የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 10/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አሰቃቂ የኮምፒዩተር ጨዋታዎች
  • በግሪክ አገር የሃይማኖት ነጻነት ጉዳይ አየተጠና ነው
  • ጭንቀት ለመኪና አደጋዎች ይበልጥ ያጋልጣል
  • ለሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ማስጠንቀቂያ
  • “በጣም ግሩም የሆነ ለስላሳ ዕፅ”?
  • አብዛኞቹ ልጆች ሌሊት ያቃዣቸዋል
  • “የሎተሪ ዕድል የሚያስገኝ ዛፍ”
  • ምግብን ማሞቅ መርዙን አያስወግደውም
  • ቴሌቪዥን በብዛት መመልከት፣ የንባብ ልማድ መቀነስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ በ2,197 ቋንቋዎች ይገኛል
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2003
  • በቤት ውስጥ እንዳይከሰት መከላከል
    ንቁ!—1997
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1998
  • ልጆችን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 10/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

አሰቃቂ የኮምፒዩተር ጨዋታዎች

በአሰቃቂነታቸው ተወዳዳሪ ካልተገኘላቸው የኮምፒዩተር ጨዋታዎች አንዱ የሆነውና ክዌክ 2 ተብሎ የሚጠራው ጨዋታ ይበልጥ አሰቃቂ የሚያደርገው ማሻሻያ ታክሎበት አዲስ ሆኖ ቀርቧል። ፕሮግራሙ “በተጫዋቾች ኮምፒዩተር ገጽ ላይ ደም እንደ ጎርፍ ሲፈስና የሰውነት ክፍሎች እየተቆራረጡ ሲወድቁ የሚያሳይ መሆኑ በርካታ ተከታዮችን ሊያፈራለት ችሏል” ይላል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል። የጨዋታው ዋና ፕሮግራመር የሆኑት ጆን ካርማክ “የሚፈሰው ደም አንሷል የሚል አስተያየት ከደንበኞቻችን ስለደረሰን ለመጨመር ተገደናል” ብለዋል። ክዌክ 2 ተጫዋቾች በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚያገኟቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች ተጫዋቾች ጋር የሞት ፍልሚያ በሚባል ጨዋታ “እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ” ያስችላል። ተጫዋቾች በተጋጣሚዎቻቸው ላይ ጸያፍ ድርጊት እንዲፈጽሙ ወይም የብልግና ስድብ እንዲሳደቡ የሚያስችል ዝግጅት አለው። ጨዋታውን የፈለሰፉት ፕሮግራመሮችና ሠዓሊዎች “ሥራቸውን የሚያከናውኑት የክብደት ማንሻ መሣሪያዎች ባሉበትና አሸር ባሸር የሆኑ ጣፋጭ ምግቦች በታጨቁበት የተቀናጣ ቤት ውስጥ ሆነው ነው። ይህ ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው . . . በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው 666 ቁጥር ተሰጥቶታል።”

በግሪክ አገር የሃይማኖት ነጻነት ጉዳይ አየተጠና ነው

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለ ሃይማኖታዊ ነጻነት የሚነሱ ጥያቄዎች [ለግሪክ] መንግሥት አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንደሚደረግ ይጠበቃል” ሲል ቶ ቪመ የተባለው የአቴንስ ጋዜጣ ዘግቧል። “በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሃይማኖታዊ ነጻነት ጋር ዝምድና ያላቸውን ሕግ ነክ ጉዳዮች፣ የአንድን ሰው ሃይማኖት ለማስለወጥ መሞከር ወንጀል እንደሆነ የሚደነግገውን በአምባገነኑ በሜታክሳስ የወጣውን ሕግ፣ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑ አናሳ ሃይማኖቶች አብያተ ክርስቲያናትና የመሰብሰቢያ ቦታዎች ሊያቋቁሙ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በመመርመር ላይ ነው።” ሪፖርቱ በመቀጠል ይህ እርምጃ ሊወሰድ የቻለው በአብዛኛው በግሪክ አገር የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባቀረቧቸው በርካታ አቤቱታዎች ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል።

ጭንቀት ለመኪና አደጋዎች ይበልጥ ያጋልጣል

በጀርመን በሚገኘው የጤና አገልግሎትና የማኅበራዊ ደህንነት ፕሮፌሽናል ማኅበር የተካሄደ አንድ ጥናት አንድ ሰው ለሥራው ያለው አመለካከት መኪና በሚያሽከረክርበት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክቷል። ሥራቸው ጭንቀት የፈጠረባቸው ሰዎች በመንገድ ላይ ለሚፈጠር አደጋ ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው ሲል ሱትዶይቼ ሳይቱንግ ዘግቧል። “አንድ ሰው በአለቃው ወይም በሥራ ባልደረቦቹ ሳቢያ የታመቀ የብስጭት ስሜት ካለው ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ አሰባስቦ ለማሽከርከር ሊቸገር ይችላል” ሲል ዘገባው ይገልጻል። በተደረገው ጥናት መሠረት ወደ ሥራ ሲሄዱ ወይም ከሥራ ሲመለሱ የመኪና አደጋ ካደረሱት ሰዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት አደጋውን ሊያደርሱ የቻሉት “ሐሳባቸውን አሰባስበው ማሽከርከር ባለመቻላቸው፣ በጥድፊያ ስሜት በመንዳታቸው፣ ሰዓት ለማክበር በሚደረግ ጥረት ወይም ደግሞ በጭንቀት” የተነሳ ነው። ምንም እንኳ መጥፎ ጭንቀት ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ በአብዛኛው ለአደጋ የሚጋለጡት ወንዶች ናቸው ይባል የነበረ ቢሆንም ሕፃናት ልጆች ያሏቸው እናቶችም ለዚህ አደጋ እጅግ የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቱ ደርሶበታል። ጋዜጣው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እናቶች በሰዓቱ ተገኝተው ልጆቻቸውን ከመዋዕለ ሕፃናት መውሰድ ስላለባቸው ወይም ደግሞ ምሳ ሰዓት ላይ ባለው የዕረፍት ጊዜ ምግብ ማብሰል ስላለባቸው ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ውጥረት አለባቸው።”

ለሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ማስጠንቀቂያ

“ታይለኖልና ኤክሰድሪን በሚባሉትና በሌሎች በርካታ የሥቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶች ውስጥ የሚገኘው አሴታሚኖፊን የሚባል ንጥረ ነገር በትንሹ እንኳን መጠኑ ከበዛና በተለይ ከአልኮል ጋር ከተደባለቀ በጉበት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል” ሲል ኸልዝ መጽሔት አስጠንቅቋል። ይህ ጉዳት እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የሳውዝ ዌስተርን ሕክምና ማዕከል የውስጥ አካላት ስፔሽያሊስት የሆኑት ዊልያም ሊ “አብዛኞቹ ሰዎች ከመደበኛው መጠን ሁለት ወይም ሦስት እጥፍ አብዝተው ቢወስዱ ምንም ጉዳት የማይደርስባቸው ይመስላቸዋል” ይላሉ። “በዚህ መድኃኒት ረገድ ግን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት አይሠራም።” ሰውነት አሴታሚኖፊንን በሚፈጭበት ጊዜ ለጉበት መርዛማ የሆነ ቅመም ይፈጠራል። ጉበት ራሱን ከጉዳት ለመከላከል ሲል ይህን መርዝ የሚያረክስ ግሉታትዮን የሚባል ቅመም ይሠራል። የአሴታሚኖፊኑ መጠን ከበዛ ግን ጉበት ሊከላከል ከሚችለው በላይ ይሆንበታል። አልኮል በጉበት ውስጥ ያለውን የግሉታትዮን ክምችት ያሟጥጣል። በመሆኑም የአልኮል መጠጥ ከወሰዱ በኋላ መድኃኒቱን መውሰድ በጣም አደገኛ ነው። አሴታሚኖፊን ከ300 በሚበልጡ መድኃኒቶች ውስጥ ስለሚገኝ ሳይታወቅ ከመጠን በላይ ሊወሰድ የሚችል ቅመም ነው።

“በጣም ግሩም የሆነ ለስላሳ ዕፅ”?

ቸኮላት ያለው የማነቃቃት፣ የደስታ ስሜት የመስጠትና የወሲብ ስሜት የመቀስቀስ ባሕርይ ለበርካታ ዘመናት ሲወደስ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የተደረጉ ምርምሮች ቸኮላት “በጭንቀት ስሜት፣ በአእምሮ ሰላምና በወሲባዊ ባሕርይ” ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማመልከታቸውን ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። ሳይንቲስቶች በቸኮላት ውስጥ ከአምፊታሚን ጋር የሚመሳሰል አንድ ንጥረ ነገርና “ጎላ ያለ የማነቃቃት ባሕርይ ያለው” ሌላ ንጥረ ነገር አግኝተዋል። በተጨማሪም ካናቢስ ወይም ዕጸ ፋርስ የሚያስከትለውን የመሰለ “ልብ የማንጠልጠልና የደስ ደስ ስሜት የማስከተል” ባሕርይ ያለው አናንዳማይድ የተባለ ንጥረ ነገር እንደሚገኝበት አዳዲስ ጥናቶች አመልክተዋል። ጋዜጣው ይህን ግኝትና የቸኮላትን እምብዛም መርዛማ አለመሆን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚከተለው ብሏል:- “ቸኮላት አካላዊና አእምሮአዊ እንቅስቃሴዎችን ስለሚቀሰቅስ፣ ኃይል ስለሚሰጥ፣ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትል የደህንነትና የደስ ደስ ስሜት ስለሚፈጥር እንዲሁም የሚፈጥረው ሱስ በጣም ደካማ ስለሆነ በጣም ግሩም የሆነ ለስላሳ ዕጽ ነው።”

አብዛኞቹ ልጆች ሌሊት ያቃዣቸዋል

ሁሉም ልጆች ማለት ይቻላል አስፈሪ ሕልም ያያሉ። በጀርመን ማንሃይም ውስጥ በሚገኘው የአእምሮ ጤና ማዕከል የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከ10 ልጆች መካከል ዘጠኙ ሕልም ከእንቅልፋቸው እንዳባነናቸው ተናግረዋል። ብዙዎቹ የሚቃዡት ሰው ሲያባርራቸው፣ ከከፍተኛ ቦታ ላይ ሲወድቁ ወይም ደግሞ በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ መካከል እንዳሉ አድርገው ሲያልሙ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ የሚያዩት በገሃዱ ዓለም ያሉና የሌሉ ነገሮች የተቀላቀሉባቸውን ሕልሞች ነው። ብዙውን ጊዜ ወንዶች ልጆች ያዩትን ሕልም ይረሳሉ። በሌላ በኩል ግን ሴቶች ልጆች ብዙውን ጊዜ ስላዩት ሕልም ይናገራሉ ወይም ይጽፋሉ። ልጆች ቅዠት ከሚፈጥርባቸው ጭንቀት መገላገል እንዲችሉ የሕልሙን ይዘት መናገር፣ በሥዕል መግለጽ ወይም በተወሰነ ደረጃ በትዕይንት መልክ ማሳየት እንዳለባቸው ጠበብት ይመክራሉ ሲል ቤርሊነር ሳይቱንግ ዘግቧል። ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሚያዩት ሕልም ብዛትም ሆነ የሕልሞቹ አስፈሪነት በእጅጉ ይቀንሳል።

“የሎተሪ ዕድል የሚያስገኝ ዛፍ”

በታይላንድ በባንኮክ አቅራቢያ የሚኖሩ በቁጣ የገነፈሉ የአንድ መንደር ነዋሪዎች ‘የሎተሪ ዕድል ያስገኛል’ የሚሉትን ዛፋቸውን ለማቃጠል ቃጥተዋል ብለው በጠረጠሯቸው ፕሮፌሽናል አወራራጆች ላይ ዛቻ ሰንዝረዋል ሲል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል። “ዕድሉን የሚያስገኘው ዛፍ” የሎተሪ ዕድል የሚያስገኝ ምክር ይሰጣል የሚል ብሔራዊ ዝና ያተረፈ በመሆኑ የአካባቢው መንደርተኞች ዛፉ በከፊል መቃጠሉን ሲሰሙ እጅግ ተቆጡ። “በጣም ነው የተናደድኩት” ስትል ዶንግማሊ ተናግራለች። “እኔ ራሴ በዛፉ አማካኝነት ገንዘብ የበላሁ ከመሆኔም በላይ ዛፉ የሚሰጠውን ምክር እንዴት መረዳት እንደሚቻል ለሌሎች በመንገር ገንዘብ ማግኘት ችያለሁ።” ይሁን እንጂ ጥቃቱ ከተሰነዘረ ወዲህ የዛፉ መንፈስ ተቆጥቷል ተብሏል፤ በመሆኑም መንፈሱ የሎተሪ ዕጣ ማግኘት የሚቻልበትን ምክር መስጠት አቁሟል ይላሉ መንደርተኞቹ። ዘገባው እንደሚለው ከሆነ መንደርተኞቹ የዛፉ መንፈስ እንደ ቀድሞው የሎተሪ ዕድል የሚያስገኘውን ምክር መስጠቱን እንዲቀጥል ለማግባባት የቡዲስት መነኩሴዎችን ለማምጣት አቅደዋል።

ምግብን ማሞቅ መርዙን አያስወግደውም

ከበሰለ በኋላ ማቀዝቀዣ ውስጥ ሳይገባ ከሁለት ሰዓት በላይ የቆየ ሥጋ መበላት የለበትም ሲል ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ኸልዝ ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር ገልጿል። ይሁን እንጂ ምግቡ ሲሞቅ ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎች ይሞቱ የለ እንዴ? “ውጪ የቆየን ሥጋ ማሞቅ ከላይ የተባዙትን ባክቴሪያዎች ሊገድላቸው ይችላል፤ ሆኖም በአንዳንድ የባክቴሪያ ዓይነቶች የሚፈጠረው በሽታ የሚያስከትል መርዝ አይወገድም” በማለት ኒውትሪሽን ሌተር ይገልጻል። ስታፊሎኮከስ የተባለው ባክቴሪያ የሚፈጥረው መርዝ ሆድ ቁርጠት፣ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ብርድ ብርድ የማለት ስሜት፣ ትኩሳትና ራስ ምታት ሊያስከትል ይችላል። “ምግቡ ምንም ያህል ቢሞቅ መርዙ አይወገድም።”

ቴሌቪዥን በብዛት መመልከት፣ የንባብ ልማድ መቀነስ

የግሪክ ኦዲዮቪዡዋል ሚድያ ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት መሠረት በአገሪቱ ውስጥ 3.5 ሚልዮን የሚሆኑት ቤተሰቦች 3.8 ሚልዮን ቴሌቪዥኖች ያሏቸው ሲሆን ከ3 ቤተሰቦች አንዱ የቪዲዮ መቅጃም አለው። ግሪካውያን በአማካይ በቀን ቴሌቪዥን ለመመልከት የሚያውሉት ጊዜ በ1990 ከሁለት ሰዓት ተኩል ያነሰ የነበረ ሲሆን በ1996 ግን ወደ አራት ሰዓት ገደማ ከፍ እንዳለ ቶ ቪመ የተባለው የአቴንስ ጋዜጣ ዘግቧል። የንባብ ልማድ በእጅጉ ማሽቆልቆሉ ምንም አያስገርምም። ጥናቱ እንደሚያመለክተው በ1989 አንድ ግሪካዊ በአማካይ 42.2 ጋዜጦችን ያነበበ ሲሆን በ1995 ግን አኃዙ አሽቆልቁሎ 28.3 ደርሷል። በተመሳሳይም በዚያው ጊዜ ውስጥ መጽሔቶችን የማንበብ ልማድ 10 በመቶ ቀንሷል።

መጽሐፍ ቅዱስ በ2,197 ቋንቋዎች ይገኛል

“ባለፈው ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በሌሎች 30 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፤ ይህም ቅዱሳን ጽሑፎች የተተረጎሙባቸውን ቋንቋዎች አጠቃላይ ቁጥር ወደ 2,197 ከፍ ያደርገዋል” ሲል በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ውስጥ የወጣው ኢ ኤን አይ ቡለቲን ሪፖርት አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኤስፐራንቶ ያሉትን አርቴፊሻል ቋንቋዎች ጨምሮ በ363 ቋንቋዎች ተተርጉሞ ይገኛል። የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት (ዩ ቢ ኤስ) ቢያንስ ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የተተረጎመባቸውን ቋንቋዎች በሙሉ መዝግቦ ይይዛል። የዩ ቢ ኤስ ዋና ጸሐፊ ፈርገስ ማክዶናልድ ግባችን “የአምላክ ቃል በሰዎች አፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዲተረጎም” ማድረግ ነው ብለዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ