የአውሬነትን ጠባይ አስወግዶ የበግ ባሕርይ መልበስ
ኤንሪኬ ቶሬስ እንደተናገረው
የተወለድኩት በ1941 ከካሪቢያን ደሴቶች አንዷ በሆነችውና የአብዛኛው ሰው መግባቢያ ቋንቋ ስፓኒሽ በሆነባት በፖርቶ ሪኮ ነው። ኑሯቸው ዝቅተኛ የነበረው ወላጆቼ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም እነሱም ሆኑ እኔ፣ እህቶቼና ወንድሜ (ገና ልጅ እያለ ነው የሞተው) ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ትምህርት አግኝተን የማናውቅ ከመሆኑም ሌላ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሄደውም ከስንት አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።
በ1949 ቤተሰባችን ፖርቶ ሪኮን ለቅቆ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደ። ከዚያም ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ኤልባሪዮ እየተባለ በሚታወቀው በኢስት ሃርሌም ተቀመጥን። እስከ 1953 ድረስ የቆየነው እዚህ አካባቢ ነበር። የእንግሊዝኛ ቋንቋን መልመድ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ስለነበር የምረባ ሰው አይደለሁም የሚል ስሜት አድሮብኝ ነበር።
መጥፎ ተጽዕኖ
ከዚያም ቤተሰባችን ወደ ብሩክሊን ፕሮስፔክት ሃይትስ አካባቢ ሄደ። በእኩዮቼ ተጽዕኖ የጎዳና ወሮበሎች ቡድን አባል የሆንኩት በዚህ ጊዜ ነበር። ትንሽ ቆይቶ የቡድኑ መሪ ሆንሁ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በተሽከርካሪዎች ስርቆት የተሠማራ ሌላ ቡድን መሪ ሆኜ ነበር። በአቅራቢያችን ለሚገኙ የውርርድ ቡድኖችም ሕገወጥ የሆነውን የቁማር ዕዳ የማሰባሰብ ሥራም እሠራ ነበር። ከዚያም ወደ ቤት ዘረፋ ወንጀል በመሸጋገሬ ዕድሜዬ ገና 15 ዓመት እንኳ ሳይሞላ በተደጋጋሚ ጊዜ ተይዤአለሁ። በዚህ ጊዜ ትምህርቴንም አቁሜ ነበር።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ባለ ሥልጣኖቹ በቅጣት መልክ ለአምስት ዓመት ወደ ፖርቶ ሪኮ ላኩኝ። የተላኩት ወደ አያቴ ቤተሰብ ነበር። አያቴ በጣም የታወቀና የተከበረ ጡረተኛ የፖሊስ መኮንን ነበር። ይሁንና ከአንድ ዓመት በኋላ ከመጥፎ ሰዎች ጋር በመግጠሜ ሰክሬ በመበጥበጥና በቤት ዘረፋ በመሰማራት ስላስቸገርኩ መልሶ ወደ ብሩክሊን ላከኝ።
አባቴ በሕይወቴ ውስጥ የተጫወተው ሚና
ከፖርቶ ሪኮ ወደ ኒው ዮርክ ተመልሼ ስሄድ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምሮ ነበር። ይሁንና እኔ የምከተለው ጎዳና ፍጹም ተቃራኒ ነበር። አምላካዊ ባልሆነው አኗኗሬ ገፍቼበት ስለነበር ለአደገኛ ዕፆችና ለአልኮል ሱሰኛነት ተዳረግሁ። የታጣቂ ዘራፊዎች ቡድን አባል ሆኜ በመገኘቴ በ1960 በቁጥጥር ሥር ዋልኩ። ከዚያም በዚሁ ወንጀል ሦስት ዓመት ተፈረደብኝና ወኅኒ ወረድሁ።
በ1963 በአመክሮ ተለቀቅሁ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እንደገና በመኖሪያ ቤት ዝርፊያ ወንጀል ተይዤ በኒው ዮርክ ከተማ በራይከርስ አይላንድ ሁለት ዓመት ታሠርሁ። ከዚያም በ1965 ተፈታሁ። ይሁንና በዚያው ዓመት በነፍሰ ገዳይነት እንደገና ተያዝሁ። እንዴት ዓይነት ጨካኝ አውሬ ሆኜ ነበር!
ሃያ ዓመት ተፈረደብኝና በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው በዳኒሞራ ታሠርሁ። እዚያም የእስር ቤቱ ሕይወት ተዋሃደኝ።
ይሁን እንጂ ቀደም ብዬ እንደጠቀስሁት አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ነበር። በኋላም ተጠምቆ ሃርሌም በሚገኘው ጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ነበር። በእስር ቤት ባሳለፍኋቸው ዓመታት እየተመላለሰ ይጠይቀኝና ሁልጊዜ ስለ አምላክ፣ ስለ ስሙና ስለ ዓላማው ይነግረኝ ነበር።
ይሁንና በዳኒሞራ እስር ቤት እያለሁ በከፍተኛ ወለድ ብድር የሚሰጡ ቡድኖች አባል ሆንኩ። በዚህ ወቅት ማለትም በ1971 በኒው ዮርክ ግዛት በሚገኘው ሌላ እስር ቤት ማለትም በአቲካ ማረሚያ ቤት ዓመፅ ተነሣ። ይህም ዓመፅ የብዙ ጋዜጦች ዋና ርዕስ ሆኖ የነበረ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በራዲዮና በቴሌቪዥን ሰፊ የዜና ሽፋን አግኝቶ ነበር። ከዚህ ዓመፅ በኋላ በዳኒሞራም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ለመከላከል ሲባል የእስር ቤቱ ኃላፊ በሌሎች እስረኞች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚባሉትን መርጦ ማውጣት እንደሚሻል ወሰነ። የተመረጡትም በሌሎች ለየት ያሉ ክፍሎች ውስጥ እንዲቀመጡ ተደረገ።
ከ2,200 እስረኞች መካከል 200 የምንሆን ሰዎች ተለየን። ተጨማሪ ማጣራት ተካሄደና አንዳንዶቻችን እንደገና ተለይተን የከፋ ድብደባ ተካሄደብን። በተጨማሪም “ባሕርይን ለማስተካከል የሚሰጥ ሕክምና” በሚል ምግባችን ውስጥ መድኃኒት ይጨመርብን ነበር።
በዲሲፕሊን ጉድለት የተነሳ ከሌሎች ተገልዬ ሌላ ክፍል እንድቀመጥ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ጭካኔ ሲፈጸምብኝ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በጣም ተጎድቼ ነበር። እጆቼና እግሮቼ በካቴና ይታሠራሉ፤ ጠባቂዎቹም በየጊዜው ክፉኛ ይደበድቡኛል። የሌላ አገር ሰው በመሆኔ ሁልጊዜ የሚሰነዘርብኝን የሚያንቋሽሽ ስድብም መቋቋም ነበረብኝ። የተፈጸመብኝን ሰብዓዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ድርጊትና ድብደባ በመቃወም ተገልዬ በቆየሁባቸው ሦስት ወራት የምበላውን ምግብ መጠን በመቀነስ የረሃብ አድማ አደረግሁ። ከዚህ የተነሣ ከ18 ኪሎ በላይ ቀነስሁ።
አባቴ ጤናዬ በጣም እየተጎዳ እንዳለ ለእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት አቤት ቢልም ሰሚ አላገኘም። ይህም ተስፋ ስላስቆረጠኝ ስለሚፈጸምብኝ ኢፍትሐዊ ድርጊት በመግለጽ እንዲረዱኝ ለፖለቲካ ሰዎች ደብዳቤ ጻፍኩ።
አባቴ በዚያ ልዩ ክፍል ውስጥ በእስረኞች ላይ ስለሚፈጸመው ድብደባና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ድርጊት እንዲሁም ምግባቸው ውስጥ ስለሚጨመረው መድኃኒት በመግለጽ ለጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርጓል። እስር ቤት ውስጥ ስላለው አሳዛኝ ሁኔታ የሚገልጽ ዘገባ ያወጣው ግን አምስተርዳም ኒውስ የተባለ አንድ ጋዜጣ ብቻ ነበር። ከዚህም ሌላ አባቴ በተለያዩ ጊዜያት አልባኒ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የማረሚያ ቤት ኮሚሽነር ሳይቀር ሄዶ ነበር። ሁልጊዜ ይነገረው የነበረው ግን በመደበኛው የእስረኞች ክፍል ውስጥ እንዳለሁ ነበር። በእስር ቤት ስላለው ሁኔታ ለፖለቲከኞች የላኩትም ሪፖርት ቢሆን ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ቀረ። እርዳታ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ የማደርግበት ምንም ነገር ስላልነበረ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልቤ በሐዘን ተሰበረ።
አባቴ ይነግረኝ የነበሩትን አንዳንድ ነገሮች ያስታወስኩት በዚህ ጊዜ ነበር። አምላክ እንዲረዳኝ ወደ እርሱ ለመጸለይ ወሰንሁ።
ፊቴን ወደ አምላክ አዞርሁ
ከመጸለዬ በፊት ግን መጸለይ ያለብኝ ለኢየሱስ ሳይሆን የኢየሱስ አባት ለሆነውና ይሖዋ ለሚባለው አምላክ እንደሆነ አባቴ ሁል ጊዜ ይነግረኝ የነበረው ነገር ትዝ አለኝ። በእስር ቤቷ ክፍል ወለል ላይ በግንባሬ ተደፍቼ፣ የተከተልኩት ጎዳና ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ሕይወቴን በእስር ቤት ለማሳለፍ እንደዳረገኝና እጅግ እንደጸጸተኝ በመግለጽ ምርር ብዬ ወደ አምላክ ጸለይሁ። ከዚህ መከራ ሊያወጣኝ የሚችል ኃይል ያለው እርሱ ብቻ መሆኑን ስለተገነዘብሁ እንዲረዳኝ ይሖዋን ከልቤ ተማጸንሁት።
ለምን ያህል ጊዜ እንደጸለይሁ ባላውቅም ስላለፈው ጊዜ ሁሉ በመዘርዘር ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ የንስሐ መንፈስ ይዤ ለመንሁት። ስለ እርሱ ይበልጥ ለመማርም ቃል ገባሁ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለብቻዬ ከታሠርኩበት ከዚያ የጨለማ ክፍል ወጥቼ ከሌሎቹ እስረኞች ጋር ተቀላቀልሁ። በዚህ ጊዜ የረሃብ አድማዬንም አቆምሁ።
ስለ ይሖዋ የበለጠ ለመማር የገባሁትን ቃል በማክበር የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ማንበብ ጀመርሁ። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከተማረኩባቸው ምክንያቶች አንዱ ሽፋኑ አረንጓዴ መሆኑ ነበር። የእስር ቤቱ ልብስም ሆነ፣ ቤቱ፣ ግድግዳው እንዲሁም መተላለፊያው ሁሉ ቀለማቸው በጣም ጭፍግግ ያለ ዳለቻ ነበር። የሚያስገርመው ግን ትንሽ ቆይቶ ሁሉም ነገር አረንጓዴ ቀለም እንዲቀባ ተደረገ። የማረሚያ ቤት ክፍሉ ይህን ቀለም ያስቀየረው በአቲካ እስር ቤት ዓመፅ ከተነሣ በኋላ ነበር።
አባቴ ይልክልኝ የነበሩትንም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ማንበብ ጀመርኩ። እምነታቸውን አጥብቀው በመያዛቸው ምክንያት ወኅኒ ስለወረዱና እኔ ከደረሰብኝ የበለጠ መከራ ስለደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮ ሳነብ በጣም ተነካሁ። እነዚህ ምንም ዓይነት ወንጀል ያልፈጸሙ ነገር ግን ለአምላካቸው የታመኑ ለመሆን ሲሉ አላግባብ መከራ የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው። እኔ ግን የሚገባኝን ነው ያገኘሁት። እነዚህን ተሞክሮዎች ሳነብብ ልቤ ተነካ። ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቡ ይበልጥ ለመማርም ተነሳሳሁ።
በመጨረሻም ከአንድ ዓመት በኋላ በአመክሮ ቦርድ ፊት ቀረብሁ። በልዩ ክፍሉ ውስጥ የደረሰብኝን ስቃይ ጨምሮ ጉዳዬ እንደገና ታየልኝ። በ1972 በአመክሮ እንደምለቀቅ ሲነገረኝ በጣም ተደሰትሁ።
ከተፈታሁ ከሁለት ሳምንት በኋላ በስፓኒሽ ሃርሌም ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄድኩ። ይሁንና ያኔም ቢሆን ከይሖዋ ሕዝብ ጋር ልሰበሰብ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም የሚል ስሜት ነበረብኝ። ስለ ይሖዋ፣ ስለ ድርጅቱና ስለ ሕዝቡ ገና ብዙ መማር ያስፈልገኝ ነበር። በእስር ቤት በጣም ረጅም ጊዜ ስላሳለፍኩ ከኅብረተሰቡም ጋር ተስማምቶ ለመኖር ራሴን ማስተካከል አስፈልጎኝ ነበር።
የሚያሳዝነው ግን ከቀድሞ ልማዶቼ መላቀቅ አልቻልኩም። እንደገና አደገኛ ዕፆች መውሰድ እንዲሁም ወንጀልና አምላካዊ ያልሆኑ ድርጊቶች መፈጸም ጀመርኩ። ይህም የኋላ ኋላ የ15 ዓመት ፍርድ እንድከናነብ አድርጎኛል። ይሁንና ይሖዋ አንድ ጥሩ ነገር እንዳየብኝና ጨርሶ እንዳልተወኝ ይሰማኝ ነበር። አንድ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር አለ። እስር ቤትም ገባችሁ የት ይሖዋ ስለ እርሱ የመማር ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ፈጽሞ አይተውም።
በእስር ቤት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት
በዚህ ጊዜ ዳኒሞራ እስር ቤት ተመልሼ ስገባ ከአንድ የይሖዋ ምሥክሮች አገልጋይ ጋር በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ የማጥናት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ከዚያም ወደ ሚድ ኦሬንጅ ማረሚያ ቤት ተላክሁ። ይህ በሰሜናዊ ኒው ዮርክ የሚገኝና ላላ ያለ ጥበቃ ያለበት እስር ቤት ነበር። ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግበት የዳኒሞራ እስር ቤት አንጻር ይህ ትልቅ ለውጥ ነበር።
በሚድ ኦሬንጅ ማረሚያ ቤት ሁለት ዓመት ከቆየሁ በኋላ በእስር ቤቱ ባለ ሥልጣኖች ፈቃድ ለአንድ እስረኛ ይመራለት በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በትጋት መካፈል ጀመርሁ። የእስረኛው እናት የይሖዋ ምሥክር ስለነበረች እንዲያጠና ዝግጅት ያደረገችለት እርሷ ነበረች። እውቀት እያዳበርኩ በመሄዴ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። ይህም መንፈሳዊ ዕድገት እንዳደርግ ረድቶኛል።
የአመክሮ ጥያቄዬ ሰባት ጊዜ ውድቅ ከተደረገብኝ በኋላ እያመነታሁ ለስምንተኛ ጊዜ ጥያቄ አቀረብሁ። ካሁን ቀደም ያቀረብኳቸው የአመክሮ ጥያቄዎች ተቀባይነት ያጡት “ወንጀል የመፈጸም ዝንባሌ የተጠናወተኝ” በመሆኔ እንደነበር ተገለጸልኝ። ከዚያም ከ15 ዓመቱ ውስጥ 8 ዓመት ከታሰርኩ በኋላ ተለቀቅሁ።
በመጨረሻ ከጨለማ ነፃ መውጣት
ከእስር ከተፈታሁ በኋላም እንደገና ለጥቂት ጊዜ አደገኛ ዕፆች መውሰድ ጀምርሁ። እንዲሁም ከአንዲት ሴት ጋር በሕጋዊ ጋብቻ ሳንተሣሠር አብረን እንኖር ነበር። ከእርሷ ጋር መኖር የጀመርኩት በ1972 ነው። ይሁን እንጂ በ1983 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጥናቴን ቀጠልሁ። በዚህ ጊዜ አዘውትሬ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እገኝ ነበር። ይሁን እንጂ አደገኛ ዕፆችን መውሰድና ትንባሆ ማጨስ ያቆምሁት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከመጀመሬ በፊት ነው።
ነገር ግን አምላክ ጋብቻን አስመልክቶ ካወጣው ሕግ ጋር በሚቃረን መንገድ በሕግ ካላገባኋት ሴት ጋር መኖሬን ቀጥዬ ነበር። ይህ ነገር ሕሊናዬን ስለረበሸኝ እርሷም መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠናና ግንኙነታችንን ሕጋዊ በማድረግ ተጋብተን እንድኖር ለማድረግ ሞከርሁ። እርሷ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የወንዶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ወንዶች የጻፉትና ሴቶችን ለመጨቆን የተዘጋጀ መጽሐፍ እንደሆነና ጋብቻ አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ ተቃወመችኝ።
የአምላክ ሕግ ስለ ጋብቻ የሚናገረውን ነገር ከማታከብር ሴት ጋር ያለኝን ይህን የመሰለ ሥነ ምግባር የጎደለው ግንኙነት እሹሩሩ እያልኩ መቀጠል እንደማልችል ተገነዘብሁ። ከዚያም ከእርሷ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጬ ወደ ብሩክሊን ሄድኩ። የእኔ የራሴ ሁኔታ ከእርሱ ሕግ ጋር የማይስማማ ከሆነ ስለ አምላክም ሆነ ስለ ዓላማው ለሌሎች ሰዎች መናገር እንደማልችል ገብቶኝ ነበር።
ከማንኛውም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ድርጊት ከተላቀቅሁና ለሦስት ዓመታት ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ካጠናሁ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ በንጹሕ ህሊና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕይወቴን ወስኜ ተጠመቅሁ። አባቴ ሁልጊዜ ስሙን ይነግረኝ የነበረውን አምላክ ይበልጥ ለማወቅ ቃል በመግባቴ መቼም ቢሆን አልጸጸትም። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃል የገባውን የተትረፈረፈ በረከት እስከሚያመጣበት ጊዜ ድረስ በዳኒሞራ እስር ቤት ጨለማ ቤት ተጥዬ ሳለ የገባሁትን ቃል ለመጠበቅ እጋደላለሁ።
ገነትን በጉጉት መጠባበቅ
ይሖዋ መላዋን ምድር ወደ ውብ ገነትነት የሚለውጥበትን ጊዜ የምጠብቀው በታላቅ ጉጉት ነው። (መዝሙር 37:11, 29፤ ሉቃስ 23:43) ሙታን ትንሣኤ አግኝተው ለዘላለም መኖር የሚችሉበት አጋጣሚ የሚያገኙበት የአምላክ ተስፋ ሲፈጸምም ለማየት እናፍቃለሁ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) አባቴን፣ ትንሹን ወንድሜንና ያለ ዕድሜያቸው የተቀጩትን ሌሎች የማውቃቸውን ሰዎች ጨምሮ የምወዳቸው ሙታን ከመቃብር ሲመለሱ የምቀበልበት ያ ጊዜ እንዴት ያለ ግሩም ጊዜ ይሆናል! ብዙውን ጊዜ እንዲህ ስላለው ተስፋ ሳስብ ልቤ በደስታ ይሞላል። አሁን የምደሰትበት ሌላው ነገር ደግሞ ሁለቱ እህቶቼና አንዳንድ ልጆቻቸው ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው መጠመቃቸውን ማየቴ ነው።
እምነቴን ለሌሎች ሰዎች በማካፍልበትም ሆነ የግል ተሞክሮዬን በምናገርበት ጊዜ በመዝሙር 72:12-14 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የሚከተሉትን የሚያጽናኑ የመዝሙራዊው ቃላት መጥቀስ ያስደስተኛል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።”
ይሖዋ ያሳየኝ ትዕግሥት ልቤን ነክቶታል። ሕዝቦቹ እንዲኖሯቸው የሚፈልጋቸውን ባሕርያት ለመማርና ለማንጸባረቅም ረድቶኛል። ይህም የአውሬ ጠባይ ማሳየት ሳይሆን አንደ በግ ሰላማዊና፣ ገር መሆንና ዝግተኛ መንፈስ ማሳየት የሚጠይቅ ነገር ነው። የአምላክ ቃል “ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል” ስለሚል ይህ አስፈላጊ ነው።—ምሳሌ 3:34
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እንደገና በመኖሪያ ቤት ዝርፊያ ወንጀል ተይዤ በኒው ዮርክ ከተማ በራይከርስ አይላንድ ሁለት ዓመት ታሰርሁ። ከዚያም በ1965 ተፈታሁ። ይሁንና በዚያው ዓመት በነፍስ ገዳይነት እንደገና ተያዝሁ። እንዴት ዓይነት ጨካኝ አውሬ ሆኜ ነበር!”
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጠመቅሁ ዕለት