የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 7/15 ገጽ 14-15
  • ስለ ወባ በሽታ ማወቅ ያለብህ ነገር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ ወባ በሽታ ማወቅ ያለብህ ነገር
  • ንቁ!—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 1 ወባ ምንድን ነው?
  • 2 ወባ የሚተላለፈው እንዴት ነው?
  • 3 ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
  • በደካማ ክንፎች ላይ የተሳፈረ ሞት
    ንቁ!—1993
  • አዲስ የወባ በሽታ መከላከያ
    ንቁ!—1993
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2011
  • ከጥገኛ ተውሳኮች ራሳችሁን ጠብቁ!
    ንቁ!—1999
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 7/15 ገጽ 14-15

ስለ ወባ በሽታ ማወቅ ያለብህ ነገር

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ግምታዊ መረጃ መሠረት በ2013 ከ198 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ በሽታ የተያዙ ሲሆን 584,000 የሚያህሉ ሰዎች በወባ በሽታ ሞተዋል። በበሽታው ከሞቱት መካከል አራት አምስተኛ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው። ይህ በሽታ ወደ መቶ በሚጠጉ አገሮችና ክልሎች በሚኖሩ 3.2 ቢሊዮን ሰዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል።

1 ወባ ምንድን ነው?

ወባ በጥገኛ ተሕዋስያን ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው። የበሽታው ምልክቶች ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ፣ ራስ ምታት፣ የሰውነት መጓጎል፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹ ከ48 እስከ 72 ሰዓት እየቆዩ በድጋሚ ይታያሉ፤ ይህን የሚወስነው ግለሰቡን ያጠቁት ተሕዋስያን ዓይነትና በበሽታው ተይዞ የቆየበት ጊዜ ነው።

2 ወባ የሚተላለፈው እንዴት ነው?

  1. የወባ በሽታ በሰውነት ውስጥ የሚሰራጭበትን መንገድ የሚያሳይ ቻርት

    የወባ ተሕዋስያን፣ ፕላዝሞዲያ ተብለው የሚጠሩ ባለ አንድ ሴል ፍጥረታት ሲሆኑ ወደ ሰው ደም ውስጥ የሚገቡት አኖፊሊስ በምትባለው ሴት ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ነው።

  2. ተሕዋስያኑ የግለሰቡ ጉበት ሴሎች ውስጥ በመግባት ይራባሉ።

  3. በጉበቱ ውስጥ ያሉት ሴሎች ሲፈነዱ ተሕዋስያኑ ይወጡና የግለሰቡን ቀይ የደም ሴሎች ይወርራሉ። ከዚያም ተሕዋስያኑ በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ መባዛታቸውን ይቀጥላሉ።

  4. የወባ ተሕዋስያን ቀይ የደም ሴሎችን ይወርሩና ሴሎቹ እንዲፈነዱ ያደርጋሉ

    ቀይ የደም ሴሎቹ በሚፈነዱበት ጊዜ ተሕዋስያኑ ይወጡና ሌሎች ቀይ የደም ሴሎችን ይወርራሉ።

  5. በቀይ የደም ሴሎቹ ውስጥ የሚካሄደው ይህ ዑደት ይቀጥላል። ቀይ የደም ሴሎቹ በፈነዱ ቁጥር በበሽታው የተያዘው ሰው የወባ በሽታ ምልክቶቹ ይታዩበታል።

3 ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ወባ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት አካባቢ የምትኖር ከሆነ . . .

  • አጎበር ተጠቀም። አጎበሩ

    • የተባይ ማጥፊያ የተረጨበት

    • ምንም ቀዳዳ የሌለው

    • በፍራሹ ዙሪያ የተጠቀጠቀ መሆን አለበት።

  • ቤት ውስጥ የሚረጭ የተባይ ማጥፊያ ተጠቀም

  • የሚቻል ከሆነ በበሮቹና በመስኮቶቹ ላይ እንደ ወንፊት ያለ መከለያ አድርግ፤ እንዲሁም ትንኞች እንዳያርፉ ሊከላከሉ ስለሚችሉ እንደ አየር ማቀዝቀዣ ያሉ መሣሪያዎችን ተጠቀም።

  • ሰውነትህን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ነጣ ያለ ቀለም ያለው ልብስ ልበስ።

  • የሚቻል ከሆነ የወባ ትንኞች በብዛት ከሚገኙበት ጥሻ የሆነ አካባቢና ለትንኝ መራቢያነት አመቺ የሆኑ የታቆሩ ውኃዎች ካሉበት ቦታ ራቅ።

  • በወባ ከተያዝክ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።

የወባ ተሕዋስያን ከትንኝ ወደ ሰው እንዲሁም ከሰው ወደ ትንኝ ይተላለፋሉ

አንድ ሰው የበሽታው ተሸካሚ በሆነች ትንኝ አማካኝነት ወባ ሊይዘው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት የወባ ትንኝ በበሽታው የተያዘን ሰው በመንደፏ ምክንያት ተሕዋስያኑ ወደ እሷ ሊተላለፉ ይችላሉ። ከዚያም ትንኟ ተሕዋስያኑን ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ትችላለች

ወባ በተደጋጋሚ ወደሚከሰትበት ቦታ ለመሄድ የምታስብ ከሆነ . . .

  • ጉዞ ከመጀመርህ በፊት ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ሞክር። በአንድ አካባቢ ያለው የወባ ዓይነት በሌላ ቦታ ካለው ሊለይ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ውጤታማ የሆነው መድኃኒት የትኛው እንደሆነ ለመወሰን ይረዳሃል። በተጨማሪም ከጤንነትህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ መረጃዎችን ለማግኘት ሐኪምህን ማነጋገርህ ጠቃሚ ነው።

  • እዚያ በምትቆይበት ወቅት፣ ወባ በሚከሰትበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚናገሩትን በዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡ ምክሮች ተግባራዊ አድርግ።

  • በበሽታው ከተያዝክ በአፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ሞክር። የበሽታው ምልክቶች የሚታዩት ተሕዋስያኑ ወደ ሰውነትህ ከገቡ ከአንድ እስከ አራት በሚሆኑ ሳምንታት ውስጥ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብሃል።

ማድረግ የምትችላቸው ተጨማሪ ነገሮች

  1. በመንግሥት ወይም በማኅበረሰቡ አማካኝነት በሚሰጡ የጤና እንክብካቤ ፕሮግራሞች ተጠቀም።

  2. መድኃኒት መግዛት የሚኖርብህ ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው ቦታዎች ብቻ መሆን አለበት። (የጥራት ደረጃው ዝቅተኛ የሆነ ወይም ተመሳስሎ የተሠራ መድኃኒት በሽታው ቶሎ እንዳይድን ሊያደርግ ወይም ለሞት ሊዳርግ ይችላል።)

  3. የትንኝ መራቢያ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎች በቤትህ አካባቢ ካሉ ለማስወገድ ጥረት አድርግ።

የምትኖረው ወባ ባለበት አካባቢ ከሆነ ወይም ወደዚህ አካባቢ ሄደህ ከነበረ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን የወባ በሽታ ምልክቶች ችላ አትበል . . .

  • ከባድ ትኩሳት

  • ላብ

  • የሚያንዘፈዝፍ ብርድ ብርድ የሚል ስሜት

  • ራስ ምታት

  • የጡንቻ መጓጎል

  • ድካም

  • ማቅለሽለሽ

  • ማስመለስ

  • ተቅማጥ

በወባ የተያዘ ሰው ሕክምና ካላገኘ ከባድ የደም ማነስ ሊያጋጥመውና ሕይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በተለይም ልጆችና ነፍሰ ጡር ሴቶች ምልክቶቹ እየተባባሱ ከመሄዳቸው በፊት አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው።a

a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኅዳር 2011 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 24-25⁠ን እና የኅዳር 2009 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 26-29⁠ን ተመልከት።

ይህን ታውቅ ነበር?

በአፍሪካ ካርታ ላይ የሚታይ ሰዓት

አፍሪካ ውስጥ ብቻ በወባ ምክንያት በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ ሕፃን ይሞታል

  • በወባ በሽታ ከተያዙ ሕመሙ ይበልጥ የሚጠናባቸው ልጆች ወይም ነፍሰ ጡር ሴቶች ናቸው።

  • በአፍሪካ ውስጥ ብቻ፣ በወባ ምክንያት በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ ሕፃን ይሞታል።

  • አልፎ አልፎ ብቻ የሚያጋጥም ቢሆንም ደም በመውሰዳቸው የተነሳ በወባ የተያዙ ሰዎች አሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ