አዲስ የወባ በሽታ መከላከያ
ሐምሌ 1993 ታትሞ በወጣው ንቁ! መጽሔት ላይ እንደተዘገበው የወባ በሽታ የዓለም መቅሠፍት በመሆን እንደገና አገርሽቷል። ኒው ዮርክ ታይምስ (መጋቢት 23, 1993) “ባለፈው ዓመት ብራዚል 560,000 የወባ በሽታ ሕሙማንን መዝግባለች” ሲል ሪፖርት አድርጓል። በየዓመቱ 8,000 ብራዚላውያን በወባ በሽታ ይሞታሉ። በአሁኑ ጊዜ ዶክተር ማኑኤል ኤልኪን ፓታሮዮ የተባሉ ኮሎምቢያዊ የፈጠራ ሰው ለሦስት ጊዜ ክትባት 30 ሳንቲም ብቻ የሚከፈልበት ሰው ሠራሽ የሆነ ኬሚካል ክትባት በማዘጋጀት አንድ ለየት ያለ ዘዴ ይዘው ቀርበዋል። ዶክተር ፓታሮዮ “ይህ ዋጋ [በኮሎምቢያ ውስጥ] ከአንድ ኮካ ኮላ ዋጋ ያነሰ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ሕክምና ወደ 67 በመቶ በሚጠጉ ሰዎች ላይ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። ቀሳፊ ለሆነው የወባ በሽታ የማያዳግም ምላሽ ባይሆንም በጸረ–ወባ በሽታ ዘመቻ ትልቅ እመርታ ሆኖ ታይቷል።