የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 7/8 ገጽ 18-21
  • ‘ከወንዝ ዓይኖች’ ተጠንቀቅ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ከወንዝ ዓይኖች’ ተጠንቀቅ!
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አደገኛ የሆኑ ‘የወንዝ ዓይኖች’
  • የቅንጦት ዕቃዎች ፍለጋ የአዞዎችን ሕልውና ሥጋት ላይ ጥሎታል
  • ለረጅም ጊዜ ይታመንባቸው የነበሩ አፈ ታሪኮች ውድቅ ሆኑ
  • ጨካኝና ዓመፀኛ ብቻ አይደለም
  • የአዞ መንጋጋ
    ንቁ!—2015
  • አዞ ትፈራለህ?
    ንቁ!—2005
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2005
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2015
ንቁ!—1997
g97 7/8 ገጽ 18-21

‘ከወንዝ ዓይኖች’ ተጠንቀቅ!

በአውስትራሊያ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በጣም ውብ በሆነው በአውስትራሊያ ሰሜናዊ ክልል በሚገኘው በካካዱ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ አንዲት ሴት አደገኛ በሆነው ወደ ኢስት አሊጌተር ወንዝ በሚፈሰው ገባር ወንዝ ላይ በዝግታ እየቀዘፈች ትዝናናለች። ድንገት የሆነ ነገር ታንኳዋን ይመታው ጀመር፤ ወንዝ ይዞት የሚሄድ ግንድ ነው ብላ አስባ ነበር። ለካስ አንድ አስፈሪ የሆነ የባሕር አዞ ኖሯል፤ ይህች ቱሪስት አዞው ወደሚኖርበት ክልል የመጣችው በጣም አደገኛ በሆነው ወቅት ላይ ነበር።

በጣም ደንግጣ እጅብ ያሉ ዛፎች ወደሚገኙበት አካባቢ በኃይል ቀዘፈች። ወደ ዛፉ ቅርንጫፍ ላይ ልትወጣ ስትል አዞው ከውኃው ውስጥ ወጥቶ ጎትቶ በመጣል ሦስት ጊዜ በጭቃ ውስጥ አንከባለላት። አዞው ሦስት ጊዜም የነከሳት የተለያየ ቦታ ላይ ሲሆን ሴትየዋ ማጥ ከሆነው የወንዙ ዳርቻ ለመውጣትና ለማምለጥ ባለ በሌለ ኃይሏ ትፍጨረጨር ነበር። በሦስተኛ ሙከራዋ እንደምንም ለመውጣት ቻለች። ከዚያም መሄድ አቅቷት የግዷን ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዘች በኋላ አንድ የደን ጠባቂ ታሰማ የነበረውን በሲቃ የተሞላ የድረሱልኝ ጩኸት ሰምቶ ደረሰላት። ይህች ሴት ክፉኛ ብትቆስልም በሕይወት ተርፋለች።

ይህ አሳዛኝ አደጋ የደረሰው በ1985 ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ አንዲት አሜሪካዊት ቱሪስት የከፋ ዕጣ ገጥሟታል። ይህች ቱሪስት የጓደኞቿን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት በምዕራብ አውስትራሊያ አዞዎች በሞሉበት በፕሪንስ ሪጀንት ወንዝ ትዋኝ ጀመር። ከዚያም በጨዋማ ውኃ አዞ ተይዛ ተገድላለች። በወቅቱ በወንዙ ውስጥ ገና ትንንሽ አዞዎች እንደነበሩ ታውቋል፤ ይህም አንዲት አዞ ልጆቿን ለመጠበቅ ስትል ገድላት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።

አደገኛ የሆኑ ‘የወንዝ ዓይኖች’

አንድ ወንዝ ወደ ባሕር በሚፈስበት አካባቢ የሚገኝ ማንኛውም ዓሣ አጥማጅ በጨረቃ ብርሃን የሚያየው ነገር አንዲት ነፍሳት መስታወት መስሎ በተነጠፈው ውኃ ላይ ስታርፍ የሚፈጠረውን የውኃ እንቅስቃሴ ነው። በሰሜናዊ የአውስትራሊያ ጠረፍ የሚገኝ ዓሣ አጥማጅ ግን ባይታዩም ‘የወንዝ ዓይኖች’ እንዳሉ ያውቀል። ባትሪውን ውኃው ላይ ቢያበራ ምንም የማይንቀሳቀሱ ቀይ ብርሃን የሚያንጸባርቁ የአዞ ዓይኖች ይመለከት ነበር። በጥንቶቹ አጥፊ እንስሳት ክልል ውስጥ የተገኘ ሰርጎ ገብ ነው።

የአውስትራሊያ የጨዋማ ውኃ አዞ በዓለም ላይ ከሚገኙ 12 የአዞ ዝርያዎች ሁሉ ትልቁና በጣም አደገኛው ሲሆን ይህ የአዞ ዝርያ በሌሎች የምድር አካባቢዎችም ይገኛል። ይህ አዞ ቁመቱ እስከ 7 ሜትር ሊደርስ ይችላል። ወደዚህ ክልል የገባ ያልጠረጠረ ሰለባ የሚያበሩትን ዓይኖች የሚያስተውላቸው አዞው ዘሎ አፈፍ ሊያደርገውና በኃይል እያጥመለመለ ይዞት ለመሄድ ሲል ነው። እንደ ጎሽ፣ ዳልጋ ከብትና ፈረስ ያሉት ትልልቅ እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ ውኃ ጠምቷቸው ዳር ላይ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ በአዞ ይበላሉ።

የቅንጦት ዕቃዎች ፍለጋ የአዞዎችን ሕልውና ሥጋት ላይ ጥሎታል

አዞ አንድን እንስሳ ከገደለ በኋላ ለእንስሳው ያዘነ ለማስመሰል የውሸት እንባ ያነባል የሚለው ጥንታዊ አፈ ታሪክ ወደ ዘመናዊው ኅብረተሰብም ዘልቆ በመግባቱ ሰዎች “የአዞ እንባ” ብለው ሲናገሩ እንሰማለን። ለአዞ ያለቀሱ ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ከዚህ ይልቅ ይህ ውኃ ወዳድ የሆነ እንስሳ በጣም ውድ ለሆነው ሌጦው ወይም ቆዳው ሲባል ያለ ምንም ርኅራኄ ይታደናል።

የጨዋማ ውኃ አዞ ቆዳ በጣም ለስላሳና ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ስለሆነ በዓለም ላይ ካሉት ከሌሎች እንስሳት ቆዳ ሁሉ ይመረጣል የሚል አመለካከት በአንዳንዶች ዘንድ ስላለ ብዙ የልብስ ፋሽን ሞዴሎች ከአዞ ቆዳ የተሠሩ የሚያማምሩ ልብሶችን ለብሰው ይታያሉ። በቅርቡ በለንደን ውስጥ በቅናሽ ዋጋ ለሽያጭ የቀረበ አንድ የሴቶች የእጅ ቦርሳ 15,000 የአሜሪካን ዶላር ተተምኗል። የአዞ ቆዳ በብዙ የዓለም ክፍሎች አሁንም እንደ አንድ ከፍተኛ የክብር ዕቃ ተደርጎ ይታያል።

ከፍተኛ ትርፍ ለመዛቅ የሚደረገው እሽቅድድም በአውስትራሊያ የሚገኙትን የጨዋማ ውኃ አዞዎች ሕልውና ሥጋት ላይ ጥሎታል። ከ1945 እስከ 1971 ባለው ጊዜ ውስጥ በሰሜናዊው ክልል ብቻ ከእነዚህ ገበሎ አስተኔዎች (reptiles) መካከል 113,000 የሚያክሉ ተገድለዋል። አዞዎች ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፉ ለመከላከል ሲባል በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአዞ አደን ላይ ገደብ ተጥሎ ነበር። ከዚህም የተነሳ በ1986 ከእርባታ ጣቢያ ውጭ ያሉ አዞዎች ቁጥር ሊያንሠራራ ችሏል። ምንም እንኳ አንዳንዶች የአዞዎች መኖሪያ አካባቢ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለው ቢከራከሩም በአውስትራሊያ በሚገኙ አዞዎች ሕልውና ላይ ተደቅኖ የነበረው ሥጋት ተወግዷል።

በአውስትራሊያ የሚኖሩ አቦርጂኖች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለብዙ መቶ ዘመናት አዞዎች እንዳይጠፉ አስተዋጽኦ አድርገዋል። አንዳንድ ጎሳዎች የታወቁ አዞ አዳኞች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በሃይማኖታዊ ምክንያት የተነሳ አዞ ማደንን በጥብቅ የሚከለክሉ ነበሩ።

በቅርብ ዓመታት ደግሞ በትምህርት የተደገፈ የአዞ እርባታ መጀመሩ ለአዞዎች መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል። የአዞ እርባታ ፕሮግራሞቹ መኖር ከእርባታ ጣቢያ ውጭ ያሉ አዞዎች ምንም ሳይነኩ የአዞ ቆዳና ሥጋ ማዘጋጀት እንዲቻል ስላደረገ የገንዘብ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ቱሪስቶች ወደ አዞ እርባታ ጣቢያዎች በመጉረፍ ላይ ናቸው።

አንድ የታወቀ አውስትራሊያዊ አዞ አርቢ ሰዎች ተንከባክበው የሚይዙት እንዲሁም የተወሰነ ጊዜያቸውንና ቦታቸውን የሚሰጡት ለሚወዱትና በሚገባ ለሚያውቁት ነገር ነው የሚል እምነት አለው። “አዞዎች ይህን እድል አላገኙም። አዞዎች ያላቸው የሥነ ኑረት (ኢኮሎጂያዊ) ጠቀሜታ ከእነሱ ቆዳ ከሚሠራ ከማንኛውም ውብ ነገር የሚተናነስ አይደለም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አንድ ሰው ጭቃ የሚመስል ገላ ያላቸውን አዞዎች ከሽቦ አጥር ውጭ ሆኖ በቅርበት የማየት አጋጣሚ ስለሚኖረው የአዞ እርባታ ጣቢያዎችን መጎብኘት በጣም ያስደስታል። የእርባታ ጣቢያው ሠራተኛ ምንም ሳይፈራ አዞዎቹ ተከልለው ወደሚገኙበት አጥር በመግባት ካጫወታቸው በኋላ ዶሮና ሌላ ሥጋ ይመግባቸዋል። ሆኖም በቅርቡ አንድ የእርባታ ጣቢያ ሠራተኛ አዞዎችን በግዴለሽነት መቅረብ አደገኛ መሆኑን ከደረሰበት አሳዛኝ ሁኔታ ተምሯል። አዞው ድንገት ዘሎ ሰውዬውን አፈፍ በማድረግ የግራ እጁን እንዳለ ቆርጦ ወሰደው!

በሌላ በኩል ደግሞ የ12 ወር ዕድሜ ያላትን አዞ በእጅ መያዝ ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ተሞክሮ ከመሆኑም በላይ ስለ አዞ ያለንን እውቀት የሚያሰፋ ነው። በሆዷ አካባቢ ያለው ቆዳዋ የሚያስደንቅ ልስላሴ ያለው ሲሆን ኦስቲኦደርምስ ተብለው በሚጠሩ እንደ አጥንት ጠንካራ በሆኑ ጠፍጣፋ ነገሮች የተሸፈነው ጀርባዋ ደግሞ የሃይድሮዲይናሚክ መከላከያ ይሆንላታል። ቆዳቸው ይህን ያህል ውድ የሆነበት ምክንያት አሁን ግልጽ ነው። ይህችንም ቢሆን ግን “ትንሽ” ነች ብለህ እንዳትንቃት። የ12 ወር ዕድሜ ያላት አዞም እንኳ ብትሆን ካላት መጠን አንፃር ሲታይ ጥብቅ የሆነው መንጋጋዋ ጠንካራ ነው።

ገና ከእንቁላላቸው ያልተፈለፈሉ አዞዎች እዚያው እንቁላሉ ውስጥ ሆነው ሲጮኹ በአካባቢው ያሉትን ሰዎች ፈገግ ያሰኛሉ፤ ከዚያም አፍንጫቸው ጫፍ ላይ ባለ ጊዜያዊ ጥርስ አማካኝነት እንቁላሉን ሰብረው ይወጣሉ። አዞ ቆንጆ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ ይህ ብቻ ነው ቢባል ብዙዎች ሳይስማሙ አይቀሩም!

ለረጅም ጊዜ ይታመንባቸው የነበሩ አፈ ታሪኮች ውድቅ ሆኑ

በእርባታ ጣቢያ ውስጥ በሚያድጉበት ጊዜ የእነዚህን አስፈሪ እንስሳት ባሕርይ በቅርብ ማጥናት መቻሉ ለረጅም ጊዜ ሲታመንባቸው የነበሩ አፈ ታሪኮች ውድቅ እንዲሆኑ አድርጓል። አዞ የሚበላውን እንስሳ በመብረቅ ፍጥነት ድንገት ዘሎ ከመያዙ በፊት ለቀናት አልፎ ተርፎም ለሳምንታት በትዕግሥት አድብቶ ይጠብቃል ተብሎ ለብዙ ዓመታት ይታሰብ ነበር። ሆኖም አዞዎች ወደ ክልላቸው በሚገባ እንስሳ ላይ ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርሱት በስግር ነፋስ (monsoon) አካባቢ ማለትም በስሪያቸው ወቅት መሆኑን በቅርብ ከተደረጉ ጥናቶች ማወቅ ተችሏል። በዚህ ወቅት ማንኛውም እንስሳ ወደ ክልላቸው ከገባ አሳደው ሊበሉት ይችላሉ። በዓመቱ ውስጥ በሌላ ወቅት ግን ማንኛውም እንስሳ ወደ ክልላቸው ቢገባ ምንም ሳይነኩት በርቀት ዝም ብለው ይመለከቱታል።

አዞዎች ዛሬ በመዝናኛ ቦታዎች ከተገኙ ልምድ ባላቸው አዞ አዳኞች አማካኝነት ተይዘው ወደ ሌላ አካባቢ ይወሰዳሉ። አዞዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ በሸምቀቆ የታችኛውን መንገጭላ ካሰሩት በኋላ በፍጥነት የላይኛውንና የታችኛውን መንገጭላ አንድ ላይ ያስሩታል። የታችኛው መንገጭላ እንዲዘጋ የሚያደርጉት ጡንቻዎች በጣም ኃይለኞች ቢሆኑም እንዲከፈት የሚያደርጉት ጡንቻዎች ግን ደካማ ስለሚሆኑ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰር አዞውን ጨርሶ አቅመ ቢስ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ አዞውን የሚያስረው ሰው ካልተጠነቀቀ አዞው በጣም ኃይለኛ በሆነው ጅራቱ መትቶ ሊጥለው ይችላል።

ጨካኝና ዓመፀኛ ብቻ አይደለም

ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉት እነዚሁ መንገጭላዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሥራ የማከናወን ችሎታም አላቸው። ገና ያልተፈለፈሉት አዞዎች ከእንቁላሉ ውስጥ ሰብረው መውጣት ሲገባቸው ዝም ካሉ ሰብረው እንዲወጡ ለማነቃቃት እናትዬዋ አዞ እንቁላሎቿን በጣም በጥንቃቄ ታንከባልላቸዋለች።

የአዞ ጥርስ ለመንከስ እንጂ ለመንጨት አያመችም። አዞው አድኖ የያዘው እንስሳ ትንሽ ከሆነ እንዳለ ይውጠዋል። ካልሆነ ግን ይዘነጣጥለውና አንድ በአንድ ይውጠዋል። በሞቱ ገበሎ አስተኔዎች ላይ ጥናት ሲደረግ በሆድቃቸው ውስጥ ድንጋዮች ተገኝተዋል። እነዚህ ድንጋዮች ሆን ተብለው የተዋጡ ሆኑም አልሆኑ በውኃ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሚዛን ለመጠበቅ ያገለግላሉ ተብሎ ይታመናል።

ጎብኚዎች ብዙውን ጊዜ አዞዎች ወንዝ ዳር ላይ ሆነው ያንን በጣም ሰፊ አፋቸውን ከፍተው ይመለከታሉ። ይህ ሁኔታ አዞው ሊባላ መዘጋጀቱን ይጠቁማል ብለው ይገምቱ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ግን አፉን የሚከፍተው የሰውነቱን ሙቀት ውጭ ካለው አየር ጋር ለማስማማት ነው። አዞዎች እንደሌሎቹ ገበሎ አስተኔዎች ሁሉ በየጊዜው የሰውነታቸውን ሙቀትና ቅዝቃዜ ያስተካክላሉ።

በጣም የሚያስገርመው አዞ ገበሎ አስተኔ ቢሆንም ልክ እንደ አጥቢ እንስሳት ባለ አራት ገንዳ ልብ አለው። ሆኖም አዞው ልክ ውኃ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ለውጥ ይከናወናል። ልቡ ሦስት ገንዳዎች እንዳሉት ሆኖ መሥራት ይጀምራል።

የጨዋማ ውኃ አዞ ከአርጃኖ የሚለየው ሾጠጥ ባለው አፍንጫውና አፉ ተገጥሞ ባለበት ጊዜ እንኳ ከውጭ በሚታዩት ጥርሶቹ ነው። አጫጭሮቹ አዞዎች ከሚኖሩባት ከአፍሪካ አንስቶ እስከ ሕንድ፤ እንዲሁም ከእስያ እስከ ፓፑአ ኒው ጊኒ ድረስ አዞዎች ይገኛሉ። በደቡባዊ የአውስትራሊያ ጠረፍ ሳይቀር ይገኛሉ። አዞዎች ጎጆአቸውን የሚሠሩት በውኃ ዳርቻዎች በመሆኑ ማንግሮቭ የሚባሉ የዛፍ ዓይነቶች የሚበቅሉባቸውንና ረግረጋማነት ያላቸው የሐሩር ክልል የውኃ ዳርቻዎችን ለመኖሪያነት ይመርጣሉ። ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ ጎጂ ተፈጥሮአዊ ጎን አለው፤ በጣም ብዙ ገና ያልተፈለፈሉ የአዞ እንቁላሎች በፈረሰኛ ውኃ ተጠርገው ይወሰዳሉ። ትልቅ አዞ፣ ባራሙንዲ የተባለው ዓሣና ናንኪን የተባለው ወፍ ስለሚበሏቸው አዲስ ከሚፈለፈሉት አዞዎች መካከል እስከ መጀመሪያው አንድ ዓመት ድረስ በሕይወት የሚተርፉት 50 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

የሚያስገርመው ነገር አዞዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ይዘው ይፈለፈላሉ። ከተፈለፈሉ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት በአካላቸው ውስጥ ካለ የአስኳል ከረጢት ይመገባሉ። ሆኖም እናታቸው በጥንቃቄ በአፏ እየወሰደች ውኃው ዳር ስታስቀምጣቸው አጠገባቸው ያገኙትን ማንኛውንም ነገር ለቀም እያደረጉ አፋቸውን ያለማምዳሉ።

‘የወንዝ ዓይኖች’ የሚለው አነጋገር ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ገና የተፈለፈሉት አዞዎች ትንንሽ ዓይኖች እንኳ ሳይቀሩ ማታ መብራት ሲበራባቸው ቀይ ሆነው ይታያሉ። ከእይታ ድራብ (retina) ጀርባ ያለው ማሀው (crystal) በማታ ማየት ከማስቻሉም በላይ ቀይ ብርሃን እንዲንጸባረቅ ያደርጋል።

አዎን፣ አዞ በጣም ትኩረት የሚስብ የገበሎ አስተኔ ዝርያ ነው፤ ምንጊዜም ቢሆን ግን በጣም መድፈር የለብህም። ማንኛውም ዓሣ አጥማጅ እንደሚያውቀው ሌዋታንን በመንጠቆ ለመያዝ መሞከር ከንቱ ነው።

ኢዮብ “ሌዋታን” በማለት ስለ አዞ የገጠመው ግጥም በጣም ተስማሚ ነው። “ሌዋታን ተብሎ የሚጠራውን የባሕር አውሬ ዓሣ በሚጠመድበት መንጠቆ ልትይዘው ወይም መላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህን? በአፍንጫው መሰነጊያ አስገብተህ፣ ጉንጩንም በመንጠቆ ወግተህ ልትይዘው ትችላለህን? እርሱስ ‘እባክህ ልቀቀኝ’ ብሎ ይለምንሃልን? ምሕረት እንድታደርግለትስ ይጠይቅሃልን? ለዘላለም እንደ አሽከር ሆኖ ሊያገለግልህ፣ ከአንተ ጋር ኪዳን የሚገባ ይመስልሃልን? ከለማዳ ወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር መጫወት ትችላለህን? ወይስ ሴቶች አገልጋዩችህን እንዲያስደስት አስረህ ታኖረዋለህን? ዓሣ ነጋዴዎች እርሱን ለመግዛት ይጫረታሉን? ቆራርጠውስ ይከፋፈሉታልን? ቆዳውን በፈለግህበት ቦታ በሾተል መብሳት፣ ጭንቅላቱንም በጦር ወግተህ መሰንጠቅ ትችላለህን? ከቻልህ እስቲ እጅህን በላዩ ላይ አሳርፍበት! ከእርሱ ጋር የምታደርገውን ትግል በፍጹም አትረሳውም፤ ዳግመኛም ከእርሱ ጋር ለመታገል አትሞክርም።”—ኢዮብ 41:1-8 የ1980 ትርጉም

የማወቅ ጉጉት ላላቸውና ቸልተኛ ለሆኑ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ:- ‘ከወንዝ ዓይኖች’ አዎን፣ ኃይለኛና አስፈሪ ከሆነው ከአዞ ተጠንቀቁ!

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

By courtesy of Australian International Public Relations

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማታ ውኃው ላይ መብራት ሲበራበት የአዞዎቹ ‘የወንዝ ውስጥ ዓይኖች ’ ቀይ ብርሃን ይሰጣሉ

[ምንጭ]

By courtesy of Koorana Crocodile Farm, Rockhampton, Queensland, Australia

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተግራ:- አዞዋ ከእንቁላሉ ውስጥ ሰብራ ስትወጣ

[ምንጭ]

By courtesy of Koorana Crocodile Farm, Rockhampton, Queensland, Australia

በስተቀኝ:- አንድ ትልቅ አዞ ጭቃማ በሆነው በሜሪ ወንዝ ዳርቻ ላይ ፀሐይ ሲሞቅ

[ምንጭ]

By courtesy of Australian International Public Relations

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ