ይሖዋ ቶሎ እንዲረዳን የምናሰማውን አጣዳፊ ጩኸት ይሰማል
እርዳታ በአስቸኳይ አስፈላጊ ሆኖ ነበር። በንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ፊት ላይ የሚታየው ታላቅ ሐዘን ይህን ያሳያል። ጠጅ አሳላፊው ምን ሆነሃል ተብሎ ሲጠየቅ ኢየሩሳሌምና ግንቦችዋ ፈርሰው በመቅረታቸው የተሰማውን ሐዘን ተናገረ። በዚያኑ ጊዜም ‘ምን ትለምናለህ?’ የሚል ጥያቄ ቀረበለት። ጠጅ አሳላፊው ነህምያ “እኔም [ወዲያውኑ (አዓት)] ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ” በማለት በኋላ ጽፏል። ይህ ፈጣንና ከይሖዋ እርዳታ ለማግኘት ድምጽ ሳይሰማ የተደረገ አጣዳፊ ጩኸት ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ ወዲያውኑ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ግንቦች እንዲሠራ ሥልጣን ሰጠው።—ነህምያ 2:1-6
አዎን፣ አምላክ የሚያፈቅሩት ሰዎች የሚያቀርቧቸውን አጣዳፊ ልመናዎች ይሰማል። (መዝሙር 65:2) ስለዚህ የሚደርስብህ ፈተና ልትሸከመው ከምትችለው በላይ እንደሆነ ሆኖ ቢሰማህ መዝሙራዊው ዳዊት መለኮታዊው እርዳታ ባስቸኳይ ባስፈለገው ጊዜ እንደጸለየው በመዝሙር 70 ላይ እንዳለው ያለ ጸሎት ልታቀርብ ትችላለህ። የዚህ መዝሙር መግቢያ የመዝሙሩ ዓላማ “ለመታሰቢያ” እንደሆነ ያሳያል። ጥቂት ለውጦችን ብቻ በማድረግ የመዝሙር 40:13-17ን ሐሳብ የሚደግም ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን ረገድ 70ኛው መዝሙር ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
በአስቸኳይ እንዲያድን የሚቀርብ ልመና
ዳዊት “አቤቱ፣ አምላክ እኔን ለማዳን፣ አቤቱ፣ ይሖዋ እኔን ለመርዳት ፍጠን” የሚል ልመና በማቅረብ ይጀምራል። (መዝሙር 70:1 አዓት) በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በምንወድቅበት ጊዜ አምላክ በፍጥነት እንዲረዳን ልንጸልይ እንችላለን። ይሖዋ በክፉ ነገር አይፈትነንም፤ “ለአምላክ ያደሩ ሕዝቦቹንም እንዴት እንደሚያድን ያውቃል።” (2 ጴጥሮስ 2:9፤ ያዕቆብ 1:13) ነገር ግን እኛን አንድ ነገር ለማስተማር ሲል ፈተናው እንዲቀጥል ቢፈቅድስ? ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥበብ እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። በእምነት ከጠየቅነውም ጥበብ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5-8) በተጨማሪም አምላክ በፈተና ለመጽናት የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። ለምሳሌም ያህል ‘በደዌ አልጋ ላይ’ ብንሆን ይረዳናል።—መዝሙር 41:1-3፤ ዕብራውያን 10:36
የተወረሰ ኃጢአተኝነት ያለ መሆኑ፣ ወደ ክፉ ድርጊት ለሚገፋፉ ፈተናዎች ሁልጊዜ የተጋለጥን መሆናችንና ዲያብሎስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የሚያደርገው ጥረት በየዕለቱ ከአምላክ ዕርዳታ ለማግኘት እንድንጸልይ ሊገፋፋን ይገባል። (መዝሙር 51:1-5፤ ሮሜ 5:12፤ 12:12) ኢየሱስ በሰጠው የጸሎት ሞዴል ላይ የሚገኙት “ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን” የሚሉት ቃላት ልብ ልንላቸው ይገባል። (ማቴዎስ 6:13) አዎን፤ አምላክ ትዕዛዙን እንድናፈርስ ስንፈተን እንድንሸነፍ እንዳይፈቅድና “ክፉው” ሰይጣን እንዳያታልለን እንዲጠብቀን ልንጠይቀው እንችላለን። ሆኖም አምላክ እንዲያድነን ከምናቀርበው ጩኸት ጋር ለፈተናዎችና ለሰይጣን ወጥመዶች ከሚያጋልጡን ሁኔታዎች ለመራቅ የሚያስችሉንን እርምጃዎች እንውሰድ።—2 ቆሮንቶስ 2:11
“እንኳን ሆነ!” የሚሉ
በምንከተለው እምነት ምክንያት ጠላቶች በሚሰነዝሩብን ስድብ ምክንያት በጣም እንፈተን ይሆናል። ይህ በአንተ ላይ ደርሶ ከሆነ የሚከተሉት የዳዊት ቃላት ትዝ ይበሉህ፦ “ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጎስቁሉም፣ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም። እንኳ እንኳ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።” (መዝሙር 70:2, 3) የዳዊት ጠላቶች ሞቶ ሊያዩት ይፈልጉ ነበር፤ ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ይፈልጉ ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ ራሱ ከመበቀል ይልቅ አምላክ እንደሚያሳፍራቸው እምነት ነበረው። ዳዊት ጠላቶቹ ‘አፍረው ወደ ኋላ እንዲመለሱ’ ግራ እንዲጋቡ፣ ክፉ ዓላማቸውን ለመፈጸም የሚያደርጉት ሙከራ እንዲከሽፍና ተስፋ እንዲቆርጡ ጸልዮአል። አዎን፣ የእርሱን መጎዳት የሚፈልጉትና በደረሰበት ችግር የሚደሰቱት ግራ ይጋቡ፤ ውርደትም ይድረስባቸው።
በጠላታችን ላይ ክፉ ነገር ሲደርስ በተንኮል የምንደሰት ከሆነ ስለ ኃጢአታችን ለይሖዋ መልስ እንሰጣለን። (ምሳሌ 17:5፤ 24:17, 18) ይሁን እንጂ ጠላቶች አምላክንና ሕዝቡን በሚሰድቡበት ጊዜ ይሖዋ ለተቀደሰው ስሙ ሲል እነዚህን ጠላቶች እንዲያከብሯቸው በሚፈልጓቸው ሰዎች ፊት ‘ወደ ኋላ እንዲመልሳቸውና እንዲያዋርዳቸው’ ልንጸልይ እንችላለን። (መዝሙር 106:8) በቀል የአምላክ ነው። ይሖዋም የእርሱንና የእኛን ጠላቶች ሊያሳፍራቸውና ሊያዋርዳቸው ይችላል። (ዘዳግም 32:35) ለምሳሌ ያህል የናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር በጀርመን ውስጥ የነበሩትን የይሖዋ ምስክሮች ለመደምሰስ ፈልጎ ነበር። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በዚያ አገር ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመንግሥቱን መልዕክት በማወጅ ላይ በመሆናቸው ዓላማው እንዴት በውርደት ከሽፏል!
ጠላቶቻችን በጥላቻ እየተሳለቁ “እንኳ እንኳ!” ሊሉ ይችላሉ። አምላክንና ሕዝቡን ስለ ሰደቡ እነዚህ ኃጢአተኞች ውርደት ደርሶባቸው ‘በእፍረታቸው ምክንያት ወደ ኋላ ይመለሱ።’ ስለዚህ ጉዳይ እየጸለይን በንጹሕ አቋማችን በጽናት ለሰይጣንና ይሖዋን ለሚሰድብ ለማንኛውም ሰው መልስ መስጠት ይቻለው ዘንድ ልቡን ደስ እናሰኝ። (ምሳሌ 27:11) “[በይሖዋ (አዓት)] የሚታመን እርሱ ይጠበቃል” ስለ ተባለ ዕብሪተኛ ጠላቶቻችንን በፍጹም መፍራት አይገባንም። (ምሳሌ 29:25) የአምላክን ሕዝቦች በምርኮ ይዞ የነበረው ትዕቢተኛው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ውርደት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ‘የሰማይ ንጉሥ በትዕቢት የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ እንደሚችል’ አምኖ ለመቀበል ተገድዷል።—ዳንኤል 4:37
“አምላክ ከፍ ከፍ ይደረግ”
ጠላቶች ችግር ቢፈጥሩብንም እንኳ ምን ጊዜም ከአምልኮ ጓደኞቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን እናወድስ። ዳዊት አምላክን ከፍ ከፍ ሳያደርግ ቀርቶ በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ እንዲህ አለ፦ “የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሴት ያድርጉ ደስም ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ [አምላክ ከፍ ከፍ ይደረግ (አዓት)] ይበሉ።” (መዝሙር 70:4) የይሖዋ ሕዝብ በእርሱ ‘ሐሴት ስለሚያደርጉና ደስ ስለሚላቸው’ በጣም ደስተኞች ሆነው ይቀጥላሉ። ለእርሱ የተወሰኑና የተጠመቁ ምስክሮቹ እንደመሆናቸው መጠን ከእርሱ ጋር ባላቸው የተቀራረበ ዝምድና ምክንያት ትልቅ ደስታ አግኝተዋል። (መዝሙር 25:14) ቢሆንም በትህትና አምላክን እንደሚፈልጉ ሰዎች ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። የአምላክን ትዕዛዛት የሚጠብቁ አማኞች ስለሆኑ ስለ እርሱና ስለ ቃሉ ያለ ማቋረጥ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ይፈልጋሉ።—መክብብ 3:11፤ 12:13, 14፤ ኢሳይያስ 54:13
የይሖዋ ምስክሮች ምሥራቹን ሲያውጁ ያለ ማቋረጥ “አምላክ ከፍ ከፍ ይደረግ” ማለታቸው ነው። ለእርሱ ከፍተኛውን ቦታ በመስጠት ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደርጉታል። እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁና እንዲያከብሩት በደስታ ይረዷቸዋል። የዓለም ተድላ እንደሚፈልጉት ሰዎች ባለመሆን የይሖዋ ሕዝቦች ‘ማዳኑን ይወዳሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ኃጢአትን እንደወረሱ ስለሚያውቁ ይሖዋ አምላክ በውድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቂያ መስዋዕት አማካኝነት ሊገኝ ለቻለው ለዘላለም ሕይወት የመዳን ፍቅራዊ ዝግጅት ጥልቅ ምስጋናቸውን ይገልጻሉ። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:8፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) አንተስ ለእርሱ ምስጋና የሚያመጣውን እውነተኛ አምልኮ በመከተልና ‘ማዳኑን እንደምትወድ’ በማሳየት አምላክን ከፍ ከፍ እያደረግኸው ነውን?—ዮሐንስ 4:23, 24
ማምለጫ በሚያዘጋጀው አምላክ ተማመኑ
ዳዊት በዚህ መዝሙር ውስጥ ስለ ራሱ ሲገልጽ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተሰምቶት ስለነበር እንዲህ አለ፦ “እኔ [የተጠቃሁና (አዓት)] ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ እርዳኝ፤ ረዳቴ [ማምለጫ የምታዘጋጅልኝም (አዓት)] አንተ ነህ፤ አቤቱ፣ [ይሖዋ (አዓት)] አትዘግይ።” (መዝሙር 70:5) በአማኞች ላይ የሚደርሱት እንደ ስደት፣ የተለያዩ ፈተናዎችና ከሰይጣን የሚደርሱ ጥቃቶችን የመሳሰሉ መከራዎች ሲደርሱብን ‘ምስኪን’ መስለን ልንታይ እንችላለን። በሥጋዊ ድሆች ባንሆንም ርኅራኄ በሌላቸው ጠላቶቻችን ፊት መከላከያ የሌለን መስለን ልንታይ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ እንደመሆናችን ሊያድነን እንደሚችልና እንደሚያድነንም እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን።—መዝሙር 9:17-20
ይሖዋ በሚያስፈልገን ጊዜ ‘ማምለጫ የሚያዘጋጅልን’ ነው። የገዛ ራሳችን ጉድለቶች ወደ ፈታኝ ሁኔታ አስገብተውን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ‘ስንፍናችን መንገዳችንን ሲያጣምምብን’ ልባችን ‘በይሖዋ ላይ አይቆጣ።’ (ምሳሌ 19:3) እርሱ ሊወቀስ አይገባውም፤ በእምነት ወደ እርሱ ከጸለይን ደግሞ ሊረዳን ዝግጁ ነው። (መዝሙር 37:5) ነገር ግን በኃጢአት ላለመሸነፍ እየታገልን ቢሆንስ? ችግሩን ለይተን በመጥቀስ እንጸልይ፤ የጽድቅን መንገድ ተከትለን ለመቀጠል እንድንችል መለኮታዊውን እርዳታ ለማግኘት እንጠይቅ። (ማቴዎስ 5:6፤ ሮሜ 7:21-25) አምላክ ከልብ ላቀረብነው ጸሎት መልስ ይሰጠናል፤ ለቅዱስ መንፈሱ አመራር የምንገዛ ከሆነም በመንፈሳዊ እንበለጽጋለን።—መዝሙር 51:17፤ ኤፌሶን 4:30
በእምነት የፈተና ውድማ ላይ በምንሆንበት ጊዜ ከዚህ በላይስ መቋቋም አልችልም ብለን እናስብ ይሆናል። ኃጢአተኛው ሥጋችን ደካማ ስለሆነ ከችግሩ በፍጥነት ለመገላገል ይፈልግ ይሆናል። (ማርቆስ 14:38) ስለዚህ “ይሖዋ ሆይ አትዘግይ” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። በተለይ በአምላክ ስም ላይ የሚመጣው ስድብ የሚያሳስበን ከሆነ ልክ እንደ ነቢዩ ዳንኤል እንደሚከተለው ብለን ለመጸለይ ልንገፋፋ እንችላለን፦ “አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)] ስማ፣ አቤቱ፣ ይቅር በል፤ አቤቱ [ይሖዋ (አዓት)]፣ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፣ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።” (ዳንኤል 9:19) ሰማያዊው አባታችን እንደማይዘገይ እምነት ሊኖረን ይችላል፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “ምህረቱን እንድናገኝና በተገቢው ጊዜ የሚረዳንን የማይገባ ደግነቱን እንድናገኝ ወደ የማይገባ ደግነቱ ዙፋን ፊት ቀርበን በነፃነት እንናገር።”—ዕብራውያን 4:16 አዓት
ይሖዋ ማምለጫውን መንገድ የሚያዘጋጅ መሆኑን በፍጹም አትርሱ። አገልጋዮቹ እንደመሆናችን ይህንና በመዝሙር 70 ላይ የሚገኙትን የጸሎት አሳቦች ብናስታውስ ጥሩ ይሆንልናል። አንዳንድ ጊዜ በጥልቅ ስለሚያሳስበን ነገር በተደጋጋሚ መጸለይ ያስፈልገን ይሆናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ለአንድ የተለየ ችግር መፍትሔ የሌለ መስሎ ሊታየን ይችላል፤ ግራ ከተጋባንበት ሁኔታ ምንም መውጫ መንገድ የሌለ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ያጠነክረናል፤ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም። ስለዚህ በዘላለማዊው ንጉሥ ዙፋን ፊት በልባዊ ጸሎት ከመቅረብ በፍጹም የምንሰለች አንሁን። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13፤ ራእይ 15:3) በእምነት ጸልዩ፤ ይሖዋ እርዳታ ለማግኘት የምናቀርበውን አጣዳፊ ጩኸት ስለሚሰማ ምንም ሳንጠራጠር በእርሱ ላይ እምነት እናድርግ።