ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ይበልጥ ተግባቢ መሆን የማልችለው ለምንድን ነው?
“ዓይን አፋርነት የሚያሽመደምድ ባሕርይ ነው። ተብትቦ የሚይዝ ፍርሃት በመሆኑ ታግለህ ልታሸንፈው የሚገባ ራሱን የቻለ ችግር ነው።”—ሪቻርድa
“ከልጅነቴ ጀምሮ የዓይን አፋርነት ችግር ነበረብኝ። እኖር የነበረው በራሴ ዓለም ውስጥ ነበር።”—የ18 ዓመቷ ኤሊዛቤት
‘ችግሬ ምንድን ነው? ይበልጥ ተግባቢ መሆን የማልችለው ለምንድን ነው?’ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ሪቻርድ አንተም ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትገናኝ የመደናገጥ ወይም የጭንቀት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። በአንድ ባለ ሥልጣን ፊት በምትቀርብበት ጊዜ ትርበተበት ይሆናል። ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች ስለ እኔ ምን ይሰማቸው ይሆን እያልክ በጣም ስለምትጨነቅ ስሜትህን ከመግለጽ ወይም አስተያየት ከመስጠት ትቆጠብ ይሆናል። “በደንብ የማላውቃቸውን ሰዎች ቀርቤ ማነጋገር በጣም ያስፈራኛል” በማለት ወጣቷ ትሬሲ ተናግራለች።
ይህን ስሜት የሚፈጥረው ምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ስሜት ለማሸነፍ የሚረዳው የመጀመሪያ እርምጃ ችግሩን በሚገባ መረዳት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 1:5) አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ከሰዎች ጋር በምሆንበት ጊዜ ለምን እንደምረበሽ ፈጽሞ አይገባኝም ነበር። አሁን ግን ችግሬ ምን እንደሆነ በትክክል ያወቅኩ በመሆኑ ችግሩን ከሥረ መሠረቱ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ እችላለሁ።” ስለዚህ አንዳንድ ወጣቶች ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚቸግራቸው ለምን እንደሆነ እስቲ አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት።
የዓይን አፋርነት ችግር
ሰዎች ከሌሎች ጋር በቀላሉ እንዳይግባቡ እንቅፋት የሚሆነው ዋነኛው ምክንያት ዓይን አፋርነት ሳይሆን አይቀርም። ከሰዎች ጋር በቀላሉ የሚግባባ አንድ ወጣት የተለያዩ ወዳጆችን ሊያፈራ ሲችል ዓይን አፋርና ቁጥብ የሆነ ወጣት ግን ብቸኝነት ሊሰማውና ራሱን ሊያገልል ይችላል። “ከልጅነቴ ጀምሮ የዓይን አፋርነት ችግር ነበረብኝ” በማለት የ18 ዓመቷ ኤሊዛቤት ትናገራለች። “እኖር የነበረው በራሴ ዓለም ውስጥ ነበር።” ዳያን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል በጀመረችበት ዓመት የገጠማትን ጭንቀት ታስታውሳለች። “ትኩረት ውስጥ መግባት አልፈልግም ነበር። አንድ አስተማሪዬ በሰዎች ዘንድ ታዋቂ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ ነው ብለን እንደምናምን የሚያሳይ ነጥብ እንድንሰጥ ጠየቀችን። የምንሰጠው ነጥብ ከዜሮ እስከ አምስት ነበር። ዜሮ ከጻፍን ፈጽሞ አስፈላጊ አይደለም ማለት ሲሆን አምስት ከጻፍን ደግሞ አስፈላጊ ነው ማለት ነበር። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ታዋቂ የሆኑት ልጃገረዶች በሙሉ አምስት ነጥብ ሰጡ። እኔ የሰጠሁት ነጥብ ግን ዜሮ ነበር። ዓይን አፋር የሆንኩት በሌሎች ዘንድ ታዋቂ መሆን ያስፈራኝ ስለነበረ ነው። ሌሎች አይወዱኝ ይሆናል የሚለው ስጋት በሌሎች ዘንድ ከመታወቅ ወይም በእነርሱ ዓይን ውስጥ ከመግባት እንድትታቀብ ያደርግሃል።”
እርግጥ ነው፣ በመጠኑ ዓይን አፋር መሆን መጥፎ ነው ማለት አይደለም። አቅማችንን እንድናውቅ የሚረዳን የልከኝነት ባሕርይ ከዓይን አፋርነት ጋር የቅርብ ዝምድና አለው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ከአምላካችን ጋር ስንጓዝ ልከኞች እንድንሆን’ ታዝዘናል። (ሚክያስ 6:8 NW) ሰዎች የበላይ ለመሆን ከሚፈልግ፣ የኃይለኝነት ባሕርይ ካለው ወይም ከሌሎች ብዙ ከሚጠብቅ ሰው ይልቅ ልከኛ ወይም ሌላው ቀርቶ በተወሰነ መጠን ዓይን አፋር የሆነን ሰው መቅረብ ይቀላቸዋል። እንዲሁም ‘ለመናገር ጊዜ እንዳለው’ ሁሉ ‘ዝም ለማለትም’ ጊዜ አለው። (መክብብ 3:7) ዓይን አፋር የሆኑ ሰዎች ዝም ለማለት ብዙም አይቸገሩም። ‘ለመስማት የፈጠኑ ለመናገርም የዘገዩ’ በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ በሌሎች ዘንድ በጥሩ አድማጭነታቸው ይወደሳሉ።—ያዕቆብ 1:19
ሆኖም አንድ ወጣት ወይም አንዲት ወጣት አብዛኛውን ጊዜ ዝም የሚሉ ወይም ዓይን አፋርነት የሚያጠቃቸው ከሆኑ ወዳጅ ለማፍራት ይቸገራሉ። እንዲሁም በአንዳንድ ወቅቶች መጠኑን ያለፈ የዓይን አፋርነት ጠባይ አንድ ጸሐፊ እንደተናገሩት “ከልክ በላይ በመጨነቅ ራስን ወደ መደበቅ” ማለትም ራስን ከኅብረተሰቡ ወደ ማግለል ሊያደርስ ይችላል።—ምሳሌ 18:1
ዓይን አፋርነት—የተለመደ ችግር
የዓይን አፋርነት ችግር ካለብህ ይህ የተለመደ ችግር መሆኑን አትዘንጋ። በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በኮሌጅ ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት “82 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በአንድ ወቅት ላይ የዓይን አፋርነት ችግር እንደነበረባቸው ተናግረዋል።” (አዶለሰንስ፣ በኢስትዉድ አትዎተር የተዘጋጀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳን ሳይቀር የዓይን አፋርነት ችግር የነበረባቸው ሰዎች ነበሩ። ሙሴና ጢሞቴዎስን የመሰሉ ጉልህ ቦታ የነበራቸው ሰዎች ከዓይን አፋርነት ጋር መታገል አስፈልጓቸው የነበረ ይመስላል።—ዘጸአት 3:11, 13፤ 4:1, 10, 13፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:6-8
የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረውን የሳኦልን ታሪክ ተመልከት። ሳኦል ደፋር ሰው ነበር። የአባቱ ከብቶች ጠፍተው በነበረ ጊዜ ሳኦል በድፍረት ከብቶቹን ለመፈለግ የተነሳ ሰው ነበር። (1 ሳሙኤል 9:3, 4) ይሁን እንጂ የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ ወዲያው በዓይን አፋርነት ስሜት ተዋጠ። ሳኦል በደስታ ስሜት ከሚያወካው ሕዝብ ጋር ከመቀላቀል ይልቅ በዕቃዎች መካከል ተሸሸገ!—1 ሳሙኤል 10:20-24
ሳኦል በራስ የመተማመን ስሜቱ እንደ ጉም በኖ መጥፋቱ ሊያስገርም ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ማራኪና መልከ ቀና ወጣት እንደነበረ ይገልጻል። “ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻው . . . ዘለግ ያለ ነበረ”! (1 ሳሙኤል 9:2) ከዚህም በላይ የአምላክ ነቢይ ይሖዋ የንግሥና ዘመኑን እንደሚባርክለት ለሳኦል አረጋግጦለት ነበር። (1 ሳሙኤል 9:17, 20) እንዲህም ሆኖ ሳኦል በራስ መተማመን አልቻለም ነበር። ንጉሥ እንደሚሆን በተነገረው ጊዜ “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ?” በማለት በትሕትና መልሷል።—1 ሳሙኤል 9:21
ሳኦል በራስ የመተማመን ስሜቱን አጥቶ ከነበረ አንተም አልፎ አልፎ በራስ የመተማመን መንፈስ ቢጎድልህ ይሄን ያህል የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ወጣት እንደመሆንህ መጠን ያለህበት የዕድሜ ክልል ሰውነትህ ፈጣን ለውጥ የሚያደርግበት ወቅት ነው። እንደ አዋቂ ሆነህ ነገሮችን እንዴት ማከናወን እንደምትችል ገና እየተማርክ ነው። ስለዚህ አልፎ አልፎ በተወሰነ ደረጃ የዓይን አፋርነት ወይም የፍርሃት ስሜት ቢሰማህ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ዶክተር ዴቪድ ኤልካይንድ ፓረንትስ በተባለ መጽሔት ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “አብዛኞቹ ወጣቶች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ፣ እንደ እኔ ግምት የራሳቸውን ምናባዊ ተመልካች በመፍጠር ማለትም ሌሎች ይመለከቱናል የሚል እምነት በማዳበር ስለ አካላዊ ሁኔታቸውና ስለእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ከልክ በላይ ስለሚጨነቁ በዓይን አፋርነት ስሜት የሚዋጡበት ወቅት ይኖራል።”
ብዙውን ጊዜ እኩዮቻቸው ለእነርሱ የሚኖራቸው አመለካከት በመልክ ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ብዙዎቹ ወጣቶች ስለ መልካቸው ይጨነቃሉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 10:7 ጋር አወዳድር፤ የ1980 ትርጉም) ሆኖም ስለ ራስ መልክ ከሚገባው በላይ መጨነቅ ጎጂ ነው። በፈረንሳይ የምትኖረው ሊልያ የተባለች አንዲት ወጣት በዚህ ረገድ ያሳለፈችውን ተሞክሮ መለስ ብላ በማሰብ እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በርካታ ወጣቶች ያለባቸው ዓይነት ችግር ነበረብኝ። ፊቴ ላይ ብጉር ይወጣብኝ ነበር! መልካችሁ ስለሚያስጨንቃችሁ ሌሎች ሰዎች ፊት ለመቅረብ አትደፍሩም።”
አዝዋሪት
ብዙውን ጊዜ ዓይን አፋር የሆኑ ሰዎች ያለባቸውን ችግር ሌሎች ስለማይረዱላቸው ራሳቸውን እንዲያገልሉ በሚያደርግ አዝዋሪት ውስጥ በቀላሉ ይገባሉ። አዶለሰንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ዓይን አፋር የሆኑ ወጣቶች ሌሎች በጥሩ ዓይን ስለማይመለከቷቸው ወዳጅ በማፍራት ረገድ ችግር ይገጥማቸዋል። ብዙውን ጊዜ ዓይን አፋር የሆኑ ሰዎች ቁጥቦች፣ የሚሰላቹ፣ ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው፣ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣ ወዳጃዊ ስሜት የሌላቸውና ሰው የሚጠሉ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ሌሎች በዚህ መንገድ ሲመለከቷቸው ይበልጥ ራሳቸውን ያገልላሉ፣ የብቸኝነት ስሜትና የመንፈስ ጭንቀትም ያድርባቸዋል።” ይህ ሁኔታ ይበልጥ ዓይን አፋር እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው ትምክህተኞች ወይም ትዕቢተኞች እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸው ሰዎች ለእነርሱ ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የበለጠ ይጠናከራል።
እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ‘ለዓለም በቲያትር መድረክ ላይ እንዳለህ ሆነህ የምትታይ’ በመሆኑ በሌሎች ላይ ስለምታሳድረው ስሜት ማሰብ ይኖርብሃል። (1 ቆሮንቶስ 4:9 NW) ከአንድ ሰው ጋር ስታወራ ዓይን ዓይኑን መመልከት ይቸግርሃል? ጠቅላላ ሁኔታህና ፊትህ ላይ የሚነበበው ስሜት እያነጋገረህ ያለው ሰው እየረበሸህ እንዳለ ሆኖ እንዲሰማው የሚያደርግ ነው? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚታይብህ ከሆነ ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሊረዱህና ሊያገልሉህ እንደሚችሉ ማወቅ ይኖርብሃል። ይህ ወዳጅ ማፍራት እንዳትችል ይበልጥ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል።
ሌሎች ምክንያቶች
ሌላው የተለመደ ችግር ደግሞ እሳሳት ይሆናል የሚለው ፍርሃት ነው። ከዚህ ቀደም ሠርተህ የማታውቀውን አንድ አዲስ ነገር በምታከናውንበት ወቅት በተወሰነ መጠን ስጋት ቢያድርብህ ምንም አያስደንቅም። ሆኖም አንዳንድ ወጣቶች በዚህ ረገድ ከመጠን ያለፈ ስጋት ያድርባቸዋል። ጌይል ወጣት በነበረችበት ወቅት ብዙ ሰው ባለበት ቦታ ስትሆን በጣም ትፈራ ነበር። እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በክፍል ውስጥ ሐሳብ አልሰጥም ነበር። በዚህም የተነሳ ወላጆቼ ‘እጅዋን አታወጣም። ሐሳቧን ገልጣ አትናገርም’ የሚሉትን የመሰሉ በርካታ እሮሮዎች ያለ ማቋረጥ ይደርሳቸው ነበር። እንደዚያ ማድረጉ በጣም የሚረብሸኝና ውጥረት ውስጥ የሚከተኝ ነገር ነበር። አሁንም ቢሆን እንደዚያ ማድረጉ ይከብደኛል።” እሳሳት ይሆናል የሚለው ፍርሃት ሙሉ በሙሉ ሊያሽመደምድ ይችላል። “እንዳልሳሳት እፈራለሁ” በማለት ፒተር የተባለ አንድ ወጣት ተናግሯል። “ማንኛውንም ነገር ሳደርግ ስጋት ያድርብኛል።” የእድሜ እኩዮች ያላንዳች ርኅራኄ የሚሰነዝሩት ፌዝና ትችት አንድ ሰው የሚሰማውን ፍርሃት ሊያባብስበትና በራስ የመተማመን መንፈሱን ለዘለቄታው ሊጎዳው ይችላል።
ሌላው የተለመደ ችግር ተጫዋች መሆን አለመቻል ነው። ምን ብለህ እንደምትናገር ግራ ስለሚገባህ ከዚህ ቀደም ከማታውቀው ሰው ጋር ለመተዋወቅ ታመነታ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ትልልቅ ሰዎችም እንኳ ከሌሎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ምን ብለው እንደሚያወሩ ግራ ሊገባቸው እንደሚችል ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ፍሬድ የተባለ አንድ ነጋዴ እንዲህ ብሎ ተናግሯል:- “በንግዱ ዓለም ማድረግ ያለብኝን ነገር እንዴት ማከናወን እንደምችል ጠንቅቄ አውቃለሁ። ከሰዎች ጋር ስለ ንግድ ጉዳይ የማወራ ከሆነ በእነርሱ ላይ ጥሩ ስሜት ለማሳደር ምንም አይከብደኝም። ሆኖም ከነዛው ሰዎች ጋር ማኅበራዊ ጉዳዮችን አንስተን ማውራት ስንጀምር ምን ብዬ ማውራት እንዳለብኝ ግራ ይገባኛል። የማሰለች ወይም የአነጋገር ለዛ የሌለኝ ወይም ችክ ያልኩ ወይም የማልስብ እንደሆንኩ ተደርጌ ልቆጠር እችላለሁ።”
ዓይን አፋር ወይም ስለ ራስህ ከልክ በላይ የምትጨነቅ አለዚያም ደግሞ ከሌሎች ጋር ስትሆን ምን ብለህ እንደምታወራ ግራ የሚገባህ ከሆንክ ከሰዎች ጋር ይበልጥ መግባባት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅህ ጥቅም ያስገኝልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘እንዲስፋፉ’ እና ሌሎችን እንዲያውቁ ያበረታታቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:13) ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው እትም ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓይን አፋር ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቁጥብ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እሳሳት ይሆናል የሚለው ፍርሃት አንዳንድ ወጣቶች ከማኅበረሰቡ ራሳቸውን እንዲያገሉ ያደርጋቸዋል