የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 2/11 ገጽ 19-21
  • ወርቅ ፍለጋ ሄደው አገር አገኙ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወርቅ ፍለጋ ሄደው አገር አገኙ
  • ንቁ!—2011
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አዲስ የወርቅ ተራራ
  • በወርቅ ማዕድን ማውጫዎች የነበረው አድካሚ ሥራ
  • ወርቁ ካለቀ በኋላ
  • በወርቅ ታሪክ ዙሪያ ያለው ምሥጢር
    ንቁ!—1998
  • “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ”
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ከወርቅ የሚልቀውን ነገር ፈልጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ሀብት የሚነገረው የተጋነነ ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ንቁ!—2011
g 2/11 ገጽ 19-21

ወርቅ ፍለጋ ሄደው አገር አገኙ

የቻይና ሠፈር። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ውስጥ ይህ ስም ሲጠራ ብዙዎች ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የቻይናውያን ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ክብረ በዓሎችና ድራገን የተባለው ጭፈራ ነው። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የቻይና ሠፈር የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። በዛሬው ጊዜ በአውስትራሊያ የሚገኙት የቻይና ሠፈሮች የተመሠረቱት አዲስ በተገኙት የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ላይ ሠርተው ሀብታም ለመሆን ተስፋ አድርገው ወደ አገሪቱ ደቡባዊ ጠረፍ በመጡ መንፈሰ ጠንካራ ቻይናውያን ስደተኞች ነው።

አዲስ የወርቅ ተራራ

እንደ ካፊያ የጀመረው የቻይናውያን ፍልሰት በ1851 ወርቅ ከተገኘ በኋላ እንደ ከባድ ዝናብ ሆነ። በሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች በቻይና ጉዋንዶንግ ክፍለ አገር ከሚገኘው የፐርል ወንዝ ዳርቻ ተነስተው ወደ ደቡብ ለመፍለስ አስቸጋሪውን የባሕር ጉዞ ተያያዙት። ቀደም ሲል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በካሊፎርኒያ ግዛት ወርቅ ተገኝቶ ስለነበረ የካንቶኒዝ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ ቻይናውያን እነዚህን የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች የወርቅ ተራራ ብለው ሰይመዋቸው ነበር። በመሆኑም የአውስትራሊያዎቹ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎች አዲስ የወርቅ ተራራ ሆኑ።

ሰዎቹ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያነሳሳቸው ወርቅ የማግኘት ፍላጎት ብቻ አልነበረም። በቻይና የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋና ድህነት ብዙ መከራና ሥቃይ አስከትሎ ነበር።

የሚያሳዝነው ግን መጀመሪያ ላይ ወደ አውስትራሊያ ከተጓዙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የአውስትራሊያን የባሕር ዳርቻ ለማየት አልታደሉም። በተጨናነቁ መርከቦች ይደረግ በነበረው ጉዞ ምክንያት በተነሱ ወረርሽኞች ሞተዋል። ከሞት ተርፈው አውስትራሊያ የደረሱትም ቢሆኑ የአዲሱ ምድር ኑሮ እንዳሰቡት ቀላል አልሆነላቸውም።

በወርቅ ማዕድን ማውጫዎች የነበረው አድካሚ ሥራ

በአገራቸው ወግ መሠረት ሚስቶችና ልጆች አገር ቤት ቀርተው የቤተሰባቸውን የዘር ሐረግ ማስጠበቅ ስለሚኖርባቸው ስደተኛ ለሆኑት ወንዶች ብቸኝነት የዘወትር ባልንጀራቸው ሆነ። በ1861 በአውስትራሊያ ከ38,000 በላይ ቻይናውያን ወንዶች ይኖሩ የነበረ ሲሆን የሴቶቹ ቁጥር ግን 11 ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ እዚያው ለመቅረት ያሰቡት በጣም ጥቂቶች ነበሩ። አብዛኞቹ ሀብት ካገኙ በኋላ በክብር ወደ ቤተሰቦቻቸውና ወደ አገራቸው ለመመለስ ቆርጠው ነበር።

ለወርቅ ፍለጋ ዋነኛ ኃይል የሆናቸው ይህ ሕልማቸው ነበር። ማዕድን ፈላጊዎቹ በድንኳን ውስጥ እየኖሩ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በጠራራ ፀሐይ ለረጅም ሰዓታት ይሠሩ ነበር። አንዳንዶች፣ መጀመሪያ አካባቢ በነበረው አጉል እምነት ምክንያት ወደ ከርሰ ምድር ገብተው ማዕድን መፈለግ ይፈሩ ነበር። ስለሆነም ከላይ ያለውን አፈር ከማሱ በኋላ አፈሩን በገበቴ ያንገዋልሉትና ጓሉን በውኃ ያጥቡታል። ልፋታቸው ከንቱ አልሆነም። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ1854 እስከ 1862 ባሉት ዓመታት ከቪክቶሪያ ግዛት 18,662 ኪሎ ግራም የሚያክል ወርቅ ወደ ቻይና ተልኳል።

የሚያሳዝነው ግን ከዚህ አዲስ ከተገኘው ሀብት ከፊሉ ብቸኝነት ያጠቃቸውን የማዕድን ሠራተኞች በተጠናወተው የቁማርና የኦፒየም ሱስ ምክንያት ባክኖ ቀርቷል። በዚህ ምክንያት ብዙዎች ጤንነታቸው የተጎዳ ከመሆኑም በላይ ለፍተው ያገኙት ሀብትም ሆነ ወደ ትውልድ አገራቸው የመመለስ ተስፋቸው እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል። አንዳንዶች ከቻይናውያን ድርጅቶችና ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች እርዳታ ያገኙ ሲሆን ሌሎቹ ግን በብቸኝነትና በችግር ማቀው ያለዕድሜያቸው ተቀጭተዋል።

ቻይናውያኑ እርስ በርስ የሚረዳዱ ከመሆኑም በላይ በሥራቸው ስኬታማ ነበሩ፤ ይህ ደግሞ ቻይናውያን ያልሆኑ ሌሎች የማዕድን ሠራተኞችን ያስቀናቸው አልፎ ተርፎም በጥርጣሬ ዓይን እንዲያዩአቸው አድርጎ ነበር። በዚህም ምክንያት ቻይናውያኑ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ወርቃቸው ተዘርፏል፤ ድንኳኖቻቸውና ንብረቶቻቸው ተቃጥለዋል። ይህ ጥላቻ ውሎ አድሮ እየረገበ የመጣ ቢሆንም ወርቅ ከተገኘ ከ50 ዓመት በኋላ ማለትም በ1901 የተጣለው እገዳ እስያውያን ወደ አውስትራሊያ እንዳይገቡ ማነቆ ሆኖባቸው ነበር፤ ይህ እገዳ የተነሳው በ1973 ነው።

ወርቁ ካለቀ በኋላ

ማዕድኑ ካለቀ በኋላ አንዳንድ ቻይናውያን እዚያው አውስትራሊያ ለመቆየት መርጠዋል። በዚህም የተነሳ በወርቅ ማዕድን ማውጫዎች ምክንያት በተቆረቆሩት ከተሞች ውስጥ የቻይናውያን የልብስ ንጽሕና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶችና የአትክልት እርሻዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። በተጨማሪም ቻይናውያኑ በጥሩ የቤት ዕቃ አምራችነታቸውና በትኩስ ፍራፍሬና አትክልት አቅራቢነታቸው ጥሩ ስም አትርፈዋል። በዚህ የተነሳ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አተርተንን፣ ብሪዝበንን፣ ብሩምን፣ ኬይርንስን፣ ዳርዊንን፣ ሜልቦርንን፣ ሲድኒንና ታወንስቪልን ጨምሮ በብዙ የአውስትራሊያ ከተሞች የቻይናውያን ሠፈሮች ተመሥርተዋል።

ወደ አውስትራሊያ የመጡ ቻይናውያን ሴቶች በጣም ጥቂት በመሆናቸው አብዛኞቹ ወንዶች ዕድሜያቸውን በነጠላነት ገፍተዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የነበረውን ጥላቻ ተቋቁመው አውስትራሊያውያን ሴቶችን አግብተዋል። ከቻይናውያኑና ከአውስትራሊያውያኑ የተወለዱት ዝርያዎች ውሎ አድሮ የአውስትራሊያ ማኅበረሰብ ዋነኛ ክፍል ሆነዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ቻይናውያን ስደተኞች በአውስትራሊያ ውስጥ ይኖራሉ። አብዛኞቹ ወደዚህ አገር የሚመጡት ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተልና የተሻለ የሥራ አጋጣሚ ለማግኘት ነው። በአሁኑ ጊዜ ከሚመጡት ቻይናውያን መካከል በርካታ ሴቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በደረሰው ለውጥ ምክንያት ብዙ ወንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ቤተሰባቸውን በአውስትራሊያ ካሠፈሩ በኋላ ወደ እስያ ተመልሰው በቻይና፣ በሆንግ ኮንግ፣ በሲንጋፖር ወይም በታይዋን ይሠራሉ።

አዎን፣ ዘመኑ ተለውጧል። ሆኖም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞ የሚፈልጉት መሠረታዊ ነገር አልተለወጠም፤ አሁንም ቢሆን የሚፈልጉት በባዕድ አገር የተደላደለና ስኬታማ ኑሮ መምራት ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ካሰቡት በላይ ርቆባቸዋል

ቻይናውያን መንገደኞች የኮቴ ላለመክፈል ሲሉ ከዋነኞቹ ወደቦችና ከወርቅ ማዕድን ቦታዎች በመቶ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀው በሚገኙ የባሕር ዳርቻዎች ይወርዱ ነበር። መንገደኞቹ ከሚወርዱባቸው ቦታዎች መካከል በደቡባዊ አውስትራሊያ የምትገኘው ሮብ አንዷ ናት። የሮብ ነዋሪዎች ብዛት ከ100 እስከ 200 የሚደርስ ቢሆንም በ1857 በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 12,000 የሚያክሉ ቻይናውያን በዚያ አልፈዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጽናት በማሳየትና እርስ በርስ በመተጋገዝ ብዙ ሰው የማይኖርበትን አካባቢ አቋርጠው ወደ ወርቅ ማዕድን ማውጫዎች መድረስ ችለዋል፤ ሆኖም መንገዱ ካሰቡት በላይ በመርዘሙ እስከ አምስት ሳምንት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል። መንገደኞቹ ለስንቅ እንዲሆናቸው ባሕር ውስጥ የሚበቅል ተክል የሚይዙ ከመሆኑም በላይ መንገድ ላይ የሚያገኟቸውን ካንጋሮዎችና ዎምባቱዎች ይበላሉ። በተጨማሪም የውኃ ጉድጓድ ይቆፍሩና ከኋላቸው ለሚመጡ ተጓዦች ዱካቸውን ይተዉ ነበር።

ወንዶቹ ፀጉራቸውን ሹርባ ተሠርተውና ሰፊ የፀሐይ መከላከያ ባርኔጣ አድርገው እያንጎራጎሩ በሰልፍ ይጓዛሉ። በመንገድ ላይ የቻይናውያን ገንዘቦች ወድቀው ተገኝተዋል። ይህ የሆነው መንገደኞቹ የቻይና ገንዘብ በአውስትራሊያ ምንም ዋጋ እንደሌለው ሲያውቁ እየጣሉት ስለሄዱ ነው።

[የሥዕሉ ምንጭ]

Image H17071, State Library of Victoria

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ከወርቅ የተሻለ ነገር አገኘን

ዌይን ቼ በቻይና የሳይንስ አካዳሚ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ሆኖ ይሠራ ነበር። ዌይን ሙያውን ለማሻሻል ሲል በ1990ዎቹ ዓመታት ሱ ከምትባለው ባለቤቱ ጋር ወደ አውሮፓ ሄዶ ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ጀመረ። ባልና ሚስቱ እዚያ ሳሉ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኙ ሲሆን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመሩ። በ2000 ዌይንና ሱ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ አውስትራሊያ ሄዱ፤ ሱ ታጠና የነበረው ሞለኪውላር ባዮሎጂ ነበር። በዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን ቀጠሉ።

ዌይን እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪዎችን ለማግኘት በርካታ ዓመታት አሳልፈናል። ይሁን እንጂ ‘ውሎ አድሮ ሁላችንም እናረጃለን፣ እንታመማለን፣ ከዚያም እንሞታለን። ታዲያ የሕይወት ዓላማ ይህ ብቻ ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር። ሁሉ ነገር ከንቱ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁንና እኔም ሆንኩ ሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እጅግ አስፈላጊ ለሆኑት ሕይወትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ምክንያታዊና አጥጋቢ መልስ አግኝተናል።

“በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን አስበነው የማናውቀውን የፈጣሪ ሕልውና ጉዳይ እንድንመረምር አድርጎናል። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ እንዲሁም ቻርልስ ዳርዊን ስለ ዝግመተ ለውጥ ያዘጋጃቸውን የጽሑፍ ሥራዎች አንብቤያለሁ። እነዚህን ጽሑፎች ማንበቤና ሳይንሳዊ ምርምር ማድረጌ ፈጣሪ እንዳለ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል። ሱም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሳለች።

“አምላክ አለ ብለን እንድናምን ያደረገን ሌላው ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል ያለው መሆኑ ነው። በእርግጥም ይህ አስደናቂ የሆነ መጽሐፍ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ እንዲኖረን ብቻ ሳይሆን ልባዊ ወዳጆችና ጠንካራ የሆነ ትዳር እንዲኖረን አስችሎናል። እኔና ሱ በ2005 የተጠመቅን ሲሆን ከከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም ‘ሊጠፋ ከሚችለው ወርቅ’ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን።”—1 ጴጥሮስ 1:7

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1860ዎቹ ዓመታት የነበረ አንድ ቻይናዊ የወርቅ ማዕድን ሠራተኛ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ

Sydney Chinatown: © ARCO/G Müller/age fotostock; gold miner: John Oxley Library, Image 60526, State Library of Queensland

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ