ሰባት ወንዶች ልጆችን ማሳደግ ያስከተለብን ፈታኝ ሁኔታና ያገኘነው በረከት
በርትና ማርጋሬት ዲክማን እንደተናገሩት
በ1927 ኦማሃ፣ ኔብራስካ፣ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ ተወለድኩ። ያደግኩት ደግሞ ሳውዝ ዳኮታ ውስጥ ነው። ዓለም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ገብታ በነበረችባቸው አስቸጋሪ ዓመታት (1929-42) ያሳለፍኩትን የልጅነት ጊዜ አሁንም ድረስ አስታውሳለሁ። እናቴ የችጋር ሾርባ ብላ ትጠራው የነበረውን ምግብ ታዘጋጅ ነበር። መጥበሻው ላይ ትንሽ ጮማ ታስቀምጥና ውኃ ጨምራ ከቀቀለችው በኋላ ዳቧችንን እያጠቀስን እንበላ ነበር። በዚያን ወቅት የነበረው ኑሮ ለብዙ ቤተሰቦች ከባድ ነበር።
ቤተሰቦቼ ሃይማኖተኞች አልነበሩም። በአካባቢው የነበሩት የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች የሚያሳዩት ግብዝነት ቅር አሰኝቷቸው ነበር። በእኔ በኩል ግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያሳለፍኳቸው ሁለት ዓመታት በአስተሳሰቤ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። መጠጥና ቁማር የለመድኩት በእነዚህ ዓመታት ነበር።
ከጦር ሠራዊቱ ፈቃድ ወስጄ ወደ አንድ ዳንስ ቤት በሄድኩበት ወቅት ማርጋሬት ሽላት ከምትባል የጀርመንና የዩክሬን ዝርያ ካላት አንዲት ልጅ ጋር ተገናኘሁ። ተፋቀርንና ለሦስት ወራት ያህል ከተጠናናን በኋላ በ1946 ተጋባን። በስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሰባት ወንዶች ልጆች ወለድን። ወላጅ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ካሳለፍነው ከባድ ተሞክሮ መረዳት ችለናል።
በ1951 እንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ላይ ስሠራ ከባድ ጉዳት ደረሰብኝ። የግራ ክንዴን አጥቼ ነበር ለማለት እችላለሁ። የቆዳና የአጥንት ማስተካከያ እንዲደረግልኝ በሆስፒታል ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆየሁ። በዚህ መሀል ማርጋሬት አምስት ልጆችን የመንከባከቡን ኃላፊነት ለመሸከም ተገድዳ ነበር። ጓደኞቻችንና ጎረቤቶቻችን ምስጋና ይግባቸውና ያን አስቸጋሪ ጊዜ መወጣት ችላለች። ሆስፒታል ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ስለ ሕይወት ዓላማ ማሰብ የምችልበት በቂ ጊዜ ነበረኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ብሞክርም ብዙም ሊገባኝ አልቻለም።
ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በዋሽንግተን ክፍለ ሀገር ውስጥ ወደምትገኘው ኦፖርቹኒቲ የተባለች ከተማ ተዛወርንና ከአማቼ ጋር የግንባታ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። አሁን ደግሞ ማርጋሬት የእሷን ታሪክ ትንገራችሁ።
ባተሌ ነበርኩ!
ያደግኩት የእህል ምርትና የወተት ከብቶች እርባታ ባለበት እንዲሁም በቆርቆሮ የሚታሸጉ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ልማት በሚካሄድበት የእርሻ ቦታ ነበር። ጥብቅ የሆነ የሥራ ግብረ ገብ የነበረኝ ሲሆን ይህም በኋለኛው የሕይወት ዘመኔ ለገጠሙኝ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች በሚገባ አሠልጥኖኛል። ቢያንስ ቢያንስ የምንበላው ምግብ አጥተን ስለማናውቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ድቀት ከአብዛኞቹ በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ችለናል።
አልፎ አልፎ በሰንበት ትምህርት እካፈል የነበረ ቢሆንም ወላጆቼ ለሃይማኖት ምንም ጊዜ አልነበራቸውም። ከጊዜ በኋላ በ19 ዓመቴ ከበርት ጋር ተጋባን። ወደ ቤተ ክርስቲያን አልሄድንም። ከዚህ ይልቅ ቃለ ቡራኬ የሚሰጥ አንድ የኮንግርጌሽናል ቤተ ክርስቲያን ቄስ በተገኘበት በወላጆቼ ሳሎን ቤት ውስጥ አንድ ቀለል ያለ ሥነ ሥርዓት አካሄድን። በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሪቻርድ፣ ዳን፣ ደግ፣ ጌሪ፣ ማይክል፣ ኬን እና በመጨረሻም በ1954 ስኮት የተባሉ ሰባት ወንዶች ልጆች ወለድኩ። እነዚህን ሁሉ ማሳደጉ ቀላል አልነበረም!
በኦፖርቹኒቲ ከተማ መኖር ከጀመርን በኋላ አንዲት ሴት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልታነጋግረን ቤታችንን አንኳኳች። በእሳታማ ሲኦል ታምን እንደሆነ ጠየቅኳት። ይህ መሠረተ ትምህርት በጣም ያስፈራኝ ነበር። እሳታማ ሲኦል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዳልሆነና አልፎ ተርፎም ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ስትነግረኝ ታላቅ እፎይታ ተሰማኝ! ሞትን ክፉኛ ስፈራ የኖርኩ ከመሆኑም በላይ እሳታማ ሲኦል አለ የሚለውን ትምህርት አፍቃሪ ከሆነው አምላክ ባሕርይ ጋር ለማስታረቅ ተቸግሬ ነበር። እንዲህ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ለልጆቼ ላለማስተማር ወሰንኩ።
በ1955 “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን”a በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። አንድ የጰንጠቆስጤ ሰባኪ በድንገት እኔን የመርዳት ፍላጎት ያደረበትና ከይሖዋ ምሥክሮች ሊያድነኝ የፈለገው በዚህ ጊዜ ነበር! ሆኖም ተሳስቶ ነበር። ስብከቱን የጀመረልኝ ስለ እሳታማ ሲኦል በመናገር ነበር! እንዲያውም እኔን አሳምነው ከምሥክሮቹ ጋር የጀመርኩትን ጥናት እንዳቋርጥ ለማድረግ የጰንጠቆስጤ አባላት የሆኑ ሦስት ሴቶችን ልኮ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርት እኔ መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠና ፊት ለፊት ባለው ክፍል ውስጥ ሆኖ ይሰማ ነበር። ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ማንበብ ሲጀምር አንዳንድ ነገሮች ግልጽ እየሆኑለት መጡ። የፈረቃ ሠራተኛ ስለነበር እስከ እኩለ ሌሊት ይሠራ ነበር። እቤት የሚመጣው ከተኛሁ በኋላ ነበር። አንድ ቀን ሌሊት ድምፅ ሳላሰማ ምድር ቤት ስወርድ ተደብቆ መጽሐፎቼን ሲያነብ አየሁት! ራሱ እየመረመረ መሆኑን ማወቄ አስደስቶኝ ቀስ ብዬ በጣቴ እየተራመድኩ ተመልሼ ተኛሁ። በመጨረሻ እሱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረና በ1956 የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።
በስምንት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሰባት ልጆች በመውለዴ ልጆቹን የመመገቡንና የማልበሱን እንዲሁም የቤቱን ንጽህና የመጠበቁን ዕለታዊ ሥራ ማከናወን ፈታኝ ሆኖብኝ ነበር። ልጆቹ የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ ማከናወን ተምረው ነበር። ብዙውን ጊዜ የዕቃ ማጠቢያ ማሽን ሳይሆን ሰባት ልጆች ነው ያሉኝ እል ነበር! ሁሉም ተራ ገብተው ይህን አስፈላጊ ሥራ ይሠሩ ነበር። በርት በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ቋሚ የሆነ ተግሣጽ ከመስጠቱም በላይ የማይለዋወጡ የቤት ውስጥ ደንቦች ያወጣ ነበር። ሆኖም ምንጊዜም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ልጆቹ አባታቸውን ያከብሩት የነበረ ቢሆንም አይፈሩትም ነበር። ልጆቻችን አባታቸው ቀለል ባለ መንገድ ስለ ጾታ ይነግራቸው የነበረውን ነገር አሁንም ድረስ ያስታውሱታል። በርት ስለዚህ ጉዳይ ልጆቹን የማስተማር ኃላፊነቱን ቸል ብሎ አያውቅም ነበር።
የመጀመሪያ ልጃችን የሆነው ሪቻርድ በ1966 በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በፈቃደኝነት ለማገልገል ሄደ። የመጀመሪያ ልጃችን ጎጆአችንን ለቅቆ ሲሄድ ማየቱ ፈተና ሆኖብኝ ነበር። በየቀኑ ማዕድ ፊት ቀርበን የእሱ መቀመጫ ክፍት ሆኖ ስመለከት በጣም ቅር ይለኝ ነበር። ሆኖም ጥሩ ተሞክሮና ሥልጠና እያገኘ ስለነበር ተደስቻለሁ።
እስቲ በርት ደግሞ ቀጣዩን ታሪክ ይንገራችሁ።
ልጆቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ኮትኩቶ ማሳደግ
እኔና ማርጋሬት የተጠመቅነው በስፖካን፣ ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነበር። ከዚያ በኋላ ልጆቻችንን የቆየ ባሕል ብላችሁ ልትጠሩት በምትችሉት መንገድ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ኮትኩቶ የማሳደጉን ፈታኝ ኃላፊነት መወጣት ነበረብን። ውሸትንም ሆነ ሁለት ዓይነት የአቋም ደረጃዎችን ችላ ብዬ አላልፍም ነበር። ልጆቹም ይህን ያውቁ ነበር። ይሖዋ ምርጣችንን ልንሰጠው የሚገባ አምላክ እንደሆነ አስተምረናቸዋል።
ይሁን እንጂ የጠበቀ ዝምድና ስለነበረንና ብዙ ነገሮች አብረን እናከናውን ስለነበር ምሥጢራቸውን ሊያካፍሉኝ እንደሚችሉ ያውቁ ነበር። በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆነን ወደ ባሕር ዳርቻዎች በመሄድ እንዝናና ነበር፣ ለሽርሽር ወደ ተራራዎች እንሄድ ነበር እንዲሁም አብረን ኳስ እንጫወት ነበር። ከብቶችና የአትክልት ሥፍራ የነበረን ሲሆን ልጆቹ በሙሉ በሁሉም ሥራ ይሳተፉ ነበር። በዚህ መንገድ መጫወትን ብቻ ሳይሆን መሥራትንም ተምረዋል። በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሚዛናዊ ለመሆን ጥረት እናደርግ ነበር።
ለየት ያለ ቲኦክራሲያዊ ክንውን
በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንም ቢሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አንድ ላይ ወደ መንግሥት አዳራሽ እንሄድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነበረን። በ1957 ሲያትል፣ ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተን ነበር። በፕሮግራሙ ላይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩ ምሥክሮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሄደው የሚያገለግሉ ቤተሰቦች እንደሚፈለጉ ተገለጸ። ቤተሰባችን ይህ ጥሩ ሐሳብ መሆኑን ስላመነበት ወደነዚህ ቦታዎች ለመዛወር ዕቅድ አወጣን። መጀመሪያ በ1958 ወደ ሚዙሪ ከዚያም በ1959 ወደ ሚሲሲፒ ሄድን።
በ1958 ምንጊዜም የማንረሳው ጊዜ አሳለፍን። እንደ ቤት ያለ ተጎታች ሠራሁና ሦስት ሰዎች በምታስቀምጥና ስድስት ሲሊንደር ባላት ዴሶቶ የምትባል የ1947 አሮጌ ሞዴል መኪና እየጎተትን ወሰድነው። በዚያ ዓመት ዘጠኛችንም በዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት በዚህ መኪና ወደ ኒው ዮርክ ተጓዝን። በምዕራብ የባሕር ዳርቻ ከምትገኘው ስፖካን ተነስተን መንገድ ላይ እያደርን 4,200 ኪሎ ሜትር አቋርጠን ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ኒው ዮርክ ገባን! ልጆቹ ያ ጉዞ ምንጊዜም የማይረሱት ትዝታ ጥሎባቸው አልፏል።
በኬክ ትምህርት መስጠት
በዚያ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከጠፋችው ገነት እስከምትመለሰው ገነት (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ የግል ቅጂዎች አገኘን።b ይህን መጽሐፍ በሳምንታዊ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ላይ ዋነኛ የማጥኛ መሣሪያ አድርገን ተጠቅመንበታል። ሁሉም ልጆች ማንበብ የተማሩት ገና በሕፃንነታቸው ነበር። ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ማርጅ አብራቸው የተወሰነ ጊዜ በማሳለፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ ታዳምጣቸው ነበር። ቴሌቪዥን አእምሯቸውን እንዲቆጣጠረው አንፈቅድም ነበር።
በቤተሰባችን ውስጥ ስርዓትና የመከባበር መንፈስ ነበር። አንድ ቀን ማርጋሬት ትልቅ ኬክ ሠራች። በዚህ የተካነች ነበረች። በዚያ ዕለት ካሮትም ተሠርቶ ነበር። ልጆቹ የሚሠራላቸውን አትክልት ቢያንስ ቢያንስ እንዲቀምሱት እናበረታታቸው ነበር። አራተኛው ልጃችን ደግ ግን ካሮት አይወድም ነበር። ካሮቱን ካልበላ ኬክ እንደማይሰጠው ነገርነው። አሁንም የተሰጠውን ምግብ ለመጨረስ ፈቃደኛ አልሆነም። ማርጋሬት “ካሮቱን ካልበላህ ኬክህ ለውሻው ይሰጣል” አለችው። ደግ ጣፋጭ ኬኩን ብላኪ ሲውጠው እስከተመለከተበት ጊዜ ድረስ ታደርገዋለች ብሎ አላመነም ነበር! እሱም ሆነ የተቀሩት ልጆች ከዚህ ሁኔታ ጥሩ ትምህርት አግኝተዋል። ወላጆች እንደ መሆናችን መጠን ያልነውን የምናደርግ መሆኑን ተገንዝበዋል።
አስደሳች ሕይወት
እኔና ማርጋሬት በማቴዎስ 6:33 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት መመሪያ አድርገን እንጠቀምባቸው ነበር:- “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” በቤተሰብ ደረጃ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስቀደም ጥረት እናደርግ ነበር። ለስብከት አንድ ላይ መውጣት ያስደስተን ነበር። ልጆቹ ደግሞ በየተራ ከእኔ ጋር ከቤት ወደ ቤት ይሄዱ ነበር። ሁሉም የየራሳቸው የመጽሐፍ ቦርሳ፣ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ነበሯቸው። ለሚያሳዩት ዕድገት ሁሉ እናመሰግናቸው ነበር። ብዙውን ጊዜ ማርጋሬት እቅፍ አድርጋ አድናቆቷን ትገልጽላቸው ነበር። ዘወትር ፍቅራችንን እንገልጽላቸው ነበር ማለት እንችላለን። ሁልጊዜ ከልጆቹ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ እንመድባለን። በእርግጥም አስደሳች ሕይወት ነበር!
ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ሰዎችን ወደ ስብሰባዎች ማድረስንና መንግሥት አዳራሹን መክፈትን የመሳሰሉ ኃላፊነቶችን ወስደው መሥራት ከመጀመራቸውም በላይ በሌሎች ሥራዎችም መርዳት ጀመሩ። መንግሥት አዳራሹን እንደ አምልኮ ቦታቸው አድርገው እንዲመለከቱት ማሠልጠኛ ስለተሰጣቸው አዳራሹን በጥሩ ሁኔታ መያዝ ያስደስታቸው ነበር።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እናበረታታቸው ነበር። በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የተማሪ ክፍሎች በማቅረብ እንዴት ጥሩ ተናጋሪ መሆን እንደሚቻል ቀስ በቀስ ተምረዋል። አምስተኛው ልጃችን ማይክል ሁልጊዜ በሰዎች ፊት ቆሞ መናገር ይጠላ ስለነበር መድረክ ላይ ሆኖ መናገር ያስቸግረው ነበር። ክፍሉን ካጋመሰ በኋላ መጨረስ ስለሚያቅተው በብስጭት ማልቀስ ይጀምራል። ውሎ አድሮ ይህን ስሜቱን ማሸነፍ በመቻሉ በአሁኑ ጊዜ አግብቶ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የተለያዩ ጉባኤዎችን በመጎብኘት በአንድ ሳምንት ብቻ እንኳ በርከት ያሉ ንግግሮች ይሰጣል። እንዴት ያለ የሚያስገርም ለውጥ ነው!
ልጆቹ ለዲሲፕሊን ያላቸው አመለካከት
ማይክል በቆየው ባሕላዊ መንገድ ተኮትኩቶ ማደጉ ያሳደረበትን ስሜት ለማወቅ የንቁ! ዘጋቢ አነጋግሮት ነበር። “አባባ ዲሲፕሊን የሚሰጠን በደግነት መንፈስ እንደሆነ እናምን ነበር። አንድ ጊዜ ትዝ ይለኛል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለሁ በአንድ የራዲዮ ጣቢያ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። በሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎትም ለመሳተፍ እንድችል መኪና መግዛት ፈልጌ ነበር። የጣቢያው ኃላፊ ሊነሳ የሚችል የሸራ ክዳን ያላትን ባለ ሁለት በር ፎርድ ሙስታንግ መኪናውን እንድገዛው ሐሳብ አቀረበልኝ። ወጣቶች የሚወዷት የስፖርት መኪና ነበረች። ሰዎችን ወደ አገልግሎት ይዞ ለመሄድ ተስማሚ እንዳልሆነች ብገነዘብም እንኳ መኪናዋን ለመግዛት ጓጉቼ ነበር። ስፈራ ስቸር ወደ አባባ ሄድኩ። ኃላፊው ያቀረበልኝን ሐሳብ ስነግረው ‘እስቲ እንነጋገርበት’ አለኝ። ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶኝ ነበር! አሳማኝ ነጥቦች እያነሳ ካነጋገረኝ በኋላ ለአገልግሎት ይበልጥ ተስማሚ የሆነ መኪና መግዛቱ ያለውን ጥቅም እንዳጤን አደረገኝ። ስለዚህ ባለ አራት በር ሴደን መኪና ገዛሁና በተሰጠኝ የአገልግሎት መስክ ከ160,000 ኪሎ ሜትር በላይ ከነዳኋት በኋላ ‘አባዬ እውነቱን ነው’ ከማለት ሌላ ምንም የምለው አልነበረኝም።
“ወጣቶች በነበርንበት ጊዜ ከዋሽንግተን ወደ ሚዙሪ ከዚያም ወደ ሚሲሲፒ ያደረግነው ጉዞ ፈጽሞ የማይረሳ ነው። በጣም አስደሳች ነበር። ዘጠኛችንም ለአንድ ዓመት ያህል እንኖር የነበረው 2.5 ሜትር በ11 ሜትር በሆነ ተጎታች ውስጥ የነበረ ቢሆንም እንኳ በጣም አስደሳች ጊዜ ነበር። እንዴት የተደራጁ መሆን እንደሚቻልና በጣም በተጨናነቀ ሁኔታ በምንኖርበት ጊዜም እንኳ እንዴት እርስ በርስ ተስማምተን መኖር እንደምንችል አስተምሮናል። እርግጥ አብዛኛውን ጊዜ እናሳልፍ የነበረው ውጪ ሆነን በመጫወት ነበር።
“ሌላው ትዝ የሚለኝና የማልረሳው ነገር አባባ የዕለት ጥቅስ ይመራበት የነበረው መንገድ ነው። በ1966 በኒው ዮርክ በደቡብ ላንሲንግ በአንድ የመንግሥቱ የእርሻ ቦታ በተካሄደ የሽማግሌዎች ትምህርት ቤት በተካፈለበት ጊዜ የቤቴል ቤተሰብ አባላት በየዕለቱ በጥቅሱ ላይ ሐሳብ ለመስጠት ምርምር እንደሚያደርጉ ተረዳ። ይህንኑ ዘዴ በእኛም ቤተሰብ ውስጥ ተግባራዊ አደረገው። ሰባታችንም ምርምር አድርገን ሐሳብ እንድንሰጥ ፕሮግራም ይወጣልን ነበር። አንዳንድ ጊዜ እናጉረመርም የነበረ ቢሆንም እንኳ እንዴት ምርምር ማድረግና ሐሳብ መስጠት እንደምንችል መማር ችለናል። እንዲህ ዓይነቶቹ ልማዶች አብረውን ዘልቀዋል።
“እማማና አባባ ለእኛ የከፈሉትን መሥዋዕት ሳስበው በጣም ይደንቀኛል። ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼ ሪቻርድና ዳን ሥራ ይዘው ቤተሰባችንን በገንዘብ መርዳት በሚችሉበት ወቅት ላይ ወላጆቻችን ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በፈቃደኛ ሠራተኝነት እንዲያገለግሉ አበረታተዋቸዋል። በተጨማሪም አራታችን በአውሮፕላን ወደ ኒው ዮርክ ተጉዘን የማኅበሩን ዋና መሥሪያ ቤት እንድንጎበኝ ወላጆቻችን ገንዘብ አጠራቅመውልናል። ይህ ልቤን በጣም ነካው። ለይሖዋ ድርጅት ያለንን አድናቆት ጨምሮልናል።
“አሁን ደግሞ ወደ አባባ ልመልሳችሁ።”
መሰናክሎችም ገጥመውናል
እንደ ሌላ ማንኛውም ቤተሰብ እኛም ችግሮችና መሰናክሎች ገጥመውናል። ልጆቹ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጠናናት ወደሚችሉበት ዕድሜ ሲደርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሜታቸውን ከማረከችው ልጅ ጋር ትዳር ለመመሥረት እንዳይጣደፉ መምከር ነበረብኝ። በተጨማሪም ተቀጣጥረው በሚጫወቱበት ጊዜ የበሰለ ሰው አብሯቸው እንዲሆን ለማድረግ እንጥር ነበር። የዕድሜ ልክ የትዳር ጓደኛ ከመምረጣቸው በፊት ትንሽ የሕይወት ተሞክሮ እንዲያገኙ እንፈልግ ነበር። ያለቀሱበትና አልፎ ተርፎም መንፈሳቸው ለጊዜው የተሰበረበት ጊዜ ነበር። ሆኖም ውሎ አድሮ በተለይ “በጌታ” ማግባትን የሚያበረታታው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥበብ የተሞላበት መሆኑን መገንዘብ ችለዋል። ላሳዩት ጥበብ ምስጋናችንን ገልጸንላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:39
ሰባተኛው ልጃችን ስኮት ሐዘን ላይ ጥሎን ነበር። በሥራ ቦታው መጥፎ ባልንጀርነት መሥርቶ ነበር። በመጨረሻ ከጉባኤ ተወገደ። ይህ ለሁላችንም በጣም አስደንጋጭ ነበር። ቢሆንም የሽማግሌዎቹን የፍርድ ውሳኔ አክብረናል። ስኮት ይሖዋን ማገልገል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መንገድ መሆኑን ካሳለፈው ከባድ ተሞክሮ ሊማር ችሏል።
አንድ ቀን ወደ ጉባኤ እንደሚመለስ ተስፋ እናደርግ ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላ በመመለሱ በጣም ተደስተናል። ያሳለፈውን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማስታወስ “ተወግጄ በነበረበት ጊዜ ከቤተሰቦች ጋር የነበረኝ ግንኙነት በጣም የተገደበ ቢሆንም እንኳ በጣም እንደሚወዱኝ መገንዘቤ በእጅጉ ጠቅሞኛል” ሲል ተናግሯል። ስኮት እድገት ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን ላለፉት ስምንት ዓመታት በሽምግልና ሲያገለግል ቆይቷል።
ሌላው አሳዛኝ ገጠመኝ በ20ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኘው የልጅ ልጃችን በ1998 መወገዱ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ዲሲፕሊን አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ማወቃችን ያጽናናናል።
በሕይወታችን ውስጥ የተፈጠረ ትልቅ ለውጥ
በመጨረሻ፣ በ1978 ልጆቹ በሙሉ ራሳቸውን ችለው ወጡ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የቤት ውስጥ ማሞቂያና ማቀዝቀዣ መሣሪያዎችን በመግጠም ሥራ ልምድ አካበትኩ። በ1980 እኔና ማርጋሬት ብሩክሊን ውስጥ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ለዘጠኝ ወራት እንድናገለግል ልዩ ግብዣ ቀረበልን። ይህ ከሆነ አሥራ ስምንት ዓመታት ያለፉ ሲሆን አሁንም እዚያው በማገልገል ላይ እንገኛለን!
ባሳለፍነው የሕይወት ዘመን በእጅጉ ተባርከናል። ልጆቻችንን በቆየው ባሕላዊ መንገድ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማሳደግ ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ተክሰንበታል። በአሁኑ ጊዜ አምስቱ ልጆቻችን የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነው። በተጨማሪም 20 የልጅ ልጆችና 4 የልጆቻችን የልጅ ልጆች ያሉን ሲሆን አብዛኞቹ በእውነት ቤት ውስጥ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው።
የሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት እውነት ሆነው አግኝተናቸዋል:- “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፣ የጎልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው።”—መዝሙር 127:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1946 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ፤ ይህ መጽሐፍ አሁን መታተም አቁሟል።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1996 በ50ኛው የጋብቻችን ክብረ በዓል ላይ ከልጆቻችንና ከምራቶቻችን እንዲሁም (በገጽ 15 ላይ ያለው) ከልጅ ልጆቻችን ጋር የተነሳነው ፎቶ