የቪዲዮ ፊልሞቻችንን ተጠቅማችሁ አስተምሩ
1 ይሖዋ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለጥንት አገልጋዮቹ ለማስተላለፍ ራእዮችንና ሕልሞችን የተጠቀመባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሕዝቅኤል በሰማይ ካለው የይሖዋ ሰረገላ ጋር በተያያዘ ያየውን ራእይ እስቲ አስብ። (ሕዝ. 1:1-28) ዳንኤል የዓለም ኃያል መንግሥታት ሲፈራረቁ የሚያሳየውን ትንቢታዊ ሕልም ከተመለከተ በኋላ ምን እንደተሰማው መገመት ትችላለህ። (ዳን. 7:1-15, 28) “በጌታ ቀን” ውስጥ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች በሚመለከት ለሐዋርያው ዮሐንስ ‘ስለተገለጠው’ አስደናቂ ራእይስ ምን ለማለት ይቻላል? (ራእይ 1:1, 10) ይሖዋ ለሕዝቅኤል፣ ለዳንኤልም ሆነ ለዮሐንስ ደማቅ ቀለማትንና ማራኪ እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም ፈጽሞ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።
2 እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች በምናስተምርበት ጊዜ መልእክቱ ከአእምሯቸው ውስጥ በቀላሉ እንዳይጠፋ ለማድረግ ከፈለግን የቪዲዮ ፊልሞቻችንን መጠቀም እንችላለን። እነዚህ ፊልሞች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሲሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በይሖዋ ድርጅትና ጥሩ ክርስቲያኖች እንድንሆን በሚያስችሉን መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ እምነት እንድንጥል ይረዱናል። እስቲ የቪዲዮ ፊልሞቻችንን ተጠቅመን ማስተማር የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት። የሚከተሉት የቪዲዮ ፊልሞች ለናሙና ያህል የቀረቡ ናቸው።
3 በአገልግሎት ላይ:- ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ስለ ዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረታችን ነግረኸው ታውቃለህ? መላው የወንድማማች ማኅበር የተባለውን የቪዲዮ ፊልም በማሳየት እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። ከቀጣዩ ጥናታችሁ በፊት አይቶት እንዲመጣ ልታውሰው አሊያም አብራችሁ ሆናችሁ ልታዩት ትችላላችሁ። ከዚያም በሰኔ 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚገኙትን የክለሳ ጥያቄዎች አንስታችሁ ተወያዩባቸው።
4 እናንት ወጣቶች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የናዚን ጥቃት በጽናት ተቋቁመዋል ወይም በሶቪዬት ሕብረት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፈተና ወቅት ያሳዩት ጽናት የተባሉትን የቪዲዮ ፊልሞች ለክፍል ጓደኞቻችሁ ለማሳየት አስተማሪያችሁን ማነጋገር ትችላላችሁ። በሰኔ 2001 አሊያም በየካቲት 2003 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች በትንሹ በማስተካከል የጥያቄ ወረቀት ካዘጋጀህ በኋላ እንደምትወያዩበት በመግለጽ ለክፍል ጓደኞችህ አስቀድመህ ልትሰጣቸው ትችላለህ።
5 ከቤተሰብና ከጓደኞቻችሁ ጋር:- ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የወጣቶች ጥያቄ—እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው? የተሰኘውን የቪዲዮ ፊልም ለመጨረሻ ጊዜ የተመለከቱት መቼ ነው? በሚቀጥለው የቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ ለምን ደግማችሁ አታዩትም? በሚያዝያ 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ አስደሳችና ግልጽ የሆነ ውይይት ለማድረግ የሚረዱ ጥያቄዎች ተዘርዝረዋል።
6 ወደ ቤትህ ጋብዘህ ልታጫውታቸው የምትፈልጋቸው የጉባኤ ጓደኞች አሉህ? የይሖዋን ሥልጣን አክብሩ የተሰኘውን የቪዲዮ ፊልም አብራችሁ ብትመለከቱ በተለይ ደግሞ በመስከረም 2004 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሰፈሩትን ጥያቄዎች ተጠቅማችሁ ያገኛችሁትን ትምህርት ብትከልሱ የሚያንጽ ጊዜ ማሳለፍ ትችላላችሁ።
7 ሌሎች አጋጣሚዎች:- የተዘጋጁልንን ሃያ የቪዲዮ ፊልሞች በጥሩ ሁኔታ እንድንጠቀም የሚያስችሉን ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግለት ሰው ከቪዲዮ ፊልሞቻችን መካከል አንዱን አሊያም ሁለቱን መመልከቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዳው ይሆን? በአካባቢያችሁ አረጋውያንን መንከባከቢያ ማዕከልን የመሳሰሉ ተቋማት ካሉ ፊልሞቹን ለማሳየት ለምን ሐሳብ አታቀርብም? የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑት ዘመዶችህ፣ ጎረቤቶችህ አሊያም የሥራ ባልደረቦችህ እነዚህን ፊልሞች ማሳየትህ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ያስችልህ ይሆን? የቪዲዮ ፊልሞቻችን በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ፣ ትምህርት የሚሰጡና ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች በመሆናቸው ተጠቀሙባቸው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. ይሖዋ የጥንት አገልጋዮቹን በሚታዩ ነገሮች አስደግፎ ያስተማራቸው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
2. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለማስተማር ምን መጠቀም እንችላለን?
3. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስለ ይሖዋ ድርጅት እንዲያውቅ ለመርዳት ምን መጠቀም ትችላለህ?
4. አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በትምህርት ቤት ውስጥ የትኞቹን የቪዲዮ ፊልሞች መጠቀም ይችላል?
5. ወላጆች በቤተሰብ ጥናት ወቅት ምን መጠቀም ይችላሉ?
6. ከጓደኞችህ ጋር የሚያንጽ ጊዜ ለማሳለፍ ምን ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ?
7. የቪዲዮ ፊልሞቻችንን እንድትጠቀም የሚያስችሉህ ምን ሌሎች አጋጣሚዎች አሉ?