ይሖዋን ስለ አምስቱ ወንዶች ልጆቼ አመሰግነዋለሁ
ሄለን ሶልስበሪ እንደተናገረችው
መጋቢት 2, 1997 በሕይወቴ ከገጠሙኝ እጅግ አሳዛኝ ቀኖች አንዱ ነበር። ወደ 600 የሚጠጉ ወዳጅ ዘመዶች በውድ ባለቤቴ በዲን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በዩ ኤስ ኤ ዴላዌር ዊልሚንግተን ውስጥ ተሰብስበዋል። ክርስቲያን ሽማግሌና በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ነበር። በትዳር ሕይወት ያሳለፍናቸውን ወደ 40 የሚጠጉ አስደሳች ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ አመስጋኝ የምሆንባቸው ብዙ ነገሮች ፊቴ ድቅን ይላሉ። ዲን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ማለትም ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ እንደሚያስታውሰውና ወደፊት እንደምናገኘው አውቃለሁ።
ዲን በ1950 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ አየር ኃይል ውስጥ ተቀጠረ። ሃይማኖተኛ ሰው አልነበረም። በተጨማሪም በወቅቱ በጣም እወዳት የነበረችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸውን ትምህርቶች አይቀበልም ነበር። ቢሆንም ልጆቻችንን ካቶሊኮች አድርገን ለማሳደግ ተስማምተን ነበር። በየዕለቱ ማታ ማታ ተንበርክከን በልባችን እንጸልያለን። እኔ የካቶሊክ ጸሎቶቼን እደግማለሁ፤ ዲን ደግሞ የተሰማውን ይጸልያል። በቀጣዮቹ ዓመታት አምስቱ ወንዶች ልጆቻችን ማለትም ቢል፣ ጂም፣ ትንሹ ዲን፣ ጆ እና ቻርሊ ተወለዱ።
አዘውታሪ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ የነበርኩ ሲሆን ልጆቹንም ሁልጊዜ ይዣቸው እሄድ ነበር። ሆኖም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚሠራው ነገር በተለይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ በቬትናም ጦርነት እጅዋን ማስገባቷ ግራ አጋብቶኝ ነበር። ሟቹ ካርዲናል ስፔልማን ዩናይትድ ስቴትስ አንግባ በተነሳችው ዓላማ ፍትሐዊነት ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ሰዎች “አገሬ ትክክል ሆነችም አልሆነች ከጎኗ እቆማለሁ” የሚል መልስ ይሰጡ ነበር። ቤተ ክርስቲያኔ በጦርነቱ እጅዋን አስገብታ የነበረ ቢሆንም እንኳ ልጆቼ በውጊያው እንዲሰለፉ አልፈቅድም ነበር። ሆኖም ቢያንስ ቢያንስ አንዳቸው ቄስ እንዲሆኑና ባለቤቴ ካቶሊክ እንዲሆን እጸልይ ነበር።
የአስተሳሰብ ለውጥ
አንድ ቅዳሜ ቀን ማታ ከተወሰኑ ካቶሊክ ጓደኞቼና ከመንደሩ ቄስ ጋር ሆነን ስንጫወት ነበር። እየጠጣንና እየተጫወትን ሳለ ከሴቶቹ አንዷ “አባ፣ እንደዚህ ሲጫወቱ ካመሹ በኋላ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነስተው ሥርዓተ ቁርባን ላይ መገኘት ባይችሉ የማይሰረይ ኃጢአት ይሆናል?” ስትል ቄሱን ጠየቀቻቸው።
“በፍጹም፣” ሲሉ መለሱላት። “ምንም ችግር የለውም። ማክሰኞ ማታ በደብር ቄሱ ቤት ሥርዓተ ቁርባን ይኖራል። እዚያ መጥተሽ ግዴታሽን መወጣት ትችያለሽ።”
ምንም ይምጣ ምን እሁድ ዕለት ከሚከናወነው ሥርዓተ ቁርባን መቅረት እንደማይገባ ከልጅነቴ ጀምሮ ተምሬአለሁ። ቄሱ በተናገሩት ሐሳብ እንደማልስማማ ስገልጽላቸው ረገሙኝ። አንዲት ሴት እንዴት አንድን ቄስ ታርማለች በማለት በቁጣ ተናገሩ።
‘ልጆቼ እንዲህ እንዲሆኑ ነው ስጸልይ የነበረው?’ ስል ራሴን ጠየቅኩ። ሁሉም ቄሶች እንደዚህ እንዳልሆኑ ባውቅም እንኳ ጥያቄ ፈጠረብኝ።
በ1960ዎች ዓመታት አጋማሽ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መጀመሪያ በፔንሲልቬንያ ፊላዴልፊያ በኋላ ደግሞ በዴላዌር ኑዋርክ መጥተው አነጋገሩን። ክርስቲያናዊ ቅንዓታቸውን አደንቅ የነበረ ቢሆንም እንኳ ሁልጊዜ “ይቅርታ። ካቶሊክ ስለሆንኩ መስማት አልፈልግም” እላቸው ነበር።
ከዚያም በ1970 ኅዳር ወር በአንድ ብርዳማ ቀን ማለዳ ላይ ምሥክሮቹ እንደገና መጡ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥያቄ አነሱና “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” የሚለውን መዝሙር 119:105ን አነበቡ። እነዚህ ቃላት ልቤን ነኩት። ‘መልሱ መጽሐፍ ቅዱስ ሊሆን ይችላል። ግን እኔ አንድም መጽሐፍ ቅዱስ የለኝም’ ብዬ እንዳሰብኩ ትዝ ይለኛል። ካቶሊኮች መጽሐፍ ቅዱስ አያስፈልጋቸውም፤ ሊያምታታችሁ ይችላል እየተባለ ይነገረን ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማብራራት ያለባቸው ቄሶች ብቻ እንደሆኑ ተምሬያለሁ። ስለዚህ አንድም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይኖረኝ በማድረግ ለካቶሊክ እምነት ታማኝ መሆኔን ያሳየሁ ይመስለኝ ነበር።
የዚያን ዕለት ምሥክሮቹ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ አንድ መጽሐፍ ሰጡኝ። በዚያው ሳምንት አነበብኩትና እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ! ምሥክሮቹ በሌላ ጊዜ ሁለት መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው መጡ። አንዱ የካቶሊክ ትርጉም ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖራቸውን ስረዳ በጣም ተገረምኩ። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩና እድገት በማድረግ እንደ እኔው መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ከነበረችው ከእህቴ ከሳሊ ጋር ነሐሴ 1972 ተጠመቅኩ።
ዲን አልተቃወመኝም። ሆኖም የካቶሊክ ሃይማኖትን ትቼ ሌላ እምነት መከተሌ በጣም አስገረመው። ዘወትር ያዳምጥና ይከታተል ነበር። ቀደም ሲል ልጆቼ እንዲሰሙኝ ለማድረግ ሁልጊዜ እጮህባቸው ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣም ጩኸትም መሳደብም” መወገድ እንዳለበት የሚያስጠነቅቅ መሆኑን ተገነዘብኩ። (ኤፌሶን 4:31, 32) በተጨማሪም ልጆችን በመጮህ ማሰልጠን አይቻልም። አንድ ቀን ባለቤቴ “እማዬ፣ እነዚህ ሰዎች የሚሰብኩትን ተግባራዊ ያደርጋሉ!” ብሎ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለእናቱ ሲናገር ሰማሁ። ከዚያ ብዙ ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ዲን፣ ጥር 1975 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
አምስት ልጆቻችንን ማሠልጠን
በመንግሥት አዳራሽ መሰብሰብ በጀመርኩበት ጊዜ ስብሰባዎቹ ለልጆቼ ይረዝሙባቸዋል ብዬ በማሰብ ከአባታቸው ጋር እቤት ትቻቸው እሄድ ነበር። ብቻዬን መሄዱ አስደሳች ከመሆኑም በላይ ከሐሳብ ነፃ ያደርገኝ ነበር። ሆኖም በጉባኤያችን አንድ ተናጋሪ ስለ ክርስቲያን ስብሰባዎች ርዝማኔ ሲናገር “ልጆቻችሁ ቴሌቪዥን እያዩ ምን ያህል ሰዓት መቀመጥ እንደሚችሉ አስባችሁ ታውቃላችሁ?” ሲል ጠየቀ። የሚገርመው በዚያች ሰዓት ልጆቼ ቴሌቪዥን እያዩ ነበር! ስለዚህ ‘በቃ! ከአሁን በኋላ አብረውኝ ይመጣሉ!’ ስል አሰብኩ። ባለቤቴ ልጆቹን ይዣቸው እንድሄድ ተስማማ። ውሎ አድሮ እሱም መሰብሰብ ጀመረ።
ዘወትር በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን የቤተሰባችን ሕይወት በደንብ የተደራጀና የተረጋጋ እንዲሆን አስችሎታል። ሌላም ጥቅም አስገኝቶልናል። ዲን እና እኔ ስንሳሳት ስህተታችንን አምነን በመቀበልና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን በጥንቃቄ ሥራ ላይ በማዋል ዘወትር ልጆቻችንን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ እንጥር ነበር። በቤታችን ውስጥ ሁለት ዓይነት መስፈርቶች እንዳይኖሩ እንጠነቀቅ ነበር። ለባለቤቴና ለእኔ ትክክል የሆነው ነገር ሁሉ ለልጆቻችንም ትክክል ነበር። የስብከቱ ሥራ የሕይወታችን ቋሚ ክፍል ነበር።
መዝናኛን በተመለከተ ዓመፅና ብልግና የሚታይባቸውን ፊልሞች ማየት አይፈቀድም ነበር። በበረዶ ላይ መንሸራተትን፣ ቦውሊንግና ጎልፍ መጫወትን፣ ወደ መዝናኛ ሥፍራዎችና ሽርሽር መሄድን እንዲሁም ዓርብ ዓርብ ማታ የፒሳ ምሽት ማዘጋጀትን ጨምሮ ጤናማ የሆኑ ቤተሰባዊ እንቅስቃሴዎችን ዘወትር በአንድነት እናካሂድ ነበር። ዲን ደግሞ አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ ነበር። በትዳር ሕይወታችን በሙሉ የቤተሰብ ሕይወት እንዲህ ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚገባ ተገንዝበን ነበር።—ኤፌሶን 5:22, 23
በ1970 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት በጀመርኩበት ጊዜ ቢሊ የ12፣ ጂሚ የ11፣ ትንሹ ዲን የ9፣ ጆ የ7፣ እና ቻርሊ የ2 ዓመት ልጆች ነበሩ። ቀደም ሲል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስ መማር ጀምረዋል። በጣም አስደሳች ሆኖልን ነበር። “እስቲ አንዴ ኑ፣ አንድ ነገር ላሳያችሁ!” እላቸው ነበር። ሁሉም ይመጡና አዲስ ሆኖ ባገኘነው ነጥብ ላይ በደስታ ስሜት ተውጠን እንወያያለን። በምድር ላይ ከፍተኛው ባለ ሥልጣን በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አማካኝነት ልጆቹ ይሖዋን እንዲያፈቅሩና በአባትና በእናታቸው ፊት ብቻ ሳይሆን በአምላካቸውና በፈጣሪያቸው ፊትም ተጠያቂነት እንዳለባቸው እንዲሰማቸው እየተማሩ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ከመማራችን በፊት ብዙ ዕዳ ውስጥ ገብተን ነበር። የተወሰነውን ዕዳ ለመክፈል ስንል ቤታችንን ሸጥንና ሌላ ቤት ተከራየን። አዲሱን መኪናችንንም ሸጥንና ሌላ የሠራ መኪና ገዛን። አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ የተቻለንን ያህል እንጥር ነበር። ይህ ደግሞ ውጪ ከመሥራት ይልቅ እቤት ውስጥ ከልጆቹ ጋር ለመዋል በር ከፍቶልኛል። ልጆቻችን እናታቸውን ከቤት ማጣት እንደሌለባቸው ተሰምቶን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ልጆቹ ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ጊዜ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ተጨማሪ ሰዓት ለማሳለፍ እንድችል ረድቶኛል። ውሎ አድሮ በመስከረም 1983 አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ) ለመሆን ቻልኩ። እርግጥ ነው፣ ልጆቻችን ሁልጊዜ ምርጥ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ነበሯቸው ማለት ባንችልም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አላግባብ እንደተነፈጉ ሆኖ የተሰማቸው ጊዜ የለም። ሁሉም የሙያ ትምህርት ቤት ገብተው የእርሻ ሳይንስ፣ የእንጨት ሥራ፣ አውቶ ሜካኒክስና የጽሑፍና የሥዕል ችሎታን የመሰሉ ሙያዎች ተምረዋል። ስለዚህ መተዳደሪያ ለማግኘት የሚያስችል ሙያ ቀስመው ነበር።
ብዙውን ጊዜ ስለ ቤተሰባችን ሕይወት አስብና ለራሴ ‘ቁሳዊ ሀብት ባይኖረንም እንኳ ቤተሰባችን በምድር ላይ ካሉት እጅግ ደስተኛ ቤተሰቦች አንዱ እንደሆነ መገመት እችላለሁ’ እላለሁ። ብዙም ሳይቆይ ዲን ለጉባኤ ኃላፊነቶች ብቁ ለመሆን መጣጣር ጀመረ። ልጆቹም ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። በ1982 ዲን ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ተሾመ። ከስምንት ዓመት በኋላ በ1990 የመጀመሪያው ልጃችን ቢል ሽማግሌ ሆነ። ከዚያም ጆ በዚያው ዓመት ተሾመ። ትንሹ ዲን በ1991፣ ቻርሊ በ1992 እና ጂም ደግሞ በ1993 ሽማግሌዎች ሆነው ተሾሙ።
የወላጅነት ኃላፊነታችንን ስንወጣ አንዳንድ ስህተቶች እንደሠራን አውቃለሁ። የሠራናቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ማስታወሱም ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። አንድ ወዳጃችን ልጆቼ ከክርስትና ሕይወታቸው የመጀመሪያ ዓመታት የሚያስታውሷቸውን ነገሮችና በተለይ ደግሞ በልጅነታቸው ከተማሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ ክርስቲያን ሽማግሌ ለመሆን እንዲጣጣሩ የረዷቸው የትኞቹ እንደሆኑ ጠይቋቸው ነበር። የሰጡት አስተያየት በጣም አስደስቶኛል።
ልጆቼ የሰጡት አስተያየት
ቢል:- “በሮሜ 12:9-12 ላይ ያገኘነው ትምህርት በአእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ አልፏል። በከፊል እንዲህ ይላል:- ‘በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ . . . በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ . . . በተስፋ ደስ ይበላችሁ።’ ወላጆቼ ሰዎችን መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማሳየት ችሎታ ነበራቸው። ለሌሎች ፍቅራቸውን መግለጽ ያስደስታቸው እንደነበረ ማየት ትችላለህ። በቤታችን ውስጥ የነበረው ይህ የፍቅር መንፈስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የአስተሳሰባችን አካል እንዲሆኑ ረድቶናል። እውነትን አጥብቀን እንድንይዝ የረዳን ይህ ነው። ወላጆቼ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍጹም ፍቅር ነበራቸው። በመሆኑም እውነትን መውደድም ሆነ አጥብቆ መያዝ አስቸጋሪ ሆኖብኝ አያውቅም።”
ጂም:- “ወደ አእምሮዬ ከሚመጡት ታላላቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዱ ማቴዎስ 5:37 ነው:- ‘ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።’ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼ ምንጊዜም ወላጆቼ ከእኛ ምን እንደሚጠብቁ እናውቅ ነበር። በተጨማሪም ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሰዎች ሆነው መገኘት እንዳለባቸው ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ሕያው ምሳሌዎች ሆነውልናል። እናትና አባታችን ምንጊዜም ስምም ነበሩ። ተጨቃጭቀው አያውቁም። በአንድ ጉዳይ ባይስማሙ እንኳ እኛ ፈጽሞ አናውቅም። አንድ ነበሩ፤ ይህ ደግሞ በሁላችንም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። እማዬንም ሆነ አባዬን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋን ማሳዘን አንፈልግም ነበር።”
ዲን:- “ምሳሌ 15:1 ‘የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች’ ይላል። አባዬ ገራም ሰው ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ እንኳ ሳለሁ ከእሱ ጋር የተጨቃጨቅኩበትን ጊዜ አላስታውስም። በሚበሳጭበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ልዝብ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሲቀጣኝ ወደ ክፍሌ እንድገባ ያዝዘኝ ነበር፤ ወይም ደግሞ አንዳንድ መብቶችን ይነፍገኝ ነበር። ሆኖም ተጨቃጭቀን አናውቅም። አባታችን ብቻ ሳይሆን ጓደኛችንም ነበር። በመሆኑም ልናሳዝነው አንፈልግም ነበር።”
ጆ:- “መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ቆሮንቶስ 10:5 ላይ ‘አእምሮን ሁሉ እየማረኩ ለክርስቶስ እንዲታዘዝ ስለማድረግ’ ይናገራል። በልጅነታችን በቤት ውስጥ ለይሖዋ መስፈርቶችና መመሪያዎች ታዛዦች እንድንሆን እንማር ነበር። እውነት ሕይወታችን ነበር። በስብሰባ ላይ መገኘት የሕይወታችን መንገድ ነበር። አሁንም ቢሆን ከስብሰባ ቀርቶ ሌላ ነገር ማድረግ ለእኔ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ክርስቲያናዊው አገልግሎትም ቋሚ የሕይወታችን ክፍል ነበር። እንደ አማራጭ ተደርጎ የታየበት ወቅት የለም። ጓደኞቻችን በመንግሥት አዳራሽ የምናገኛቸው ናቸው። ከሌላ ቦታ ጓደኛ ለማግኘት የምንሞክርበት ምንም ምክንያት አልነበረም። አንድ አባት ልጆቹን በሕይወት ጎዳና ከመምራት የበለጠ ምን ነገር ሊያደርግላቸው ይችላል!”
ቻርሊ:- “ምሳሌ 1:7 አሁንም ድረስ በአእምሮዬ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ‘የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ’ ይላል። ወላጆቼ ይሖዋ እውን እንደሆነ እንድንገነዘብና ለእሱ የፍርሃትና የፍቅር ስሜት የማዳበርን አስፈላጊነት እንድናስተውል ረድተውናል። ‘ይህን ነገር ማድረግ የሌለብህ እኛ አታድርግ ስላልንህ መሆን የለበትም። እስቲ አንተ ራስህ ምን ይመስልሃል? ይሖዋ ይህን ስታደርግ ሲያይ ምን የሚሰማው ይመስልሃል? ሰይጣንስ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?’ እያሉ ጉዳዩን እንድናስብበት ያደርጉናል።
“ይህ ዋናውን ጉዳይ እንድናስተውል ይረዳናል። አባዬና እማዬ ሁልጊዜ አብረውን ሊሆኑ አይችሉም። ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ቢኖር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በልባችንና በአእምሯችን ውስጥ መቅረጽ ብቻ ነው። በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም ከጓደኞቻችን ጋር ስንሆን ብቻችንን ነው። ያ ለይሖዋ ያደረብን ጤናማ ፍርሃት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። እስከ ዛሬም ድረስ አብሮን አለ።
“በተጨማሪም እማዬ ዘወትር ስለ አቅኚነት አገልግሎቷና ስላገኘቻቸው ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች ትናገር ነበር። ለአገልግሎት ዘወትር አዎንታዊ አመለካከት ነበራት። ይህ ደግሞ በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። እርሷ ለሰዎች የነበራትን ፍቅር እኛም ኮርጀናል። ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎትም እጅግ አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበናል።”
አመስጋኝ የምሆንባቸው ምክንያቶች
በአሁኑ ጊዜ ልጆቼ ያገቡ ሲሆን ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ አምስት ተወዳጅ ምራቶች አግኝቻለሁ። ከዚህም ሌላ አምስት የልጅ ልጆች ለማየት በቅቻለሁ! ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ ይሖዋን እንዲወዱና መንግሥቱን በሕይወታቸው ውስጥ ከምንም ነገር በላይ እንዲያስቀድሙ ጥሩ ማሠልጠኛ ተሰጥቷቸዋል። አንድ ቀን እነሱም እንደ አባቶቻቸውና እንደ አያታቸው ሽማግሌዎች እንዲሆኑ ጸሎታችን ነው።
ዲን ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከልጆቼ አንዱ እንዲህ ሲል ጻፈ:- “አባዬን ማጣቴ በጣም ያሳዝነኛል። አሁን አንቀላፍቷል። ምንም የሚሰማው ሥቃይም ሆነ ሕመም የለም። ከዚህ በኋላ ቀዶ ሕክምና፣ መርፌም ሆነ የጉሉኮስ ቱቦ አያስፈልገውም። ዕረፍት ላይ ነው። ከመሞቱ በፊት ልሰናበተው አልቻልኩም። ነገሮች ሁልጊዜ እንደታሰበው አይሳኩም። እንኳን ደህና መጣህ ብለው ከሚቀበሉት ሰዎች መካከል ለመሆን ጠንክሬ መሥራት አለብኝ ከማለት ሌላ የምጨምረው ነገር የለኝም!”
ይሖዋ አፍቃሪ ባልና አስተማማኝ የትንሣኤ ተስፋ ስለሰጠኝ እጅግ አመሰግነዋለሁ! (ዮሐንስ 5:28, 29) ስለ አምስቱ ወንዶች ልጆቼም ከልብ አመሰግነዋለሁ!
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ወቅት ሄለን ሶልስበሪና ቤተሰቧ