የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 9/13 ገጽ 6-9
  • ሃሎዊን—እውነታው ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሃሎዊን—እውነታው ምንድን ነው?
  • ንቁ!—2013
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሃሎዊን አመጣጥ ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • “ሃሎዊንን ማክበር አንፈልግም!”
    ንቁ!—2004
  • ሃሎዊንን የማላከብረው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2006
  • የአቀራረብ ናሙናዎች
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2013
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2013
g 9/13 ገጽ 6-9

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሃሎዊን—እውነታው ምንድን ነው?

አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሃሎዊን ይከበራል? በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ሃሎዊን በስፋት የሚታወቅ በዓል ሲሆን በየዓመቱ ጥቅምት 31 ቀን ይከበራል። ይሁን እንጂ ከሃሎዊን አከባበር ጋር የተያያዙ ልማዶች በሌሎች የዓለም ክፍሎችም በብዛት ይታያሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ሃሎዊን በሚለው ስም ባይታወቁም ተመሳሳይ ልማዶች የሚንጸባረቁባቸው ሌሎች በዓላት አሉ፤ በእነዚህ በዓላት ላይ ሰዎች ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ለመገናኘት ጥረት ያደርጋሉ። ይህም ከሙታን መናፍስት፣ ከአድባር፣ ከጠንቋዮች ሌላው ቀርቶ ከዲያብሎስና ከአጋንንት ጋር እንኳ መገናኘትን ይጨምራል።—“በዓለም ዙሪያ የሚከበሩ ከሃሎዊን ጋር የሚመሳሰሉ በዓላት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[ሥዕል]

ምናልባት አንተ መናፍስታዊ ኃይላት አሉ ብለህ አታምን ይሆናል። በሃሎዊን ወይም ተመሳሳይ በሆኑ ሌሎች ክብረ በዓላት ላይ የምትካፈለው የደስታ ጊዜ ለማሳለፍና ልጆችህ የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለመርዳት ብለህ ይሆናል። ብዙ ሰዎች ግን በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ እነዚህ ክብረ በዓላት ጎጂ እንደሆኑ ይሰሟቸዋል፦

  1. ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አሜሪካን ፎክሎር እንደሚለው “ሃሎዊን ከመንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ለመገናኘት ታስቦ የሚደረግ ክብረ በዓል ነው፤ አብዛኞቹ ፍጥረታት ደግሞ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው።” (“ከሃሎዊን ጋር የተያያዘ የጊዜ ሰሌዳ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በተመሳሳይም እንደ ሃሎዊን ያሉ ብዙ ክብረ በዓላት ሥረ መሠረታቸው አረማዊ ሲሆን ከቀድሞ አባቶች አምልኮ ጋርም በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች በዓሉ በሚከበርበት ዕለት፣ የሙታን መናፍስት ብለው ከሚጠሯቸው የሞቱ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ጥረት ያደርጋሉ።

  2. ሃሎዊን በዋነኝነት የአሜሪካውያን በዓል እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም ይህን በዓል የሚያከብሩ አገሮች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓሉን ማክበር የጀመሩ ብዙ ሰዎች፣ ከመናፍስታዊና ከአስማታዊ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የሃሎዊን ምልክቶች፣ ጌጣጌጦችና ልማዶች ምንጫቸው አረማዊ አምልኮ መሆኑን አይገነዘቡም።— “ምንጫቸው ከየት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

  3. የጥንቶቹን የአውሮፓ ኬልቶች ሥርዓተ አምልኮ የሚከተሉ በሺህ የሚቆጠሩ የዊካ እምነት (የጥንቆላ ሥርዓት የሚከተል ሃይማኖት) ተከታዮች ዛሬም ሃሎዊንን የሚጠሩት ሳምሄን በተባለው ጥንታዊ ስሙ ሲሆን በዓመቱ ውስጥ እጅግ ቅዱስ እንደሆነ ምሽት አድርገው ይቆጥሩታል። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው ጋዜጣ አንዲት ጠንቋይ ነኝ የምትል ሴት “ክርስቲያኖች ልብ ሳይሉት የእኛን በዓል አብረውን እያከበሩ ነው። . . . በዚህም ተደስተናል” በማለት እንደተናገረች ጽፏል።

  4. እንደ ሃሎዊን ያሉ ክብረ በዓላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ።”—ዘዳግም 18:10, 11፤ በተጨማሪም ዘሌዋውያን 19:31⁠ን እና ገላትያ 5:19-21⁠ን ተመልከት።

ቤተሰቦች አጋንንታዊ በሆኑ በዓላት ላይ መካፈል ሳያስፈልጋቸው ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ይችላሉ

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ስለ ሃሎዊንና ተመሳሳይነት ስላላቸው ሌሎች በዓላት አመጣጥ ማወቅህ ጥሩ ይሆናል። በዚህ ረገድ የተሟላ ግንዛቤ ማግኘትህ እነዚህን በዓላት ከማያከብሩ ሰዎች መካከል እንድትሆን ሊያነሳሳህ ይችላል።

“ክርስቲያኖች ልብ ሳይሉት የእኛን በዓል አብረውን እያከበሩ ነው። . . . በዚህም ተደስተናል።” —ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተሰኘው ጋዜጣ አንዲት ጠንቋይ ነኝ የምትል ሴት የሰጠችውን ሐሳብ ጠቅሶ የተናገረው

በዓለም ዙሪያ የሚከበሩ ከሃሎዊን ጋር የሚመሳሰሉ በዓላት

ሃሎዊን በአብዛኛው የሚታወቀው የአሜሪካውያን በዓል እንደሆነ ተደርጎ ነው። ይሁን እንጂ ይህ በዓል በብዙ የዓለም ክፍሎች ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪም ከሃሎዊን ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ይኸውም በመንፈሳዊ ፍጡራንና በእንቅስቃሴያቸው ላይ የሚያተኩሩ ሌሎች በዓላት አሉ። በዓለም ዙሪያ ከሚከበሩና ከሃሎዊን ጋር ከሚመሳሰሉ በርካታ በዓላት መካከል ጥቂቶቹ በካርታው ላይ ተጠቅሰዋል።

  • ሰሜን አሜሪካ - የሙታን ቀን

  • ደቡብ አሜሪካ - ካውሳስካንቺስ

  • አውሮፓ - የሙታን ቀን እና በሌላ ስያሜ የሚጠሩ የሃሎዊን በዓላት

  • አፍሪካ - ኤገንገን የሚባሉ የተከናነቡ ሰዎች የሚያደርጉት ጭፈራ

  • እስያ - የቦን ክብረ በዓል

ምንጫቸው ከየት ነው?

አንዳንድ የሃሎዊን ልማዶችና ተምሳሌት የሆኑ ነገሮች አመጣጥ

ቫምፓየሮች፣ እንደ ጭራቅ ያሉ ዌርዉልቮች፣ ጠንቋዮች፣ ዞምቢዎች፦ እነዚህ ፍጥረታት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚጠቀሱት ከክፉ መናፍስት ጋር ተያይዘው ነው።

ከረሜላ፦ የጥንቶቹ ኬልቶች ክፉ መናፍስትን በጣፋጮች በመደለል ቁጣቸውን ለማብረድ ይሞክሩ ነበር። ውሎ አድሮ ቤተ ክርስቲያን የበዓሉ አክባሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ምግብ እንዲጠይቁ አደረገች፤ እነሱም በምላሹ ለሙታን ጸሎት ያቀርባሉ። ይህም ቀስ በቀስ የሃሎዊን ማታለያ ወይም ማባበያ የተባለውን ልማድ አስገኘ።

አልባሳት፦ ኬልቶች የሚያስፈሩ ጭንብሎችን ያደርጉ ነበር፤ እንዲህ የሚያደርጉት ክፉ መናፍስትን ለማታለል ይኸውም እነሱን እንደ መናፍስት ቆጥረው እንዲርቋቸው ለማድረግ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ነፍሳት (ኦል ሶልስ) እና የሁሉም ቅዱሳን (ኦል ሴንትስ) ተብለው የሚጠሩት ክብረ በዓላት ቀስ በቀስ ከአረማዊ ልማዶች ጋር እንዲዋሃዱ አደረገች። ውሎ አድሮ የበዓሉ አክባሪዎች ቅዱሳንን፣ መላእክትንና ዲያብሎሶችን የሚያስመስሏቸውን አልባሳት ለብሰው ከቤት ወደ ቤት መሄድ ጀመሩ።

ዱባ፦ ክፉ መናፍስትን ለማባረር ሲባል የተቀረጹና ውስጣቸው ሻማ የበራባቸው ቀይ ሥር የመሰሉ አትክልቶች ይቀመጡ ነበር። አንዳንዶች በቀይ ሥሩ ውስጥ የተቀመጠው ሻማ መንጽሔ ውስጥ የተያዘችን ነፍስ እንደሚወክል ይሰማቸዋል። ውሎ አድሮ ግን የተቀረጸ ዱባ መጠቀም በጣም የተለመደ ሆነ።

ከሃሎዊን ጋር የተያያዘ የጊዜ ሰሌዳ

አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.

ኬልቶች ከሌላው ጊዜ ይልቅ ጣረ ሞቶችና አጋንንት በምድር ላይ ይዘዋወራሉ ብለው በሚያምኑበት በጥቅምት ወር መጨረሻ የሳምሄንን በዓል ያከብሩ ነበር።

አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.

ሮማውያን ኬልቶችን ከወረሩ በኋላ የሳምሄንን መናፍስታዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ተቀበሉ።

ሰባተኛው መቶ ዘመን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቦነፌስ አራተኛ ሰማዕታትን ለማስታወስ ሲሉ “የሁሉም ቅዱሳን ቀን” የተባለው በዓል በየዓመቱ እንዲከበር እንዳደረጉ ይነገራል።a

አሥራ አንደኛው መቶ ዘመን

ኅዳር 2 ሙታንን ለማሰብ “የሁሉም ነፍሳት ቀን” (ኦል ሶልስ ዴይ) ተብሎ መከበር ጀመረ። በኦል ሴንትስ ዴይ እና በኦል ሶልስ ዴይ ዙሪያ የሚደረጉ የአከባበር ሥርዓቶች በአጠቃላይ ሃሎታይድ ተብለው ይጠራሉ።

አሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን

የሃሎ ኢቭኒንግ (የቅዱሳን ምሽት) አጭር መጠሪያ የሆነው ሃሎ-ኢን የሚለው ስያሜ በጽሑፍ ላይ ሲወጣ ሃሎዊን መባል ጀመረ።

አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን

ከአየርላንድ የፈለሱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሃሎዊንን ልማዶች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይዘው መጡ፤ ከጊዜ በኋላ እነዚህ ልማዶች ከብሪታንያ፣ ከጀርመን፣ ከአፍሪካና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የፈለሱ ሕዝቦች ካመጧቸው ተመሳሳይ ባሕሎች ጋር ተዋሃዱ።

ሃያኛው መቶ ዘመን

ሃሎዊን በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የሚከበር ተወዳጅ በዓል ሆነ።

ሃያ አንደኛው መቶ ዘመን

በዓለም ዙሪያ የሃሎዊን በዓል በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ ማስገኘት ጀመረ።

a ሎ “ቅዱስ” የሚል ትርጉም ያለው ጥንታዊ የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ኦል ሃሎውስ ዴይ ወይም ኦል ሴንትስ ዴይ (“የሁሉም ቅዱሳን ቀን”) የሞቱ ቅዱሳን የሚታወሱበት በዓል ነው። የኦል ሃሎውስ ዴይ የዋዜማ ምሽት ኦል ሃሎ ኢቭን ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ይህ ስም አጥሮ ሃሎዊን መባል ጀመረ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ