የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • rj ክፍል 5 ገጽ 12-15
  • ‘ወደ ነፍስህ እረኛና ጠባቂ ተመለስ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ወደ ነፍስህ እረኛና ጠባቂ ተመለስ’
  • ወደ ይሖዋ ተመለስ
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ወደ እኔ ተመለሱ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ጠንካራ ያደርግሃል
    ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’
  • ጠንካራ ያደርግሃል
    ለይሖዋ ዘምሩ
  • ይሖዋ ውድ አድርጎ ይመለከትሃል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
ለተጨማሪ መረጃ
ወደ ይሖዋ ተመለስ
rj ክፍል 5 ገጽ 12-15

ክፍል አምስት

‘ወደ ነፍስህ እረኛና ጠባቂ ተመለስ’

በዚህ ብሮሹር ላይ ከተገለጹት ፈተናዎች መካከል አንተን ያጋጠመህ አለ? ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰብህ አንተ ብቻ አይደለህም። ጥንትም ሆነ በዘመናችን የኖሩ በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ተመሳሳይ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። እንደዚህ ያሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሸነፍ ከይሖዋ እርዳታ እንዳገኙ ሁሉ አንተም የእሱን እርዳታ ማግኘት ትችላለህ።

ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስታስብ እሱ እጁን ዘርግቶ ይጠብቅሃል

ወደ ይሖዋ ለመመለስ ስታስብ እሱ እጁን ዘርግቶ እንደሚጠብቅህ እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ ጭንቀትን እንድትቋቋም፣ ስሜትህ ተጎድቶ ከነበረ ጠባሳው እንዲሽር እንዲሁም ከንጹሕ ሕሊና የሚገኘው የአእምሮና የልብ ሰላም እንዲኖርህ ይረዳሃል። ይህ መሆኑ ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ሆነህ እንደገና ይሖዋን ለማገልገል ሊያነሳሳህ ይችላል። ሁኔታህ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ከጻፈላቸው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጋር ይመሳሰላል፦ “እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።”—1 ጴጥሮስ 2:25

ወደ ይሖዋ መመለስ ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ እንደሆነ አትጠራጠር። ለምን? ምክንያቱም መመለስህ የይሖዋን ልብ ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ ስሜት ያለው አምላክ ነው፤ በመሆኑም የምናደርገው ነገር ሊያስደስተው ወይም ሊያሳዝነው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እንድንወደውና እንድናገለግለው አያስገድደንም። (ዘዳግም 30:19, 20) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልብ ከውጭ በኩል መክፈቻ የለውም። መከፈት ያለበት ከውስጥ ነው።” ይሖዋን በፍቅር በተሞላ ልብ ተገፋፍተን ስናመልክ የልባችንን በር ለመክፈት እንደመረጥን እናሳያለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋ ውድ ስጦታ እንሰጠዋለን፤ በሌላ አባባል ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ ልቡን በጣም እናስደስተዋለን። በእርግጥም ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ በመስጠት የምናገኘው ደስታ ከምንም ነገር ጋር አይወዳደርም።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ራእይ 4:11

ከጉባኤ ርቃ የቆየችን እህት የጉባኤው አባላት ሞቅ ባለ መንገድ ሲቀበሏት

ከዚህም በላይ በክርስቲያናዊ አምልኮ እንደገና መካፈል ስትጀምር መንፈሳዊ ፍላጎትህ ይሟላል። (ማቴዎስ 5:3) በምን መንገድ? በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ‘የተፈጠርነው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል። ስለ ሕይወት ዓላማ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጓጓሉ። የሰው ልጆች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች የምናነሳው ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ስለፈጠረን ነው። እሱን በማገልገል እርካታ ማግኘት እንድንችል ተደርገን ተፈጥረናል። ይሖዋን የምናመልከው በፍቅር ተነሳስተን እንደሆነ ከማወቅ የሚበልጥ አስደሳች ነገር ሊኖር አይችልም።—መዝሙር 63:1-5

ምንጊዜም ቢሆን አንድ ነገር አትርሳ፤ ይሖዋ ወደ እሱ እንድትመለስ በጣም ይፈልጋል። ይህን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይህን ብሮሹር ለማዘጋጀት ብዙ መጸለይ አስፈልጓል፤ እንዲሁም በጥሞና ታስቦበታል። ብሮሹሩ አንተ እጅ እንዲገባ ያደረገው ደግሞ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ወይም የእምነት አጋርህ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ብሮሹሩን ለማንበብና በውስጡ ያለውን ሐሳብ በሥራ ላይ ለማዋል ተነሳሳህ። ይህ ሁሉ፣ ይሖዋ እንዳልረሳህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። በደግነት ወደ ራሱ እየሳበህ ነው።—ዮሐንስ 6:44

ይሖዋ የጠፉ አገልጋዮቹን ፈጽሞ እንደማይረሳ ማወቃችን ያጽናናናል። ዶና የምትባል አንዲት እህት ይህን ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከእውነት ቀስ በቀስ እየራቅኩ ብሄድም በ​መዝሙር 139:23, 24 ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስል ነበር፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ። መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም ሐሳቦች እወቅ። በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።’ ዓለም ለእኔ እንደማይሆን ገብቶኝ ነበር፤ እዚያ ሆኜ ባይተዋርነት ይሰማኝ ነበር። በመሆኑም መኖር ያለብኝ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይሖዋ መቼም ቢሆን እንዳልተወኝ ማስተዋል ጀመርኩ፤ ከእኔ የሚጠበቀው ወደ እሱ መመለስ ነው። ደግሞም በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ!”

“ይሖዋ መቼም ቢሆን እንዳልተወኝ ማስተዋል ጀመርኩ፤ ከእኔ የሚጠበቀው ወደ እሱ መመለስ ነው”

አንተም ይሖዋ የሚሰጠውን ደስታ እንደገና እንድታጣጥም ልባዊ ጸሎታችን ነው። (ነህምያ 8:10) ወደ ይሖዋ በመመለስህ ፈጽሞ አትቆጭም።

ወደ ይሖዋ መመለስ —ጥያቄዎችህና መልሶቻቸው

መጀመሪያ ምን ላድርግ?

ከጉባኤ ርቃ የቆየች እህት መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ

ጤንነቱ የተጓደለ አንድ ሰው ቀድሞ ያከናውናቸው ወደነበሩት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የሚመለሰው ቀስ በቀስ ነው። አንተም በየቀኑ ጥቂት መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ጥረት በማድረግ መንፈሳዊ ብርታት ማግኘት ትችላለህ። ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ማድረግ እንዳለብህ አይሰማህ። ለጥቂት ደቂቃዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወይም የተቀዳውን ንባብ ማዳመጥ፣ ከጽሑፎቻችን አንዱን ማጥናት፣ jw.org የተባለውን ድረ ገጽ መቃኘት ወይም በ​jw.org ላይ ከሚተላለፉት ፕሮግራሞች መካከል አንዱን ማየት ትችል ይሆናል። በተጨማሪም ዛሬ ነገ ሳትል በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥረት አድርግ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ በጸሎት ቀርበህ እንዲረዳህ ለምነው። ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣል፤ ምክንያቱም እሱ ስለ አንተ ያስባል።’—1 ጴጥሮስ 5:7

“በመንፈሳዊ ከተዳከምኩ በኋላ ለመጸለይ እንኳ በጣም እሸማቀቅ ጀመር። እንደምንም ራሴን አደፋፍሬ ስጸልይ ግን አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አነጋገረኝ። እሱም ይሖዋ ተስፋ እንዳልቆረጠብኝ እንድገነዘብ ረዳኝ። ሽማግሌው መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ለማንበብ እንድጥር ሐሳብ አቀረበልኝ። ይህን ሳደርግ እንደገና ወደ ስብሰባዎች ለመሄድ ብርታት አገኘሁ። ከጊዜ በኋላ እንደቀድሞው በአገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ይሖዋ ተስፋ ስላልቆረጠብኝ በጣም ደስተኛ ነኝ።”—ኤቫ

ጉባኤው እንዴት ይቀበለኝ ይሆን?

የጉባኤው አባላት ሞቅ ያለ አቀባበል እንደሚያደርጉልህ እርግጠኛ ሁን። አንተን ከመተቸት ወይም በአንተ ላይ ከመፍረድ ይልቅ እንደሚወዱህ የሚያረጋግጡልህ ከመሆኑም ሌላ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ያበረታቱሃል።—ዕብራውያን 10:24, 25

“ወደ መንግሥት አዳራሹ እንደገና መሄድ አሳፍሮኝ ነበር። ‘ወንድሞችና እህቶች እንዴት ይቀበሉኝ ይሆን?’ ብዬ ሰግቼ ነበር። ከ30 ዓመታት በፊት በጉባኤው የነበሩ አንዲት አረጋዊት እህት ‘ልጄ፣ ወደ ቤትህ እንኳን ደህና መጣህ!’ አሉኝ። ይህን ስሰማ ልቤ በጣም ተነካ። በእርግጥም ወደ ቤቴ እንደተመለስኩ ተሰማኝ።”—ሃቪዬር

“ወደ መንግሥት አዳራሹ ሄድኩና ማንም እንዳያየኝ ከኋላ ተቀመጥኩ። ይሁን እንጂ በልጅነቴ ስብሰባዎች ላይ ስገኝ የሚያውቁኝ ብዙዎች አስታወሱኝ። ሞቅ ባለ መንገድ ሲቀበሉኝና እቅፍ ሲያደርጉኝ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ ሰላም ተሰማኝ። ወደ ቤቴ ተመልሼ የመጣሁ ያህል ነበር።”—ማርኮ

ሽማግሌዎች የሚረዱኝ እንዴት ነው?

ሽማግሌዎች በደግነት ይቀበሉሃል። “መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር” እንደገና ለማቀጣጠል በመፈለግህ ያመሰግኑሃል። (ራእይ 2:4) የፈጸምከውን ማንኛውንም ስህተት ማረም እንድትችል ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድና “በገርነት መንፈስ” ይረዱሃል። (ገላትያ 6:1፤ ምሳሌ 28:13) ሽማግሌዎች ለዘላለም በደስታ ኑር! ወይም ወደ ይሖዋ ቅረብ እንደሚሉት ያሉትን መጻሕፍት አንድ ክርስቲያን እንዲያስጠናህ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንደሚያጽናኑህና በምትወስደው በእያንዳንዱ እርምጃ እንደሚደግፉህ እርግጠኛ ሁን።—ኢሳይያስ 32:1, 2

“ከጉባኤ በራቅኩባቸው ስምንት ዓመታት ውስጥ ሽማግሌዎች እኔን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም ነበር። አንድ ቀን፣ አንድ ሽማግሌ አብረን የተነሳናቸውን አንዳንድ ፎቶግራፎች አሳየኝ። ፎቶግራፎቹን ስመለከት በርካታ ግሩም ትዝታዎች ወደ አእምሮዬ መጡ፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን በማገለግልበት ወቅት የነበረኝን ደስታ መልሼ ለማግኘት እንድጓጓ አደረገኝ። ሽማግሌዎቹ እንደገና መንፈሳዊ ልማድ እንዳዳብር በፍቅር ረዱኝ።”—ቪክተር

“ጠንካራ ያደርግሃል”

ሁለት እህቶች በጉባኤ ስብሰባ ላይ በአንድ መዝሙር መጽሐፍ ሲዘምሩ

ለይሖዋ ‘በደስታ ዘምሩ’ የተባለው የመዝሙር መጽሐፋችን እንደ ቀድሞው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈልህን ስትቀጥል ሊያበረታቱህ የሚችሉና ልብ የሚነኩ በርካታ መዝሙሮችን ይዟል። የመዝሙር 38⁠ን ግጥም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በ​1 ጴጥሮስ 5:10 ላይ የተመሠረተው ይህ መዝሙር “ጠንካራ ያደርግሃል” የሚል ርዕስ አለው።

  1. አምላክ ምክንያት ኖሮት እውነትን አሰማህ፤

    ከጨለማ ወደ ብርሃን ጠራህ።

    የልብህን ምኞት እሱን መሻትህን፣

    አስተዋለ ጽድቅን መውደድህን።

    ፈቃዱን ለማድረግ ቃል ገብተሃል፤

    እንደ ቀድሞ ዛሬም ይረዳሃል።

  2. ውድ ልጁን አምላክ ላንተ ሲል ሰጥቶሃል፤

    እንዲሳካልህም ይፈልጋል።

    ውድ ልጁን ላንተ መስጠት ካላሳሳው፣

    ያጸናሃል አትጠራጠረው።

    እምነትና ፍቅርህን አይረሳም፤

    መንከባከቡን አያቋርጥም።

    (አዝማች)

    በ’የሱስ ደም ገዝቶሃል፣ የራሱም አ’ርጎሃል፤

    እናም ያጸናሃል፤ ያጠነክርሃል።

    እንደ ቀድሞው ይመራሃል፤ ይጠብቅሃል።

    አዎ ያጸናሃል፤ ያጠነክርሃል።

ለይሖዋ ዘምሩ—በሰዎች ድምፅ የተዘመረ

ይህን መዝሙርና ሌሎች የመንግሥቱ መዝሙሮችን በተለያዩ ቋንቋዎች ለመስማት jw.org​ን ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ