የይሖዋን ቀን አቅርቦ እያሰቡ መኖር
ተራኪ ላይል ሮይሽ
ከሕጻንነቴ ጀምሮ መላው የቤተሰባችን ኑሮ በመጪው የጽድቅ ሥርዓት በነበረው እምነት ላይ የተመሰረተ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። እናቴና አባቴ ለእኛ ለልጆች ‘ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር’፣ ላምና ድብ አብረው እንደሚሰማሩ፣ አንበሳ እንደ በሬ ገለባ እንደሚበላ፣ ትንሽ ልጅም እንደሚመራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነቡልን ነበር።—2 ጴጥሮስ 3:11-13፤ ኢሳይያስ 11:6-9
በ1890ዎቹ ዓመታት አያቴ ኦገስት ሮይሽ ከቻርልስ ቴዝ ራስል ጋር በመጻጻፍ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን አወቀ። በካናዳ ግዛት ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘውና በአሁኑ ጊዜ ዮርክተን ሰስኬችዋን በሚባለው የትውልድ አካባቢው በሰፊው ሰብኮአል። ልጆቹን “ልጆቼ፣ 1914ን አተኩራችሁ ጠብቁ” እያለ ዘወትር ይመክራቸው ነበር። አባቴም የይሖዋ ቀን በጣም ቅርብ እንደሆነ ጠንካራ እምነት ስለነበረው በሕይወቱ በሙሉ የመጣደፍ ስሜት ነበረው። የእኔም ስሜት ከዚሁ የተለየ አይደለም።
አባቴና እናቴ በእንግዳ ተቀባይነታቸው በጣም የታወቁ ነበሩ። የሳስካቱን ሳስከችዋን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ዘወትር በቤታችን ውስጥ ይሰበሰብ ነበር። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች (ፕሊግሪም ይባሉ ነበር) ሁልጊዜ እቤታችን ያርፉ ነበር። ወንድሜ ቨርን፣ እህቴ ቬራና እኔም ጭምር መንፈሳዊ ጥቅም አግኝተንበታል። ሁልጊዜ የመንግሥቱን መልእክት እውን ሆኖ ይታየን ነበር። ለሰዎችም ለመናገር እንጣደፍ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) አብዛኛውን የሕይወቴን ክፍል እንደነዚህ ፕሊግሪሞች የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንደማገለግል በዚያ ጊዜ አላወቅኩም ነበር።
በ1927 አባቴ ቤተሰቡን ይዞ ወደ በርክሌይ ካሊፎርኒያ ተዛወረ። ታላቅ የኢኮኖሚ ውድቀት ደርሶ በነበረበት ዓመት በ1933 ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቅሁ። ወንድሜ ቨርንና እኔ በሪችሞንድ ካሊፎርኒያ በሚገኘው የፎርድ መኪና ኩባንያ ሥራ ለማግኘት በመቻላችን ራሳችንን በጣም ዕድለኞች እንደሆንን ቆጠርን። ይሁን እንጂ በ1935 በአንድ የጸደይ ቀን ‘ይህን ያህል በሥራ መድከም ከኖረብኝ ዋጋ ላለው ነገር መድከም ይገባኛል’ ብዬ ስለ ራሴ አሰብሁ። በዚያው ቀን ለመሥሪያ ቤቴ የስንብት ወረቀት ጻፍኩና በማግስቱ በብሩክሊን ኒውዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገል ማመልከቻ ላክሁ። በዋሽንግተን ዲ ሲ በ1935 ተደርጎ በነበረው ልዩ የደስታ ስሜት በሚቀሰቅሰው ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ በቤቴል እንዳገለግል ማመልከቻዬ ተቀባይነት አገኘ።
የቤቴል አገልግሎት
የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ የነበረው ናታን ኖር በሕንጻ ጥገና ሥራ እንዳገለግል መደበኝ። የምሠራው ብቻዬን ነበር። ገና የ20 ዓመት ጎረምሳ ስለነበርኩ በጣም አስፈላጊ ሰው የሆንኩ መስሎ ተሰማኝ። ፋብሪካውን የማንቀሳቅሰው እኔ ነበርኩ። እንዲህ አድርግ የሚለኝ ሰው አልነበረም። ወንድም ኖር አሠራሬን ቢወድልኝም የአመለካከት ችግር እንደነበረኝ አስተዋለ። ራሴን ዝቅ የማድረግ መንፈስ እንዲያድርብኝ ብዙ ጥረት አደረገ።
ይሁን እንጂ ወንድም ኖር እኔን ለመርዳት ጥረት ያደርግ እንደነበረ ለማስተዋል ጊዜ ወሰደብኝ። በዚህም ምክንያት ስላሳየሁት ዝንባሌ ይቅርታ ጠየቅኩና የተሻለ ጠባይ ለማሳየት ለመጣር ቁርጥ ውሳኔ ማድረጌን ገለጽኩለት። በ1942 በጥር ወር ሶስተኛው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዚደንት ከሆነው ከወንድም ኖር ጋር የረዥም ዓመት ወዳጅነት የጀመርነው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር።
ከጥገና ሥራ በተጨማሪ በመጻሕፍት መጠረዣ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን አብዛኞቹን ማሽኖች ማንቀሳቀስ ተማርሁ፤ አለዚያም በረዳትነት እሠራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በፋብሪካው ውስጥ የሥራ ትዕዛዞችን በማስተላለፍና በመመዝገብ የቢሮ ሥራ መሥራት ጀመርኩ። በተለይ የ1943 የጸደይና የበጋ ወራት በጣም የሚያስደስቱና ሥራ የበዛባቸው ወራት ነበሩ። በዚህ ዓመት ዓለም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በየምክንያቱ አለአግባብ እየተወነጀሉ ድብደባና እስራት ይደርስባቸው የነበረበት ጊዜ ነው። በ1940 የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጡ ሊያስገድዱ ይችላሉ የሚል ደንብ አወጣ። ይህም ደንብ በዚያ ጊዜ ከነበሩት 48 ክፍለ ሀገሮች መካከል በ44ቱ ውስጥ ከፍተኛ የስደት ማዕበል እንዲነሳ አደረገ። የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ከትምህርት ቤቶች ተባረሩ። ወላጆች ተይዘው ታሠሩ። ረብሻ በማነሳሳት የይሖዋ ምሥክሮችን ከየከተሞች አባርረው አስወጡ። አንዳንድ ግለሰቦች ተረሽነው ሞቱ። ሌሎች ደግሞ ሬንጅ ከፈሰሰባቸው በኋላ ቆዳቸው ተላጠ።
የይሖዋ ምሥክሮች በየፍርድ ቤቶች የሚያደርጉትን ትግል በቀጠሉ መጠን ከማህበሩ የሕግ ሠራተኞች እየተዘጋጁ ለመታተም ወደ እኔ የሚመጡት ማመልከቻዎች፣ ሰነዶችና ማሳሰቢያዎች በጣም እየበዙ መጡ። ሁላችንም የቀጠሮው ቀን ሳያልፍ ለማድረስ ትርፍ ሰዓት እንሠራ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከግንቦት እስከ ሰኔ 1943 በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀረቡት 13 ጉዳዮች በ12 መርታታቸው በሕግ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚይዝ ሆኖአል። ይሖዋ ምሥራቹ በሕግ የሚቋቋምበትንና ሕጋዊ መከላከያ የሚያገኝበትን መንገድ እንዴት እንደከፈተ ግንባር ቀደም ሆኜ ለማየት በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።—ፊልጵስዩስ 1:7
ቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት
በዚያ ጊዜ በአንዳንድ መንገዶች በፊታችን የተዘረጋውን ‘ምሥራቹን ለአሕዛብ ሁሉ ለመስበክ’ የተሟላ ዝግጅት አልነበረንም። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወንድም ኖር የሥልጠና ፕሮግራም ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ተገነዘበ። በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ወንዶች ጋር በ“ቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ከፍተኛ ኮርስ” እንድካፈል ተጋበዝኩ። ይህ ኮርስ ተለውጦ በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ሁሉ የሚካሄደው ቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሆነ።
የካቲት 16 ቀን 1942 ሰኞ ዕለት ምሽት ላይ በቤቴል ቤተሰብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰብንና ወንድም ኖር የመጀመሪያውን የመምሪያ ንግግር አቀረበ። የንግግሩ ርዕስ “የመጽሐፍ ቅዱስ የብራና ጽሑፎች” የሚል ነበር። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ወንድም ቲ ጄ ሱሊቫን ሲሆን ለመሻሻል የሚረዳንን ምክር ይሰጠን ነበር። ከጊዜ በኋላ የዚህ የቤቴል ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ሆንኩ። እንደ ታላቅ መብት የምቆጥረው ሥራ ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ተግሣጽ መቀበል ያስፈልገኝ ነበር።
ለአንድ ሸምገል ያለ ወንድም በጣም ጠንካራና ነቀፋ የተሞላበት ምክር ሰጠሁ። በዚህም ምክንያት ወንድም ኖር በግልጽ “ቦታህን ሰዎችን ለማንቋሸሽ ስትጠቀምበት የሚደሰት ሰው አይኖርም” አለኝ። ወንድም ኖር የፈለገውን ቁም ነገር ካስገነዘበኝና ፊቴ በድንጋጤ ከቀላ በኋላ ትልልቅ ዐይኖቹን ከእኔ መለስ አደረገ። ለስለስ ባለ አነጋገር “ጻድቅ ይዝለፈኝ፣ ደግነት ይሆንልኛል። ይገስጸኝም፣ ራሴን የማይሰብር ጥሩ ዘይት ይሆንልኛል” የሚለውን መዝሙር 141:5ን ጠቀሰልኝ። ለሌሎች የእርማት ምክር የመስጠት ኃላፊነት በተሰጠኝ ጊዜ ሁሉ ይህን ጥቅስ ተጠቅሜበታለሁ።
ቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከመጀመሩ በፊት ብዙዎቻችን የሕዝብ ንግግር የመስጠት አጋጣሚ አናገኝም ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ ሲሞት ወንድም ኖር የመናገር ችሎታውን ለማሻሻል በጣም ተግቶ ይጣጣር ነበር። ቤቴል ውስጥ መኖሪያ ክፍሌ እርሱ ከሚኖርበት ፎቅ ወደታች ያለው በመሆኑ ንግግሮቹን ሲለማመድ አዳምጠው ነበር። “ሰላም፣ ዘላቂነት ይኖረው ይሆንን?” የሚለውን ንግግሩን በ1942 በክሊቭላንድ ኦሃዮ በተደረገው ስብሰባ ላይ ከመስጠቱ በፊት በደርዘን ለሚቆጠሩ ጊዜያት ደጋግሞ ጮክ ብሎ እያነበበ ሲለማመድ ሰምቼአለሁ።
በጉዞ ላይ
በቤቴል 13 ዓመት ያህል ካገለገልኩ በኋላ ወንድም ኖር የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ በመስክ እንዳገለግል መደበኝ። ስለ አዲሱ ሥራዬ ሲነግረኝ “ላይል፣ አሁን ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚያደርገውን አያያዝ በቀጥታ ለማየት አጋጣሚ ታገኛለህ” አለኝ። ይህን የነገረኝን ቃል በአእምሮዬ፣ በእጆቼ ደግሞ ሁለት ሻንጣዎች ይዤ ግንቦት 15 ቀን 1948 የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራዬን ጀመርኩ። የወረዳ ሥራ ከመጀመሬ በፊት ለጥቂት ወራት በክልል የበላይ ተመልካችነት አገለገልሁ።
ያገለገልኩት የመጀመሪያ ጉባኤ በዋሴካ ሚኔሶታ የሚገኝ አነስተኛ የገጠር ጉባኤ ነበር። የቡድኑ አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ መሪ የበላይ ተመልካች የሚባለው) ዲክካይን ባቡር ጣቢያ መጥቶ እንዲቀበለኝ ደብዳቤ ጽፌለት ነበር። ልዩ አቅኚ ስለነበረ ገንዘብ ለመቆጠብ ሲል ክረምቱን ይኖርበት ከነበረው የኪራይ ቤት ወጥቶ በድንኳን ውስጥ ይኖር ነበር። የበጋ ቤቱ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ በግንቦት ወር በሚኔሶታ አካባቢ ገና በጋው አይጀምርም ነበር። በዚያ ምሽት በድንኳኑ ውስጥ ብርድ ሲያንዘፈዝፈኝ እንዲህ ያለውን ኑሮ እችለው ይሆንን ብዬ አሰብኩ። ለብዙ ሣምንታት የቆየ ጉንፋን ያዘኝ። ሆኖም አልሞትኩም።
በእነዚያ ዓመታት የተለያዩ ጉባኤዎችንና ክልሎችን በምጎበኝበት ጊዜ በየወንድሞች ቤት እኖርና ሻንጣዎችን ይዤ እጓጓዝ ነበር። በተለያዩ ዓይነት መኝታዎች ላይ አድሬአለሁ። በወጥ ቤት ወለል ላይ፣ በሶፋ ወንበር ላይ፣ ከጣሪያ ሥር ባለው የዕቃ ማስቀመጫ ቦታ የተኛሁባቸው ጊዜያት ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ አንደኛው የቤተሰብ አባል እምነታችንን በሚቃወምበት ቤት ውስጥ ለማደር ተገድጄአለሁ። በዊስኮንሲን አንድ የማያምን ባል በሚኖርበት ቤት ውስጥ አርፌ ሣምንቱን በሙሉ ስወጣና ስገባ ዐይኑን ያፈጥብኝ ነበር። አንድ ቀን ሰክሮ መጣና “ያን ሰውዬ እገድለዋለሁ” ብሎ ሲፎክር ሰማሁት። አሁን ለቅቄ መሄድ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት መጥፎ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙኝ አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። ሲያጋጥሙኝም ለሥራዬ ቅመም ይጨምሩለት ነበር። ካለፉ በኋላ እያስታወስኩ የሚያስቁኝ ነገሮች ሆኑ።
ጓደኛ አገኘሁ
በደንብ አስታውሳለሁ። በቲፊን ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው የክልል ስብሰባ ላይ ሊዮና ኤህርማን የምትባል ከፎርት ዌይን ኢንድያና የመጣች መልከ መልካም፣ ቡናማ ዐይን ያላት ወጣት ሴት አገኘሁ። እርስዋም በክርስቲያን ቤት ውስጥ ያደገች ስትሆን ለብዙ ዓመታት በአቅኚነት አገልግሎት ቆይታለች። ሁልጊዜ መንገደኛ ስለሆንኩ ብዙ ጊዜ አብረን ለማሳለፍ አልቻልንም። ቢሆንም በደብዳቤ መገናኘት ጀመርን። በኋላም በ1952 ታዲያ እንዴት ነው ብዬ ጠየቅኳት፤ እርስዋም እስማማለሁ አለችኝና ተጋባን። የራሳችንን ቤት ይዘን ልጆች ወልደን ለምን እንዳልኖርን ብዙ ጊዜ እንጠየቃለን። ቤተሰብ እንዳለን፣ ባገለገልንባቸው 44 ክፍላተ ሀገር ሁሉ ወንድሞች፣ እህቶች፣ አባቶችና እናቶች እንዳሉን እንነግራቸዋለን።—ማርቆስ 10:29, 30
ሰልችቶአችሁ አገልግሎታችሁን ለማቋረጥ አስባችሁ አታውቁምን ብለው የሚጠይቁን አሉ። አዎ፣ ከአንድ ጊዜ በላይ አስበናል። ይሁን እንጂ አንዳችን ስንደክምና ተስፋ ስንቆርጥ አንዳችን እናበረታታለን። እንዲያውም አንድ ጊዜ የቤት ቀለም በመቀባት ሥራው አብሬው እንድሠራ ይፈቅድልኝ እንደሆነ ለመጠየቅ ለወንድሜ ለቨርን ጽፌለት ነበር። በልጅነታችን በጣም እንቀራረብ ስለነበረ የብዙ ጊዜ ምኞቱ እንደሆነና በጣም ደስ እንደሚለው መልሶ ጻፈልኝ። ይሁን እንጂ ውሳኔዬን በጥንቃቄ እንዳመዛዝን መከረኝ። በዚህ ጊዜ ወንድም ኖር ለቤቴል ቤተሰቦች “ለማቋረጥ ብዙ ጥረት አይጠይቅም። በሥራ ምድባችሁ ለመቆየት ግን ድፍረትና የአቋም ጽኑነት ያስፈልጋችኋል” እያለ ደጋግሞ የሚነግረው ቃል ትዝ አለኝ። ምክሩ ለዚያ ወቅት የሚረዳ ጥሩ ምክር ነበር።
እንደ ሊዮና ያለች ታማኝና ጥሩ ደጋፊ ሚስት የሌለው ያገባ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በተመደበበት ሥራ ጸንቶ ለመቆየት ሊመኝ አይችልም። ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜትዋና ዘወትር የማይለያት ደስተኛ ፊት በየጉባኤዎቹ ባሉት በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች ዘንድ ተወዳጅ አድርጎአታል። ምን ያህል እንደምወዳት መናገር አይሰለቸኝም። በሥራዋ ጸንታ እንድትቆይ ከረዱአት ነገሮች አንዱ ይህ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።
ለይሖዋ በረከት የዐይን ምሥክር ሆኜአለሁ
የወረዳ የበላይ ተመልካች ዋነኛ ሥራ በክልል ስብሰባ ላይ ያተኮረ ነው። በእያንዳንዱ የክልል ስብሰባ ላይ ሊቀመንበር፣ የሕዝብ ተናጋሪና የትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግላል። የበላይ ተመልካች ከሆንኩባቸው በመቶ የሚቆጠሩ የክልል ስብሰባዎች መካከል ሳይደረግ የቀረ አንድም ስብሰባ ባለመኖሩ በዚህ ዝግጅት ላይ የይሖዋ በረከት እንደነበረበት ማረጋገጫ ነው። እርግጥ በአንዳንዶቹ ላይ ረብሻ ቢነሳም አንዳቸውም እንኳን አልተሰረዙም።
በ1950 የጸደይ ወራት በዉስተር ኦሃዮ የቅዳሜ ምሽቱን ስብሰባ ለመዝጋት የመደምደሚያ መዝሙር እንዲዘመር ስጠይቅ ከሺህ የሚበልጡ ተቃዋሚዎች ስብሰባው ይደረግበት በነበረው ቲያትር ቤት በራፍ ላይ ረብሻ ለማንሳት ተሰበሰቡ። ረብሸኞቹ ስንወጣ ሊወረውሩብን የበሰበሱ እንቁላሎች በሣጥን ውስጥ ይዘው ነበር። ይህን ሁኔታ ስንመለከት መዝሙር እየዘመርን፣ ተሞክሮና በዚያው ቦታ ላይ ድንገት የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን እያሰማን ስብሰባችንን ቀጠልን። 800 የሚያክሉት የይሖዋ ምሥክሮች ሳይረበሹ ጸጥ ብለው ተቀመጡ።
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ሲሆን ከፍተኛ ቅዝቃዜ መጣ። የስብሰባው አስተናጋጆች የመውጫ መንገድ የሚያዘጋጁልን ይመስል በእሳት ማጥፊያው ላስቲክ ውሃ ለቅቀው በመውጫው በራፍ ላይ የወደቁትን እንቁላሎች ማጠብ ጀመሩ። ረብሸኞቹ ከተጠለሉበት የአውቶቡስ ጣቢያ መውጣት ጀመሩ። ይሁን እንጂ አስተናጋጆቹ እንደዚያ ያደረጉት የረብሸኞቹን ትኩረት ለማሳሳት ነበር። እኛም ተሰብሳቢዎቹን በሙሉ በኋለኛው በር እንዲወጡ አደረግን። ሁሉም ምንም ነገር ሳይደርስባቸው መኪናቸው ውስጥ ገቡ። በሌሎች የኦሃዮ ስብሰባዎችም በካንቶን፣ በዴፋያንስና በቺልኮት ረብሻ ተነስቶ ነበር። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያደረጋቸው እኛን የሚደግፉ ውሳኔዎች ሕገወጦችን መቆጣጠር ስለጀመሩ ረብሻው እየቀነሰ ሄደ።
ከጊዜ በኋላ በጤንነት ምክንያት ለውጥ ለማድረግ ተገደድን። በዚህም ምክንያት ማህበሩ በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ጉባኤዎች በጣም ተቀራርበው በሚገኙበትና ሕክምና እንደ ልብ በሚገኝበት በደቡብ ካሊፎርኒያ አካባቢ የክልል የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሥራ ብዙ መጓዝን፣ የብዙ ክልሎችን ሁኔታ መቆጣጠርን የሚያጠቃልል ሲሆን የክልል የበላይ ተመልካች ሥራ ደግሞ የክልል ስብሰባዎችን ማዘጋጀትንና የስብሰባ ክፍሎችን መመደብንና ትዕይንት ያላቸውን ማለማመድን የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪም የአቅኚዎችን ትምህርት ቤት ማዘጋጀትና ማገልገል ያስፈልጋል። ስለዚህ የወረዳ የበላይ ተመልካችነትም ሆነ የክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለጥረቱ መልሶ የሚክስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ነው።
አሁንም የይሖዋን ቀን እንጠብቃለን
ከ70 ዓመት በላይ ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስታውስ ሁልጊዜ የመጣደፍ ስሜት ነበረኝ። ሁልጊዜ አርማጌዶን ከነገ ወዲያ እንደሚሆን አስብ ነበር። (ራእይ 16:14, 16) ልክ እንደ አባቴና እንደ አያቴ ሐዋርያው እንዳስገነዘበው ‘የይሖዋን ቀን አቅርቤ እያሰብኩ’ ኖሬአለሁ። ተስፋ የምናደርገው አዲስ ዓለም ገና ያልታየ ቢሆንም እውን ሆኖ ሲታየኝ ቆይቶአል።—2 ጴጥሮስ 3:11, 12፤ ዕብራውያን 11:1
ከሕጻንነቴ ጀምሮ የተቀረጸብኝ ይህ ተስፋ በቅርቡ ይፈጸማል። “በሬና ድብ አብረው ይሰማራሉ”፣ “አንበሳ እንደበሬ ገለባ ይበላል” “ትንሽም ልጅ ይመራቸዋል።” (ኢሳይያስ 11:6-9) እነዚህ አስደሳች የተስፋ ቃላት ለእውነተኝነታቸው በራዕይ 21:5 ላይ ኢየሱስ ለዮሐንስ በተናገረው ቃል ዋስትና ተሰጥቷል። “በዙፋኑም የተቀመጠው እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”