የክርስትና አምልኮ ከሁሉ የበለጠ የሆነው ለምንድን ነው?
ከዕብራውያን መልዕክት የተገኙ ዋና ዋና ነጥቦች
ይሖዋ አምላክ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር በላከ ጊዜ ከሁሉ የላቁ የአምልኮ ገጽታዎችን አስተዋወቀ። ይህም የሆነው የክርስትና መስራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክትም ሆነ ከሙሴ የበለጠ ስለሆነ ነው። የክርስቶስ ክህነት በጥንትዋ እሥራኤል ከነበረው የሌዋውያን ክህነት ጋር ሲወዳደር በጣም የላቀ ነበር። የኢየሱስም መሥዋዕት በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርብ ከነበረው የእንስሳት መሥዋዕት በጣም የበለጠ ነበር።
እነዚህ ነጥቦች ለዕብራውያን በተጻፈው መልእክት በግልጽ ተብራርተዋል። ይህ መልእክት በ61 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማ ሆኖ የጻፈውና ወደ አይሁዳውያን አማኞች የላከው ይመስላል። ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የግሪክና የእስያ ክርስቲያኖች የዚህ ደብዳቤ ፀሐፊ ጳውሎስ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ፀሐፊው ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር በደንብ የሚተዋወቅ መሆኑና በሐዋርያው ጽሑፎች ሁሉ ላይ የሚታየው ማብራሪያዎችን ምክንያታዊ በሆነ ቅደም ተከተል ማቅረብ በዚህም መልእክት ላይ የሚታይ መሆኑ ይህንን እምነት ያጠናክረዋል። ስሙን ሳይገልጽ ያለፈው አይሁዳውያን በእርሱ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራቸውና “የአሕዛብ ሐዋርያ” ይባል ስለነበረ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 11:13) አሁን ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ በተገለጸው መሰረት ክርስትና ብልጫ ያገኘባቸውን የአምልኮ ገጽታዎች እንመልከት።
ክርስቶስ ከመላእክትም ሆነ ከሙሴ ይበልጣል
በመጀመሪያ የተገለጸው የአምላክ ልጅ ያለው ከፍተኛ ደረጃ ነበር። (1:1 እስከ 3:6) መላእክት ይሰግዱለታል። ንግሥናውም ከአምላክ የተገኘ ነው። ስለዚህ ልጁ ለተናገራቸው ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባናል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሰው ሲሆን ከመላእክት ዝቅ ቢልም በኋላ ከመላእክት ሁሉ የበለጠ ሆኖ ከፍ እንደተደረገና ወደፊት የሰው መኖሪያ የምትሆነው ምድር ግዛት እንደተሰጠው ማስታወስ ይኖርብናል።
በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙሴ ይበልጣል። እንዴት? ሙሴ በእስራኤላውያን የአምላክ ቤት ውስጥ አገልጋይ ብቻ ነበር። ኢየሱስ ግን ይሖዋ አምላክ የዚህ ቤት ወይም የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤ የበላይ አድርጎታል።
ክርስቲያኖች ወደ አምላክ ዕረፍት ይገባሉ
ሐዋርያው ቀጥሎ ወደ አምላክ ዕረፍት መግባት እንደሚቻል ገለጸ። (3:7 እስከ 4:13) ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡት እሥራኤላውያን ባለመታዘዛቸውና እምነት የለሽ በመሆናቸው ወደ ዕረፍቱ ለመግባት አልቻሉም። እኛ ግን በአምላክ ብናምንና በታዛዥነት ክርስቶስን ብንከተል ወደዚህ ዕረፍት ለመግባት እንችላለን። በዚያ ጊዜ እንደነበረው ሳምንታዊ ሰንበት ከማክበር ይልቅ በየቀኑ ከስስት ሥራዎች ሁሉ ከማረፍ በሚገኘው በረከት እንደሰታለን።
ወደ አምላክ ዕረፍት መግባት “ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ” የሚወጋው የአምላክ ቃል ከሚሰጠን ተስፋዎች አንዱ ነው። የአምላክ ቃል ይህን የሚያደርገው የሰዎችን ዝንባሌና ግፊት እንዲሁም ሥጋዊ ፍላጎቶችንና የአእምሮ ዝንባሌዎችን ጠልቆ በመመርመርና በመከፋፈል ነው። (ከሮሜ 7:25 ጋር አወዳድር) “ነፍሳችን” ወይም የግለሰብ ሕይወታችን አምላካዊ “መንፈስ” ወይም ዝንባሌ ከታከለበት ወደ አምላክ ዕረፍት ለመግባት እንችላለን።
የተሻለ ክህነትና ቃል ኪዳን
ጳውሎስ ቀጥሎ የሚገልጸው የክርስቶስ ክህነትና አዲሱ ቃል ኪዳን ያለውን ብልጫ ነው። (4:14 እስከ 10:31) ምንም ዓይነት ኃጢአት ያልነበረበት ኢየሱስ እንደ እኛ በሁሉ ነገር ስለተፈተነ ለኃጢአተኞቹ የሰው ልጆች ይራራል። ከዚህም በላይ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት” የዘላለም ሊቀ ካህን እንዲሆን አምላክ ሾሞታል። ኢየሱስ እንደ ሌዋውያን ካህናት የሚጠፋ ሕይወት ስለሌለው በአዳኝነት ሥራው ወራሽ አያስፈልገውም። በጣም ከፍተኛ የሆነውንና ኃጢአት የሌለበትን ሥጋውን ሰጥቶ ከደሙ ዋጋ ጋር ወደ ሰማይ ስለገባ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም።
በኢየሱስ ደም የተመረቀው አዲስ ቃል ኪዳን ከሕጉ ቃል ኪዳን ብልጫ አለው። በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉ ሁሉ የአምላክ ሕግ በልባቸው ውስጥ የተጻፈባቸው ስለሆኑ የኃጢአት ይቅርታ ያገኛሉ። (ኤርምያስ 31:31-34) ለዚህም ያላቸው አመስጋኝነት ስለ ተስፋቸው ለሰዎች እንዲናገሩና ከእምነት ባልደረቦቻቸው ጋር እንዲሰበሰቡ ይገፋፋቸዋል። ወደው ኃጢአት የሚሰሩ ግን ወደፊት ምንም ዓይነት መሥዋዕት አይቀርብላቸውም።
እምነት በጣም አስፈላጊ ነው
በጣም ከፍተኛ ከሆነው አዲስ ቃል ኪዳን ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን እምነት ያስፈልገናል። (10:32 እስከ 12:29) በተጨማሪም ይሖዋ የሰጠንን ተስፋ ለማግኘት ከፈለግን መጽናት ያስፈልገናል። እንድንጸና የሚያበረታቱን ከክርስትና በፊት የነበሩ ‘እንደ ታላቅ ዳመና’ ያሉ ምሥክሮች በዙሪያችን አሉልን። በተለይ ግን ክርስቶስ ያሳለፈውን እንከን የሌለበት ሕይወት በቅርብ መከታተል ይኖርብናል። አምላክ እንዲደርስብን የሚፈቅደው ማንኛውም መከራ የሰላም ፍሬ የሆነውን ጽድቅ የሚያስገኝልን ተግሣጽ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። የይሖዋ ተስፋ አስተማማኝ መሆኑ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ‘በአምላካዊ ፍርሐትና አክብሮት’ እንድናቀርብ ሊገፋፋን ይገባል።
ጳውሎስ ደብዳቤውን የሚደመድመው የማበረታቻ ምክር በመስጠት ነው። (13:1-25) እምነት የወንድማማች ፍቅር እንድናሳይ፣ እንግዳ ተቀባዮች እንድንሆን፣ ችግር ያለባቸውን አማኞች እንድናስብ፣ ጋብቻን በአክብሮት እንድንጠበቅ፣ አሁን ባገኘነው ነገር እንድንረካ ሊገፋፋን ይገባል። በጉባኤ ውስጥ የሚመሩትን ወንድሞች እምነት መምሰልና እነርሱንም መታዘዝ ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ክህደትን ማስወገድ፣ ኢየሱስ የተሸከመውን ስድብ መሸከም፣ ሁልጊዜ ለአምላክ የምሥጋና መሥዋዕት ማቅረብና መልካም ሥራ በመስራት መጽናት ይገባናል። እንደነዚህ ያለው አኗኗርም እውነተኛውን የክርስትና እምነት የላቀ ያደርገዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የተለያዩ ጥምቀቶች፦ በእሥራኤላውያን ቤተ መቅደስ ይፈጸም የነበረው አምልኮ “ምግብን፣ መጠጥንና የተለያዩ ጥምቀቶችን” ብቻ የሚመለከት ነበር። (ዕብራውያን 9:9, 10 አዓት) እነዚህ ጥምቀቶች የሙሴ ሕግ የሚያዛቸውን የመታጠብ ሥነ ስርዓቶች ለመንጻት የራስን ልብስና ገላ መታጠብ ያስፈልግ ነበር። (ዘሌዋውያን 11:32፤ 14:8, 9፤ 15:5) ካህናት ይታጠቡ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡባቸው ነገሮች ሁሉ ውሃ ውስጥ መነከር ነበረባቸው። (ዘፀአት 29:4፤ 30:17-21፤ ዘሌዋውያን 1:13፤ 2 ዜና 4:6) ይሁን እንጂ ‘የተለያዩት ጥምቀቶች’ መሲሑ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አንዳንድ አይሁዳውያን ይፈጽሙ የነበረውን ‘ጽዋንም፣ ማድጋንም፣ የናስ ዕቃንም’ የማጠብ ልማድ አይጨምርም። በተጨማሪም ዕብራውያን 9:10 የአጥማቂው ዮሐንስን የውሃ ጥምቀትም ሆነ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት የሚያደርጉትን የውሃ ጥምቀት አያመለክትም።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ማርቆስ 7:4፤ ሉቃስ 3:3