በደካማ ክንፎች ላይ የተሳፈረ ሞት
ናይጄሪያ ውስጥ በሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንደተጠናቀረው
ጦርነቱ የጋዜጦች ዋና ዜና ሆኖ የተዘገበ አይደለም፤ ሆኖም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት እንደቀጠፈ ይነገርለታል። በቦምቦችና በጥይቶች የሚካሄድ ጦርነት አይደለም፤ ካስከተለው ሥቃይና ካጠፋው ሕይወት አንጻር ሲታይ ግን ከጦርነቶች እኩል የሚወዳደር ወይም ከእነርሱ የላቀ ነው። በዚህ ጦርነት ሞት የሚመጣው ቦምብ ጣይ በሆኑ ከባድ የጠላት አውሮፕላኖች ሳይሆን ምንም አቅም በሌላቸው የአንዲት ሴት የወባ ትንኝ ክንፎች ላይ ተሳፍሮ ነው።
ቀኑ መሽቷል፤ ቤተሰቡ እንቅልፍ ላይ ነው። አንዲት የወባ ትንኝ በአየር ላይ እየቀዘፈች ወደ መኝታ ቤቱ ትመጣለች፤ ክንፎቿ በሴኮንድ ከ200 እስከ 500 ጊዜ ይርገበገባሉ። የሰው ደም ተጠምታለች። ቀስ ብላ በአንድ ልጅ ክንድ ላይ አረፈች። ክብደቷ 0.000284 ግራም ብቻ በመሆኑ ልጁ ቀስቀስ እንኳን አላለም። ከዚያ በኋላ የልጁን ቆዳ በቀጭኑ የደም ሥሩ በኩል የምትወጋበትን ስለታም በሆነው የአፏ ክፍል ጫፍ ላይ የሚገኘውን የመጋዝ ጥርስ የመሰለ ቀጭን መርፌ ትዘረጋለች። በጭንቅላቷ ላይ የሚገኙትን ሁለት የደም መምጠጫዎች በመጠቀም ደሙን ትመጣለች። በዚያው ወቅት የወባ ጥገኛ ህዋሳት ከወባ ትንኟ የምራቅ ዕጢዎች ወደ ልጁ ደም ሥሮች ሰተት ብለው ይገባሉ። የማጥቃት ዘመቻው በቅጽበት ተከናውኗል። ልጁ ምንም ነገር አልተሰማውም። የወባ ትንኟ የሰውነቷ ክብደት በደም ሶስት ጊዜ እጥፍ ጨምሮ ተመልሳ ትበራለች። ብዙም ቀናት ሳያልፉ ልጁ እስከሞት በሚያደርስ ሁኔታ ይታመማል። የወባ በሽታ ይዞታል።
ይህ ትዕይንት በሺህ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተደጋግሟል። ይህም ለከፍተኛ ሥቃይና ለብዙ ሰዎች ሕይወት እልፈት ምክንያት ሆኗል። የወባ በሽታ ጨካኝና አይምሬ የሆነ የሰው ዘር ጠላት መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።
ይህን ጠላት ለማግኘት በትዕግሥት የተደረገ ፍለጋ
የወባ በሽታን ለማጥፋት በተደረገው ውጊያ ከአንጋፋዎቹ ግኝቶች አንዱ በአውሮፓ ታላላቅ ሳይንቲስቶች ሳይሆን ሕንድ ውስጥ በሚኖር የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት የቀዶ ጥገና ሐኪም በነበሩት ሰው አማካኝነት የተገኘ ነው። ቀደም ሲል በነበሩት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ የነበረውን አስተሳሰብ በመቀበል የ19ኛው መቶ ዘመን ሳይንቲስቶችና ዶክተሮች ሰዎች ረግረጋማ በሆነ ቦታ የሚገኘውን መጥፎ ሽታ በመሳብ በበሽታው ይያዛሉ ብለው ያስቡ ነበር።a ዶክተር ሮናልድ ሮስ ከዚህ የተለየ አቋም በመያዝ በሽታው በወባ ትንኞች አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል ብለው ያምኑ ነበር። ሌላው ቀርቶ የወባ በሽታ ጥገኛ ህዋሳት በሰው ደም ሥር ውስጥ ከተገኙ በኋላም ተመራማሪዎች በረግረጋማ ቦታ የበሽታውን መኖር የሚጠቁሙ ነገሮችን ለማግኘት በዚያ አካባቢ የሚገኘውን አየርና ውኃ መመርመራቸውን ቀጥለው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሮስ በወባ ትንኞች የሆድ ዕቃ ላይ ምርምር አካሄዱ።
በመጀመሪያው ላቦሯቶሪያቸው ውስጥ ይጠቀሙበት ከነበረው መሣሪያ አንጻር ሲታይ የወባ ትንኞችን የሆድ ዕቃ ማየቱ ቀላል ሥራ አልነበረም። ምርምራቸውን ባካሄዱበት ወቅት ሮስ እንደሚሉት “የጓደኞቻቸውን ሞት” ለመበቀል ቆርጠው የተነሱ የወባ ትንኞች ወረሯቸው።
በመጨረሻ በነሐሴ 16, 1897 ሮስ አኖፈለስ በተባለች የወባ ትንኝ የሆድ ዕቃ ዳርና ዳር ላይ በአንድ ሌሊት ያደጉ ጥምዝ ቅርጽ ያላቸው ሕዋሳትን አገኙ። የወባ በሽታ ሕዋሳት ነበሩ!
ሮስ በደስታ ተፍለቅልቀው “ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች” ሕይወት የሚያድነውን የተደበቀ ምስጢር እንደፈቱት በማስታወሻቸው ላይ ጻፉ። የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ከሆነው ከቆሮንቶስ ላይም አንድ ጥቅስ በመጥቀስ “ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ?” ሲሉ ጽፈዋል። — ከ1 ቆሮንቶስ 15:55 ጋር አወዳድር።
የወባ በሽታ ያስከተለው ከፍተኛ ጥፋት
የሮስ ግኝት የወባ በሽታን ለማጥፋት በተደረገው ውጊያ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ይህ ግኝት የሰው ልጅ በበሽታውና በሽታውን በሚሸከሙ ነፍሳት ላይ የመጀመሪያውን ከፍተኛ የማጥቃት እርምጃ እንዲወስድ በር ከፍቶለታል።
በአብዛኛዎቹ የታሪክ ዘመናት በወባ በሽታ የጠፋው የሰው ልጅ ሕይወት ከፍተኛ ነው፤ ችግሩም ለረጅም ጊዜ ዘልቋል። የግብጻውያን የጥንት ጽሑፎችና ፓፒረስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከመኖሩ ከ1,500 ዓመታት በፊት የወባ በሽታ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለእልፈት እንደዳረገ ያረጋግጣሉ። በቆላማ ሥፍራ በነበሩት የጥንቷ ግሪክ ውብ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል። የታላቁን አሌክሳንደርንም ሕይወት በለጋነቱ ቀጭቷል። በሮማውያን ከተሞች የነበሩትን ሰዎች ረፍርፏል። ባለጠጋ የሆኑ ሰዎችንም በማባረር ወደ ደጋማ ስፍራዎች እንዲሸሹ አድርጓል። በመስቀል ጦርነቶች፣ በአሜሪካውያን የእርስ በእርስ ጦርነቶችና በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት በብዙ ከፍተኛ ውጊያዎች ላይ ካለቁት የበለጡ ሰዎችን ፈጅቷል።
የወባ በሽታ በአፍሪካ ውስጥ ምዕራብ አፍሪካን “የነጮች መቃብር” የሚል ቅጽል ስም አሰጥቷታል። እንዲያውም በሽታው አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የተሻኮቱትን አውሮፓውያን አላማቸውን ዳር ማድረስ እንዳይችሉ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል። በዚህም የተነሣ አንድ የምዕራብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የወባ ትንኟን ትልቅ ጀብዱ የፈጸመች ብሔራዊ ጀግና ሲል ጠርቷታል! በመካከለኛው አሜሪካ የወባ በሽታ ፈረንሳውያን የፓናማን ቦይ ለመክፈት ያደረጉትን ጥረት ለማኮላሸት አስተዋጽኦ አበርክቷል። በደቡብ አሜሪካ በብራዚል ውስጥ የማሞሬ–ማዴራ የባቡር ሐዲድ ሲዘረጋ የወባ በሽታ አንድ የሐዲድ ብረት በተነጠፈ ቁጥር የአንድን ሰው ሕይወት ይቀጥፍ ነበር ተብሎ ተነግሮለታል።
በሽታውን ድል ለማድረግ የተደረገ ውጊያ
የወባ በሽታን ለመከላከል እንደሚረዳ በማወቅ የተደረገ ባይሆንም የወባ ትንኟን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ ከጀመሩ ብዙ ሺህ ዓመታት አልፈዋል። በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ግብጻውያን የወባ ትንኝን ከአካባቢያቸው ለማራቅ ባሌኒትስ ዊልሶኒያና ተብሎ ከሚጠራ ዛፍ የሚሠራ ዘይት ይጠቀሙ ነበር። ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ግብጻውያን ዓሣ አጥመጆች ነፍሳቱ እንዳይጠጓቸው ሌሊት ሌሊት መረቦቻቸውን በአልጋቸው ዙሪያ ይዘረጓቸው እንደነበረ ሄሮዱተስ ፅፏል። አሥራ ሰባት መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ የሕንድ ባለጠጎች ነፍሳትን የሚከላከሉ ሌሊት ሌሊት ሊዘረጉ የሚችሉ መጋረጃዎች ባሏቸው አልጋዎች ላይ ይተኙ እንደነበረ ማርኮ ፖሎ ዘግቧል።
በሌሎች ሥፍራዎች ሰዎች ትክክለኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ተፈጥሮአዊ መድኃኒቶች ፈልስፈዋል። ከ2,000 ለሚበልጡ ዓመታት የወባ በሽታ በቻይና ውስጥ ኪንጋሱ በተባለ የእሬት ተክል አማካኝነት ስኬታማ የሆነ ሕክምና ሲደረግለት ቆይቷል። በቅርብ ዓመታት እንደገና የተደረሰበት የተፈጥሮ መድኃኒት ነው። በደቡብ አሜሪካ ውስጥ የፔሩ ሕንዶች ሲንኮና የተባለ በደቡብ አሜሪካ የሚበቅል ዛፍ ቅርፊት ይጠቀሙ ነበር። በ17ኛው መቶ ዘመን ሲንኮና ወደ አውሮፓ ተወሰደ፤ በ1820 ደግሞ ሁለት ፋርሳውያን መድኃኒት ቀማሚዎች ከዚህ ዛፍ ኩዊኒን የተባለ ንጥረ ነገር አወጡ።
አዳዲስ የማጥቂያ መሣሪያዎች
ኩዊኒን የወባ በሽታን በመከላከልና በመፈወስ ረገድ ያለው ጠቀሜታ ቶሎ አልተስተዋለም ነበር። አንዴ ከታወቀ በኋላ ግን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከሁሉ የተሻለ መድኃኒት ሆኖ ቆይቷል። ከዚያ በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ አካባቢ የጃፓን ወታደሮች በሩቅ ምሥራቅ የሚገኝ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የሲንኮና ዛፍ ልማትን ተቆጣጠሩ። በዚህም ሳቢያ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኩዊኒን እጥረት በማየሉ ሰው ሰራሽ ጸረ ወባ መድኃኒት ለመፈልሰፍ ጥልቅ ምርምር ተካሄደ። በውጤቱም አስተማማኝ፣ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ የሆነና ለማምረት ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ክሎሮኩዊን የተባለ መድኃኒት ተፈለሰፈ።
ክሎሮኩዊን ወዲያውኑ የወባ በሽታን ለማጥቃት ትልቅ መሣሪያ ሆነ። እንዲሁም በ1940ዎቹ ከፍተኛ ኃይል ያለው የወባ ትንኞችን የሚገድል ዲዲቲ የተባለ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት በገበያ ላይ ዋለ። ምንም እንኳን ዲዲቲ የሚለው ምህጻረ ቃል የሚወክለው ዳይክሎሮ ዳይፌኒሊትሪክሎሮኢቴን የተባለውን ለመጥራት የሚያስቸግር የኬሚካል መጠሪያ ቢሆንም ብዙ የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ፊደላቱን “ድሮፕ ዴድ ቱዋይስ” (በሁለት መንገዶች የሚገድል) በሚሉት ቃላት ያስታውሷቸዋል። ዲዲቲ ሲረጭ ብቻ ሳይሆን ከተረጨም በኋላ ግድግዳ ላይ የሚቀረው መርዝ ነፍሳትን የሚገድል በመሆኑ ቃሉን ለማስታወስ የሚረዳ ተገቢ ስያሜ ነው።b
ተስፋ የተጣለበት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሳይንቲስቶች ዲዲቲንና ክሎሮኩዊንን ታጥቀው በዓለም ዙሪያ በወባ በሽታና በወባ ትንኞች ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ አደራጁ። ውጊያው በሁለት ግንባሮች የሚካሄድ ነበር። መድኃኒቶች በሰው አካል ውስጥ የሚገኙ ህዋሳቶችን ለመግደል እንዲሠራባቸው፤ የወባ ትንኞችን ጠራርጎ ለማጥፋት ደግሞ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶችን ለመርጨት ሰፊ ዘመቻ ለማድረግ ተወሰነ።
ግቡ ሙሉ ድልን ለመቀዳጀት ነበር። የወባ በሽታ ተጠራርጎ እንዲጠፋ ዕቅድ ተነደፈ። የጥቃት ዘመቻውን በግንባር ቀደምትነት የመራው ለዚህ የማጥፋት ፕሮግራም ከፍተኛውን ቅድሚያ የሰጠው አዲስ የተቋቋመው የዓለም የጤና ድርጅት ነበር። ቁርጥ ውሳኔው በገንዘብ የታገዘ ነበር። ከ1957 እስከ 1967 በነበሩት ዓመታት ብሔራት ለዓለም አቀፉ ዘመቻ 1.4 ቢልዮን ዶላር አፈሰሱ። በመጀመሪያ ላይ የተገኙት ውጤቶች በጣም አስደናቂ ነበሩ። በሽታው በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በሶቭየት ኅብረት፣ በአውስትራሊያና በአንዳንድ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ተደመሰሰ። የወባ በሽታን ለማጥፋት በተደረገው የማጥቃት ዘመቻ የተሳተፉት ፕሮፌሰር ኤል ጄ ብሩስ ቻት “ትውስ ሲሉ በሚያስደስቱት በእነዚያ ጊዜያት በመላው ዓለም ተሰራጭቶ የነበረውን በሽታውን የማጥፋት ጽንሰ ሐሳብ አስደናቂ የጋለ ስሜት ዛሬ ለመግለጽ ያስቸግራል” በማለት ምን ያህል አስገራሚ እንደነበረ ገልጸዋል። የወባ በሽታ መንበርከክ ጀመረ። “የወባ በሽታ መጥፋት በእኛ ዘመን እውን ሆኗል” ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ተኩራራ።
የወባ በሽታ እንደገና ጥቃቱን ጀመረ
ድል ግን እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም። ከኬሚካሉ ጥቃት የተረፉት የወባ ትንኝ ዝርያዎች የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ሆኑ። ዲዲቲ እንደ ቀድሞው በቀላሉ ሊገድላቸው አልቻለም። ልክ እንደዚሁም በሰዎች አካል ውስጥ የሚገኙት የወባ ህዋሳትም ክሎሮኩዊንን የሚቋቋሙ ሆኑ። እነዚህና ሌሎች ችግሮች ድል የተረጋገጠባቸው መስለው በነበሩ አገሮች ውስጥ ሽንፈትን አስከተሉ። ለምሳሌ በ1963 የወባ በሽታ ከምድረ ገጿ ተጠራርጎ ጠፍቷል በተባለላት ስሪ ላንካ አምስት ዓመታት ብቻ ካለፉ በኋላ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያዳረሰ ወረርሽኝ ተከሰተ።
በ1969 የወባ በሽታ ድባቅ የሚመታ ጠላት አለመሆኑ በሰፊው ተቀባይነት አገኘ። “ጠራርጎ ማጥፋት” በሚለው ቃል ፋንታ “መቆጣጠር” የሚለው ቃል የተለመደ ሆነ። “መቆጣጠር” ሲባል ምን ማለት ነው? የደብሊው ኤች ኦ የወባ በሽታ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ብራያን ዶበርስቲን “አሁን ልናደርገው የምንችለው ነገር የሚሞቱ ሰዎችና በበሽታው የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር መጠነኛ እንዲሆን መጣር ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላ የዓለም የጤና ድርጅት ባለሥልጣን እንዲህ በማለት እሮሮአቸውን አሰምተዋል:- “የወባ በሽታን ለማጥፋት በ1950ዎቹ ጥረቶች ከተደረጉና ነፍሳትን ለመከላከል ዲዲቲ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የዓለም ሕዝብ ለዘብ ብሏል። ድህነት፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች አለመሟላት፣ በሽታው መድኃኒቶቹንና የተባይ ማጥፊያዎቹን መቋቋሙ በሽታው ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲያውም በሽታው አሸንፎናል።”
ሌላው ምክንያት ደግሞ መድኃኒቱን የሚያመርቱት ኩባንያዎች የሚያደርጉትን ምርምር ማቋረጣቸው ነው። አንድ የወባ በሽታ ሳይንቲስት “ምርምሩ ብዙ ገንዘብ ማፍሰስን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ምንም የሚገኝ ውጤት የለም። አንዳችም የሚያበረታታ ነገር የለም። ችግሩ ይህ ነው” ብለዋል። አዎን፣ በብዙ ውጊያዎች ድል የተገኘ ቢሆንም ከወባ በሽታ ጋር የሚደረገው ጦርነት ግን ማብቂያ የሌለው ሆኗል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያ የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ” የማይልበት ጊዜ በደጅ የቀረበ መሆኑን ይጠቁማል። (ኢሳይያስ 33:24) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን በሽታና ሞት በደካማ ክንፎች ላይ ተሳፍረው መምጣታቸውን ይቀጥላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የወባ በሽታ የሚል ትርጉም ያለው “ማሌሪያ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የመጣው ማሌ (መጥፎ) ኤሪያ (አየር) ከሚለው የጣሊያንኛ ቃል ነው።
b ዲዲቲ አካባቢን የሚመርዝ ኬሚካል መሆኑ ተደርሶበታል፤ በ45 አገሮች ውስጥም የታገደ ወይም በጥብቅ የተከለከለ ኬሚካል ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የወባ ትንኝና ሰው
የወባ ትንኝ በአብዛኛው በሐሩር ክልል ውስጥ በሚገኙ ከመቶ በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩትን ከሰው ዘር መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉትን ሰዎች በቀጥታ ተፈታትናለች። በተለይ አፍሪካ የበሽታው ምሽግ ናት።
የወባ ትንኞች ከሐሩር ክልሎች አውሮፕላኖችን ተፈናጠው በመምጣት በዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያዎች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን እንደሚያጠቁ ተደርሶበታል።
የዚህ አደጋ ሰለባዎች። የወባ ትንኝ በየዓመቱ 270 ሚልዮን ሰዎችን ታጠቃለች። ወደ 2 ሚልዮን ሰዎችን ለሞት ትዳርጋለች። በተለይ ለእርጉዝ ሴቶችና ለልጆች አደጋው የከፋ ነው። በአማካይ ሁለት ልጆች በየደቂቃው ሕይወታቸው ይቀጠፋል።
ለጉብኝት ወደሐሩር ክልል የሚመጡ ሰዎችን ታጠቃለች። በአውሮፓ ውስጥ ወደ 10,000 የሚጠጉና በሰሜን አሜሪካ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች በየዓመቱ በበሽታው ተይዘው “ከውጪ ወደ አገራቸው” እንደሚመለሱ ሪፖርት ይደረጋል።
በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶች። ሴቷ አኖፈለስ የወባ ትንኝ በአብዛኛው ሰዎችን ሌሊት ታጠቃለች። የወባ በሽታ ደም በመውሰድም ይተላለፋል። አልፎ አልፎም በበሽታው በተበከሉ መርፌዎች ይተላለፋል።
የሰው ልጅ በሽታውን መከላከል የሚችልበትን እውቀትና ስልት ያገኘው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው። መቅሰፍቱን ድል ለማድረግ 105 አገሮች የተቀናጀ ጥረት ቢያደርጉም የሰው ልጅ ለበሽታው እጁን እየሰጠ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የወባ ትንኝ እንዳትነድፍህ ተከላከል
አልጋህን ኮርኒስ ላይ በሚንጠለጠል ትንሽ ዘርዘር ባለ ጨርቅ ጋርደህ ተኛ። የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ውስጥ የተነከሩ በኮርኒስ ላይ ተንጠልጥለው አልጋን የሚጋርዱ ዘርዛራ ጨርቆች የተሻሉ ናቸው።
ማግኘት የሚቻል ከሆነ ሌሊት ሌሊት በአየር ማጣሪያ መሣሪያ ተጠቀም። ወይም በሮቻቸውና መስኮቶቻቸው በወንፊት ሊጋረዱ በሚችሉ ክፍሎች ውስጥ ተኛ። የሚጋርድ ወንፊት ከሌለ መስኮቶቹንና በሮቹን ዝጋቸው።
ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ እጅን የሚሸፍኑ ረጅም እጅጌ ያላቸው ልብሶችና ረጃጅም ሱሪዎችን መልበስ ጠቃሚ ነው። ደብዘዝ ያለ ቀለም የወባ ትንኞችን ይስባል።
በልብስ የማይሸፈኑ የአካል ክፍሎችህን ትንኟን የሚያባርር መድኃኒት ቀባቸው። ዳይኢቴልቶሎሚድ (ዲት) የተባለውን ወይም ዳይሚቴል ታሌት የተባለው ኬሚካል ያለበትን መድኃኒት ተጠቀም።
የወባ ትንኝን የሚያጠፉ የሚረጩ መድኃኒቶችን፣ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒት መርጫ መሣሪያ ወይም ከሽቦ የተሠሩ ጥቃቅን ቀዳዳዎች ያሏቸው መረብ የመሠሉ የወባ ትንኝ መከላከያዎችን ተጠቀም።
ከዓለም የጤና ድርጅት የተገኘ
[ምንጭ]
H. Armestrong Roberts
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“አንድም ‘አስማታዊ ጥይት’ የለም”
ምንም እንኳን የተሟላ ድል ይገኛል የሚለው ተስፋ የጨለመ ቢሆንም የወባ በሽታን ለማጥፋት የሚደረገው ውጊያ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በጥቅምት ወር 1991 በኮንጎ ብራዛቪል ውስጥ የወባን በሽታ አስመልክቶ በተደረገው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካዮች “ከሞት ከበባ” እንላቀቅ የሚል ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ለዚህ መፍትሔው ወባን ለማጥፋት አዲስ ዓለም አቀፍ የክተት አዋጅ ማወጅ ነው ብለዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥረቶች ምን ያህል ስኬታማ ይሆኑ ይሆን?
“የወባ በሽታን የሚያጠፋ አንድም ‘አስማታዊ ጥይት’ የለም” በማለት በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ሂሮሺ ናካጂማ ገልጸዋል። “ስለዚህ በብዙ ግንባሮች ልንዋጋው ይገባል” ብለዋል። በቅርብ ጊዜ በስፋት ተቀባይነት ያገኙት ሦስቱ የውጊያ ግንባሮች የሚከተሉት ናቸው:-
ክትባቶች። ሳይንቲስቶች ለብዙ ዓመታት የወባ በሽታን የሚከላከል ክትባት ለማግኘት ሲመራመሩ ቆይተዋል፤ የዜና አውታሮችም አልፎ አልፎ የተገኙትን “አዳዲስ ውጤቶች” ሪፖርት ያደርጋሉ። ከሚገባ በላይ ተስፋ ማድረግን በመቃወም የዓለም የጤና ድርጅት “የጸረ ወባ በሽታ ክትባት በቅርብ ጊዜ ውስጥ መሰጠት ይጀምራል የሚለውን ሕልም” ማመን እንደማይገባ ያስጠነቅቃል።
ክትባትን መፍጠር እንዳይቻል እንቅፋት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ በሰው ውስጥ የሚገኘው የወባ ሕዋስ ከሰው አካል የበሽታ መከላከያ በዘዴ እያመለጠ ለመዳን መቻሉ ነው። ሰዎች ለብዙ ዓመታት በተደጋጋሚ በበሽታው ቢጠቁም ሰውነታቸው በሽታውን ለመከላከል ያዳበረው መከላከያ ውሱን ነው። አትላንታ በሚገኘው የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ውስጥ በበሽታ ስርጭትና ቁጥጥር ጥናት ሊቅ የሆኑት ዶክተር ሀንስ ሎቤል “በበሽታው ተደጋግሞ ቢጠቃም ሰውነት በሽታውን ለመቋቋም የሚያስችል መከላከያ መሥራት አይችልም። ስለዚህ [አንድ ክትባት ለማግኘት ስትጥር] ተፈጥሮን ለማሻሻል እየጣርክ ነው ማለት ነው” በማለት ተናግረዋል።
መድኃኒቶች። የወባ ሕዋስ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን መድኃኒቶች የመቋቋም ኃይሉ እየጨመረ በመምጣቱ የዓለም የጤና ድርጅት ኪንጋሱ ከተባለ የቻይና የእሬት ተክል የተሠራ አርቲተር የተባለ አዲስ መድኃኒት እያሰራጨ ነው።c የዓለም የጤና ድርጅት ኪንጋሱ በአሥር ዓመት ውስጥ ለዓለም ኅብረተሰብ ለሚቀርቡት ሙሉ በሙሉ አዲስ ለሆኑ ለየት ያለ ይዘት ላላቸው የተፈጥሮ መድኃኒቶች መገኛ ምንጭ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ አለው።
ኮርኒስ ላይ የሚንጠለጠሉ አልጋን የሚጋርዱ ዘርዛራ ጨርቆች። ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ይሠራበት የነበረው የወባ ትንኝ መከላከያ የሆነው ይህ ዘዴ አሁንም ውጤታማ ነው። የወባ ትንኞች ሰውን የሚያጠቁት ሌሊት ነው፤ ኮርኒስ ላይ የሚንጠለጠሉት ጨርቆች ደግሞ አያሳልፏቸውም። እጅግ ውጤታማ የሆኑት እንደ ፐርሜትሪን ባሉ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች ውስጥ የተነከሩ ጨርቆች ናቸው። በአፍሪካ ውስጥ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መድኃኒቶች ውስጥ የተነከሩ ጨርቆች ጥቅም ላይ በዋሉባቸው መንደሮች በወባ በሽታ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 60 በመቶ ቀንሷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
c ኪንጋሱ አርቴሚሲያ አኑአ ከተባለ የእሬት ተክል የሚገኝ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ወደ ሐሩር ክልል ለመጓዝ አስበሃልን?
ወባ ወዳለበት አካባቢ ለመሄድ ካሰብክ የሚከተሉትን ነገሮች በሥራ ማዋል ይኖርብሃል:-
1. የግል ሐኪምህን ወይም ክትባት የሚሰጥበትን ጣቢያ አማክር።
2. የተሰጡህን መመሪያዎች በትክክል ሥራባቸው፤ ጸረ ወባ መድኃኒት የምትወስድ ከሆነም ወባ ያለበትን ክልል ለቀህ ከሄደክ በኋላም ለአራት ሳምንት መድኃኒቱን መውሰድህን ቀጥል።
3. የወባ ትንኝ እንዳትነድፍህ ራስህን ጠብቅ።
4. የወባ በሽታን ምልክቶች እወቅ። ምልክቶቹ:- ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት መቀረጣጠፍ፣ ማስመለስ እና/ወይም ተቅማጥ ናቸው። ጸረ ወባ መድኃኒቶች የተጠቀምክ ቢሆንም እንኳን የወባ በሽታ ወባ ያለበትን አካባቢ ለቀህ ከሄድክ ከአንድ ዓመት በኋላም ሊከሰት እንደሚችል ማስታወስ አለብህ።
5. ምልክቶቹ ከታዩብህ ወደ ሐኪም ሂድ። የወባ በሽታ በፍጥነት ሊባባስና የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ከ48 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊገድል ይችላል።
ከዓለም የጤና ድርጅት የተገኘ
[ምንጭ]
H. Armestrong Roberts