ጥናት 46
የተለመዱ ነገሮችን ምሳሌ አድርጎ መጠቀም
የምትጠቀምበት ምሳሌ ምንም ይሁን ምን ከትምህርቱ ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ጥሩ ውጤት እንዲኖረው ከተፈለገ ከትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ከአድማጮችም ሁኔታ ጋር ሊጣጣም ይገባል።
ንግግር ስትሰጥ የምትጠቀምባቸውን ምሳሌዎች በመምረጥ ረገድ የአድማጮችህ ማንነት ወሳኝ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያደርግ ነበር? እርሱን ለመስማት ለሚሰበሰቡት ሰዎችም ይሁን ለደቀ መዛሙርቱ ንግግር ሲሰጥ የሚጠቀምባቸው ምሳሌዎች በእስራኤል ምድር የሚኖር ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚያውቃቸው ነበሩ። በሌሎች ባሕሎች ብቻ የሚታወቁ ነገሮችን እንደ ምሳሌ ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ ለአድማጮቹ እንግዳ ይሆንባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ ግብፅ የቤተ መንግሥት ሕይወት ወይም ስለ ሕንድ ሃይማኖታዊ ልማድ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም። ያም ሆኖ ምሳሌዎቹ በሁሉም አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ከሚያውቋቸው ነገሮች ጋር የተያያዙ ነበሩ። ልብስ ስለ መጣፍ፣ ስለ መነገድ፣ ውድ ዕቃ ስለጠፋበት ሰው እንዲሁም ለሠርግ ስለ መታደም ጠቅሷል። ሰዎች የተለያየ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን እንደሚሰማቸው ያውቅ ስለነበር ምሳሌዎቹም ይህንኑ የሚያንጸባርቁ ነበሩ። (ማር. 2:21፤ ሉቃስ 14:7-11፤ 15:8, 9፤ 19:15-23) ኢየሱስ በዋነኝነት ይሰብክ የነበረው ለእስራኤል ሕዝብ ስለሆነ በምሳሌዎቹ የሚጠቅሰው በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያዩአቸውንና የሚያደርጓቸውን ነገሮች ነበር። ከዚህ የተነሳ ስለ ግብርና፣ በበጎችና በእረኛቸው መካከል ስላለው ግንኙነት እንዲሁም ከእንስሳት ቆዳ የተሠራ አቁማዳ ለወይን ጠጅ ማከማቻነት እንዴት እንደሚያገለግልና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ጠቅሷል። (ማር. 2:22፤ 4:2-9፤ ዮሐ. 10:1-5) በተጨማሪም አድማጮቹ የሚያውቋቸውን ታሪኮች እየጠቀሰ ተናግሯል። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት መፈጠር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የሰዶምና ጎሞራ ጥፋት እንዲሁም የሎጥ ሚስት አሟሟት ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። (ማቴ. 10:15፤ 19:4-6፤ 24:37-39፤ ሉቃስ 17:32) አንተስ የምትጠቀምባቸውን ምሳሌዎች ስትመርጥ በአድማጮችህ ዘንድ የተለመዱ ተግባሮችን እንዲሁም ባሕላቸውን ግምት ውስጥ ታስገባለህ?
ለአንድ ሰው ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ እየተናገርህ ቢሆንስ? ለእነዚህ ሰዎች የሚስማማ ምሳሌ ለመምረጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት ሲመሠክር ‘የሕይወት ውኃ፣’ “ለዘላለም አይጠማም” እንዲሁም “ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ” የሚሉትን አነጋገሮች ተጠቅሟል። እነዚህ ሁሉ ከሴትዮዋ ሥራ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ናቸው። (ዮሐ. 4:7-15) መረባቸውን ሲያጥቡ ካገኛቸው ሰዎች ጋር ሲነጋገር የተጠቀመባቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች ከዓሣ ማጥመድ ሥራ ጋር የተያያዙ ነበሩ። (ሉቃስ 5:2-11) ሳምራዊቷ ሴትም ሆነች ዓሣ አጥማጆቹ የሚኖሩበት ኅብረተሰብ በግብርና የሚተዳደር ስለነበር ስለ ግብርና የሚጠቅሱ ምሳሌዎችን ሊጠቀም ይችል ነበር። ሆኖም በቀጥታ ከሰዎቹ ሥራ ጋር የተያያዘ ምሳሌ መጥቀሱ ነጥቡ ቁልጭ ብሎ እንዲታያቸው አድርጓል። አንተስ እንዲህ ለማድረግ ትጥራለህ?
ኢየሱስ የሰበከው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ የተላከው ለእስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብም ጭምር ነበር። (ማቴ. 15:24፤ ሥራ 9:15) ታዲያ ይህ ጳውሎስ በሚጠቀምባቸው ምሳሌዎች ላይ ያመጣው ለውጥ ነበር? አዎን። በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ ስለ ሩጫ ውድድር፣ በጣዖት ቤት ተገኝቶ ስለመመገብ እንዲሁም ስለ ድል ሰልፍ ጠቅሷል። እነዚህ ምሳሌዎች ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች በደንብ የሚያውቋቸው ነገሮች ነበሩ።—1 ቆሮ. 8:1-10፤ 9:24, 25፤ 2 ቆሮ. 2:14-16
እንደ ኢየሱስና እንደ ጳውሎስ የምታስተምርባቸውን ምሳሌዎች በጥንቃቄ ትመርጣለህ? የአድማጮችህን ሕይወትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ታስገባለህ? እርግጥ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ወዲህ በዓለም ላይ ብዙ ለውጦች ተካሂደዋል። ብዙ ሰዎች በቴሌቪዥን አማካኝነት የዓለምን ዜና ስለሚከታተሉ በተለያዩ አገሮች ስላሉት ሁኔታዎች ያውቃሉ። አድማጮችህ ይህ አጋጣሚ ካላቸው በዜና የሰማሃቸውንና ያየሃቸውን ነገሮች እንደ ምሳሌ ብትጠቅስ ምንም አይደለም። ያም ሆኖ ሰዎች ልባቸው ይበልጥ የሚነካው ከግል ሕይወታቸው ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማለትም ስለ ቤታቸው፣ ስለ ቤተሰባቸው፣ ስለ ሥራቸው፣ ስለሚመገቡት ምግብና ስለ አካባቢያቸው የአየር ጠባይ ቢጠቀስ ነው።
አድማጮች የተጠቀምህበትን ምሳሌ እንዲረዱት ብዙ ማብራራት የሚያስፈልግህ ከሆነ የጠቀስከው ነገር በእነርሱ ዘንድ የተለመደ አይደለም ማለት ነው። እንዲህ ያለው ምሳሌ የትምህርቱን ቁም ነገር ያድበሰብስብሃል። ከዚህ የተነሣ አድማጮችህ ልታስተምር የፈለግኸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ረስተው ምሳሌውን ብቻ ሊያስታውሱ ይችላሉ።
ኢየሱስ እንደ ምሳሌ የተጠቀመው ቀላልና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉዳዮችን እንጂ የተወሳሰቡ ነገሮችን አልነበረም። ከባድ ወይም ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስረዳት ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ኢየሱስ ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጋር በማዛመድ ትምህርቱን እንዲረዱትና እንዲያስታውሱት አድርጓል። ይህ የማስተማር ዘዴ ልንኮርጀው የሚገባ እንዴት ግሩም ምሳሌ ነው!