ስለ ሃይማኖት መወያየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
“ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።”—ምሳሌ 27:17፣ መጽሐፍ ቅዱስ
ቢላዎችን እንዲሁ እርስ በርስ በማጋጨት ብቻ መሳል አይቻልም። ቢላዎችን ለመሳል ዘዴ ይጠይቃል። በተመሳሳይም እንደ ሃይማኖት ባሉ ጥንቃቄን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ አእምሮን በትክክል ወይም በተሳሳተ መንገድ መሳል ይቻላል።
በመጀመሪያ ደረጃ የሌላውን ሰው ክብር መጠበቅና ይህን አክብሮታችንን በቃልም ሆነ በምግባራችን ማሳየት አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ “ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን” ይላል። (ቆላስይስ 4:6) በጸጋ የሚነገርና በጨው የተቀመመ ንግግር ተናጋሪው እሱ ትክክል እንደሆነና የሚያነጋግረው ሰው እንደተሳሳተ በሚገነዘብበት ጊዜም እንኳ ግትር አቋም የሚንጸባረቅበት አይሆንም።
ጸጋ በምንሰማበት ጊዜም ሊንጸባረቅ ይችላል። ጣልቃ እየገባን የሰውየውን ንግግር የምናቋርጥ ከሆነ ወይም ደግሞ ቀጥለን ስለምንናገረው ነገር በማሰብ ሰውየው የሚናገረውን ነገር የማንከታተል ከሆነ በጸጋ እያዳመጥን ነው ለማለት አይቻልም። የሚናገረው ሰው ለእሱ አመለካከት ግድየለሾች መሆናችንን ሊገነዘብና ውይይቱን ሊያቆም ይችላል። በተጨማሪም የምናነጋግረውን ሰው አስገድደን ወይም ተጭነን አመለካከቱን ለማስቀየር መሞከር የለብንም። ጥሩ ምላሽ በሚሰጥ አድማጭ ልብ ውስጥ ‘የእውነት ዘር እንዲያድግ የሚያደርገው አምላክ’ ነው።—1 ቆሮንቶስ 3:6
በአገልግሎቱ “ምክንያት እያቀረበ ያስረዳ” እና “ያሳምን” የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። (ሥራ 17:17 NW፤ 28:23, 24 NW) ጳውሎስ የገበያ ቦታዎችንና መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሰዎችን በሚያገኝበት ቦታ ሁሉ ስለ ሃይማኖት ይወያይ ነበር። (ሥራ 17:2, 3፤ 20:20) የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ወደሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ በመሄድና ከቅዱሳን ጽሑፎች አሳማኝ ነጥቦችን እየጠቀሱ በመወያየት ይህን ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ።
የተሳሳተ ግንዛቤን አስወግድ
የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ መሠዊያ የተሠራበትን ምክንያት በትክክል ባለመረዳታቸው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ምንም ያህል አልቀራቸውም ነበር። ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩት ሰዎች መሠዊያ ሠርተው ነበር። ሆኖም ሌሎቹ ነገዶች መሠዊያው ለሐሰት አምልኮ የተሠራ መስሏቸው ነበር። ስለዚህ ወንድሞቻቸውን ለማረም ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጁ። ሆኖም ከዚያ በፊት የጥበብ እርምጃ ወሰዱ። ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት መሠዊያው የተሠራበትን ምክንያት የሚያጣራ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው ላኩ። መሠዊያው ሁሉም ነገዶች በይሖዋ አምላክ ዘንድ ያላቸውን አንድነት የሚያስታውስ ሐውልት ወይም “ምስክር” መሆኑን ሲገነዘቡ ታላቅ እፎይታ ተሰማቸው። አስቀድመው መነጋገራቸው ሊፈጠር የነበረውን ግጭት በማስወገድ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል!—ኢያሱ 22:9-34
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ በአብዛኛው መለያየትንና አልፎ ተርፎም ወገናዊ ጥላቻን ያስከትላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ደም የማይወስዱ መሆኑን በመስማታቸው ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ናቸው የሚል አመለካከት አድሮባቸዋል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ስለዚህ ጉዳይ በግል ምሥክሮቹን ቀርበው ያነጋገሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ለዚህ አቋማቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዳላቸውና አስተማማኝና ውጤታማ የሆኑ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች መኖራቸውን ሲረዱ በመገረም አመለካከታቸውን ይለውጣሉ። (ዘሌዋውያን 17:13, 14፤ ሥራ 15:28, 29) እንዲያውም ለሕክምና የሚለገሰው ደም በሚያስከትላቸው ችግሮች ሳቢያ አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ “አምላክ ምስጋና ይግባውና ለደም ምትክ የሚሆኑ ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት በሚደረገው ምርምር የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
ልክ እንደዚሁም የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ ክርስቶስ አያምኑም ተብሎ የተነገራቸው አንዳንድ ሰዎች ከምሥክሮቹ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች አይሆኑም። ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው! እንዲያውም ምሥክሮቹ ኢየሱስ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት እንዲቤዥ አምላክ ወደ ምድር የላከው የአምላክ ልጅ መሆኑን በመግለጽ ኢየሱስ በመዳናችን ረገድ የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርገው ያሳያሉ። ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ከምሥክሮቹ ጋር በመወያየት የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስወገድ ችለዋል።—ማቴዎስ 16:16፤ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ 14:28፤ 1 ዮሐንስ 4:15
እውነት—በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው?
ምናልባት ለብዙዎች አስገራሚ የሚሆነው ሃይማኖትን በተመለከተ በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንገድ የተሳሳተው መንገድ መሆኑ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲህ ሲል አስተምሯል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14
በኖኅ ዘመን መንፈሳዊ እውነት ይናገሩ የነበሩት ኖኅ፣ ሚስቱ፣ ሦስት ወንዶች ልጆቹና የልጆቹ ሚስቶች በጠቅላላው ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። የማስጠንቀቂያ መልእክት መናገራቸውና መርከብ መሥራታቸው ማሾፊያና መሳለቂያ አድርጓቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ለጥቃት ዒላማነት አጋልጧቸው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኖኅና ቤተሰቡ ፈርተው ወደ ኋላ አላሉም። መስበካቸውንና መርከብ መሥራታቸውን ቀጥለዋል። (ዘፍጥረት 6:13, 14፤ 7:21-24፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) በተመሳሳይም ለአምላክ መመሪያዎች ታዝዘው በሰዶምና በገሞራ ላይ ከደረሰው ጥፋት የተረፉት ሦስት ሰዎች ብቻ ናቸው።—ዘፍጥረት 19:12-29፤ ሉቃስ 17:28-30
በእኛስ ጊዜ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? አንድ ሰው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ሲነጋገር “በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር ቢመጣ ሰዎች ዳግመኛ ሳይገድሉት አይቀርም” ሲል ተናግሯል። ይህ ሰው የኢየሱስ ትምህርቶችና ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከ2,000 ዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉ አሁንም በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ተሰምቶታል። በዚህ ትስማማለህ?
የምትስማማ ከሆነ ትክክል ነህ፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋል። ይህ ትንቢት እውነት ሆኖ ተገኝቷል። (ማቴዎስ 24:9) በሮም የነበሩ የአይሁድ መሪዎች ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ክርስትናን በተመለከተ ሲናገሩ “ይህን ... የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን” ብለውታል። (ሥራ 28:22 የ1980 ትርጉም) ይሁን እንጂ ክርስትና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱ የክርስቶስ ተከታዮች እምነታቸውን ለሌሎች ከማካፈል እንዲታቀቡ አላደረጋቸውም። ቅን ልብ ያላቸውንም ሰዎች ክርስቲያኖችን ከማነጋገር አላገዳቸውም።—ሥራ 13:43-49
በዛሬው ጊዜ የኢየሱስ መልእክት ከምንጊዜውም ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም የዓለም ሁኔታዎች በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ እየኖርን እንዳለንና እነዚህ ቀኖች መጥፎ ድርጊትን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ለማስወገድ በሚወሰደው እርምጃ እንደሚደመደሙ ያመለክታሉ። ኢየሱስ ያለንበትን ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር አመሳስሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:37-39) የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት አምላክን የሚያውቁና ‘በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩት’ ብቻ ስለሆኑ እምነቶቻችንን እንዲሁ በጸጋ ተቀብለን የምንኖርበት ጊዜ ላይ አይደለንም።—ዮሐንስ 4:24፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-9
ትክክለኛውን መንገድ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
የ17ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ፈላስፋ፣ የብዕር ሰው፣ የሕግ ባለሙያና መራሔ መንግሥት ፍራንሲስ ቤከን እውነት ፈላጊዎች “እንዲያመዛዝኑና እንዲመረምሩ” መክረዋል። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “ከስህተት የሚጠብቁት ብቸኞቹ መሣሪያዎች መመራመርና በነፃነት መጠየቅ ናቸው። . . . እነዚህ ከመሳሳት የሚጠብቁ ተፈጥሯዊ ዘቦች ናቸው።” ስለዚህ እውነትን ለማግኘት ከልባችን የምንጥር ከሆነ ‘እናመዛዝናለን፣ እንመረምራለን እንዲሁም በነፃነት እንጠይቃለን።’
ብሪታንያዊው ሳይንቲስት ሰር ኸርመን ቦንዲ እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ እንደሚከተለው ብለዋል:- “እውነት ሊሆን የሚችለው አንዱ እምነት ብቻ ስለሆነ ሰዎች አምላክ ለሰው ልጆች ገልጦላቸዋል በሚባለው ሃይማኖት መስክ እውነት ባልሆኑ ነገሮች ላይ ልባዊ የሆነ ጽኑ እምነት ሊያሳድሩ የሚችሉበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ይህ ግልጽ እውነታ አንዳንዶች የትሕትና ዝንባሌ እንዲያሳዩና ምንም ያህል ጥልቅ እምነት ቢኖራቸው ተሳስተው ሊሆን እንደሚችል እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን።”
ታዲያ አንድ ሰው ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ’ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? አምላክ “በእውነት” መመለክ እንዳለበት ኢየሱስ አስተምሯል። ስለዚህ አንድ ሰው ያለው የማስተዋል ችሎታ ሁለት ነገሮች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ከሆኑ ሁለቱም እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ እንዲገነዘብ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል ነፍስ ሟች ነች ወይም አይደለችም። አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባል ወይም አይገባም። አምላክ ሥላሴ ነው ወይም አይደለም። እውነት ፈላጊዎች ለእነዚህ ዋና ዋና ጥያቄዎች በሐቅ ላይ የተመሠረቱ መልሶች ማግኘት ይፈልጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ መልሶቹን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሰጠን ያምናሉ።a
‘ቅዱሳን ጽሑፎች ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ’ እንደመሆናቸው መጠን የተለያዩ ትምህርቶችን መፈተን የሚቻልበት ዋናው መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ በመመዘን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንዲህ በማድረግ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ [ታውቃላችሁ]።” (ሮሜ 12:2፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እምነትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ‘ለራስህ ማረጋገጥ’ ትችላለህ? አምላክ ‘ከመላው ዓለም’ ጋር አብረህ እንድትስት ስለማይፈልግ እንዲህ ማድረግ መቻልህ በጣም አስፈላጊ ነው።—ራእይ 12:9
አስተማሪዎች ያስፈልጋሉ?
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጥቂት ጥቅል ጽሑፎች ሰጥቶ “ለጥያቄዎቻችሁ በሙሉ የሚሆኑ መልሶች እዚህ ውስጥ ታገኛላችሁ። ወደ ቤታችሁ ሄዳችሁ መልሶቹን ራሳችሁ ፈልጉ” አላላቸውም። ከዚህ ይልቅ በትዕግሥትና በደግነት የአምላክን ቃል አስተምሯቸዋል። ትምህርቱን የተቀበሉት ሰዎች እነሱም በተራቸው ሌሎችን ሲያስተምሩ የእሱን ዘዴዎች ተጠቅመዋል። የደቀ መዝሙሩን የፊልጶስን ምሳሌ እንውሰድ። ፊልጶስ ቀደም ሲል ከአይሁዶች ጋር በነበረው ግንኙነት ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ትውውቅ የነበረውን አንድ ልበ ቅን ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን ቀርቦ አነጋግሮታል። ሰውየው እርዳታ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ወኪል የሆነው ፊልጶስ እንዲረዳው መመሪያ ተሰጠው። ይህ ባለ ሥልጣን ስለ ሃይማኖት ለመወያየት ፈቃደኛ ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ማወቅ አይችልም ነበር። ይህ ኢትዮጵያዊ እውነትን ለሚፈልጉ ሁሉ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—ሥራ 8:26-39
ልክ እንደዚህ ኢትዮጵያዊ ስለ እምነትህ ለመወያየትና ጥያቄዎች ለመጠየቅ ፈቃደኛ ነህ? እንዲህ በማድረግ ብዙ ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ከሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ጋር ለመወያየት ዝግጁዎች ናቸው። ምሥክሮቹ የራሳቸውን የግል አመለካከት ለማስተላለፍ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ምን እንደሚል ለሰዎች ለማሳየት ይጥራሉ።
ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን ከእኛ መዳን ጋር በተያያዘ አምላክ ኢየሱስን እንዴት እንደሚጠቀምበት የሚገልጸውን ሐሳብ ጨምሮ ስለ ክርስቶስ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮች መማር ችሏል። በዛሬው ጊዜ የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። በቅርቡ አስፈሪና ድንቅ የሆኑ ነገሮች በዚህ ምድር ላይ ይከናወናሉ። የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው በምድር ላይ ያለ ሁሉ በእነዚህ ነገሮች ይነካል። እርግጥ፣ በምን መልኩ ነው የምንነካው የሚለው ጉዳይ በአመለካከታችንና በምንወስደው እርምጃ ላይ የተመካ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ እባክህ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል