በልጅነታቸው የወሲባዊ በደል ሰለባ የሆኑ ሰዎች
“አሁን 40 ዓመት ገደማ ሆኖኛል” ትላለች ኢሌን።a “ችግሩ ከደረሰብኝ 30 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም አሁንም ድረስ አእምሮዬ ውስጥ እየተመላለሰ ይረብሸኛል። ብስጭት፣ የጥፋተኝነት ስሜትና በትዳሬ ውስጥ ያሉት ችግሮች ይበጠብጡኛል! ሰዎች ችግሬን ለመረዳት ቢጥሩም አልሆነላቸውም።” ኢሌን የደረሰባት ችግር ምንድን ነው? በልጅነቷ ወሲባዊ በደል የተፈጸመባት ሲሆን መዘዙም ለረጅም ጊዜ አብሯት ሊዘልቅ ችሏል።
እንዲህ ዓይነት በደል የተፈጸመባት ኢሌን ብቻ አይደለችም። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ወንዶች ይህ ዓይነቱ በደል እንደተፈጸመባቸው የተካሄዱት ጥናቶች አመልክተዋል።b እንግዲያው በልጆች ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ በደል አልፎ አልፎ የሚከሰት ያልተለመደ ምግባር ሳይሆን የትኛውም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊና ጎሳዊ ድንበር ያልገደበው በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኝ መቅሰፍት ነው።
ደግነቱ አብዛኞቹ ወንዶችና ሴቶች በአንድ ሕፃን ላይ እንዲህ ዓይነት በደል መፈጸም ጨርሶ የማያስቡት ነገር ነው። ይሁን እንጂ አደገኛ የሆኑ የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይህ ጸያፍ ዝንባሌ ተጠናውቷቸዋል። ብዙዎች ከሚያስቡት በተቃራኒው ደም እንደተጠማ ነፍሰ ገዳይ በመጎምጀት ስሜት ተውጠው ልጆች በሚጫወቱባቸው አካባቢዎች በማድባት ወሲባዊ በደል የሚፈጽሙ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኞቹ የጨዋነት ካባ የደረቡ ናቸው። ርኩስ የሆነ ምኞታቸውን የሚያረኩት ምንም የማያውቁ፣ ሁሉን የሚያምኑና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሕፃናትን ብዙውን ጊዜም የራሳቸውን ሴቶች ልጆች ዒላማ በማድረግ ነው።c በሌሎች ፊት ሲሆኑ በደግነትና በርኅራኄ መንፈስ ይይዟቸው ይሆናል። ብቻቸውን ሲሆኑ ግን ያስፈራሯቸዋል፣ የኃይል ድርጊት ይፈጽሙባቸዋል፣ እንዲሁም ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ርካሽ ወሲባዊ ጥቃት ያደርሱባቸዋል።
እርግጥ ነው፣ የተከበሩ በሚመስሉ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ እንዲህ ያሉ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ድርጊቶች ይፈጸማሉ ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንኳ ሕፃናትን “ለጊዜያዊ . . . የጾታ ስሜት እርካታ” ይጠቀሙባቸው ነበር። (ዚ ኢንተርናሽናል ክሪቲካል ኮሜንቴሪ፤ ከኢዩኤል 3:3 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሮ ነበር:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ . . . ፍቅር የሌላቸው ... ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ” ይሆናሉ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በልጆች ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ በደል በእጅጉ መስፋፋቱ ሊያስገርመን አይገባም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3, 13
በልጅነት የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ምንም ዓይነት አካላዊ ጠባሳ ላይተው ይችላል። በተጨማሪም በልጅነታቸው የእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ዐዋቂ ሰዎች በሙሉ በግልጽ የሚታይ ጭንቀት ላይኖርባቸው ይችላል። ሆኖም አንድ ጥንታዊ ምሳሌ እንደሚለው “ሳቅ ሐዘንን ይሰውራል።” (ምሳሌ 14:13 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ብዙዎቹ ሰለባዎች ጥልቅ የሆነ የስሜት ጠባሳ ማለትም ውስጥ ውስጡን የሚበላ ስውር ቁስል አለባቸው። ይሁንና በልጅነት የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት የአንዳንዶችን ሕይወት ይህን ያህል የሚያመሰቃቅለው ለምንድን ነው? በጊዜ ሂደት ብቻ የሁሉም ሰለባዎች ቁስል ሊሽር ይችላል ብሎ መጠበቅ የማይቻለው ለምንድን ነው? ይህ በጣም አሳሳቢ የሆነ ችግር መጠነ ሰፊ መሆኑ ትኩረት እንድንሰጠው ያስገድደናል። እርግጥ ነው፣ በተለይ ልጅ በነበርሽበት ጊዜ ወሲባዊ በደል ተፈጽሞብሽ ከነበረ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን አንዳንድ ሐሳቦች ማንበቡ ሊከብድሽ ይችል ይሆናል። ሆኖም ማገገም የምትችይበት አጋጣሚ እንዳለ እርግጠኛ ሁኚ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሁሉም ስም ተለውጧል።
b በልጆች ላይ የሚፈጸመውን ወሲባዊ በደል በተመለከተ የሚሰጡት ፍቺዎችና ጥናቶቹ የሚካሄዱባቸው መንገዶች በእጅጉ ስለሚለያዩ ትክክለኛ አኃዛዊ መረጃ ማግኘት በጣም አዳጋች ነው።
c አብዛኞቹ ሕፃናት ወሲባዊ በደል የሚፈጸምባቸው በገዛ አባቶቻቸው ወይም በእንጀራ አባቶቻቸው ነው። በተጨማሪም ታላላቅ ወንድሞቻቸው፣ አጎቶቻቸው፣ የወንድ አያቶቻቸው፣ ሌሎች የሚያውቋቸው ትልልቅ ሰዎችና ምንም የማያውቋቸው ሰዎችም ይህን በደል ይፈጽሙባቸዋል። አብዛኞቹ ሰለባዎች ሴቶች በመሆናቸው በአንስታይ ጾታ መጠቀም መርጠናል። ሆኖም እዚህ ላይ የቀረበው አብዛኛው መረጃ ለሁለቱም ጾታዎች ይሠራል።