ከብዙ ዓመታት በኋላ ፍሬ ያፈሩ ዘሮች
ቀጥሎ የቀረበው ደብዳቤ የተላከልን፣ በሚያዝያ 1999 “ንቁ!” እትም ላይ በወጣ “ሰባት ወንዶች ልጆችን ማሳደግ ያስከተለብን ፈታኝ ሁኔታና ያገኘነው በረከት” በሚለው ርዕስ ምክንያት ነው።
ውድ ወንድም እና እህት ዲክማን፣
ተሞክሯችሁን አሁን ገና አንብቤ መጨረሴ ሲሆን የግድ ደብዳቤ ልጽፍላችሁ እንደሚገባ ተሰማኝ። ከዓመታት በፊት በሚሲሲፒ [1960-61] ስትኖሩ ከቤተሰባችሁ ጋር እተዋወቅ ነበር። እንዲያውም ከወንዶች ልጆቻችሁ ጋር አብሬ ተምሬአለሁ። እንዲሁም ብዙ ጊዜ ቤታችሁ እየመጣሁ ከልጆቻችሁ ጋር እጫወት ነበር። ሆኖም በልጅነት አእምሮዬ ፈጽሞ በማይረሳ ሁኔታ የተቀረጹት ነገሮች እነዚህ አይደሉም። በዚያ የልጅነት ዕድሜዬ እንኳን ልጆቻችሁ በክርስቲያናዊ ሕሊናቸው ምክንያት ትምህርት ቤት ውስጥ ለባንዲራ ሰላምታ ያለመስጠታቸው ጉዳይ በጣም ያስገርመኝ ነበር። ምንም እንኳ የግራንድቪው ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል የነበርኩ ቢሆንም ከልጆቻችሁ አንዱ ያለውን ጽኑ አቋም ሲገልጽልኝ ትክክል እንደሆነ ተረድቼ ነበር።
ከልጆቻችሁ አንዱ ፍሮም ፓራዳይዝ ሎስት ቱ ፓራዳይዝ ሪጌይንድa የተባለውን መጽሐፍ ወይ ይስጠኝ አሊያም ሰርቄ ልውሰድበት ባላስታውስም ከዳር እስከ ዳር አንብቤ መጨረሴ ግን ትዝ ይለኛል። በወቅቱ መጽሐፉ አንድ ጥሩ የታሪክ መጽሐፍ ሆኖልኝ ነበር። ለበርካታ ዓመታት ተዳፍነው የሚቆዩ የእውነት ዘሮች መተከላቸውን አላስተዋልኩም ነበር።
በ1964 ቤተሰባችን ወደ ሰሜን የተዛወረ ሲሆን እኔ ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቆምኩ። በሃይማኖት ውስጥ የሚታየው ግብዝነት ግራ ስላጋባኝ ለበርካታ ዓመታት በማንኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ አልፈለግሁም ነበር።
ከዓመታት በኋላ ስለ ሕይወት ዓላማ በቁም ነገር ማሰብ ስጀምር ከፈጣሪ ጋር ዝምድና መመሥረት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህ ዝምድና ከሃይማኖት ግብዝነት ነፃ እንዲሆን ፈለግሁ። ከዓመታት በፊት የተዘሩት እነዚያ የእውነት ዘሮች ሳላውቀው ማቆጥቆጥ ጀምረው ነበር።
ወደ ሰማይ የመሄድ ፍላጎት ስላልነበረኝ ይህ ጉዳይ በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። የእኔ ፍላጎት እዚችው ምድር ላይ ለመኖር ነው። ይህች ፕላኔት በራስዋ እጅግ ግሩም የፍጥረት ሥራ ስለሆነች አምላክ ለምን ያጠፋታል የሚል ስሜት ነበረኝ። እንዲሁም ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚል አመለካከት አልነበረኝም። ኢየሱስ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ መሥዋዕቱ የይስሙላ ይሆን ነበር። እነዚህ አመለካከቶች፣ ስሜቶችና ከፈለጋችሁም ጽኑ እምነት ልትሏቸው ትችላላችሁ በባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ከተማርኳቸው ነገሮች ጋር ሊስማሙልኝ አልቻሉም። ስለዚህ ደጋግሜ ከልብ መጸለይ ጀመርኩ፤ ይሖዋም ፈጣን ምላሽ ሰጠኝ። በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በሬን ያንኳኩ ሲሆን ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩ። ምንም እንኳ ከቤተሰባችሁ ጋር እተዋወቅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ጥናት እስከጀመርኩበት ጊዜ ድረስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቼ ባላውቅም ለልጆቻችሁና ትክክለኛ ለሆነው ነገር ቆራጥ አቋም በመውሰድ ረገድ ላሳዩት ድፍረት የነበረኝ አድናቆት አልጠፋም ነበር። ማጥናትና እውቀት ማካበት ከጀመርኩ በኋላ ሁሉም ነገር ትርጉም ይሰጠኝ ጀመር። ሕይወቴን መልክ ለማስያዝ አንድ ዓመት ተኩል ፈጀብኝ። በመጨረሻም በ1975 ተጠመቅሁ።
እኛ ጨርሶ ሳናውቀው ባሕርያችን እንዴት ምሥክርነት ሊሰጥ እንደሚችል የሚገልጽ ጽሑፍ በወጣ ቁጥር የእናንተ ቤተሰብ ትዝ ይለኛል። የዘራነው ዘር የት ወይም መቼ ሥር እንደሚሰድ ሁልጊዜ ማወቅ ስለማንችል የመንግሥቱን ዘሮች አብዝቶ የመዝራትን አስፈላጊነት የሚገልጹ ጽሑፎች ሲወጡ ይህ በእርግጥ እውነት መሆኑን ከራሴ ተሞክሮ ተረድቻለሁ።
በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ስለሆናችሁና በዚያን ጊዜ ለምታምኑባቸው ነገሮች ታማኞች ስለነበራችሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። እናንተ ሳታውቁት አንድ ሰው እውነትን እንዲያገኝ ረድታችኋል። የእናንተም ሆነ የልጆቻችሁ ባሕርይ እንዲሁም የጸና እምነት የእውነት ብርሃን እንዲፈነጥቅ አድርጓል። አሁን ያላችሁበትን ሁኔታ ማወቅም ሆነ እናንተን ለማመስገን የምችልበት አጋጣሚ አገኛለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም። በድጋሚ አመሰግናችኋለሁ።
ክርስቲያናዊ ፍቅሬ ይድረሳችሁ፣
ኤል ኦ
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1958 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ። አሁን መታተም አቁሟል።