የኑሮ ውድነትን መቋቋም
በቃኝ በል
በቃኝ የሚሉ ሰዎች ባሏቸው ነገሮች ይረካሉ። ሁኔታቸው ሲቀየር ደግሞ እንደ አቅማቸው ለመኖር ሲሉ ማስተካከያ ማድረግ አይከብዳቸውም።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ጄሲካ ኮለር እንደተናገሩት በቃኝ የሚሉ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ ለነገሮች አዎንታዊ አመለካከት አላቸው። በአብዛኛው ሲታይ በሌሎች አይቀኑም። ከዚህ አንጻር በቃኝ የሚሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይበልጥ ደስተኛና ብዙም የማይጨነቁ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። እንዲያውም በጣም ደስተኛ ከሚባሉት ሰዎች አንዳንዶቹ ብዙ ሀብት የላቸውም። እነዚህ ሰዎች በተለይ ደስተኛ ያደረጋቸው ገንዘብ ሊገዛቸው ለማይችላቸው ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸው ነው፤ ለምሳሌ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስታቸዋል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ከሌሎች ጋር አትፎካከር። የአንተን ኑሮ ከሌሎች ቅንጡ የሚመስል ሕይወት ጋር ካወዳደርከው አንተ ያለህ ነገር ያንስብሃል፤ እንድትቀና ሊያደርግህም ይችላል። ከዚህ ባለፈ እንዲህ ያለው ንጽጽር እውነታውን የሚያንጸባርቅ ላይሆን ይችላል። አንዳንዶች ብዙ ንብረት ያላቸው ቢመስሉም በዕዳ ተዘፍቀው ሊሆን ይችላል። በሴኔጋል የምትኖረው ኒኮል እንዲህ ብላለች፦ “ደስተኛ ለመሆን ብዙ ነገሮች አያስፈልጉኝም። ሌሎች ከእኔ የበለጠ ነገር ቢኖራቸውም እንኳ ያለኝ ይበቃኛል የምል ከሆነ ደስተኛ እሆናለሁ።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የሌሎችን ሀብት ወይም ቅንጡ አኗኗር የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችን ወይም ማኅበራዊ ሚዲያዎችን አትመልከት።
አመስጋኝ ሁን። በጥቅሉ ሲታይ አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች ያላቸው ነገር እንደሚበቃቸው ይሰማቸዋል፤ ይህም ያም ያስፈልገኛል ወይም ይገባኛል ብለው አያስቡም። በሄይቲ የሚኖረው ሮቤርቶን እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች ለእኔና ለቤተሰቤ ስላሳዩን ደግነት ቆም ብዬ ለማሰብ እሞክራለሁ። ከዚያም ለሰዎቹ፣ ያደረጉልንን ነገር ምን ያህል እንደማደንቅ እነግራቸዋለሁ። የስምንት ዓመቱ ልጄም ለሚደረግለት ነገር ሁሉ ‘አመሰግናለሁ’ እንዲል አስተምሬዋለሁ።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በየቀኑ አመስጋኝ የሆንክባቸውን ነገሮች የመጻፍ ልማድ ይኑርህ። ለምሳሌ ጥሩ ጤንነትህን፣ ቤተሰብህን፣ ጓደኞችህን ሌላው ቀርቶ ፀሐይ ስትጠልቅ የሚፈጥረውን የሚያምር እይታ መጥቀስ ትችላለህ።
ሁላችንም በቃኝ ማለት ትግል የሚሆንብን ጊዜ አለ። እንዲህ ማድረጋችን ግን ይክሰናል! በቃኝ ለማለት መምረጥ ደስታን መምረጥ ነው፤ ደስታ ደግሞ ገንዘብ የማይገዛው ሌላ ባሕርይ ነው።