ጥናት 31
ሰዎችን ማክበር
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉን እንድናከብርና’ ‘ማንንም እንዳንሰድብ’ ይመክረናል። (1 ጴጥ. 2:16, 17፤ ቲቶ 3:1, 2) ደግሞም ሁሉም ሰው “እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ” የተፈጠረ ነው። (ያዕ. 3:9) በዚህ ምድር ላይ ላለ ለማንኛውም ሰው ክርስቶስ ሞቶለታል። (ዮሐ. 3:16) ሁሉም ሰው እርምጃ እንዲወስድና እንዲድን ምሥራቹን መስማት ይኖርበታል። (2 ጴጥ. 3:9) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በሥልጣን ወይም በሌላ ምክንያት ለየት ያለ አክብሮት ይሰጣቸዋል።
አንዳንዶች ሰዎችን በማክበር ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ከመከተል ወደኋላ የሚሉት ለምን ሊሆን ይችላል? የአካባቢው ባሕል ሰዎችን በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በጤና፣ በዕድሜ፣ በሀብት ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ በመከፋፈል አክብሮት ሊሰጠው የሚገባው ማን እንደሆነ ይወስን ይሆናል። በሕዝብ ባለ ሥልጣናት መካከል ተንሰራፍቶ የሚታየው ሙስና ሰዎች ለሥልጣን ያላቸውን አክብሮት እንዲያጡ አድርጓል። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኛ አይደሉም። ምናልባትም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ብቻ ሌት ተቀን መሥራት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ከዚህም በላይ በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች ለሌሎች አክብሮት የላቸውም። ልጆች ወላጆቻቸውን ሲያሞኙና በእነርሱ ላይ ሲሠለጥኑ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችም በብዙዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዲህ ያለው ዓለማዊ አስተሳሰብ ለሌሎች ያለንን አመለካከት እንዳያዛባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይሁንና ሰዎችን ማክበራችን የመግባባት መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል።
በአክብሮት መቅረብ። በሃይማኖታዊ ተግባር የተሰማራ አንድ ሰው አለባበሱም ሆነ ድርጊቱ ለሰዎች ያለውን አክብሮት የሚያሳይ እንዲሆን ይጠበቅበታል። ሰዎች ተገቢ እንደሆነ የሚቆጥሩት ነገር ከቦታ ቦታ ይለያያል። አንዳንዶች ባርኔጣ አድርጎ ወይም እጅን ኪስ ውስጥ ከትቶ ሰው ፊት መቅረብ አክብሮት የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ያስባሉ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ይህ ምንም ነውር የለውም። ሰዎችን እንዳታስቀይም የአካባቢውን ልማድ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ይህም ምሥራቹን እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሚሆን ነገር ከማድረግ እንድትቆጠብ ይረዳሃል።
ከሰዎች ጋር በተለይም ደግሞ በዕድሜ ከገፉት ጋር ስንነጋገር ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ብዙውን ጊዜ ሰዎቹ ራሳቸው ካልፈቀዱላቸው በስተቀር ወጣቶች አዋቂዎችን በስማቸው ብቻ መጥራታቸው ነውር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። በአንዳንድ አካባቢዎች አዋቂዎችም ቢሆኑ የማያውቋቸውን ሰዎች በስማቸው ብቻ አይጠሩም። ከዚህም በተጨማሪ በብዙ ቋንቋዎች በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ወይም ከባለ ሥልጣኖች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ አክብሮታቸውን ለመግለጽ የአንቱታ ቃላትን ወይም ሌሎች መግለጫዎችን ይጠቀማሉ።
አክብሮት የሚገለጽባቸው የተለያዩ መንገዶች። በአንዳንድ አካባቢዎች መንገድ ላይ ስትሄድም ይሁን አንድ ቤት ስትገባ ለምታገኛቸው ሰዎች ያለህን አክብሮት ለማሳየት በአጭሩ ሰላምታ መስጠት፣ ፈገግ ማለት፣ ባርኔጣን ማንሳት ወይም እጅ መንሳት ይጠበቅብሃል። ሰውን ችላ ብሎ ማለፍ እንደ ንቀት ይቆጠራል።
ይሁንና አንዳንዶች ችላ ባትላቸውም ችላ እንዳልካቸው ሊሰማቸው ይችላል። ለምን? በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንዳልሰጠኻቸው ስለሚሰማቸው ነው። ሰዎችን በውጫዊ ሁኔታቸው ከአንድ ጎራ መመደብ የተለመደ ነገር ነው። ብዙዎች የአካል ጉዳት ወይም ሌላ የጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች ያገልላሉ። ይሁንና የአምላክ ቃል እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች እንዴት ፍቅርና አክብሮት ልናሳያቸው እንደሚገባ ይገልጻል። (ማቴ. 8:2, 3) ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሁላችንም ከአዳም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት የየራሳችን ጉድለት አለን። ሰዎች ሁልጊዜ ጉድለትህን የአንተ መለያ እንደሆነ አድርገው ቢናገሩ እንዳከበሩህ ይሰማሃልን? ከዚህ ይልቅ በመልካም ጎኖችህ ቢያስታውሱህ ደስ አይልህም?
ሌሎችን ማክበር የራስነት ቦታቸውን መቀበልንም ይጠይቃል። በአንዳንድ አካባቢዎች ለቤተሰቡ አባላት ከመመስከራችን በፊት የቤቱን አባወራ ማነጋገር ያስፈልገናል። የመስበክና የማስተማር ተልዕኮ የሰጠን ይሖዋ ቢሆንም አምላክ ልጆችን የማሰልጠን፣ የመገሰጽና የመምራት ሥልጣን የሰጠው ለወላጆች መሆኑን እንገነዘባለን። (ኤፌ. 6:1-4) ከዚህ የተነሣ ብዙውን ጊዜ ከልጆቹ ጋር ሰፊ ውይይት ከመጀመራችን በፊት ከወላጆቻቸው ጋር መነጋገራችን ተገቢ ይሆናል።
ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ላካበቱት ተሞክሮም አክብሮት ልናሳይ ይገባል። (ኢዮብ 32:6, 7) በስሪ ላንካ የምትገኝ አንዲት ወጣት አቅኚ በዚህ ረገድ ለአንድ አረጋዊ ሰው አክብሮት በማሳየቷ ጥሩ ውጤት አግኝታለች። መጀመሪያ ላይ “አንቺን የምታክል አንዲት ፍሬ ልጅ እንዴት እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ልታስተምረኝ ትችላለች?” ሲሉ ተቃውመዋት ነበር። እርሷ ግን “የተማርኩት ነገር በጣም ስላስደሰተኝና ይህንንም ለሰዎች ሁሉ መንገር እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ያንን ላካፍልዎ እንጂ እርስዎን ለማስተማር አልመጣሁም” በማለት መለሰችላቸው። አቅኚዋ በአክብሮት መልስ በመስጠትዋ ሰውዬው የምትናገረውን ለማዳመጥ ጉጉት አደረባቸው። “እሺ እስቲ ንገሪኝ። ምንድን ነው የተማርሽው?” አሏት። እርሷም “ለዘላለም መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምሬአለሁ” በማለት መለሰችላቸው። ከዚህ የተነሳ እኚህ በዕድሜ የገፉ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሁሉ እንደዚህ ይሰማቸዋል ማለት ባይሆንም አብዛኞቹ እንዲህ ዓይነቱ አክብሮት ቢሰጣቸው ደስ ይላቸዋል።
ይሁንና ለሌሎች አክብሮት በማሳየት ረገድ ገደቡን እንዳናልፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የይሖዋ ምሥክሮች በፓስፊክ ደሴቶችና በሌሎችም ቦታዎች የመንደር ወይም የነገድ አለቆችን በተለመደው መንገድ በአክብሮት ማነጋገራቸው ሰሚ ጆሮ እንዲያገኙና አለቆቹንም ሆነ በእነርሱ ሥር የሚተዳደሩትን ሰዎች ለማነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ የሽንገላ አክብሮት ለማሳየት መሞከር ተገቢ አይሆንም። (ምሳሌ 29:5 አ.መ.ት ) በተመሳሳይም በአንድ ቋንቋ ሰዋስው ውስጥ የአክብሮት መግለጫዎች ሊኖሩ ቢችሉም አንድ ክርስቲያን አክብሮቱን ለማሳየት እነዚህን መግለጫዎች በተጋነነ መንገድ መጠቀም አለበት ማለት አይደለም።
ለአድማጮች አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ አነጋገር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተስፋችን ለሚጠይቁን ሰዎች መልስ የምንሰጠው ‘በትሕትናና በአክብሮት’ ሊሆን እንደሚገባ አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ጴጥ. 3:15) የግለሰቡ አመለካከት ስህተት መሆኑን እዚያው ፍርጥ አድርገን መናገር ላይከብደን ይችላል። ይሁንና የሰውዬውን ክብር በሚነካ መንገድ ስህተቱን መግለጻችን ጥበብ ይሆናልን? በመጀመሪያ ሰውዬውን በትዕግሥት ማዳመጥ ምናልባትም ይህን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ መጠየቅና ያንን ስሜቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረዳታችን የተሻለ አይሆንም?
ከአንድ ግለሰብ ጋር ስትነጋገር የምታሳየው አክብሮት መድረክ ላይ ሆነህ ለብዙ አድማጮች በምትናገርበትም ጊዜ ሊንጸባረቅ ይገባል። አንድ ተናጋሪ ለአድማጮቹ አክብሮት ካለው በአነጋገሩ አይነቅፋቸውም ወይም “ስላልፈለጋችሁ እንጂ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ አያቅታችሁም ነበር” የሚል ስሜት በሚያስተላልፍ መንገድ አይናገርም። በዚህ መንገድ መናገር አድማጮችን ተስፋ ከማስቆረጥ ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም። አድማጮቻችን ለይሖዋ ፍቅር ያላቸውና እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች እንደሆኑ ማሰባችን ምንኛ የተሻለ ይሆናል! በመንፈሳዊ የደከሙትን፣ ብዙም ተሞክሮ የሌላቸውን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ለመከተል የሚያመነቱትን ለማገዝ ስንጥር እንደ ኢየሱስ ሁኔታቸውን ለመረዳት መሞከር ይገባናል።
አንድ ተናጋሪ የአምላክን ቃል በተሟላ መንገድ ስለመታዘዝ ሲገልጽ ራሱን ጨምሮ የሚናገር ከሆነ አድማጮቹ እንደሚያከብራቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም ጥቅሱ አድማጮችን የሚጠቅማቸው እንዴት እንደሆነ ስትናገር “እናንተ” የሚለውን መግለጫ ደጋግመህ አለመጠቀምህ ጥበብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል “የቻላችሁትን ሁሉ እያደረጋችሁ ነውን?” በሚለው ጥያቄና “እያንዳንዳችን ‘የምችለውን ሁሉ እያደረግሁ ነውን?’ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ይሆናል” በሚለው ዓረፍተ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። የሁለቱም ጥያቄዎች መልእክት አንድ ነው። ሆኖም የመጀመሪያው ጥያቄ ተናጋሪው ከአድማጮቹ የሚጠበቀው ነገር እርሱን እንደማይመለከት አድርጎ የሚያስብ ያስመስለዋል። ሁለተኛው ጥያቄ ተናጋሪውን ጨምሮ ሁሉም ሰው የየራሱን ሁኔታና ውስጣዊ ግፊት እንዲመረምር የሚያበረታታ ነው።
አድማጮችህን ለማሳቅ ብለህ ብቻ አስቂኝ ነገር ከመናገር ተቆጠብ። ይህ አድማጮች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያላቸውን አክብሮት ሊቀንስ ይችላል። አምላክን ስናገለግል ደስ ሊለን እንደሚገባ የታወቀ ነው። የምናቀርበውም ትምህርት ቢሆን ፈገግ የሚያሰኙ ነጥቦች ይኖሩት ይሆናል። ቁም ነገሩን እንደ ተራ ቀልድ አድርጎ ማቅረብ ግን ለአድማጮችም ሆነ ለአምላክ አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ይሆናል።
ለሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ይሖዋ አስተምሮናል። እንግዲያው ሰዎችን የምንቀርብበት መንገድም ሆነ አነጋገራችን ዘወትር ይህንን የሚያንጸባርቅ ይሁን።