ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ይበልጥ ተግባቢ መሆን የምችለው እንዴት ነው?
“ከሰዎች ጋር ሞቅ ያለ ጭውውት ያደረግኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። አንድ ነገር ብናገር ሰው ሁሉ የሚርቀኝ ይመስለኛል። እናቴ በጣም ዓይን አፋር ነች። እኔም ዓይን አፋር የሆንኩት ለዚህ ይመስለኛል።”—አርቲ
አንዳንድ ጊዜ ከዓይን አፋርነት ቀንበር ተላቅቀህ ይበልጥ ተጫዋችና ተግባቢ መሆን ትመኛለህ? ባለፈው እትም በዚህ ዓምድ ሥር የወጣው ጽሑፍ እንዳመለከተው ዓይን አፋርነት የተለመደ ባሕርይ ነው።a ስለዚህ ዝምተኛ፣ ጭምት ወይም ቁጥብ ብትሆን ምንም ስህተት የለበትም። ሆኖም ከልክ ያለፈ ዓይን አፋርነት ችግር ሊፈጥር ይችላል። ሌላው ቢቀር ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዳትመሠርት ደንቃራ ሊሆንብህ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች በርከት ባሉ ሰዎች መካከል በምትሆንበት ጊዜ ጭንቅ ጥብብ ሊልህ ይችላል።
ዐዋቂዎች እንኳ ሳይቀሩ ዓይን አፋርነት ያጠቃቸዋል። ቤሪb በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም እንኳ በርከት ባሉ ሰዎች መካከል ሲሆን ዝም ማለት ይመርጣል። “ትርጉም ያለው ነገር የመናገር ችሎታ እንዳለኝ ሆኖ አይሰማኝም” ሲል ሐቁን ሳይሸሽግ በግልጽ ተናግሯል። ሚስቱ ዳያንም እንደዚሁ ተመሳሳይ ችግር አለባት። ለችግሯ መፍትሔ አድርጋ የተጠቀመችበት ዘዴ ምንድን ነው? “ተግባቢ የሆኑ ሰዎች የጨዋታውን መድረክ ስለሚይዙት ከእነርሱ ጋር መሆን ያስደስተኛል” ብላለች። አንተ ራስህ ይበልጥ ተግባቢ መሆን የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
ራስህን ከማንኳሰስ ተቆጠብ
በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ራስህ ያለህን አመለካከት መለስ ብለህ መመርመር ሊያስፈልግህ ይችላል። የሚወደኝ ሰው የለም ወይም ደግሞ ምንም እርባና ያለው ነገር መናገር አልችልም እያልክ ዘወትር ራስህን ታንኳስሳለህ? ስለ ራስህ አሉታዊ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ተግባቢ እንዳትሆን እንቅፋት ከመፍጠር በቀር የሚፈይድልህ ነገር አይኖርም። ኢየሱስም ቢሆን “ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” አለ እንጂ ከአንተ ይልቅ ባልንጀራህን ውደድ አላለም! (ማቴዎስ 19:19) ስለዚህ ራስህን ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ መውደድህ ትክክልና ተገቢ ነው። ሌሎችን ለመቅረብ የሚያስችል በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል።
ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከት መንፈስ የሚያጠቃህ ከሆነ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶችc በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን “ራሴን የማልወደው ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን 12ኛውን ምዕራፍ ማንበቡ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኘው ሐሳብ በአንተነትህ ልታበረክተው የምትችለው ብዙ ነገር እንዳለህ እንድታስተውል ሊረዳህ ይችላል። ሌላው ቢቀር ክርስቲያን መሆንህ ራሱ አምላክ በአንተ ላይ ያየው ዋጋማ የሆነ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ነው! እንዲያውም ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል።—ዮሐንስ 6:44
ለሌሎች ሰዎች ጥቅም አስብ
ምሳሌ 18:1 “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል” ሲል ያስጠነቅቃል። አዎን፣ ራስህን የምታገልል ከሆነ ለራስህ ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠትህ አይቀርም። ፊልጵስዩስ 2:4 ‘ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚጠቅመውን ነገር እንድናስብ’ ያበረታታናል። ስለ ሌሎች ጥቅምና ፍላጎት በምታስብበት ጊዜ ስለ ራስህ ብዙም አትጨነቅም። በተጨማሪም ስለ ሌሎች ይበልጥ ባሰብክ መጠን ቅድሚያውን ወስደህ ከሰዎቹ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ትገፋፋለህ።
ለምሳሌ ያህል ወዳጃዊ ስሜትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ለመሆን የበቃችውን ልድያን እንውሰድ። የሐዋርያው ጳውሎስን ቃል ሰምታ ከተጠመቀች በኋላ ጳውሎስንና የሥራ አጋሮቹን “በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፣ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ” ብላ እንደለመነቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ሥራ 16:11-15) ልድያ አዲስ አማኝ የነበረች ቢሆንም እንኳ ከእነዚህ ወንድሞች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ ቅድሚያውን ወስዳለች። እንዲህ በማድረጓም ብዙ በረከት እንዳገኘች ጥርጥር የለውም። ጳውሎስና ሲላስ ከወኅኒ ከወጡ በኋላ ወዴት ነበር የሄዱት? ተመልሰው ወደ ልድያ ቤት መሄዳቸው ትኩረት የሚስብ ነው!—ሥራ 16:35-40
በተመሳሳይም አብዛኞቹ ሰዎች ትኩረት እንደሰጠሃቸው ሲሰማቸው ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። ይህን ለማድረግ ምን እርምጃዎችን ልትወስድ ትችላለህ? ከዚህ ቀጥሎ ጥቂት ጠቃሚ ሐሳቦች ቀርበዋል።
● በትንሹ ጀምር። ተግባቢ መሆን ማለት ከልክ በላይ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ መጠመድ ወይም ዋና ተዋናይ ለመሆን መሞከር ማለት አይደለም። በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ በማነጋገር ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ለመጫወት ሞክር። በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በተገኘህ ቁጥር ቢያንስ ቢያንስ ከአንድ ሰው ጋር ውይይት ለመክፈት ግብ ልታወጣ ትችላለህ። በፈገግታ ለመቅረብ ሞክር። የሰውየውን ዓይን እያየህ የመጫወት ልማድ አዳብር።
● ቅድሚያውን ወስደህ የዝምታን መጋረጃ ግፈፍ። ‘እንዴት?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለሌሎች ከልብህ የምታስብ ከሆነ ብዙውን ጊዜ የውይይት ርዕስ መክፈቱ አስቸጋሪ አይሆንብህም። በስፔይን የሚኖር ሆርሄ የተባለ አንድ ወጣት “ሰዎችን እንዲሁ ስለ ደህንነታቸው መጠየቅ ወይም ደግሞ ስለ ሥራቸው መጠየቅ ይበልጥ እንድታውቋቸው ሊረዳችሁ ይችላል” ሲል ተናግሯል። ፍሬድ የተባለ ወጣት “ምን እንደምትሏቸው ግራ ከገባችሁ አንዳንድ ጥያቄዎች ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ” ሲል የበኩሉን ሐሳብ ሰጥቷል። እርግጥ ነው፣ እንዲህም ሲባል ግን የፖሊስ ዓይነት ጥያቄ ትጠይቃቸዋለህ ማለት አይደለም። ግለሰቡ ለምታቀርብለት ጥያቄ መልስ መስጠት እንዳልፈለገ ሆኖ ከተሰማህ ስለ ራስህ አንዳንድ ነገር ልትነግረው ትችላለህ።
ወጣት ልጅ ያላት ሜሪ የተባለች አንዲት ሴት “ሰዎች ዘና እንዲሉ ለማድረግ ከሁሉ የተሻለ ዘዴ ሆኖ ያገኘሁት ስለ ራሳቸው እንዲናገሩ ማድረግ ነው” ብላለች። “ሰዎችን በአለባበሳቸው ወይም በሌላ ነገር ማሞገሱ ጠቃሚ ነው። እንደሚወደዱ ሆኖ እንዲሰማቸው ታደርጓቸዋላችሁ” ስትል ኬት የተባለች ወጣት አክላ ተናግራለች። እርግጥ ነው፣ አድናቆትህ ከልብ የመነጨ መሆን ይገባዋል እንጂ ከንቱ ሽንገላ መሆን የለበትም። (1 ተሰሎንቄ 2:5) አብዛኞቹ ሰዎች አሳቢነት የተሞላባቸው ከልብ የመነጩና ያማሩ ቃላት ሲነገሯቸው አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።—ምሳሌ 16:24
● ጥሩ አድማጭ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን” ይላል። (ያዕቆብ 1:19) ጭውውት በሰዎች መካከል የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ እንጂ አንድ ሰው ብቻ የሚያቀነቅንበት መድረክ አይደለም። ስለዚህ መናገር የሚያሳፍርህ ከሆነ ይህ ራሱ ሊጠቅምህ የሚችልበት መንገድ አለ! ሰዎች በደንብ የሚያዳምጣቸው ሰው ሲያገኙ ደስ ይላቸዋል።
● ሌሎች በሚያደርጉት ውይይት ውስጥ ተካፈል። ከተለያዩ ሰዎች ጋር በግል ጥሩ ውይይት የማድረግ ችሎታ ካዳበርክ በኋላ በቡድን በሚደረጉ ውይይቶች ለመካፈል ጥረት አድርግ። አሁንም ቢሆን ይህን ችሎታ ለማዳበር ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። አንዳንድ ጊዜ ቀደም ብሎ በተጀመረ ውይይት መካከል መግባት በቡድን በሚደረግ ውይይት ውስጥ ለመካፈል የሚያስችል ቀላል ዘዴ ሊሆን ይችላል። እርግጥ በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ጥንቃቄ ማድረግና ሥርዓታማ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ሰዎች በሚያደርጉት የግል ውይይት ውስጥ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ብሎ መግባት ተገቢ አይደለም። ሰዎች በቡድን ሆነው በአንድ ተራ ጉዳይ ላይ በሚወያዩበት ጊዜ ግን አንተም በውይይቱ ለመካፈል ጥረት አድርግ። ዘዴኛ ሁን፤ እየተናገረ ያለን ሰው ለማቋረጥና የውይይቱን መድረክ ለመቆጣጠር አትሞክር። ለጥቂት ጊዜ ዝም ብለህ አዳምጥ። ከዚያ በኋላ የመናገር ዕድሉን ስታገኝ ጥቂት ሐሳቦች መስጠት ትችላለህ።
● ከራስህ ፍጽምናን አትጠብቅ። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ያልሆነ ነገር እናገራለሁ ብለው ይፈራሉ። በኢጣሊያ የምትኖር አንዲት ኤሊዛ የተባለች ልጅ “አንድ ነገር ብናገር ሌሎችን ቅር ያሰኝ ይሆናል ብዬ ሁልጊዜ እጨነቅ ነበር” ስትል ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ ተናግራለች። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም አለፍጽምና እንዳለብን ስለሚያሳስበን ፈጽሞ እንከን የማይወጣለት ነገር መናገር አንችልም። (ሮሜ 3:23፤ ከያዕቆብ 3:2 ጋር አወዳድር።) ኤሊዛ “ጓደኞቼ እንደ መሆናቸው መጠን ያልሆነ ነገር ብናገር አክብደው እንደማይመለከቱት ተገንዝቤያለሁ” ብላለች።
● ተጫዋችና ሳቂታ ሁን። ሳያስቡት ያልሆነ ነገር መናገር እንደሚያሳፍር የታወቀ ነው። ሆኖም ፍሬድ እንዳለው “ዘና ካላችሁና በራሳችሁ ከሳቃችሁ ነገሩ ወዲያው ይረሳል። ከተረበሻችሁ፣ ከተበሳጫችሁ ወይም ከተጨነቃችሁ ግን ትንሿ ኩይሳ ተራራ ሆና ትታያችኋለች።”
● ታገሥ። ሁሉም ሰው ፈጣን ምላሽ ይሰጣል ብለህ አትጠብቅ። በመካከላችሁ ለጥቂት ጊዜ ዝምታ መስፈኑ ሰውየው እንዳልወደደህ አድርገህ ለመደምደም ወይም ለመናገር ከምታደርገው ጥረት ለመታቀብ ምክንያት ሊሆንህ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በሐሳብ ሊዋጡ ይችላሉ። ወይም ደግሞ እንዳንተው ዓይን አፋር ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ግለሰቡ ከአንተ ጋር እስኪላመድ ድረስ ጥቂት ጊዜ ብትሰጠው የተሻለ ይሆናል።
● ከዐዋቂዎች ጋር ለመጫወት ሞክር። አንዳንድ ጊዜ ዐዋቂዎች በተለይ ደግሞ የበሰሉ ክርስቲያኖች ከዓይን አፋርነት ጋር የሚታገሉ ወጣቶች የሚሰማቸውን ስሜትና ችግር ይረዳሉ። ስለዚህ ከአንድ ትልቅ ሰው ጋር ውይይት መክፈት ሊያስፈራህ አይገባም። ኬት “ዐዋቂ የሆኑ ሰዎች እንደ እኩዮቼ እንደማይተቹኝ፣ እንደማያሾፉብኝና እንደማያሳፍሩኝ ስለማውቅ ከእነሱ ጋር ስሆን ነፃነት ይሰማኛል” ብላለች።
በፍቅር መገፋፋት
እነዚህ ሐሳቦች ጥሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቢሆንም እንኳ ዓይን አፋርነትን ማሸነፍ የሚያስችል ቁልጭ ያለ ደንብ ማውጣት አይቻልም። ልዩ ብልሃት ወይም ደንብ በመከተል በጊዜ ሂደት የሚፈታ ችግር አይደለም። ዓይን አፋርነትን ለማሸነፍ ቁልፉ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ’ ነው። (ያዕቆብ 2:8) አዎን፣ ለሌሎች ሰዎች በተለይ ደግሞ ለክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ አሳቢ ሁን። (ገላትያ 6:10) በልብህ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር ካለ ፍርሃትንና ጭንቀትን በማሸነፍ ከሌሎች ጋር ዝምድና ለመፍጠር ጥረት ታደርጋለህ። ኢየሱስ እንዳለው “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።”—ማቴዎስ 12:34
መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ቤሪ “ሌሎች ሰዎችን ይበልጥ ባወቅኳቸው መጠን ከእነሱ ጋር መጫወቱ የዚያኑ ያህል ይቀለኛል” ሲል ተናግሯል። በሌላ አባባል ተግባቢ ለመሆን በጣርክ መጠን የዚያኑ ያህል ሁኔታው እየቀለለህ ይሄዳል። በዚህ መንገድ አዳዲስ ጓደኞች እያፈራህ ስትሄድና በሌሎች ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዳገኘህ ሲሰማህ የኋላ ኋላ የምታገኘው ውጤት ቢደከምለት የማያስቆጭ እንደሆነ መገንዘብህ አይቀርም!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በኅዳር 1999 እትም ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ይበልጥ ተግባቢ መሆን የማልችለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅድሚያውን በመውሰድ ሌሎች በሚያካሂዱት ጨዋታ ውስጥ ለመካፈል ጥረት አድርግ!