የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 47 ገጽ 247-ገጽ 250 አን. 2
  • በሚታዩ ነገሮች አስደግፎ ማስተማር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በሚታዩ ነገሮች አስደግፎ ማስተማር
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተለመዱ ነገሮችን ምሳሌ አድርጎ መጠቀም
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሞ ማስተማር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • ሰዎችን ማክበር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የቪዲዮ ፊልሞቻችንን ተጠቅማችሁ አስተምሩ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2006
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 47 ገጽ 247-ገጽ 250 አን. 2

ጥናት 47

በሚታዩ ነገሮች አስደግፎ ማስተማር

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የትምህርቱ ቁልፍ ነጥቦች ሕያው ሆነው እንዲታዩ ለማድረግ ሥዕሎችን፣ ካርታዎችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ተጠቀም።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅሞ ማስተማር ብዙውን ጊዜ በአፍ ብቻ ከሚነገረው ቃል ይልቅ መልእክቱ በአእምሮ ውስጥ ግልጽ ሆኖ እንዲሳልና ቶሎ እንዳይረሳ ይረዳል።

ስታስተምር የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅመህ ማስረዳት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግህ በተሻለ መንገድ ለማስተማር ስለሚረዳህ ነው። ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅመው አስተምረዋል። እኛም የእነርሱን ምሳሌ ልንኮርጅ እንችላለን። የምናስተምረውን ትምህርት በሚታይ ነገር አስደግፈን የምናስረዳ ከሆነ አድማጮች በጆሯቸው ብቻ ሳይሆን በዓይናቸው ጭምር ይከታተሉናል። ይህም በትኩረት እንዲከታተሉና ትምህርቱን እንዳይረሱት ለማድረግ ሊረዳ ይችላል። ምሥራቹን በምትሰብክበት ጊዜ የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅመህ ማስተማር የምትችለው እንዴት ነው? ጥሩ አድርገህ እየተጠቀምህባቸው እንደሆነስ እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

ይሖዋና ኢየሱስ በሚታዩ ነገሮች ተጠቅመው ያስተማሩት እንዴት ነው? ይሖዋ በተለያየ ጊዜ የሚታዩ ነገሮችን በመጠቀም የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷል። አንድ ቀን ምሽት አብርሃምን ወደ ሜዳ አውጥቶ “ወደ ሰማይ ተመልከት፣ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቁጠር። . . . ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው።” (ዘፍ. 15:​5) ምንም እንኳ የተሰጠው ተስፋ በሰው ዓይን ሲታይ የማይቻል ነገር ቢመስልም አብርሃም ልቡ ስለተነካ በይሖዋ ላይ እምነት አሳድሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኤርምያስ ወደ አንድ ሸክላ ሠሪ ቤት ሄዶ ሸክላ ሠሪው ለጭቃው ቅርፅ ሲሰጥ እንዲመለከት ልኮት ነበር። ፈጣሪ በሰው ልጆች ላይ ያለውን ሥልጣን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እንዴት የማይረሳ ትምህርት ነው! (ኤር. 18:​1-6) ዮናስ በአንዲት የቅል ዛፍ አማካኝነት ይሖዋ ስለ ምሕረት ያስተማረውን ትምህርት እንዴት ሊረሳ ይችላል? (ዮናስ 4:​6-11) ይሖዋ ነቢያቱ አንዳንድ ቁሳቁሶችን ተጠቅመው ትንቢታዊ መልእክቱን በሠርቶ ማሳያ ጭምር እንዲያቀርቡ ያደረገበት ጊዜ አለ። (1 ነገ. 11:​29-32፤ ኤር. 27:​1-8፤ ሕዝ. 4:​1-17) የማደሪያው ድንኳንና ቤተ መቅደሱም ቢሆኑ በሰማይ ያለውን ሁኔታ እንድናስተውል የሚረዱ ተምሳሌት ናቸው። (ዕብ. 9:​9, 23, 24) አምላክ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተላለፍ ብዙ ራእይዎችንም ተጠቅሟል።​—⁠ሕዝ. 1:​4-28፤ 8:​2-18፤ ሥራ 10:​9-16፤ 16:​9, 10፤ ራእይ 1:​1

ኢየሱስ በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሞ ያስተማረው እንዴት ነው? ፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑ ሰዎች በንግግሩ ሊያጠምዱት በፈለጉ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ዲናር እንዲያመጡለት በመጠየቅ በሳንቲሙ ላይ ያለውን የቄሣር ምስል አሳያቸው። ከዚያም የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ደግም ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንዳለባቸው አስረድቷል። (ማቴ. 22:​19-21) ኢየሱስ ባለን ነገር ሁሉ ይሖዋን ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት ያላትን ሁለት ሳንቲም በቤተ መቅደስ መዝገብ የጣለችን አንዲት ድሀ መበለት እንዲመለከቱ አድርጓል። (ሉቃስ 21:​1-4) በሌላ ጊዜ ደግሞ ስለ ትሕትና ወይም ከሥልጣን ጥመኝነት ስለመራቅ ሲያስረዳ አንድን ሕፃን በመካከላቸው አቁሞ አሳይቷቸዋል። (ማቴ. 18:​2-6) እንዲሁም የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትና ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይቷል።​—⁠ዮሐ. 13:​14

በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሞ ማስተማር። እኛ እንደ ይሖዋ በራእይ አማካኝነት መልእክት ማስተላለፍ አንችልም። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጁዋቸው ጽሑፎች ላይ ብዙ የሚመስጡ ሥዕሎች ይወጣሉ። የምታወያያቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው የገነት ተስፋ ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናቸው እንዲመለከቱት ለመርዳት በእነዚህ ሥዕሎች ተጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ተማሪው ከምትወያዩበት ርዕስ ጋር ግንኙነት ያለውን አንድ ሥዕል ተመልክቶ ምን እንዳስተዋለ እንዲነግርህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ይሖዋ ለአሞጽ ራእይ ሲያሳየው “አሞጽ ሆይ፣ የምታየው ምንድር ነው?” ብሎ እንደጠየቀው ልብ በል። (አሞጽ 7:​7, 8፤ 8:​1, 2) ሰዎች ለማስተማር ታስበው በተዘጋጁት ሥዕሎች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ አንተም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ልትጠይቅ ትችላለህ።

የሒሳብ ስሌቶችን ወይም የዘመናትን ቅደም ተከተል ስታስረዳ በወረቀት ላይ እየጻፍህ የምታሳያቸው ከሆነ በ⁠ዳንኤል 4:​16 ላይ እንደተጠቀሱት “ሰባት ዘመናት” እና በ⁠ዳንኤል 9:​24 ላይ እንደሚገኘው “ሰባ ሱባኤ” ያሉትን ትንቢታዊ መልእክቶች በቀላሉ መረዳት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሥዕላዊ መግለጫዎች በብዙ ጽሑፎቻችን ላይ ይገኛሉ።

ስለ ማደሪያው ድንኳን፣ በኢየሩሳሌም ስለነበረው ቤተ መቅደስ እንዲሁም ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ቤተ መቅደስና ስለመሳሰሉት ነገሮች በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ በምትወያዩበት ጊዜ ሥዕሎችን ብትጠቀሙ ማብራሪያው ይበልጥ ግልጽ ይሆንላችኋል። እንዲህ ያሉትን ሥዕላዊ መግለጫዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ፣ በባለማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ተጨማሪ ክፍል ላይ እንዲሁም በተለያዩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት እትሞች ላይ ማግኘት ትችላለህ።

ከቤተሰብህ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብብ ካርታዎችን ተጠቀም። አብርሃም ከዑር ተነስቶ እስከ ካራን ከዚያም እስከ ቤቴል ያደረገውን ጉዞ በካርታ ላይ ተመልከት። የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲሄድ በየት በየት እንደተጓዘ እንዲሁም ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ርስት ተደርገው የተሰጡት ቦታዎች የትኞቹ እንደሆኑ ካርታ ላይ ለማመልከት ሞክር። የሰሎሞን ግዛት የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚያካልልና ኤልያስ የኤልዛቤልን ዛቻ በሰማ ጊዜ ከኢይዝራኤል አንስቶ ከቤርሳቤህ ማዶ እስከሚገኘው ምድረ በዳ ድረስ የተጓዘበትን መንገድ ካርታ ላይ ለማየት ሞክር። (1 ነገ. 18:​46–19:​4) ኢየሱስ የሰበከባቸውን ከተሞችና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን ጳውሎስ የተጓዘባቸው ቦታዎች ተመልከት።

የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅሞ ማስረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ከጉባኤው አሠራር ጋር እንዲተዋወቅ ለመርዳትም ያስችልሃል። የትላልቅ ስብሰባዎችን ፕሮግራም አሳይተኸው የሚቀርበው ትምህርት ምን እንደሆነ ልትገልጽለት ትችላለህ። ብዙ ሰዎች የመንግሥት አዳራሾችን ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ በመጎብኘታቸው ልባቸው ተነክቷል። ይህ ስለ ሥራችን ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ በመርዳት ረገድ ትልቅ ድርሻ ሊኖረው ይችላል። የመንግሥት አዳራሹን ስታስጎበኛቸው ከሌሎች የአምልኮ ቦታዎች በምን እንደሚለይ አስረዳቸው። የመንግሥት አዳራሾቻችን ብዙ ጌጣጌጥ ያልበዛባቸው ለመማር ምቹ የሆኑ ቦታዎች እንደሆኑ ጎላ አድርገህ ግለጽ። የጽሑፍ ማደያውን፣ የአገልግሎት ክልል ካርታውንና የመዋጮ ሣጥኖቹን (በሌሎች የአምልኮ ቦታዎች ከሚዞረው ሙዳየ ምፅዋት የተለዩ መሆናቸውን) ስለመሳሰሉት ከአገልግሎታችን ጋር የተያያዙ ነገሮች አስረዳው።

የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጁዋቸውን የቪዲዮ ክሮች ማግኘት የምትችል ከሆነ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት ለመገንባት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር እንዲተዋወቁ ለመርዳትና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ለማበረታታት ልትጠቀምባቸው ትችላለህ።

ለብዙ አድማጮች ስታስረዳ። በደንብ ከተዘጋጀህና ጥሩ አድርገህ ማቅረብ ከቻልክ አድማጮችህ ብዙ በሚሆኑበት ጊዜም ቢሆን የሚታዩ ነገሮችን ተጠቅሞ ማስረዳት ግሩም የማስተማሪያ ዘዴ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። ታማኝና ልባም ባሪያ በዚህ መንገድ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አዘጋጅቷል።

የሚጠኑት የመጠበቂያ ግንብ ክፍሎች ብዙውን ጊዜ ሥዕሎች ያሏቸው ሲሆን ጥናቱን የሚመራው ወንድም ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማጉላት በእነዚህ ሥዕሎች ሊጠቀም ይችላል። በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የሚጠኑት ጽሑፎችም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም።

አንዳንድ የንግግር አስተዋጽኦዎች በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሞ ለማስረዳት የሚያመቹ ነጥቦች ይኖሯቸዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አድማጮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚኖራቸው ብዙውን ጊዜ የተሻለ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ እንዲያተኩሩ ብታደርግ ነው። አድማጮች የንግግሩን ቁም ነገር እንዲጨብጡት ስትል ሥዕል ለመጠቀም ወይም ዋና ዋና ነጥቦቹን በወረቀት ጽፈህ ለማሳየት ካሰብህ ከኋላ የተቀመጡት አድማጮች ሳይቀሩ በደንብ ማየት (ማንበብ) ይችሉ እንደሆነ ቀደም ብለህ ማረጋገጥ ያስፈልግሃል። እንዲህ ዓይነቱን ዘዴ መጠቀም የሚኖርብህ አልፎ አልፎ ብቻ ነው።

በምንናገርበትም ሆነ በምናስተምርበት ጊዜ በሚታዩ ነገሮች ተጠቅመን የምናስረዳው አድማጮችን ለማዝናናት በማሰብ አይደለም። ለማስረዳት የምትጠቀምበት ነገር ክብር ያለው ከሆነ ለየት ያለ አጽንዖት እንዲሰጣቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች የሚያጠናክር ይሆናል። እነዚህ ነገሮች የምታስተላልፈውን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ የሚረዱ ወይም የመልእክቱን ክብደት የሚያጠናክሩ ከሆኑ ለንግግርህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ለማስተማር የምትጠቀምበት ነገር ተስማሚ ከሆነና በደንብ ከተገለገልክበት ትምህርቱም ሆነ የተጠቀምህበት ነገር ለብዙ ዓመታት ከአድማጮች አእምሮ አይጠፋም።

ትምህርት በመቅሰም ረገድ የመስማትም ሆነ የማየት ችሎታዎቻችን ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ። ሰዎች የስሜት ሕዋሶቻቸውን እንዲጠቀሙ በማድረግ ይሖዋና ኢየሱስ እንዴት እንዳስተማሩ በማስተዋል አንተም በምታስተምርበት ጊዜ የእነርሱን ምሳሌ ለመኮረጅ ሞክር።

ለማስተማር የምትጠቀምባቸው የሚታዩ ነገሮች . . .

  • አጽንዖት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦችን የሚያጎሉ ወይም ግልጽ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋል።

  • ዋነኛ ዓላማቸው ማስተማር ሊሆን ይገባል።

  • ከመድረክ የምትጠቀምባቸው ከሆነ ደግሞ ለሁሉም አድማጮች በግልጽ የሚታዩ መሆን አለባቸው።

መልመጃ፦ ለማስተማር ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ነገሮች ዝርዝር ከዚህ በታች ጻፍ . . .

ለይሖዋ ድርጅት ያላቸውን አድናቆት ለማሳደግ የሚረዱ

․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․․

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለልጆች ለማስተማር የሚረዱ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ