ለሕዝብ የሚቀርብ ንግግር መዘጋጀት
በአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በየሳምንቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ንግግር ይቀርባል። ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ከሆንክ ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪ ወይም አስተማሪ መሆንህ በግልጽ ይታያልን? እንደዚያ ከሆነ የሕዝብ ንግግር የማቅረብ አጋጣሚ ይሰጥህ ይሆናል። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች ለዚህ የአገልግሎት መብት ብቁ እንዲሆኑ ረድቷል። የሕዝብ ንግግር እንድታቀርብ በምትመደብበት ጊዜ ዝግጅትህን ለመጀመር በቅድሚያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አስተዋጽኦውን አጥና
ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ከመጀመርህ በፊት አስተዋጽኦውን በማንበብና በዚያ ላይ በማሰላሰል የንግግሩን መልእክት ለማግኘት ሞክር። ጭብጡን ማለትም የንግግሩን ርዕስ አስብ። አድማጮችህን የምታስተምራቸው ስለ ምን ነገር ነው? ዓላማህ ምንድን ነው?
የንግግሩን ዋና ዋና ነጥብ ከያዙት ርዕሶች ጋር በሚገባ ተዋወቅ። እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከጭብጡ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? በእነዚህ ነጥቦች ሥር የተወሰኑ ንዑስ ነጥቦች ተዘርዝረዋል። እነዚህን ንዑሳን ነጥቦች የሚደግፉ ሐሳቦች ደግሞ ከእነርሱ ሥር ይዘረዘራሉ። በእያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ ሥር ያለው ሐሳብ ከፊተኛው ጋር የሚዛመደውና ወደሚቀጥለው ንዑስ ርዕስ የሚያሸጋግረው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የንግግሩን ዓላማ ለማሳካት ምን ሚና እንደሚጫወት ልብ በል። ጭብጡን ማለትም የንግግሩን ዓላማ ከተረዳህና ዋና ዋና ነጥቦቹ ይህንን ዓላማ የሚያሳኩት እንዴት እንደሆነ ከተገነዘብክ ትምህርቱን ለማዳበር ዝግጁ ነህ ማለት ነው።
መጀመሪያ ላይ ንግግርህን በየንዑስ ርዕሱ ከፋፍለህ ማየቱ ይጠቅምህ ይሆናል። ይህም ማለት አንዱን ንግግር የየራሳቸው ዋና ነጥብ ያላቸው አራት ወይም አምስት አጫጭር ንግግሮች ስብስብ አድርገህ ትመለከተዋለህ ማለት ነው። ከዚያም ተራ በተራ ተዘጋጃቸው።
አስተዋጽኦው የሚረዳህ ለዝግጅት ብቻ ነው። ንግግርህን በምትሰጥበት ጊዜ በቀጥታ እንደ ማስታወሻ እንድትጠቀምበት ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም። አስተዋጽኦ የንግግሩ አፅም ብቻ ነው ለማለት ይቻላል። ይህን አፅም ሥጋ ልታለብሰውና ነፍስ ልትዘራበት ይገባል።
የጥቅሶች አጠቃቀም
ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ የሚያስተምሩት ጥቅሶችን መሠረት በማድረግ ነበር። (ሉቃስ 4:16-21፤ 24:27፤ ሥራ 17:2, 3) አንተም እንደዚህ ማድረግ ትችላለህ። የንግግርህ መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መሆን አለባቸው። በንግግር አስተዋጽኦው ላይ ያሉትን ዓረፍተ ነገሮች እያብራራህ በማስረዳት ብቻ መወሰን የለብህም። ከዚህ ይልቅ ጥቅሶቹ ዓረፍተ ነገሮቹን የሚደግፉት እንዴት እንደሆነ በማስተዋል እነዚህን ጥቅሶች መሠረት አድርገህ አስተምር።
ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ እያንዳንዱን ጥቅስ አውጥተህ አንብብ። በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ተመልከት። አንዳንዶቹ ጥቅሶች ከጉዳዩ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ግልጽ ለማድረግ የገቡ ሊሆኑ ይችላሉ። በንግግርህ ወቅት የግድ ሁሉንም ጥቅስ እያነበብህ ሐሳብ ልትሰጥበት ይገባል ማለት አይደለም። ለአድማጮችህ ይበልጥ ይስማማሉ የምትላቸውን ጥቅሶች ምረጥ። በንግግሩ አስተዋጽኦ ላይ ባሉት ጥቅሶች ላይ ካተኮርህ ተጨማሪ ጥቅሶችን መጠቀም ላያስፈልግህ ይችላል።
ንግግርህ አድማጮችህን የሚጠቅም መሆኑ የተመካው በምታነብባቸው ጥቅሶች ብዛት ሳይሆን በትምህርቱ የአቀራረብ ጥራት ላይ ነው። ጥቅሶችን በምታስተዋውቅበት ጊዜ የተጠቀሱበትን ምክንያት ግልጽ አድርግ። ጥቅሶቹን ከነጥቡ ጋር ጥሩ አድርገህ ማዛመድ ይኖርብሃል። አንድ ጥቅስ ካነበብህ በኋላ ስለ ጥቅሱ ስታብራራ መጽሐፍ ቅዱስህን አትክደነው። አድማጮችህም እንደ አንተ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው እንደሚቆዩ የታወቀ ነው። አድማጮችህ በትኩረት እንዲከታተሉህና ከአምላክ ቃል ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? (ነህ. 8:8, 12) በማብራራት፣ ምሳሌ በመጠቀምና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን በማስረዳት ይህንን ማድረግ ትችላለህ።
ማብራራት። አንድን ቁልፍ የሆነ ጥቅስ ለማብራራት ስትወስን ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህ ምን ማለት ነው? በንግግሬ ውስጥ የምጠቅሰው ለምንድን ነው? አድማጮች ስለ ራሳቸው ምን ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል?’ በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ፣ ከጥቅሱ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ፣ መቼቱን፣ ቃላቱ ያላቸውን ኃይል እንዲሁም ጸሐፊው በመንፈስ አነሳሽነት መልእክቱን ሲጽፍ ዓላማው ምን እንደነበረ ማጤን ያስፈልግህ ይሆናል። ይህ ደግሞ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ውስጥ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ታገኛለህ። (ማቴ. 24:45-47) ስለ ጥቅሱ ሁሉንም ነገር ለማብራራት አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ አድማጮች ጥቅሱን እንዲያነብቡ ያደረግኸው ለምን እንደሆነ አብራራ።
በምሳሌ መጠቀም። በምሳሌ ማስረዳት አድማጮች ነጥቡን ይበልጥ በጥልቀት እንዲያስተውሉ እንዲሁም አንድን ነጥብ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት እንዲያስታውሱ ይረዳል። ምሳሌ መጠቀም አድማጮችህ እየተናገርህ ያለኸውን ነገር አስተውለው ከአሁን ቀደም ከሚያውቁት ጉዳይ ጋር እንዲያዛምዱ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ወቅት ያደረገው ይህንኑ ነበር። “የሰማይ ወፎች፣” “የሜዳ አበቦች፣” ‘የጠበበ ደጅ፣’ ‘በዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት’ የሚሉትና እነዚህን የመሰሉት ብዙ ምሳሌዎቹ ትምህርቱን ትኩረት የሚስብ፣ ግልጽና የማይረሳ እንዲሆን አድርገውታል።—ማቴ. ምዕ. 5–7
እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ማስረዳት። አንድን ጥቅስ ስታብራራና በምሳሌ ስታስረዳ አድማጮችህ እውቀት ያገኛሉ። ይሁን እንጂ ይበልጥ ውጤት የሚኖረው ያንን እውቀት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ማስረዳቱ ነው። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱሱን መልእክት ሰምቶ እርምጃ መውሰድ የእያንዳንዱ አድማጭ ኃላፊነት እንደሆነ አይካድም። ይሁንና ምን ማድረግ እንደሚገባቸው እንዲያስተውሉ ልትረዳቸው ትችላለህ። ጥቅሱ ለአድማጮችህ ግልጽ ከሆነላቸውና ከነጥቡ ጋር ያለው ዝምድና ከገባቸው በኋላ በእምነታቸውና በአኗኗራቸው ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እንዲያስተውሉ አድርግ። እየተብራራ ካለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የማይጣጣሙ አስተሳሰቦችን ወይም ድርጊቶችን መተው ምን ጥቅም እንዳለው ጎላ አድርገህ ግለጽ።
ጥቅሱ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ለማስረዳት ስታስብ አድማጮችህ የተለያየ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብህም። ምናልባት ፍላጎት ያሳዩ አዲሶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና ከተለያዩ ችግሮች ጋር የሚታገሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ንግግርህ አድማጮች በሕይወታቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉ እንዲሆን አድርግ። የተወሰኑ ሰዎችን በአእምሮህ ይዘህ እንደምትናገር የሚያስመስል ምክር ከመስጠት ተቆጠብ።
ለተናጋሪው የተተዉ ውሳኔዎች
ንግግርህን በተመለከተ አንዳንዶቹ ነገሮች አስቀድመው ተወስነዋል። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በግልጽ ተቀምጠዋል እንዲሁም እያንዳንዱን ንዑስ ርዕስ ለማብራራት የሚያስፈልገው ጊዜ ተመድቧል። ሌሎቹ ግን ለአንተ የተተዉ ናቸው። አንዳንዶቹን ንዑሳን ነጥቦች ለማብራራት ከሌሎቹ ይልቅ ሰፋ ያለ ጊዜ ትፈልግ ይሆናል። ሁሉንም ንዑስ ነጥብ በእኩል መጠን መሸፈን አለብኝ ብለህ አታስብ። ይህ ትምህርቱን ለመሸፈን ስትል እንድትሯሯጥና አድማጮችህ ሊይዙት ከሚችሉት በላይ ብዙ ሐሳብ እንድትጭንባቸው ሊያደርግ ይችላል። የትኛውን ነጥብ በጥልቀት አብራርተህ የትኛውን ነጥብ በአጭሩ እንደምትጠቅስ ወይም እግረ መንገድህን ጠቆም አድርገህ ብቻ እንደምታልፍ ለመወሰን የሚረዳህ ምንድን ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የንግግሩን ዋና መልእክት ለማስተላለፍ የሚረዱኝ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? አድማጮቼን ይበልጥ ሊጠቅሙ የሚችሉትስ የትኞቹ ናቸው? አንድን ጥቅስና ከዚያ ጋር ዝምድና ያለውን ሐሳብ ባስቀር የማቀርበውን ማስረጃ ያዳክምብኛልን?’
ግምታዊ ሐሳብ ወይም የግል አመለካከት ላለመጨመር ጥንቃቄ አድርግ። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ‘ከራሱ አንዳች አልተናገረም።’ (ዮሐ. 14:10) ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት መጽሐፍ ቅዱስ ሲብራራ ለማዳመጥ እንደሆነ አስታውስ። ጥሩ ተናጋሪ ነው የሚል ስም አትርፈህ ከሆነ እንዲህ ያለ ስም ልታተርፍ የቻልከው የሰዎችን ትኩረት ወደ ራስህ ስለሳብክ ሳይሆን አድማጮችህ በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩሩ ስላደረግህ እንደሆነ እሙን ነው። እንደዚያ ከሆነ ሰዎች የምትሰጠውን ንግግር ያደንቃሉ።—ፊልጵ. 1:10, 11
መሠረታዊ ነጥቦችን ብቻ የያዘውን አስተዋጽኦ በማዳበር ጥቅሶችን በጥልቀት የሚያብራራ ሕያው ንግግር አድርገኸዋል። አሁን ንግግርህን መለማመድ ያስፈልግሃል። ድምፅህን እያሰማህ ብትለማመድ ጥሩ ነው። የልምምዱ ዋና ዓላማ ሁሉም ነጥቦች በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀረጹ ማድረግ ነው። በንግግሩ ተመስጠህ፣ ሕያው አድርገህና ግለት ባለው መንገድ ልታቀርብ ይገባል። ንግግርህን ከማቅረብህ በፊት ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ይህን ንግግር ሳቀርብ ዓላማዬ ምንድን ነው? ዋና ዋና ነጥቦቹ ግልጽ ሆነው ተቀምጠዋልን? ንግግሬ በጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነውን? እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከሚቀጥለው ሐሳብ ጋር በቀላሉ ይያያዛልን? ንግግሩ አድማጮች ለይሖዋና ለዝግጅቶቹ አድናቆት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነውን? መደምደሚያው በቀጥታ ከጭብጡ ጋር የሚዛመድና አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም እንዲሁም ለሥራ የሚያነሳሳ ነውን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ አዎንታዊ ከሆነ ጉባኤውን በሚጠቅምና ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ ‘እውቀትን አሳምረህ ለማቅረብ’ ዝግጁ ነህ ማለት ነው!—ምሳሌ 15:2