ከዘራፊዎችና ከአራዊት ጥቃት ለመጠበቅ የሚያገለግል አጥር ግቢ ነው። እረኞች መንጎቻቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጉረኖ ውስጥ ያሳድሯቸው ነበር። በጥንት ዘመን የሚሠሩት ጉረኖዎች የተለያየ ቅርጽና መጠን ያላቸው ሲሆን በአንድ በኩል በር እንዲኖራቸው ተደርገው በድንጋይ ይገነቡ ነበር፤ ጉረኖዎቹ ጣሪያ አይሠራላቸውም። (ዘኁ 32:16፤ 1ሳሙ 24:3፤ ሶፎ 2:6) ዮሐንስ “በበሩ” በኩል ወደ ጉረኖ ስለመግባት የተናገረ ሲሆን “በር ጠባቂ” እንዳለም ገልጿል። (ዮሐ 10:1, 3) ጉረኖውን ብዙ እረኞች በጋራ የሚጠቀሙበት ከሆነ በርከት ያሉ መንጎች አንድ ላይ ያድራሉ፤ በሩ ላይ ደግሞ ጠባቂ ይኖራል። ጠዋት ላይ ለእረኞቹ በሩን የሚከፍትላቸው በር ጠባቂው ነው። ከዚያም እያንዳንዱ እረኛ የራሱን በጎች ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል፤ በጎቹም የእረኛቸውን ድምፅ ስለሚያውቁ ይከተሉታል። (ዮሐ 10:3-5) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን የሚንከባከብበትን መንገድ በምሳሌ ለማስረዳት ይህን ልማድ ጠቅሷል።—ዮሐ 10:7-14
ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ነቅታችሁ ኑሩ’
5 በእረኛና በበጎች መካከል ያለው ግንኙነት በእውቀትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ነው። እረኛው በጎቹን በደንብ ያውቃቸዋል፤ በጎቹም እረኛቸውን የሚያውቁት ከመሆኑም ሌላ ይተማመኑበታል። ድምፁን ለይተው ያውቁታል፤ እንዲሁም ይታዘዙታል። ኢየሱስ “በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል” ብሏል። ጉባኤውን የሚያውቀው እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ አይደለም። እዚህ ላይ ‘ማወቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በግለሰብ ደረጃ ጠንቅቆ ማወቅን” ያመለክታል። አዎን፣ ጥሩው እረኛ እያንዳንዱን በግ ያውቀዋል። በጎቹ በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲሁም ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ያውቃል። አርዓያችን የሆነው ኢየሱስ ስለ በጎቹ የማያውቀው ነገር የለም። በጎቹም ቢሆኑ እረኛቸውን በሚገባ የሚያውቁት ሲሆን በሚሰጣቸው አመራር ይተማመናሉ።
(ዮሐንስ 10:4, 5) የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። 5 እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።”
“ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር”
17 ጆርጅ አዳም ስሚዝ በዓይናቸው የተመለከቱትን ነገር ዘ ሂስቶሪካል ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት አስፍረዋል፦ “አንዳንድ ጊዜ የምሳ እረፍታችንን በይሁዳ ከሚገኙት የውኃ ጉድጓዶች መካከል በአንደኛው አጠገብ ቁጭ ብለን እናሳልፍ ነበር፤ በአንድ ወቅት ሦስት ወይም አራት እረኞች መንጎቻቸውን ይዘው ወደዚያ መጡ። በጎቹ ወደ ውኃው ጉድጓድ ሲቃረቡ ተደባለቁ፤ እኛም ‘እያንዳንዱ እረኛ የየራሱን በግ እንዴት አድርጎ ይለይ ይሆን?’ ብለን አሰብን። በጎቹ ውኃ ከጠጡና ወዲያ ወዲህ እያሉ ከቦረቁ በኋላ እረኞቹ ተራ በተራ ከሸለቆው ወደተለያዩ አቅጣጫዎች በመውጣት ሁሉም ለበጎቻቸው የተለየ የጥሪ ድምፅ አሰሙ፤ በጎቹም ከመንጋው እየተለዩ ወደ እረኞቻቸው ተሰበሰቡ፤ ከዚያም እንዳመጣጣቸው ተመልሰው ሄዱ።” ኢየሱስ ነጥቡን ለማስረዳት ይኸውም ትምህርቶቹን ለይተን የምናውቅና የምንታዘዝ እንዲሁም አመራሩን የምንከተል ከሆነ ‘የጥሩውን እረኛ’ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደምናገኝ ለማሳየት ከዚህ የተሻለ ሌላ ምን ምሳሌ ሊጠቀም ይችላል?
(ዮሐንስ 10:16) “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 10:16
ማምጣት፦ ወይም “መምራት።” እዚህ ላይ የገባው ኣጎ የሚለው የግሪክኛ ግስ እንደየአገባቡ “ማምጣት” ወይም “መምራት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በ200 ዓ.ም. ገደማ የተዘጋጀ አንድ የግሪክኛ ጥንታዊ ጽሑፍ ኣጎ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ቃል (ሲናጎ) ይጠቀማል፤ ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ “መሰብሰብ” ተብሎ ተተርጉሟል። ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ፣ ከዚህ ጉረኖ የሆኑትን በጎች (ሉቃስ 12:32 ላይ “ትንሽ መንጋ” ተብለዋል) እና ሌሎች በጎችን ይሰበስባል፣ ይመራል፣ ይጠብቃል እንዲሁም ይመግባል። እነዚህ በጎች በአንድ እረኛ ሥር ያሉ አንድ መንጋ ይሆናሉ። ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ የኢየሱስ ተከታዮች የሚኖራቸውን አንድነት ጎላ አድርጎ ያሳያል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐ 9:38) እሱም “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 9:38
ሰገደለት፦ ወይም “እጅ ነሳው፤ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ።” ፕሮስኪኔኦ የሚለው የግሪክኛ ግስ ለአምላክ ወይም ለጣዖት አምልኮ ማቅረብን ለማመልከት በሚሠራበት ጊዜ ‘ማምለክ’ ተብሎ ተተርጉሟል። (ማቴ 4:10፤ ሉቃስ 4:8) እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ሰው ግን ዓይኑ ሲበራ ለኢየሱስ የሰገደው ኢየሱስ የአምላክ ወኪል መሆኑን ስለተገነዘበ ነው። ኢየሱስን እንደ አምላክ አድርጎ አልተመለከተውም፤ ከዚህ ይልቅ በትንቢት የተነገረለት ‘የሰው ልጅ’ ማለትም መለኮታዊ ሥልጣን ያለው መሲሕ መሆኑን ተረድቶ ነበር። (ዮሐ 9:35) ይህ ሰው ያደረገው ነገር በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ካደረጉት ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ሰዎች ለነቢያት፣ ለነገሥታት ወይም ለሌሎች የአምላክ ወኪሎች ሰግደዋል። (1ሳሙ 25:23, 24፤ 2ሳሙ 14:4-7፤ 1ነገ 1:16፤ 2ነገ 4:36, 37) ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለኢየሱስ የሰገዱለት፣ አምላክ ለገለጠላቸው ነገር አመስጋኝ መሆናቸውን ወይም ኢየሱስ የአምላክ ሞገስ እንዳለው መገንዘባቸውን ለማሳየት ነው።
(ዮሐ 10:22) በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም የመታደስ በዓል ይከበር ነበር። ወቅቱም ክረምት ነበር፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 10:22
የመታደስ በዓል፦ ይህ በዓል በዕብራይስጥ ሃኑካ (ኻኑካ) ተብሎ ይጠራል፤ ትርጉሙም “ምረቃ፤ ውሰና” ማለት ነው። በዓሉ መከበር የሚጀምረው ኪስሌው (ወደ ታኅሣሥ መገባደጃ አካባቢ) በተባለው ወር በ25ኛው ቀን ሲሆን ለስምንት ቀናት ይቆያል (ተጨማሪ መረጃ ለ15ን ተመልከት)፤ ይህ በዓል የሚከበረው በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ በ165 ዓ.ዓ. በድጋሚ የተወሰነበትን ጊዜ ለማሰብ ነው። የሶርያው ንጉሥ አንታይከስ አራተኛ ኤፒፋነስ፣ የአይሁዳውያን አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ያለውን ንቀት ለማሳየት ሲል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ አርክሶት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በየዕለቱ ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት ይቀርብበት በነበረው በታላቁ መሠዊያ ላይ ለአረማዊ አምላክ መሠዊያ አቁሞ ነበር። በኪስሌው 25, 168 ዓ.ዓ. አንታይከስ የይሖዋን ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ለማርከስ ሲል በመሠዊያው ላይ የአሳማ መሥዋዕት ያቀረበ ሲሆን መረቁንም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አርከፈከፈው። ከዚህም ሌላ የቤተ መቅደሱን በሮች አቃጠለ፣ የካህናቱን ክፍሎች አፈረሰ እንዲሁም የወርቁን መሠዊያ፣ ገጸ ኅብስቱ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛና የወርቁን መቅረዝ ወሰደ። ከዚያም የይሖዋ ቤተ መቅደስ የኦሊምፐሱ ዙስ ለተባለ የአረማውያን አምላክ አምልኮ እንዲወሰን አደረገ። ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ይሁዳ መቃቢስ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ነፃ አወጣ። ቤተ መቅደሱ ከጸዳ በኋላ በኪስሌው 25, 165 ዓ.ዓ. እንደገና ለይሖዋ አምልኮ ተወሰነ፤ ይህም አንታይከስ ለዙስ አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ካቀረበ ልክ ከሦስት ዓመት በኋላ ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ለይሖዋ በየዕለቱ የሚቃጠል መሥዋዕት እንደገና መቅረብ ጀመረ። ይሁዳ መቃቢስ ድል እንዲጎናጸፍና ቤተ መቅደሱን ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመልስ የረዳው ይሖዋ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከእሱ አምልኮ ጋር በተያያዘ ፈቃዱን ለማስፈጸም እንደ ፋርሱ ቂሮስ ያሉ የሌላ አገር ሰዎችን ተጠቅሟል። (ኢሳ 45:1) ከዚህ አንጻር ይሖዋ ለእሱ የተወሰነው ብሔር አባል የሆነውን ይሁዳን ዓላማውን ለማስፈጸም ተጠቅሞበት ሊሆን ይችላል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ስለ መሲሑ፣ ስለሚያከናውነው አገልግሎት እንዲሁም ስለሚያቀርበው መሥዋዕት የሚናገሩት ትንቢቶች እንዲፈጸሙ ቤተ መቅደሱ ሊኖርና አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ቅዱሳን መጻሕፍት ያሳያሉ። በተጨማሪም መሲሑ ለሰው ዘር ሕይወቱን በመስጠት የላቀ መሥዋዕት እስከሚያቀርብበት ጊዜ ድረስ ሌዋውያኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን መቀጠል ነበረባቸው። (ዳን 9:27፤ ዮሐ 2:17፤ ዕብ 9:11-14) የክርስቶስ ተከታዮች የመታደስ በዓልን እንዲያከብሩ አልታዘዙም። (ቆላ 2:16, 17) ይሁንና ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ይህን በዓል እንዳወገዙ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 9:1-17) በመንገድ እያለፈ ሳለም ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አየ። 2 ደቀ መዛሙርቱም “ረቢ፣ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። 3 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ሆኖም ይህ የሆነው የአምላክ ሥራ በእሱ እንዲገለጥ ነው። 4 ቀን ሳለ፣ የላከኝን የእሱን ሥራ መሥራት አለብን፤ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል። 5 በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።” 6 ይህን ካለ በኋላ መሬት ላይ እንትፍ በማለት በምራቁ ጭቃ ለወሰ፤ ጭቃውንም በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ፤ 7 ሰውየውንም “ሄደህ በሰሊሆም ገንዳ ታጠብ” አለው (ሰሊሆም ማለት “ተላከ” ማለት ነው)። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ ዓይኑም በርቶለት መጣ። 8 ከዚያም ጎረቤቶቹና ቀደም ሲል ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” አሉ። 9 አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ይሉ ነበር። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” ይል ነበር። 10 በመሆኑም “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። 11 እሱም “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ” ሲል መለሰ። 12 በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” አሉት። እሱም “እኔ አላውቅም” አለ። 13 እነሱም ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14 እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስ ጭቃውን የለወሰበትና የሰውየውን ዓይኖች ያበራበት ቀን ሰንበት ነበር። 15 በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። እሱም “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው። 16 ከፈሪሳውያንም መካከል አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ አይደለም” አሉ። ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ተአምራዊ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” አሉ። በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ። 17 በድጋሚም ዓይነ ስውሩን “ይህ ሰው ዓይኖችህን ስላበራልህ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም “እሱ ነቢይ ነው” አለ።
ከጥቅምት 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 11-12
“ኢየሱስን በርኅራኄው ምሰሉት”
(ዮሐንስ 11:23-26) ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” አላት። 24 ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። 25 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል፤ 26 በሕይወት ያለና በእኔ የሚያምን ሁሉ ደግሞ ፈጽሞ አይሞትም። ይህን ታምኛለሽ?”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 11:24, 25
እንደሚነሳ አውቃለሁ፦ ማርታ፣ ኢየሱስ ወደፊት ማለትም በመጨረሻው ቀን ስለሚከናወነው ትንሣኤ የተናገረ መስሏት ነበር። ማርታ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላት እምነት የሚያስገርም ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ትንሣኤ በግልጽ የሚናገሩ ቢሆንም እንኳ በዘመኑ የነበሩ ሰዱቃውያን የሚባሉ የሃይማኖት መሪዎች ይህን ትምህርት አይቀበሉም ነበር። (ዳን 12:13፤ ማር 12:18) በሌላ በኩል ደግሞ ፈሪሳውያን ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ነበር። ማርታ ግን ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ እንዳስተማረ እንዲያውም የሞቱ ሰዎችን እንዳስነሳ ታውቅ ነበር፤ በእርግጥ ኢየሱስ ያስነሳቸው ሰዎች ሞተው የአልዓዛርን ያህል አልቆዩም።
ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፦ ኢየሱስ መሞቱና ከሞት መነሳቱ ሙታን ትንሣኤ ማግኘት እንዲችሉ መንገድ ከፍቷል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ይሖዋ፣ ሙታንን የማስነሳት ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወት የመስጠት ሥልጣን ጭምር ሰጥቶታል። በራእይ 1:18 ላይ ኢየሱስ ራሱን “ሕያው የሆነው” ብሎ የጠራ ሲሆን “የሞትና የመቃብር ቁልፎች” እንዳሉት ተናግሯል። በመሆኑም ኢየሱስ ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ተስፋ ፈንጥቋል። ኢየሱስ በመቃብር ያሉት ሁሉ እንደሚወጡ ይኸውም ሙታን ሕያው እንደሚሆኑ ቃል ገብቷል፤ ከሞት የተነሱት ሰዎችም በሰማይ ከእሱ ጋር ይገዛሉ አሊያም በሰማያዊ መንግሥቱ በሚተዳደረው አዲስ ምድር ላይ ይኖራሉ።—ዮሐ 5:28, 29፤ 2ጴጥ 3:13
(ዮሐንስ 11:33-35) ኢየሱስ እሷ ስታለቅስና አብረዋት የመጡት አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ፤ ተረበሸም። 34 እሱም “የት ነው ያኖራችሁት?” አለ። እነሱም “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ” አሉት። 35 ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 11:33-35
ሲያለቅሱ፦ “ማልቀስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አብዛኛውን ጊዜ ድምፅ አውጥቶ ማልቀስን ያመለክታል። ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት በተናገረው ትንቢት ላይ የተጠቀሰውም ይኸው ግስ ነው።—ሉቃስ 19:41
እጅግ አዘነ፤ ተረበሸም፦ ወይም “በመንፈሱ ቃተተ፤ ተረበሸም።” እዚህ ላይ የገቡት ሁለት የግሪክኛ ቃላት አንድ ላይ መጠቀሳቸው ኢየሱስ በዚያ ወቅት በጣም ጥልቅ የሆነ ስሜት እንደተሰማው ይጠቁማል። “እጅግ አዘነ” (ኤምብሪማኦሜ) ተብሎ የተተረጎመው ግስ በአብዛኛው ኃይለኛ ስሜትን የሚያመለክት ነው፤ በዚህ አገባቡ፣ ኢየሱስ በጣም ማዘኑን የሚያሳይ ነገር እንዳደረገ ይኸውም እንደቃተተ ያመለክታል። “ተረበሸ”(ታራሶ) ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም መታወክን ያመለክታል። አንድ ምሁር እንደገለጹት ይህ ቃል በዚህ አገባቡ “አንድ ሰው ውስጡ እንደተረበሸ እንዲሁም ከፍተኛ ሥቃይ ወይም ሐዘን እንደተሰማው” ይጠቁማል። ይኸው ግስ በዮሐ 13:21 ላይ ኢየሱስ፣ ይሁዳ እንደሚከዳው ሲያስብ የተሰማውን ስሜት ለመግለጽ ተሠርቶበታል።—ለዮሐ 11:35 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።
እንባውን አፈሰሰ፦ እንደ ሉቃስ 7:38፤ ሥራ 20:19, 31፤ ዕብ 5:7፤ ራእይ 7:17፤ 21:4 ባሉት ጥቅሶች ላይ “እንባ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም በዮሐ 11:35 ላይ የተሠራበት ግስ ሆኖ (ዳክሪኦ) ነው። የግሪክኛው ቃል፣ በዋነኝነት የሚገልጸው ድምፅ አውጥቶ ከማልቀስ ይልቅ እንባን ማፍሰስን ሳይሆን አይቀርም። ይህ የግሪክኛ ግስ (ዳክሪኦ) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተሠራበት በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ሲሆን ቃሉ በዮሐ 11:33 (ለጥናት የሚረዳውን መረጃ ተመልከት) ላይ ማርያምና አይሁዳውያን ማልቀሳቸውን ለመግለጽ ከገባው ቃል ይለያል። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሳው ቢያውቅም የቅርብ ወዳጆቹ ምን ያህል በሐዘን እንደተደቆሱ ሲመለከት በእጅጉ አዝኗል። ወዳጆቹን በጣም ይወዳቸውና ይራራላቸው ስለነበር በሕዝብ ፊት እንባውን አፍስሷል። ይህ ዘገባ ኢየሱስ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ሰዎችን ስሜት እንደሚረዳ በግልጽ ያሳያል።
(ዮሐንስ 11:43, 44) ይህን ከተናገረ በኋላ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ። 44 የሞተው ሰው እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደተገነዙ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ ተጠምጥሞ ነበር። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ” አላቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት፦
(ዮሐንስ 11:49) ከመካከላቸው አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ምንም አታውቁም፤
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 11:49
ሊቀ ካህናት፦ እስራኤል ራሷን የምታስተዳድር ብሔር በነበረችበት ጊዜ፣ ሊቀ ካህናቱ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በዚህ ኃላፊነት ይቀጥል ነበር። (ዘኁ 35:25) እስራኤል በሮም ቁጥጥር ሥር ከወደቀች በኋላ ግን ሮማውያን ያስቀመጧቸው ገዢዎች ሊቀ ካህናቱን የመሾምና የመሻር ሥልጣን ነበራቸው። (ከቃላት መፍቻው ላይ “ሊቀ ካህናት” የሚለውን ተመልከት።) በሮማውያን የተሾመው ቀያፋ ከእሱ በፊት ከነበሩት ሊቃነ ካህናት ይበልጥ ረዘም ላለ ጊዜ በዚህ ኃላፊነት መቆየት የቻለ ዘዴኛ ሰው ነበር። ቀያፋ የተሾመው በ18 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን እስከ 36 ዓ.ም. ገደማ ድረስ በሥልጣን ላይ ቆይቷል። ዮሐንስ በዚያ ዓመት ማለትም በ33 ዓ.ም. ቀያፋ ሊቀ ካህናት እንደነበረ የገለጸው ይህ ሰው በዚህ ኃላፊነት የቆየበት ጊዜ ኢየሱስ የተገደለበትን ዓመትም እንደሚጨምር ለማመልከት ፈልጎ ሊሆን ይችላል።—የቀያፋ ቤት ይገኝበት እንደነበረ የሚገመተውን ቦታ ለማየት ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ12ን ተመልከት።
(ዮሐንስ 12:42) ያም ሆኖ ከገዢዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእሱ አመኑ፤ ይሁንና ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር፤
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 12:42
ገዢዎች፦ እዚህ ላይ “ገዢዎች” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሳንሄድሪን የተባለውን የአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ አባላት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ይኸው ቃል በዮሐ 3:1 ላይ የዚህ ሸንጎ አባል ከሆነው ከኒቆዲሞስ ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል።
ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው፦ ወይም “እንዳያወግዟቸው፤ ከምኩራብ እንዳያግዷቸው።” ኣፖሲናጎጎስ የሚለው የግሪክኛ ቅጽል የተሠራበት ዮሐ 9:22፤ 12:42 እና 16:2 ላይ ብቻ ነው። ከምኩራብ የተባረረ ሰው ይፌዝበትና ከማኅበረሰቡ ይገለል ነበር። አንድ ሰው ከሌሎች አይሁዳውያን መገለሉ በቤተሰቡ ላይ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስከትል ነበር። ምኩራቦች በዋነኝነት የሚያገለግሉት ለማስተማሪያነት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ በምኩራቦች ውስጥ የፍርድ ሸንጎም ይሰየም ነበር፤ እነዚህ ሸንጎዎች ሰዎችን በማስገረፍ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ በመወሰን የመቅጣት ሥልጣን ነበራቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 12:35-50) ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ብርሃኑ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ይቆያል። ጨለማ እንዳይውጣችሁ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃን ሂዱ፤ በጨለማ የሚሄድ ሁሉ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም። 36 የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ ሄደ፤ ከእነሱም ተሰወረ። 37 በፊታቸው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች ቢፈጽምም በእሱ አላመኑም፤ 38 ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ከእኛ የሰማውን ነገር ያመነ ማን ነው? የይሖዋስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” 39 ደግሞም ኢሳይያስ ሊያምኑ ያልቻሉበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ 40 “በዓይናቸው አይተውና በልባቸው አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳይፈውሳቸው ዓይናቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል።” 41 ኢሳይያስ ይህን የተናገረው የክርስቶስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እሱም ተናገረ። 42 ያም ሆኖ ከገዢዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእሱ አመኑ፤ ይሁንና ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር፤ 43 ይህም የሆነው ከሰው የሚገኘውን ክብር ከአምላክ ከሚገኘው ክብር አስበልጠው ስለወደዱ ነው። 44 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ጭምር ያምናል፤ 45 እኔን የሚያይ ሁሉ የላከኝንም ያያል። 46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። 47 ይሁንና ማንም ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቅ ከሆነ የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ እኔ የመጣሁት ዓለምን ለማዳን እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለምና። 48 እኔን የሚንቀውንና ቃሌን የማይቀበለውን ሁሉ የሚፈርድበት አለ። በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት የተናገርኩት ቃል ነው። 49 እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው። 50 ደግሞም የእሱ ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ። ስለዚህ ምንጊዜም የምናገረው ልክ አባቴ በነገረኝ መሠረት ነው።”
ከጥቅምት 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| ዮሐንስ 13-14
“አርዓያ ሆኜላችኋለሁ”
(ዮሐንስ 13:5) ከዚያም በመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና ባሸረጠው ፎጣ ማድረቅ ጀመረ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 13:5
የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ፦ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ብዙ ሰዎች የሚያደርጉት ክፍት ጫማ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ጫማዎች ሶልና ማሰሪያ ብቻ ያላቸው ሲሆኑ ማሰሪያው እግር ወይም ቁርጭምጭሚት ላይ የሚታሰር ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም አቧራማ ወይም ጭቃማ በሆኑት መንገዶች ላይ የተጓዘ መንገደኛ እግሩ መቆሸሹ አይቀርም። ስለዚህ አንድ ሰው ወደ ቤት ሲገባ ጫማውን ማውለቁ የተለመደ ነገር ነበር፤ እንግዶቹን ጥሩ አድርጎ የሚያስተናግድ ሰውም እግራቸው እንዲታጠብ ያደርጋል። ይህ ልማድ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ተጠቅሷል። (ዘፍ 18:4, 5፤ 24:32፤ 1ሳሙ 25:41፤ ሉቃስ 7:37, 38, 44) በዚህ ልማድ መሠረት ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትሑት እንዲሆኑና አንዳቸው ሌላውን እንዲያገለግሉ አስተምሯቸዋል።
(ዮሐንስ 13:12-14) እግራቸውን አጥቦ ካበቃና መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? 13 እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። 14 ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 13:12-14
ይገባችኋል፦ ወይም “ግዴታ አለባችሁ።” እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ነው፤ የቃሉ መሠረታዊ ትርጉም “ባለዕዳ የሆነ ወይም ብድር ያለበት ሰው” የሚል ነው። (ማቴ 18:28, 30, 34፤ ሉቃስ 16:5, 7) ይህ ቃል በዚህና በሌሎች ጥቅሶች ላይ ከዚህ ይበልጥ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ሲሆን አንድን ነገር ለማድረግ መገደድን ወይም ግዴታ ውስጥ መግባትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።—1ዮሐ 3:16፤ 4:11፤ 3ዮሐ 8
(ዮሐንስ 13:15) እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ።
ታላቁ ሰው ትሕትና የሚጠይቅ አገልግሎት ሰጠ
ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትሕትናን በተመለከተ ከባድ ትምህርት ሰጥቷል። በእርግጥም፣ ክርስቲያኖች በጣም ተፈላጊ እንደሆኑና ሌሎች ሁልጊዜ እነሱን ሊያገለግሏቸው እንደሚገባ አድርገው ማሰብም ሆነ የላቀ ክብርና ቦታ እንዲሰጣቸው መፈለግ አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል፤ እርሱ “ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ማቴዎስ 20:28) አዎን፣ የኢየሱስ ተከታዮች አንዳቸው ለሌላው እጅግ ትሕትና የሚጠይቅ ነገርም እንኳ ለማከናወን ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 14:6) ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 14:6
እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ፦ ኢየሱስ መንገድ የተባለው ወደ አምላክ በጸሎት መቅረብ የሚቻለው በእሱ በኩል ብቻ ስለሆነ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሰዎች ከአምላክ ጋር መታረቅ የሚችሉበት “መንገድ” ነው። (ዮሐ 16:23፤ ሮም 5:8) ኢየሱስ እውነት የተባለው የተናገረው ነገርም ሆነ ሕይወቱ ከእውነት ጋር የሚስማማ በመሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በርካታ ትንቢቶች እንዲፈጸሙ አድርጓል፤ ይህም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለው ያሳያል። (ዮሐ 1:14፤ ራእይ 19:10) እነዚህ ትንቢቶች “በእሱ አማካኝነት ‘አዎ’ ሆነዋል” ወይም ተፈጽመዋል። (2ቆሮ 1:20) ኢየሱስ ሕይወት የተባለው ደግሞ በቤዛው አማካኝነት የሰው ዘር “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም “የዘላለም ሕይወት” እንዲያገኝ መንገድ ስለከፈተ ነው። (1ጢሞ 6:12, 19፤ ኤፌ 1:7፤ 1ዮሐ 1:7) በተጨማሪም ትንሣኤ አግኝተው በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ሕይወት” ይሆናል።—ዮሐ 5:28, 29
(ዮሐንስ 14:12) እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 14:12
ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች፦ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሱ ከፈጸማቸው የሚበልጡ ተአምራት እንደሚፈጽሙ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ይበልጥ በስፋት እንደሚሰብኩና እንደሚያስተምሩ በትሕትና መግለጹ ነበር። ተከታዮቹ ብዙ ክልል ይሸፍናሉ፤ ለብዙዎች ይሰብካሉ፤ እንዲሁም ከእሱ ይበልጥ ረዘም ላለ ጊዜ ያስተምራሉ። ኢየሱስ የተናገረው ነገር፣ ተከታዮቹ እሱ የጀመረውን ሥራ ማከናወናቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠብቅ እንደነበር በግልጽ ያሳያል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 13:1-17) የፋሲካ በዓል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደደረሰ ስላወቀ በዓለም የነበሩትንና የወደዳቸውን ተከታዮቹን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው። 2 በዚህ ጊዜ ራት እየበሉ ነበር። ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ውስጥ ኢየሱስን አሳልፎ የመስጠት ሐሳብ አሳድሮ ነበር። 3 ኢየሱስ፣ አብ ሁሉን ነገር በእጁ እንደሰጠው እንዲሁም ከአምላክ እንደመጣና ወደ አምላክ እንደሚሄድ ያውቅ ስለነበር 4 ከራት ተነስቶ መደረቢያውን አስቀመጠ። ፎጣ ወስዶም ወገቡ ላይ አሸረጠ። 5 ከዚያም በመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና ባሸረጠው ፎጣ ማድረቅ ጀመረ። 6 ከዚያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ መጣ። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ልታጥብ ነው?” አለው። 7 ኢየሱስም መልሶ “እያደረግኩት ያለውን ነገር አሁን አትረዳውም፤ በኋላ ግን ትረዳዋለህ” አለው። 8 ጴጥሮስም “በፍጹም እግሬን አታጥብም” አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ምንም ድርሻ አይኖርህም” ሲል መለሰለት። 9 ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ” አለው። 10 ኢየሱስም “ገላውን የታጠበ ሁለመናው ንጹሕ በመሆኑ ከእግሩ በስተቀር መታጠብ አያስፈልገውም። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ ሁላችሁም ግን አይደላችሁም” አለው። 11 ምክንያቱም አሳልፎ የሚሰጠው ሰው ማን እንደሆነ ያውቅ ነበር። “ሁላችሁም ንጹሐን አይደላችሁም” ያለው ለዚህ ነው። 12 እግራቸውን አጥቦ ካበቃና መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? 13 እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። 14 ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። 15 እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ። 16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ የተላከም ከላከው አይበልጥም። 17 እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ።
ከጥቅምት 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት| ዮሐንስ 15-17
“የዓለም ክፍል አይደላችሁም”
(ዮሐንስ 15:19) የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 15:19
ዓለም፦ ኮስሞስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በዚህ አገባቡ፣ የአምላክ አገልጋዮች ያልሆኑ የሰው ልጆችን በሙሉ ይኸውም ከአምላክ የራቀውንና እሱን የማይታዘዘውን ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ያመለክታል። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ ወይም ከዓለም የተለዩ እንደሆኑ መናገሩን የዘገበው ብቸኛው የወንጌል ጸሐፊ ዮሐንስ ነው። ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ባቀረበው የመጨረሻ ጸሎት ላይም ይህን አገላለጽ ሁለት ጊዜ ተጠቅሞበታል።—ዮሐ 17:14, 16
(ዮሐንስ 15:21) ሆኖም የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 15:21
በስሜ ምክንያት፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስም” የሚለው ቃል የስሙ ባለቤት የሆነውን አካል፣ በሌሎች ዘንድ ያተረፈውን ስም እንዲሁም አጠቃላይ ማንነቱን ለማመልከት ተሠርቶበታል። የኢየሱስ ስም፣ አባቱ የሰጠውን ሥልጣንና ቦታ ጭምር ያመለክታል። (ማቴ 28:18፤ ፊልጵ 2:9, 10፤ ዕብ 1:3, 4) በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ፣ በዓለም ያሉ ሰዎች በተከታዮቹ ላይ መጥፎ ነገር የሚያደርጉት እሱን የላከውን አካል ስለማያውቁት እንደሆነ ገልጿል። አምላክን ቢያውቁ የኢየሱስ ስም የሚወክለውን ነገር መረዳትና መቀበል ይችላሉ። (ሥራ 4:12) የኢየሱስ ስም፣ አምላክ ኢየሱስን ገዢ ይኸውም የነገሥታት ንጉሥ አድርጎ በመሾም የሰጠውን ሥልጣን ይጨምራል፤ ሰዎች ሁሉ ሕይወት ለማግኘት ከፈለጉ ለኢየሱስ መገዛት ይኖርባቸዋል።—ዮሐ 17:3፤ ራእይ 19:11-16፤ ከመዝ 2:7-12 ጋር አወዳድር።
(ዮሐንስ 16:33) እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
it-1-E 516
ድፍረት
ክርስቲያኖች የይሖዋ አምላክ ጠላት በሆነው ዓለም አመለካከትና ምግባር እንዳይበከሉ እንዲሁም ዓለም ቢጠላቸውም ለአምላክ ታማኝ ሆነው መኖር እንዲችሉ ድፍረት ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ “በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ 16:33) የአምላክ ልጅ ለዓለም ተጽዕኖ በፍጹም አልተንበረከከም፤ እንዲያውም በምንም መልኩ ዓለምን ባለመምሰል ዓለምን አሸንፏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ድል አድራጊ በመሆን የተወው አስደናቂ ምሳሌ እንዲሁም እንከን የለሽ አካሄድ መከተሉ ያስገኘው ውጤት፣ ክርስቲያኖች እሱን በመምሰል ከዓለም የተለዩ ለመሆንና በዓለም ሳይበከሉ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ድፍረት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።—ዮሐ 17:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 17:21-23) ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ ይኸውም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ ያምን ዘንድ አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው። 22 እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ ለእኔ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23 እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት አለኝ፤ አንተም ከእኔ ጋር አንድነት አለህ፤ ይህ ደግሞ እነሱም ፍጹም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ በተጨማሪም ዓለም አንተ እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 17:21-23
አንድ፦ ወይም “አንድነት።” ኢየሱስ እሱና አባቱ “አንድ” እንደሆኑ (በመካከላቸው ትብብርና የአስተሳሰብ አንድነት እንዳለ) ሁሉ እውነተኛ ተከታዮቹም “አንድ” እንዲሆኑ ይኸውም ተመሳሳይ ለሆነ ዓላማ ተባብረው እንዲሠሩ ጸልዮአል። (ዮሐ 17:22) በ1ቆሮ 3:6-9 ላይ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከአምላክ ጋር ተባብረው ሲሠሩ በመካከላቸው እንዲህ ዓይነት አንድነት እንደሚኖር ገልጿል።—የ1ቆሮ 3:8ን ግርጌ ተመልከት።
ፍጹም አንድ እንዲሆኑ፦ ወይም “ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው።” እዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ፍጹም የሆነ አንድነትን በአብ ከመወደድ ጋር አያይዞ ገልጾታል። ይህም በቆላ 3:14 ላይ ከሚገኘው “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል። እንዲህ ያለው ፍጹም አንድነት ግን አንጻራዊ ነው። በግለሰቦች መካከል ያሉት ልዩነቶች በሙሉ ይወገዳሉ ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ እያንዳንዱ ሰው የተለያየ ችሎታ፣ ልማድና ሕሊና እንደሚኖረው የታወቀ ነው። ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች ከምግባራቸው፣ ከሚያምኑባቸው ነገሮችና ከትምህርታቸው ጋር በተያያዘ አንድነት አላቸው።—ሮም 15:5, 6፤ 1ቆሮ 1:10፤ ኤፌ 4:3፤ ፊልጵ 1:27
(ዮሐ 17:24) አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 17:24
ዓለም ከመመሥረቱ፦ እዚህ ጥቅስ ላይ “መመሥረት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በዕብ 11:11 ላይ “ዘር” ከሚለው ቃል ጋር ተያይዞ የተሠራበት ሲሆን “መፀነስ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። “ዓለም ከመመሥረቱ በፊት” በሚለው አገላለጽ ላይ ‘የዓለም መመሥረት’ የአዳምና የሔዋን ልጆችን መወለድ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ‘የዓለምን መመሥረት’ ከአቤል ጋር አያይዞ ገልጾታል፤ አቤል በቤዛው ሊዋጁ ከሚችሉትና “ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል” ላይ ከሰፈሩት መካከል የመጀመሪያ ሰው መሆን አለበት። (ሉቃስ 11:50, 51፤ ራእይ 17:8) ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ከረጅም ጊዜ በፊት ማለትም አዳምና ሔዋን ዘር ከመፀነሳቸው አስቀድሞ አንድያ ልጁን ይወደው እንደነበረም ያሳያሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 17:1-14) ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል። ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ 2 ይህም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው። 3 የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው። 4 እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። 5 ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ። 6 “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል። 7 የሰጠኸኝ ነገር ሁሉ ከአንተ የተገኘ መሆኑን አሁን አውቀዋል፤ 8 ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል። 9 ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤ 10 ደግሞም የእኔ የሆነው ነገር ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ እኔም በእነሱ መካከል ከብሬአለሁ። 11 “ከእንግዲህ እኔ በዓለም ውስጥ አልኖርም፤ እነሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔ ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው። 12 እኔ ከእነሱ ጋር ሳለሁ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስል ስጠብቃቸው ቆይቻለሁ፤ ደግሞም ጠብቄአቸዋለሁ፤ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ከጥፋት ልጅ በቀር አንዳቸውም አልጠፉም። 13 አሁን ግን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ደስታዬ በውስጣቸው ሙሉ እንዲሆን አሁን በዓለም ላይ እያለሁ እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ። 14 ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ ሆኖም እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል ስላልሆኑ ዓለም ጠላቸው።
ከጥቅምት 29–ኅዳር 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት |ዮሐንስ 18-19
“ኢየሱስ ስለ እውነት መሥክሯል”
(ዮሐንስ 18:36) ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።”
(ዮሐንስ 18:37) በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “እንግዲያው አንተ ንጉሥ ነህ?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ራስህ እየተናገርክ ነው። እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው። ከእውነት ጎን የቆመ ሁሉ ቃሌን ይሰማል።”
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 18:37
ለመመሥከር፦ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “መመሥከር” ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት ሰፋ ያለ ትርጉም አላቸው። እነዚህ ቃላት በዋነኝነት የሚያመለክቱት ያዩትን ወይም የሚያውቁትን ነገር ማስረዳትን ቢሆንም “ማወጅ፤ ማረጋገጥ፤ በመልካም ማንሳት” የሚሉትን ሐሳቦችም ሊገልጹ ይችላሉ። ኢየሱስ ስለሚያምንባቸው እውነቶች ከመመሥከርና ከማወጅም አልፎ አባቱ የተናገራቸው ትንቢቶችና ተስፋዎች እውነት መሆናቸውን በሚያረጋግጥ መንገድ ሕይወቱን መርቷል። (2ቆሮ 1:20) አምላክ ከመንግሥቱና ከመሲሐዊው ገዢ ጋር በተያያዘ ስላለው ዓላማ በዝርዝር የሚገልጹ ትንቢቶች ተነግረው ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወትም ሆነ በመሥዋዕታዊ ሞቱ፣ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን ጥላ ወይም አምሳያ የሆኑ ነገሮች ጨምሮ ስለ እሱ የተነገሩ ትንቢቶች በሙሉ እንዲፈጸሙ አድርጓል። (ቆላ 2:16, 17፤ ዕብ 10:1) በመሆኑም ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ‘ስለ እውነት መሥክሯል’ ሊባል ይችላል።
እውነት፦ ኢየሱስ ስለ አጠቃላይ እውነት መናገሩ ሳይሆን ስለ አምላክ ዓላማዎች የሚገልጸውን እውነት መጥቀሱ ነበር። በአምላክ ዓላማ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር “የዳዊት ልጅ” የሆነው ኢየሱስ፣ ሊቀ ካህናትና የአምላክ መንግሥት ገዢ ሆኖ በማገልገል የሚጫወተው ሚና ነው። (ማቴ 1:1) ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣበት፣ በምድር ላይ የኖረበትና አገልግሎቱን ያከናወነበት ዋነኛ ምክንያት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን እውነት ማወጅ እንደሆነ ተናግሯል። መላእክት ኢየሱስ ከመወለዱ በፊትም ሆነ የዳዊት ከተማ በሆነችው በቤተልሔም በተወለደበት ወቅት ተመሳሳይ መልእክት አውጀዋል።—ሉቃስ 1:32, 33፤ 2:10-14
(ዮሐንስ 18:38ሀ) ጲላጦስም “እውነት ምንድን ነው?” አለው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 18:38ሀ
እውነት ምንድን ነው?፦ ጲላጦስ ጥያቄ ያነሳው ኢየሱስ ስለተናገረለት “እውነት” ሳይሆን ስለ አጠቃላይ እውነት መሆን አለበት። (ዮሐ 18:38) ጲላጦስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው እውነተኛ የማወቅ ፍላጎት ኖሮት ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ መልሱን ይነግረው እንደነበር አያጠራጥርም። ጲላጦስ ግን ይህን ጥያቄ ያነሳው ፌዝ ወይም ጥርጣሬ በሚንጸባረቅበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም፤ “እውነት? ደግሞ እሱ ምንድን ነው? እውነት የሚባል ነገር የለም!” ብሎ የተናገረ ያህል ነው። ደግሞም ጲላጦስ ኢየሱስ መልስ እስኪሰጠው እንኳ ሳይጠብቅ ትቶት በውጪ ወዳሉት አይሁዳውያን ሄዷል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 19:30) ኢየሱስ የኮመጠጠውን ወይን ጠጅ ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ፤ ራሱንም ዘንበል አድርጎ መንፈሱን ሰጠ።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 19:30
መንፈሱን ሰጠ፦ ወይም “ሞተ፤ እስትንፋሱ ቀጥ አለ።” “መንፈስ” (በግሪክኛ ኒውማ) የሚለው ቃል እዚህ ላይ “እስትንፋስን” ወይም “የሕይወት ኃይልን” ሊያመለክት ይችላል። በማር 15:37 እና በሉቃስ 23:46 በሚገኙት ተመሳሳይ ዘገባዎች ላይ ኤክፕነኦ (ቃል በቃል “ትንፋሽ ማውጣት”) የሚለው የግሪክኛ ግስ የተሠራበት መሆኑ ይህን ሐሳብ የሚደግፍ ነው፤ (ይህ ግስ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “ሞተ” ወይም በግርጌ ማስታወሻው መሠረት “እስትንፋሱ ቆመ” ተብሏል)። አንዳንዶች እዚህ ጥቅስ ላይ “ሰጠ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ ኢየሱስ፣ ሁሉ ነገር ስለተፈጸመ በሕይወት ለመቆየት መታገሉን እንዳቆመ የሚጠቁም መሆኑን ይናገራሉ። ኢየሱስ በፈቃደኝነት “ሕይወቱን እስከ ሞት ድረስ አፍስሷል።”—ኢሳ 53:12፤ ዮሐ 10:11
(ዮሐ 19:31) ዕለቱ የዝግጅት ቀን ስለነበር አይሁዳውያን በሰንበት (ያ ሰንበት ታላቅ ሰንበት ስለነበር) አስከሬኖቹ በመከራ እንጨቶቹ ላይ ተሰቅለው እንዳይቆዩ ሲሉ እግራቸው ተሰብሮ እንዲወርዱ ጲላጦስን ጠየቁት።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 19:31
ያ ሰንበት ታላቅ ሰንበት ስለነበር፦ የፋሲካ ማግስት ይኸውም ኒሳን 15 በየትኛውም የሳምንቱ ቀን ላይ ቢውል ምንጊዜም ሰንበት ይሆን ነበር። (ዘሌ 23:5-7) ይህ ልዩ ሰንበት፣ ከመደበኛው ሰንበት (የአይሁዳውያን ሳምንት ሰባተኛ ቀን፤ ዓርብ ፀሐይ ከምትጠልቅበት ጊዜ ጀምሮ ቅዳሜ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ይቆያል) ጋር ሲገጣጠም “ታላቅ ሰንበት” ይሆናል። ኢየሱስ የሞተው ዓርብ ዕለት ሲሆን በማግስቱ ታላቅ ሰንበት ነበር። ከ29 እስከ 35 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ ኒሳን 14 ዓርብ ቀን የዋለው በ33 ዓ.ም. ብቻ ነው። ይህ ማስረጃ ኢየሱስ የሞተው ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. መሆን አለበት የሚለውን መደምደሚያ የሚደግፍ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐ 18:1-14) ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነገሮች ከጸለየ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ ወደ አንድ የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ እሱና ደቀ መዛሙርቱም ወደ አትክልት ስፍራው ገቡ። 2 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ጊዜ በዚህ ስፍራ ይገናኝ ስለነበር አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ቡድን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አስከትሎ መጣ፤ እነሱም ችቦና መብራት እንዲሁም መሣሪያ ይዘው ነበር። 4 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚደርስበትን ነገር ሁሉ ስላወቀ ወደ ፊት ራመድ ብሎ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። 5 እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ሲሉ መለሱለት። እሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም ከእነሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6 ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ሲላቸው ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ። 7 ዳግመኛም “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” አሉት። 8 ኢየሱስም መልሶ “እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” አለ። 9 ይህም የሆነው “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ መካከል አንዱም እንኳ አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 10 በዚህ ጊዜ ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው። የባሪያውም ስም ማልኮስ ነበር። 11 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጴጥሮስን “ሰይፉን ወደ ሰገባው መልስ። አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት አይኖርብኝም?” አለው። 12 ከዚያም ወታደሮቹና የጦር አዛዡ እንዲሁም ከአይሁዳውያን የተላኩት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። 13 በመጀመሪያም ወደ ሐና ወሰዱት፤ ምክንያቱም ሐና በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው የቀያፋ አማት ነበር። 14 ቀያፋ ደግሞ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት ለእነሱ የተሻለ እንደሚሆን ለአይሁዳውያን ምክር የሰጠው ሰው ነው።