አበቦችን የሚስመው ወፍ
ብራዚላውያን ቤዣ ፍሎር ማለትም አበቦችን የሚስመው ወፍ ብለው ይጠሩታል። በአበቦች መካከል እየሄደ ከሚያደርገው ነገር አንጻር ይህ ስም በእንግሊዝኛ ሃሚንግበርድ በመባል ለሚታወቀው ወፍ በጣም ተስማሚ ነው። ሌሎች ተመልካቾች ደግሞ የወፉን ደማቅ ላባዎች በመመልከት እነዚህን ትናንሽ ፍጥረታት “ሕያው ፈርጦች” ወይም “የሚያማምሩ የቀስተ ደመና ስብርባሪዎች” በማለት የሚጠሯቸው ሲሆን የተለያዩ ዝርያዎቻቸውንም ቶጳዝዮኖች፣ የሚያብረቀርቅ ዕንቁዎች ወይም ነሐስ የመሰለ ጅራት ያላቸው ኮከቦች የሚሉትን በመሳሰሉ ውብ ስሞች ይጠሯቸዋል።
በጣም አስደናቂ የሆነው ቀለማቸው በተለይ በአንገታቸው ዙሪያና በወንዶቹ ሃመሮች ጉትያ ላይ በሚገኙት ልዩ ላባዎች ላይ ጎልቶ ይታያል። ላባዎቻቸው በአየር የተሞሉ የሕዋሳት ንብብሮች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ ሕዋሳት የብርሃን ሞገዶችን በማንጸባረቅ በሚልዮን እንደሚቆጠሩ የሳሙና አረፋዎች የቀስተ ደመና ቀለማት ይፈጥራሉ።
ክሪኤቸር ኮምፎርትስ የተባለው የጆን ዋርድ-ሃሪስ መጽሐፍ በምዕራባዊው ሰሜን አሜሪካ በብዛት ስለሚገኘው ቡናማ መልክ ስላለው ሩፈስ ሃሚንግበርድ እንደሚከተለው ይላል:- “አንገቱ በተለያዩ ቀለማት ባጌጡ ላባዎች ያሸበረቀ ነው፤ . . . ከጉንጮቹ በታች በመጀመር በአገጩ ሥር አልፈው አንገቱንና ደረቱን የሚሸፍኑት እነዚህ ላባዎች በሕፃናት አንገት ላይ ከሚታሰረው መሃረብ ጋር ይመሳሰላሉ። አንገቱን የሸፈኑት ላባዎች ቡፍ ሲሉ የሚፈጥሩት እይታ ቀልብን የሚስብ ነው፤ ወፉ ካለው መጠን በሁለት እጥፍ ገዝፎ እንዲታይ የሚያደርጉት ሲሆን ቃል በቃል በእሳት የተያያዘ ይመስላል።” ሩፈስ በፍጥነት ሲንቀሳቀስ አንገቱ ላይ ያሉት ላባዎች ሐምራዊ፣ አረንጓዴ ወይም አንዳንዴ ሁሉንም ዓይነት ቀለሞች ሊያሳዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከብርሃን ዘወር ሲል አንገቱ ሥር ያሉት ላባዎች ወዲያውኑ ደማቅ ወደ ሆነ ወይን ጠጅማ ጥቁር ቀለም ይለወጣሉ።
አስገራሚ የአየር ላይ ትርዒት
ሃሚንግበርድ በሚያሳየው አስገራሚ የሆነ የአየር ላይ ትርዒት የታወቀ ነው። ክንፉን በፍጥነት በማርገብገብ በአንድ አበባ ላይ ካንዣበበ በኋላ የአበባ ወለላውን ይመጥጣል። ከዚያም ይህ ከፍተኛ ኃይል ያለው አነስተኛ ፍጥረት ክንፉን በሰከንድ ከ50 እስከ 70፣ አንዳንዶች እንደሚሉትም እስከ 80 ጊዜ ድረስ በማርገብገብ ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደ ጎን ወይም ወደ ላይና ወደ ታች ሳይቀር በፍጥነት ሊንቀሳቀስ ይችላል! በሰዓት ከ50 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ሊጓዝና ከዚያም በድንገት ሊቆም እንደሚችል ይነገራል። ሃሚንግበርድ እነዚህን የመሳሰሉ አስደናቂ ችሎታዎች ሊኖሩት የቻሉት እንዴት ነው?
ምስጢሩ ያረፈው እጹብ ድንቅ በሆነው የሃሚንግበርድ የሰውነት ክፍል አሠራር ላይ ነው። ከደረቱ ጋር የተያያዙት ጠንካራ የሆኑ ጡንቻዎቹ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን የሰውነት ክብደት ይይዛሉ። ከትከሻው እስከ ክንፉ ጫፍ ድረስ የሚደርሱት ጥብቅ ክንፎቹ ወደ ላይም ሆነ ወደ ታች ሲያርገበግባቸው ኃይል እንዲያገኝ ያስችሉታል፤ ሌሎች ወፎች ግን ኃይል የሚያገኙት ክንፋቸው ወደ ታች በሚመለስበት ጊዜ ብቻ ነው። በመሆኑም ክንፉ ወደ ላይም ሆነ ወደ ታች ሲርገበገብ ወደ ላይ እንዲነሳም ሆነ ወደፊት እንዲጓዝ የሚያስችለው ሲሆን የትከሻው መጋጠሚያ ደግሞ በ180 ዲግሪ ለመሽከርከር ይረዳዋል። በመሆኑም ወፉ የሚያሳየው የአየር ላይ ትርዒት አስገራሚ ቢሆን ምንም አያስደንቅም!
ሃመሮች ጽናት የሚጠይቅ ፈተና ያልፉ ይሆን? ያለ ምንም ጥርጥር። ለምሳሌ ያህል በየዓመቱ አንዳንድ ሩፈስ ሃሚንግበርዶች ሜክሲኮ ከሚገኘው ቀዝቃዛ ቤታቸው ተነሥተው በሰሜን አቅጣጫ ከሦስት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ አላስካ ድረስ ርቀው ሊሄዱ ይችላሉ። ግዙፍ ተራሮች፣ ሰፋፊ የውኃ አካላትና መጥፎ የአየር ሁኔታ አይበግሯቸውም።
በቃኝ የማያውቅ በላተኛ
ሃሚንግበርድ ከአበቦች ጋር ያለው የፍቅር ግንኙነት ተሻጋሪ ርክበብናኝ (cross-pollination) እንዲካሄድ በመርዳት ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ያበረክታል። ይሁን እንጂ ወደ አበቦቹ የሚስባቸው ዋነኛ ነገር የአበባ ወለላ ነው። ከፍተኛ ጉልበቱን በኃይል ለመሙላት በየዕለቱ የክብደቱን ግማሽ (አንዳንዶች ሁለት እጥፍ ይላሉ) የሚያክል በካርቦሃይድሬት የበለጸገ የአበባ ወለላ መመገብ አለበት። አንድ ሰው በዚህ ስሌት መሠረት መብላት ቢያስፈልገው ኖሮ ምን እንደሚፈጠር መገመት ትችላለህ?
ከአብዛኞቹ ወፎች በተለየ ሃሚንግበርድ የሚባሉት ወፎች በእግራቸው የሚራመዱት ከስንት አንዴ ነው። ምግባቸውን የሚመገቡት በመብረር ላይ እንዳሉ ነው። ምንቃራቸው እንደየዘራቸው የተለያየ ርዝመትና ቅርጽ ያለው በመሆኑ ለእነሱ የሚስማሟቸውን የአባባ ዓይነቶች ይመርጣሉ። ዋነኛ ምግባቸው ከሆነው ከአበባ ወለላ በተጨማሪ የፍራፍሬ ዝንቦችን እየያዙና ከእፀዋት ላይ ትላትሎችን እየለቀሙ ይመገባሉ። ወፉ ከሚስማቸው አበቦች የአበባ ወለላ የሚያገኘው እንዴት ነው?
የእነዚህ ወፎች የመመገቢያ መሣሪያ ምላሳቸው ነው። ጆን ዋርድ-ሃሪስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የሃሚንግበርድ ምላስ ረዥም፣ ሰፊና መንታ ሲሆን ጫፉ ላይ ጥቂት ፀጉር አለው፤ በሁለት የተሸበለሉ ትልሞች የተከፈለ ሲሆን እነዚህም ጥቃቅን ቀዳዳዎችን በመፍጠር በተግባረ ርቂት (capillary action) አማካኝነት የአበባ ወለላ ተሸክመው በማስገባት እንዲዋጥ ያደርጋሉ።”
በመስኮትህ አካባቢ ሃሚንግበርዶችን የሚስብ ምግብ ብታስቀምጥ እነዚህ ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው አስደናቂ ፍጥረታት በፍጹም አይተህ አትጠግባቸውም። ይሁን እንጂ ለአንድ ሙሉ ወቅት ይህን ለማድረግ መዘጋጀት አለብህ፤ ምክንያቱም ቤተሰባቸውን በአቅራቢያው በሚገኝ ጎጆ ውስጥ ስለሚያሳድጉ ምግብ ለማግኘት ሙሉ በሙሉ የሚመኩት በአንተ ላይ ነው።
የተጓዳኝ ፍለጋ
በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የሃሚንግበርድ ዘሮች ፍቅረኞቻቸውን የሚስቡት በዜማቸው ነው። በጓቲማላ የሚገኘው አንገቱ ላይ የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሃሚንግበርድ የድምጽ አሰባበር እጅግ ግሩም የሆነ ሙዚቃዊ ቃና አለው። ጆሮው አካባቢ ነጣ ያለ ቀለም ያለው ሃሚንግበርድ ሙዚቃ ድምጽ ደግሞ “አንዲት ትንሽ የብር ደውል ከምታሰማው ደስ የሚል የድምጽ ቃና” ጋር ይመሳሰላል። ይሁንና አብዛኞቹ ደስ የሚል የድምጽ ቅላጼ ያላቸው አይደሉም። ጥቂት ሸካራ የሆኑ ኖታዎችን ይደጋግማሉ ወይም በሌላ ጊዜያት ምንቃራቸውን ገጥመው ኩልኩልታቸውን በመንፋት ያዜማሉ።
አንዳንድ ሃመሮች ተጓዳኝ ለማግኘት ሲሉ አስገራሚ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ። በተለይ ሩፈስ ሃሚንግበርድ ከከፍተኛ ርቀት በመነሳት ቁልቁል ተምዘግዝጎ ይወርድና የምትመለከተው ሴት ወፍ አናት አካባቢ ሲደርስ ወደ ላይ እጥፍ በማለት የመቁያ ዓይነት ቅርጽ ይሰራል። ከዚያም በታጠፈበት አካባቢ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ካለ በኋላ መጀመሪያ ወደነበረበት ከፍተኛ ርቀት ይመለሳል አሊያም ከአዲሲቷ ተጓዳኙ ጋር ይበርራል። ይህን መሳዩን ትርዒት በሚያሳይበት ጊዜ ክንፉ በሰከንድ ሁለት መቶ ጊዜ ያክል ሊርገበገብ ይችላል!
ውብ ጎጆዎች
አንድ ተመልካች የሃሚንግበርድ ጎጆ “በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ውብ መኖሪያዎች ጎን እንደሚፈረጅ” ተናግረዋል። ጆን ዋርድ-ሃሪስ ለአንድ የንቁ! ዘጋቢ ያገኙትን ጎጆ አሳይተውታል። የጎን ርዝመቱ 4.5 ሴንቲ ሜትር ሲሆን የውስጥ ቁመቱ ደግሞ አንድ ሴንቲ ሜትር ነበር፤ የጎጆው አሠራር እነዚያ ንብ የሚያካክሉት ጫጩቶች እያደጉ ሲሄዱ የሞቀው መኖሪያቸው ሊሰፋ በሚችልበት መንገድ ነው። ለስላሳ ከሆኑ ተክሎች የተሠራ የአሻንጉሊት ኩባያ የሚመስለውን የወፍ ጎጆ በእጆችህ መዳፍ መያዙ በጣም የሚያስደስት ነው። በሸረሪት ድሮች በተሰፉ ውብ ላባዎች የተሠሩ ጎጆዎችም ይገኛሉ። በውስጡ “እኩል መጠን ያላቸውን ሉሎች የሚመስሉ” እንደ በረዶ የነጡ ሁለት ወይም ሦስት እንቁላሎችን ይጥላሉ።
እናትየው ጫጩቶቿን ለመመገብ በጠባቡ ጉሮሯቸው ውስጥ ምንቃሯን በመክተት አስፈላጊውን ምግብ ታጎርሳቸዋለች። አብዛኛውን ጊዜ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ጫጩቶቹ በደመ ነፍስ ጎጆአቸውን ጥለው በመብረርና ራሳቸውን በመመገብ እድገታቸውን ከቀጠሉ በኋላ ተፈጥሮ በጣም ቀዝቃዛ ያልሆነ የክረምት አየር ወዳለበት ቦታ እንዲፈልሱ ያደርጋቸዋል።
ደፋር
ከሃሚንግበርድ አስደናቂ ባሕርያት አንዱ ደፋር መሆኑ ነው። ይህን ሁኔታ የመመገቢያ ጣቢያቸው ወይም ክልላቸው በሚደፈርበት ጊዜ ከሚያደርጉት ነገር ለመመልከት ይቻላል። በደቡብ አሜሪካ የወይን ጠጅ ቀለም ጉትያ ያላቸው ሁለት ሃሚንግበርዶች ጎጆአቸው ያለበትን አካባቢ በወረረ ንስር ዙሪያ በድፍረት ሲያንዣብቡና ካስፈለገም ያንን ጎልያድ ለመግጠም ሲጋበዙ ታይተዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ወፎች እባቦችን፣ እንቁራሪቶችን፣ የሸረሪት ድሮችን፣ እሾሃማ አበቦችንና ወፎችን የሚሰበስቡ ሰዎችን በመሳሰሉ ጠላቶቻቸው ሕይወታቸው ይቀጠፋል።
ይሁንና በርካታ ሰዎች የሚወዳጁአቸው ሲሆን እነዚህ ወፎች ዓላማ ያለውን ሕይወታቸውን ለመጀመር ተመልሰው የሚመጡበትን እያንዳንዱን ወቅት በጉጉት ይጠባበቃሉ። በአትክልት ቦታህ ያሉትን አበቦች ለመሳም ከመረጡ እነዚህን ውብ የፍጥረት ፈርጦች በቅርብ ከማጥናት ይህ ነው የማይባል ደስታ ታገኛለህ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ሃሚንግበርድን የሚመለከቱ አንዳንድ መረጃዎች
• ሃሚንግበርድ 320 ዝርያዎች ያሉት ሲሆን በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙት የአእዋፍ ቤተሰቦች ውስጥ በብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል
• ከአእዋፍ ሁሉ የመጨረሻዎቹ ትንሽ ፍጥረታት እነሱ ናቸው:- በኩባ የምትገኘው ንብ ሃሚንግበርድ ተብላ የምትጠራው ወፍ ከጭራዋ ጫፍ አንስቶ እስከ ምንቃሯ ጫፍ ድረስ ያላት ርዝመት 6 ሴንቲ ሜትር ነው
• ትልቁ ሃሚንግበርድ 22 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን በደቡብ አሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል ከኢኳዶር አንስቶ እስከ ቺሊ ድረስ ይገኛል
• ከዋነኛ የመኖሪያ ቦታዎቻቸው መካከል በደቡብ አሜሪካ በምድር ወገብ ክልል ከባሕር ወለል አንስቶ እስከ 4,500 ሜትር ከፍታ ድረስ ያለው ክልል እንዲሁም በካረቢያንና በፓሲፊክ ያሉ አንዳንድ ደሴቶች ይገኙበታል
• በበጋ ወራት በሰሜን አቅጣጫ አላስካ ድረስ የሚገኙ ሲሆን በደቡብ አቅጣጫ ደግሞ እስከ ቲየራ ዴል ፉጎ ድረስ ይገኛሉ
• በአንድ ወቅት በአውሮፓ የሴቶችን ባርኔጣ ለማስጌጥ ሲባል በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሃሚንግበርዶች የተገደሉ ሲሆን ይህም አንዳንድ ዝርያዎች ከምድር ገጽ እንዲጠፉ ሳያደርግ አልቀረም
[ሥዕሎች]
ጃያንት (እድገቱን የጨረሰ)
ንብ ሃሚንግበርድ (እድገቱን የጨረሰ)
[ምንጮች]
© C. H. Greenewalt/VIREO
© 1990 Robert A. Tyrrell
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩፈስ ሃሚንግበርድ
[ምንጭ]
THE HUMMINGBIRD SOCIETY/Newark Delaware USA
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንብ ሃሚንግበርድ (ጎላ ብሎ ሲታይ)
[ምንጭ]
© 1990 Robert A. Tyrrell
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንቲሊያን ማንጎ
[ምንጭ]
© 1990 Robert A. Tyrrell
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀይማ ደረት ያለው ሃሚንግበርድ
[ምንጭ]
© 1990 Robert A. Tyrrell
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አናስ (ጎላ ብሎ ሲታይ)
[ምንጭ]
Patricia Meacham/Cornell Laboratory of Ornithology
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ረቢ-ትረውትድ ሃሚንግበርድና ጫጩቶቿ