የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ
ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ ክፍል 15:- ከ1095-1453 እዘአ—ሰይፍ መምዘዝ
“ሰዎች ስለ ሃይማኖት ይከራከራሉ፣ ስለ ሃይማኖት ይጽፋሉ፣ ለሃይማኖታቸው ይዋጋሉ፣ ለሃይማኖታቸው ይሞታሉ፤ ሃይማኖታቸው እንደሚያዛቸው መኖር ግን አይሆንላቸውም።”—ቻርለስ ካሌብ ኮልተን የተባሉ የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ቄስ
ክርስትና በተመሠረተባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከእምነታቸው ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ብዙ አባላት ነበሩት። እነዚህ ሰዎች እምነታቸውን ለመከላከል ‘የመንፈስ ሰይፍ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል’ ይጠቀሙ ነበር። (ኤፌሶን 6:17) ቆየት ብሎ ግን ከ1095 እስከ 1453 ባሉት ዘመናት መካከል የተፈጸሙት ድርጊቶች እንደሚያሳዩት ከእውነተኛ ክርስትና ጋር ተስማምተው የማይኖሩ የስም ክርስትያኖች ሌላ ዓይነት ሰይፍ መምዘዝ ጀመሩ።
በስድስተኛው መቶ ዘመን ምዕራባዊው የሮም መንግሥት ከሕልውና ውጪ ሆኖ ነበር። ርዕሰ ከተማውን ቁስጥንጥንያ ላይ ባደረገው የምሥራቃዊው የባይዛንታይን መንግሥት ተተክቶ ነበር። ይሁን እንጂ ለሁለት ተከፍለው የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት አንድ የጋራ ጠላት እንደመጣባቸው ወዲያው ተገነዘቡ። እስልምና በታላቅ ፍጥነት በመስፋፋት ላይ ነበር።
ምሥራቃዊቷ ቤተ ክርስቲያን ይህን የተገነዘበችው በሰባተኛው መቶ ዘመን ሙስሊሞች ግብፅንና በሰሜን አፍሪካ የሚገኙትን ሌሎች የባይዛንታይን ግዛት ክፍሎች በቁጥጥራቸው ሥር ሲያውሉ ነበር።
ምዕራባዊቷ ቤተ ክርስቲያን አንድ መቶ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስልምና ስፔይንን አዳርሶ ወደ ፈረንሳይ በመገስገስ ላይ እንደሚገኝና ከፓሪስ መቶ ስልሳ ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ላይ እንደ ደረሰ ስትረዳ ደነገጠች። ብዙ የስፔይን ካቶሊኮች እምነታቸውን ለውጠው ሙስሊሞች ሆኑ። ሌሎች ደግሞ የእስልምናን ሥርዓቶችና ባህሎች ተቀበሉ። ኧርሊ እስላም የተባለው መጽሐፍ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናኗን በማጣቷ በስፔናውያን ልጆቿ መካከል የበቀል እሳት ለማነሣሣት የማያቋርጥ ጥረት አድርጋለች” ብሏል።
የስፔይን ካቶሊኮች አብዛኛውን የአገራቸውን ክፍል በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሉ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ “በሙስሊም ዜጎቻቸው ላይ ተነሥተው ያለ ርኅራኄ አሳደዷቸው። እምነታቸውን እንዲክዱ አስገደዷቸው፤ ከአገራቸውም አባረሯቸው። በተጨማሪም ማናቸውንም ዓይነት የእስልምና ባህል ርዝራዥ ከስፔይን ምድር ለማስወገድ ጥብቅ እርምጃዎችን ወሰዱ።”
በሰይፍ ስለት
በ1095 ሊቀ ጳጳስ ዳግማዊ ኧርባን አውሮፓውያን ካቶሊኮች ቃል በቃል ሰይፍ እንዲያነሡ ጥሪ አቀረቡ። ሕዝበ ክርስትና ብቸኛ ባለቤት ነኝ ትልባቸው ከነበሩት የመካከለኛው ምሥራቅ ቅዱሳን መሬቶች እስልምናን ለማጥፋት ተወሰነ።
“ትክክለኛ” ጦርነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በዚህ ዘመን ብቻ የተፈጠረ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በስፔይንና በሲሲሊ በሙስሊሞች ላይ የተደረገው ጦርነት “ትክክለኛ” ጦርነት ነው ተብሎ ነበር። በተጨማሪም ቢያንስ ኧርባን ጥሪ ከማቅረባቸው ከአሥር ዓመት በፊት ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ ሰባተኛ “ማናቸውንም የአምላክ ጠላቶች የሚዋጋ ሚሊሺያ ክርስቲ እንዲቋቋም ሐሳብ ያመነጩ ከመሆናቸውም በላይ አንድ ሠራዊት ወደ ምሥራቅ ለማዝመት አስበው ነበር” በማለት የፕሪንስተን ሃይማኖታዊ ኮሌጅ አባል የሆኑት ካርልፍሬድ ፍሮሊክ ገልጸዋል።
ኧርባን ይህን ለማድረግ ያሰቡት በከፊል አሌክሰስ የተባለው የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ላቀረበው የእርዳታ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነበር። ይሁን እንጂ ሊቀ ጳጳሱ ይህን ለማድረግ የተነሳሱበት ሌላው ምክንያት በሕዝበ ክርስትና ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ክፍል መካከል የነበረው ግንኙነት እየተሻሻለ የመጣ ይመስል ስለ ነበር እነዚህ ጥለኞች የነበሩ እህትማማች አብያተ ክርስቲያናት አንድነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለው በማሰባቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሊቀ ጳጳሱ የክሌርሞንት ጉባኤ እንዲጠራ አደረጉ። ጉባኤው በዚህ “ቅዱስ” ተግባር ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉ ከማንኛውም ኃጢአት ሥርየት እንደሚያገኙ ገለጸ። ለዚህ ጥሪ የተሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ከተጠበቀው በላይ ነበር። “ዲየስ ቮልት” (“አምላክ ፈቅዷል”) የሚለው መፈክር በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ቤተ ክርስቲያናት ሰዎችን የሚያስተባብር ሆነ።
ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎች ተደረጉ። (በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) መጀመሪያ ላይ ሙስሊሞች ወረራውን የፈጸሙባቸው ባይዘንታውያን መስለዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ የወራሪዎቹን ትክክለኛ ምንጭ ከተገነዘቡ በኋላ ፍራንካውያን በማለት ጠሯቸው። ፍራንካውያን የጀርመን ሕዝቦች ሲሆኑ ፈረንሳይ ከጊዜ በኋላ ስሟን ያገኘችው ከእነዚህ ሕዝቦች ስም ነው። ሙስሊሞች የእነዚህን አውሮፓውያን “አረመኔዎች” ዘመቻ ለመመከት ጂሃድ ማለትም ቅዱስ ጦርነት ወይም ፍልሚያ ለማወጅ ተነሣሱ።
እንግሊዛዊ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴዝሞንድ ስቴዋርት ስለ ሁኔታው ሲያብራሩ “በምሳሌነታቸውና የሃይማኖቱን ሕጎች በማስተማር እስልምናን የተከሉ ምሁራንና ነጋዴዎች የመኖራቸውን ያህል እስልምና ማለት የጦርነት ጥሪ የሚመስላቸው ወታደሮች ነበሩ” ብለዋል። ኑረዲን የተባለው የሙስሊሞች መሪ ከ12ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ በሰሜናዊ ሶርያና በላይኛው መስጴጦምያ የነበሩትን ሙስሊሞች በማስተባበር ጥሩ ብቃት ያለው ወታደራዊ ኃይል አደራጅቶ ነበር። ስለዚህ “በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የክርስቶስን ሃይማኖት ለማስፋፋት ጦራቸውን እንዳነሡ ሁሉ ሙስሊሞችም የነቢዩን ሃይማኖት ለማስፋፋት ሰይፋቸውን መዝዘዋል” በማለት ስቴዋርት ተናግረዋል።
እርግጥ ብዙውን ጊዜ ለዘመቻ ለመነሳሳት ምክንያት ይሆናቸው የነበረው ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት የነበራቸው ፍላጎት ብቻ አልነበረም። ዘ በርዝ ኦቭ ዩሮፕ የተባለው መጽሐፍ አብዛኞቹ አውሮፓውያን በመስቀል ጦርነቶች የተካፈሉት “ዝና ለማትረፍ ወይም ምርኮ ለመሰበሰብ፣ ወይም ግዛታቸውን ለማስፋፋት ወይም አገሮችን አጠቃሎ ለመግዛት ወይም የዕለት ተለት ኑሯቸው ሰልችቷቸው ጀብዱ ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ ለማግኘት ሲሉ ነበር” ይላል። የኢጣሊያ ነጋዴዎች በምሥራቅ ሜድትራኒያን አገሮች ውስጥ ንግዳቸውን ለማስፋፋት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ሆኖም ዓላማቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉም በሕዝበ ክርስትና “ትክክለኛ” ጦርነትም ሆነ በሙስሊሞች ጂሃድ በመሳተፍ ለሃይማኖታቸው ለመሞት ፈቃደኞች ነበሩ።
ሰይፉ ያልተጠበቁ ውጤቶችን አመጣ
ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንዲህ ይላል:- “የመስቀል ጦርነቶች በስተ ምሥራቅ ይኖሩ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠሩ ቢሆኑም በጋለ ስሜት የተነሳሱት የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎች በተመለመሉባቸው አገሮች ማለትም በአውሮፓ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ አይሁዳውያን ላይ ዘምተዋል። የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎች ከነበራቸው ዓላማ አንዱ የኢየሱስን ሞት መበቀል እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ስለ ነበር አይሁዳውያን የጥቃቱ የመጀመሪያ ሰለባዎች ሆኑ። በ1096 በሩወን በአይሁዳውያን ላይ ስደት ተቀሰቀሰ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በቮርምስ፣ በሜይንዝና በኮሎኝ ውስጥ እልቂት ደረሰባቸው።” እነዚህ ስደቶች በናዚ ጀርመን ዘመን ሴማውያንን ለማጥፋት ለታለመው ታላቅ እልቂት መቅድም ነበሩ።
በተጨማሪም የመስቀል ጦርነቶች የምሥራቁ ፓትሪያርክ ማይክል ሴሩላርየስና የምዕራቡ ካርዲናል ሁምበርት እርስ በርሳቸው ከተወጋገዙበት ከ1054 ጀምሮ እየከረረ የመጣው የምሥራቁና የምዕራቡ ቤተ ክርስቲያናት ጥላቻ ይበልጥ እንዲፋፋም አድርገዋል። የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎች በያዟቸው ከተሞች የነበሩትን የግሪክ ቀሳውስት በላቲን ጳጳሳት ሲተኩ የምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን ከምዕራቡ ጋር የነበረው ክፍፍል ተራውን ሕዝብ መንካት ጀመረ።
በሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነት በአራተኛው የመስቀል ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ። የቀድሞው የካንተርበሪ የአንግሊካን ቄስ ሀርበርት ዋደምስ እንደጻፉት በዚያን ጊዜ ሊቀ ጳጳስ ኢኖሰንት ሣልሳዊ “እርስ በርስ የሚቃረኑ ሁለት ነገሮችን” አድርገዋል። በአንድ በኩል የቁስጥንጥያ መወረር አስቆጥቷቸዋል። (በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ሊቀ ጳጳሱ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ላቲኖች በክፋት ምሳሌ ሲሆኑና የዲያብሎስን ተግባር ሲፈጽሙ የግሪኮች ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያት መንበር ወደ መገዛት ትመለሳለች ብሎ መጠበቅ እንዴት ይቻላል? ስለዚህ ግሪኮች ላቲኖችን ከውሾች ይበልጥ የሚጠሉበት በቂ ምክንያት አላቸው።” በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጠረው አጋጣሚ በመጠቀም በቁስጥንጥንያ በምዕራባዊ ፓትሪያርክ የሚመራ የላቲን መንግሥት እንዲቋቋም አድርገዋል።
የባይዛንታይን መንግሥት ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ ከተዋጋ በኋላ በጣም ከመዳከሙ የተነሣ የኦቶማን ቱርኮችን ኃይለኛ ጥቃት መቋቋም ተሳነው። በመጨረሻም ግንቦት 29, 1453 ኦቶማን ቱርኮች ቁስጥንጥንያን ያዙ። ይህ አጼያዊ መንግሥት ድል ተነሥቶ የፈራረሰው በእስልምና ሰይፍ ብቻ ሳይሆን በሮም በነበረችው እህት ቤተ ክርስቲያን ከሚመራው አጼያዊ መንግሥት በተሰነዘረው ሰይፍ ጭምር ነበር። የሕዝበ ክርስትና መከፋፈል እስልምና በአውሮፓ ውስጥ የሚስፋፋበትን የተመቻቸ ሁኔታ ፈጠረ።
የፖለቲካና የስደት ሰይፍ
የመስቀል ጦርነቶች ሊቃነ ጳጳሳት በሃይማኖትና በፖለቲካ አመራር ያላቸውን የወሳኝነት ሥልጣን አጠናክረዋል። የመስቀል ጦርነቶች “ሊቃነ ጳጳሳት የአውሮፓን ዲፕሎማሲ እንዲቆጣጠሩ አስችለዋል” በማለት ታሪክ ጸሐፊው ጆን ኤች ሙንዲ ጽፈዋል። ብዙም ሳይቆይ “ቤተ ክርስቲያን ከየትኛውም ምዕራባዊ መንግሥት የበለጠ ፖለቲካዊ ሥልጣን ያላት . . . የአውሮፓ ታላቅ መንግሥት ልትሆን ችላ ነበር።”
ይህን ለማድረግ የቻለችው ምዕራባዊው የሮም መንግሥት በወደቀ ጊዜ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ብቸኛ አስተባባሪ ኃይል ስለ ሆነች በዚያን ጊዜ ጠንካራ በሆነ ዓለማዊ ንጉሥ ማለትም በባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ትተዳደር ከነበረችው ከምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ሚና መጫወት ጀመረች። የምዕራቧ ቤተ ክርስቲያን የነበራት ፖለቲካዊ የበላይነት ሊቀ ጳጳሱ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የበላይነት አለው የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ አስችሏል። የምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሐሳብ አትቀበለውም። የምሥራቋ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሱ መከበር እንደሚገባው ብታምንም መሠረተ ትምህርቶችንና ሕጎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች የመጨረሻ ሥልጣን አለው በሚለው ሐሳብ አትስማማም።
የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በነበራት የፖለቲካ ሥልጣንና በተሳሳተ ሃይማኖታዊ እምነት በመጠቀም በሰይፍ አማካኝነት የተነሣባትን ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞ ለማጥፋት ተነሣች። መናፍቃንን ማደን ዋንኛ ሥራዋ ሆነ። በቺኮዝላቫኪያ ፕራግ ውስጥ በሚገኘው የካርልስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሮች የሆኑት ሚሮስላቭ ሮችና አና ስካይቦቫ ኢንኩዊዝሽን የተባለው መናፍቃንን ለመዳኘት የተሰየመ ልዩ ችሎት እንዴት ይሠራ እንደ ነበር ሲገልጹ “ከተለመደው አሠራር ውጪ በሆነ መንገድ የጠቋሚዎቹ ስም . . . አይገለጽም ነበር” ብለዋል። በ1252 ሊቀ ጳጳስ ኢኖሰንት አራተኛ ሰዎችን ማሠቃየትን የሚፈቅደውን “አድ ኤክስቲርፓንዳ” የተባለ ድንጋጌ አወጡ። “በ13ኛው መቶ ዘመን መናፍቃንን ለመግደል በብዛት ይጠቀሙበት የነበረው በእንጨት ላይ የማቃጠል ዘዴ . . . ቤተ ክርስቲያን ደም ከማፍሰስ ወንጀል ነፃ እንድትሆን ታስቦ የሚፈጸም አገዳደል ነበር።”
የኢንኩዊዝሽን አስፈጻሚዎች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀጥተዋል። ሌሎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእንጨት ላይ ታስረው ተቃጥለዋል። በዚህም ምክንያት ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት የሚከተለውን አስተያየት ለመሰንዘር ተገደዋል:- “አንድ የታሪክ ሰው ወይም አንድ ክርስቲያን ምንም ያህል ዓይኑን ቢጨፍን ኢንኩዊዝሽን . . . ማንኛውም አውሬ የማያሳየው ጭካኔ የተገለጸበትና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት የሥነ ምግባር ጉድለቶች ሁሉ የከፋ እንደሆነ አድርጎ ለመመልከት ይገደዳል።”
በኢንኩዊዝሽን የተፈጸሙት ድርጊቶች “ሰዎች በሃይማኖት ተገፋፍተው የሚያደርጉትን ያህል ክፋትን በተሟላ መንገድና በደስታ የሚፈጽሙበት ጊዜ የለም” በማለት የ17ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ ፈላስፋና ሳይንቲስት የነበረው ብሌዝ ፓስካል የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል። እውነቱን ለመናገር ቃየን አቤልን ከገደለበት ጊዜ አንሥቶ ሰዎች ከእነርሱ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ለማጥፋት የስደት ሰይፍ መጠቀማቸው የሐሰት ሃይማኖት ዋነኛ ባሕርይ ሆኖ ቆይቷል።— ዘፍጥረት 4:8
በሚከፋፍል ሰይፍ መለያየት
በወቅቱ የነበረው ብሔራዊ ሽኩቻና የፖለቲካ እንቅስቃሴ በ1309 የሊቀ ጳጳሱ መኖሪያ ከሮም ወደ አቪኞ እንዲዛወር ምክንያት ሆነ። የሊቀ ጳጳሱ መኖሪያ በ1377 ወደ ሮም እንዲመለስ ቢደረግም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኧርባን ስድስተኛ የተባሉት አዲስ ሊቀ ጳጳስ ሲመረጡ ሌላ ግጭት ተፈጠረ። ሆኖም ኧርባንን የመረጡት እነዚያው ካርዲናሎች የኧርባን ተቀናቃኝ የሆኑትን ሊቀ ጳጳስ ክሊመንት ሰባተኛን መረጡ። እርሳቸውም መቀመጫቸውን በአቪኞ አደረጉ። እንዲያውም በ15ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ለጥቂት ጊዜያት ሦስት ሊቀ ጳጳሳት በአንድ ጊዜ ይገዙ ስለ ነበር ነገሮች በይበልጥ ግራ የሚያጋቡ ሆኑ!
ይህ የምዕራቡ ወይም ታላቁ ክፍፍል የተባለው ሁኔታ በኮንስታንስ ጉባኤ እልባት አገኘ። ይህ ጉባኤ የመጨረሻ ክህነታዊ ሥልጣን የሚኖረው ሊቀ ጳጳሱ ሳይሆን ጠቅላላ ጉባኤው እንደ ሆነ የሚገልጽ ደምብ በማውጣት ተጠናቀቀ። ስለዚህ በ1417 ጉባኤው ማርቲን አምስተኛን አዲስ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ለመምረጥ ቻለ። ቤተ ክርስቲያኒቱ አጥታ የነበረችውን አንድነት ለማግኘት ብትችልም በጣም ተዳክማ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ጠባሳዎች እያሉ መንበረ ጵጵስናው ሊቀ ጳጳሱ ሃይማኖታዊ ተሐድሶ እንደሚያስፈልግ ለመቀበል አሻፈረኝ አለ። የሴንት ቭላዲሚር የኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ ኮሌጅ አባል የሆኑት ጆን ኤል ቡጃምራ እንደተናገሩት ይህን ለመቀበል አለመቻሉ “በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ለተከሰተው ተሐድሶ ምክንያት ሆኗል።”
ከሃይማኖታቸው ጋር ተስማምተው ይኖሩ ነበርን?
የክርስትና መሥራች ተከታዮቹን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አዟል፤ ሆኖም ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም በሥጋዊ ኃይል እንዲጠቀሙ አላዘዛቸውም። እንዲያውም “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በተመሳሳይም ተከታዮቹ መልእክታቸውን በማይቀበል ሰው ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ተከታዮቹን አላስተማረም። እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ማክበር ይኖርበታል:- “የጌታ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነ ሰው፣ በሁሉም ዘንድ ገር፣ የማስተማር ችሎታ ያለውና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት እንጂ መጣላት አይገባውም። . . . ተቃዋሚዎችንም በገርነት የሚያርም መሆን አለበት።”— ማቴዎስ 26:52፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25 የ1980 ትርጉም
ሕዝበ ክርስትና በሰይፍም ሆነ ምሳሌያዊ በሆነው የፖለቲካና የስደት ሰይፍ በመጠቀሟ መሥራቿ እንደ ሆነ የምትናገረውን የክርስቶስን አመራር እንዳልተከተለች ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ በእጅጉ ተከፋፍላ የምትገኘው ሕዝበ ክርስትና ፈጽማ እንዳትፈራርስ ያሰጋታል። የሮም ካቶሊክ ሃይማኖት “ከፍተኛ ተሐድሶ የሚያስፈልገው ሃይማኖት” ነበር። ሆኖም ተሐድሶ ተደርጎ ይሆን? ከተደረገስ መቼና በማን ተደረገ? ሃይማኖታዊ ተሐድሶውን ያካሄደው ማን ነው? የሚቀጥለው እትማችን ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠናል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
መልካም ክርስቲያናዊ ገድል ነውን?
የመስቀል ጦርነቶች ክርስቲያኖች እንዲፈጽሟቸው የታዘዟቸው መልካም ክርስቲያናዊ ገድሎች ነበሩን?— 2 ቆሮንቶስ 10:3, 4፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:18
የመጀመሪያው የመስቀል ጦርነት (1096-99) ኢየሩሳሌም እንደገና እንድትያዝና በምሥራቅ አራት የላቲን መንግሥታት ማለትም የኢየሩሳሌም ንጉሣዊ መንግሥት፣ የኤዴሳ ካውንቲ፣ የአንጾኪያ ፕርንሲፓሊቲና የትሪፖሊ ካውንቲ እንዲመሠረቱ አስችሏል። ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ የጠቀሱት አንድ ጽሑፍ ኢየሩሳሌም ስለ ተያዘችበት ሁኔታ እንዲህ ይላል:- “በጣም አሠቃቂ እልቂት ተፈጽሞ ነበር፤ ሰዎች በፈረስ በሚጋልቡበት ወቅት እስኪፈናጠቅባቸው ድረስ የተሸናፊዎቹ ደም በመንገድ ላይ እንደ ጎርፍ ፈስሶ ነበር። ውድቅት ላይ የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎች የወይን መጥመቅያውን ከረገጡበት ቦታ ‘የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው’ ወደ ክርስቶስ ቅዱስ መቃብር መጡና በደም የተጨማለቁ እጆቻቸውን ለጸሎት አነሡ።”
ሁለተኛው የመስቀል ጦርነት (1147-49) የተቀሰቀሰው በ1144 የኤዴሳ ካውንቲ በሶርያውያን ሙስሊሞች ስለ ተወሰደች ነበር፤ ሙስሊሞች የሕዝበ ክርስትናን “አረመኔዎች” በተሳካ ሁኔታ መክተው ሲመልሷቸው ጦርነቱ አበቃ።
ሦስተኛው የመስቀል ጦርነት (1189-92) የተካሄደው ሙስሊሞች ኢየሩሳሌምን እንደገና በቁጥጥራቸው ሥር ካደረጉ በኋላ ሲሆን ከጦር መሪዎቹ መካከል “አንበሳው” በመባል የሚታወቀው የእንግሊዙ ቀዳማዊ ሪቻርድ ይገኝበት ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንደሚለው ወዲያው “በመዳከማቸው፣ እርስ በርሳቸው በመጋጨታቸውና ቅንጅት በማጣታቸው ምክንያት ተበታተኑ።”
አራተኛው የመስቀል ጦርነት (1202-4) በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከግብፅ ወደ ቁስጥንጥንያ ዞረ፤ በወቅቱ በስደት ላይ የነበረውና የባይዘንታይን ዘውድ ይገባኛል ይል የነበረው አሌክሰስ ወደ ሥልጣን ከመለሱት ቁሳዊ እርዳታ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቶ ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ጦርነቶች ተዋጊዎች በቁስጥንጥንያ ላይ ያደረሱትን ዘረፋ ፈጽሞ አትረሳም” ካለ በኋላ አክሎ ሲናገር “በኦርቶዶክስና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሊጠገን የማይችል ክፍፍል የተፈጠረበትን ጊዜ በትክክል መጥቀስ ካስፈለገ ቢያንስ ከሥነ ልቦና አንፃር ይበልጥ ትክክለኛ ጊዜ የሚሆነው 1204 ዓመት ነው” ብሏል።
በሕፃናት የመስቀል ጦርነት (1212) ምክንያት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የጀርመንና የፈረንሳይ ሕፃናት ገና ውጊያው ቦታ ሳይደርሱ ሞተው አልቀዋል።
አምስተኛው የመስቀል ጦርነት (1217-21) በሊቀ ጳጳሳት መሪነት ከተደረጉት ጦርነቶች የመጨረሻው ሲሆን በአመራር ጉድለትና በቀሳውስት ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል።
ስድስተኛው የመስቀል ጦርነት (1228-29) ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ ዘጠነኛ ቀደም ሲል አውግዘዋቸው የነበሩት የሆኸነስታፈን ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ ፍሬደሪክ የመሩት ጦርነት ነው።
ሰባተኛውና ስምንተኛው የመስቀል ጦርነት (1248-54 እና 1270-72) በፈረንሳዩ ሉዊ ዘጠነኛ የተመራ ሲሆን በሰሜን አፍሪካ በመሞታቸው ምክንያት ዘመቻው ቆመ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው የመስቀል ጦርነት መታሰቢያ የሆነው በጀርመን ቮርምስ የሚገኘው የአይሁዳውያን መቃብር