የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 7/1 ገጽ 28-30
  • በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት መሳተፍ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት መሳተፍ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዛሬ ላለነው ጥሩ ምሳሌ ነው
  • አንተ የበኩልህን ድርሻ እየፈጸምህ ነውን?
  • ሚዛናዊ አገልግሎት መልሶ ይክሳል
  • ራስህን አቅርብ!
  • በአገልግሎታችሁ ‘ትጉ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • “መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ላንተ የሚሆን አገልግሎት ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ እየፈጸምክ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 7/1 ገጽ 28-30

በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት መሳተፍ

ሐዋርያው ጳውሎስ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የማያውቁት ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። የገንዘብ እጥረት አጋጠመው። ስለዚህ ወደ ቆሮንቶስ በሄደ ጊዜ በልጅነቱ የተማረውን ዝቅተኛ ሥራ ማለትም ድንኳን የመስፋት ሥራ ጀመረ። ሥራው ከባድ ነበር። ምናልባትም ሸካራውን ሸራ ሲያገላብጥ እጆቹ ይደሙበት ኖረው ይሆናል። ገቢው ምግቡንና ልብሱን በችግር ይሸፍንለት ነበር። ሆኖም ደስተኛ ነበር፤ ምክንያቱም በየዕለቱ ሰብዓዊ ሥራውን ከጨረሰ በኋላ መሣሪያዎቹን ያስቀምጥና ወደ ቆሮንቶስ የመጣበትን ቀዳሚ ሥራ ይሠራ ነበር። ይህም የምሥራቹ ሥራ ነበር።​—ፊልጵስዩስ 4:11, 12

የሰንበት ቀን ሲመጣ ጳውሎስ ወደ ምኩራብ ይሄዳል። እርግጥ ነው፤ ጳውሎስ የቆሮንቶስን አድማጮቹ በመጀመሪያ የቀረባቸው “በድካምና በፍርሃት፣ በብዙ መንቀጥቀጥም” ነበር። (1 ቆሮንቶስ 2:1, 3) ነገር ግን ለሰዎች ያቀረበው አንዳንዱ መልዕክት ተቀባይነት በማግኘቱ ተበረታቶ “በየሰንበቱ ሁሉ በምኩራብ ይነጋገር ነበር፤ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር።”​—ሥራ 18:1-4

ለተወሰነ ጊዜ ግን ጳውሎስ ለስብከቱ ሥራ ከፊሉን ጊዜ ብቻ ከመጠቀም በላይ ማለፍ አልቻለም ነበር። ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ከሚበቃው በላይ የሆነ የልግስና መዋጮ ይዘው መጡ። (2 ቆሮንቶስ 11:9፤ ፊልጵስዩስ 4:15) የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ስደት ቢደርስባቸውም ጸንተው እንደቆሙ መስማቱ ልብን የሚያስደስትና የሚያጠነክር ነበር።​—1 ተሰሎንቄ 3:6

ይህስ በጳውሎስ ላይ ምን ውጤት አመጣ? “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር” ወይም እንደ ጀሩሳሌም ባይብል “ጊዜውን ሁሉ ለስብከቱ ሥራ አዋለው።” (ሥራ 18:5) ከገንዘብ ችግር ለጊዜው ስለተላቀቀ ጳውሎስ ወደ ሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ እስኪመለስ ድረስ ልቡ አላረፈም። ወደዚህ ሥራ በከፍተኛ ደስታና ብርታት ተመለሰ። ለአይሁድ በመስበክ ብቻ ሳይረካ በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፋቸው መልዕክት ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን የተሰሎንቄ ደብዳቤ ጻፈ!

ዛሬ ላለነው ጥሩ ምሳሌ ነው

ጳውሎስ በቆሮንቶስ በሥራ በጣም የተወጠረ ጊዜ እንዳሳለፈ የሚገልጸው ዘገባ ተጽፎና ተጠብቆ የቆየልን ሁላችንም ክርስቲያኖች በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት እንድንሳተፍ ለማበረታታት ነው። ጌታ ኢየሱስ ራሱ “የዓለም ብርሃን” የመሆንን ከፍተኛ ክብር ለደቀ መዛሙርቱ እንዳስተላለፈ ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ይህንን ብርሃን ደብቀው መያዝ አይገባቸውም። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴዎስ 5:14-16) ይህም ኢየሱስ ወደፊት ይከናወናል ብሎ በተናገረለት የስብከት ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ማለት ነበር። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 1:6-8) የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመበት ዋነኛው ምክንያት ይህን የመንግሥት ምሥራች ለመስበክ ነው።

እንደ ጳውሎስ ያሉ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ይህንን የስብከት ሥራ እንደ ትልቅ ቁም ነገር በመቁጠር ይሠሩት ነበር። ስለዚህ የአምላክ ጠላቶች “ሕይወትን በማስገኘት ረገድ ዋና መሣሪያ የሆነውን” በጭካኔ በማስገደል እውነተኛውን ብርሃን ያጠፉት በመሰላቸው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ከፍተኛ የስብከት ዘመቻ በማካሄድ የዓለም ብርሃን ሆነው ቀጥለዋል። (ሥራ 3:15) ሌላው ቀርቶ ስደትም እንኳ ጥረታቸውን አላፈነውም። የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ እንዲህ ይላል፦ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” (ሥራ 5:42) ምንም ነገር ሊገታቸው አልቻለም!

በዘመናችንም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች ምሥክርነት ለመስጠት ከፍተኛ መሯሯጥ አድርገዋል። 19ኛው መቶ ዘመን ሊያልቅ አካባቢ የአምላክን ቃል በጥንቃቄ የሚያጠኑ ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች የማካፈልን አስፈላጊነት መገንዘብ ጀመሩ። በ1884 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበር ተቋቋመ። በአሁኑ ጊዜ ይህ ድርጅት ዓለም አቀፍ ስፋት አግኝቷል። ከ1931 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምድርን በአምላክ ቃል ዕውቀት ቃል በቃል ሸፍነዋታል። በከፍተኛ ሁኔታ ሥራውን መያያዛቸው ከአራት ሚልዮን በላይ ቁጥር ያለውን ታላቅ ሠራዊት አስገኝቷል! ይሖዋ በሚያደርገው አመራር ቁጥራቸው እያደገ እንደሚሄድ አያጠራጥርም።​—ኢሳይያስ 60:22

አንተ የበኩልህን ድርሻ እየፈጸምህ ነውን?

ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 9:37, 38) በ1990 በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር አሥር ሚልዮን ለመሙላት የቀረው ጥቂት ነበር። በዓለም ዙሪያ የሚሰበሰበው መከር ከፍተኛ እንደሚሆን ይህ ይጠቁማል። እየቀጠለ በሄደው በዚህ ጭማሪ ደስ ይለናል፤ ሆኖም እያንዳንዳችን ራሳችንን ‘በዚህ ታላቅ ሥራ እኔ የቱን ያህል ተሳትፎ አደርጋለሁ? ዘወትር፣ ቢቻል ደግሞ በየሣምንቱ በሥራው እካፈላለሁን?’

ሽማግሌዎች “ለመንጋው ምሳሌ” መሆን ስላለባቸው በዚህ ሥራ ቀዳሚ ሆነው መምራት አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 5:3) እውነት ነው፤ አብዛኞቹ ሽማግሌዎች ሰብዓዊ ሥራ አላቸው። ጳውሎስም ቢሆን ቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ እንደዚህ ያለ ሥራ ነበረው። ያም ሆኖ ግን ዘወትር በስብከቱ ሥራ ለመሳተፍ ጊዜ ይመድብ ነበር። ዛሬ ብዙ ሽማግሌዎች ልክ እንደ እርሱ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ በመንፈሣዊ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳሉ። እንደዚያ ማድረጋቸው በጉባኤው ላይ ኃይለኛና አበረታች የሆነ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። በአንዳንድ ወራት ላይ ልዩ ጥረት ከተደረገ በርካታ ጉባኤዎች አብዛኞቹ አስፋፊዎቻቸው በአቅኚነት አገልግሎት ይሠማራሉ። ይህን ያስገኘው ምስጢር ምንድን ነው? ሽማግሌዎቹ በስብከቱ ሥራም ሆነ ለጉባኤው የመስክ አገልግሎት በማደራጀት በኩል ቀዳሚ ሆነው ስለሚገኙ ነው።

ዲያቆናትም እንደዚሁ በመስክ አገልግሎት አዘውትረው የሚሳተፉ ከሆነ ለጉባኤው ጥሩ ግፊት የሚሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ቅዱሳን ጽሑፎች ዲያቆናት ‘ጭምቶች . . . በመልካም የሚያገለግሉ’ መሆን አለባቸው ብለው መናገራቸውን አስታውሱ። (1 ጢሞቴዎስ 3:8, 13) አንድ ወንድም ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ለመሆን ከፈለገ በመስክ አገልግሎት ታማኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው።​—ቲቶ 1:8, 9

አንዳንዶቹ አቅኚ ሆነው ለማገልገል ሲሉ ልክ ጳውሎስ እንዳደረገው ለሰብኣዊ ሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ይቀንሳሉ። ከአሥር ዓመት በፊት 137,861 የነበረው የዘወትር፣ የረዳትና የልዩ አቅኚዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ በማድረግ በ1990 ላይ 536,508 ደርሷል። በእውነቱ ይህ ሊመጣ የሚችለው ይሖዋ ሲባርክና ሲወድ ብቻ ነው። ሆኖም አቅኚዎች ሰዓት በመቁጠር ብቻ እንዳይረኩ ይልቁንስ በአገልግሎት ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት ጥሩ አድርገው እንዲጠቀሙበት መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ታዲያ እናንተ አቅኚዎች ለአገልግሎት የምትዘጋጁና ውጤታማ አገልግሎት የምታከናውኑ ናችሁን? አገልግሎታችሁ በእውነትም ፍሬያማ እንዲሆን ዘወትር ለማሻሻል ትጥራላችሁን?

ሚዛናዊ አገልግሎት መልሶ ይክሳል

በየወሩ በመጠበቂያ ግንብ እና የእርሱ ጓደኛ በሆነው በንቁ መጽሔት ላይ የሚወጣውን ሕይወት አድን መልዕክት ታደንቃለህን? እንደምታደንቅ አያጠራጥርም። ታዲያ አድናቆትህ እነዚህን መጽሔቶች ለማሰራጨት በሚደረገው ጥረት እንድትሳተፍ አድርጎሃልን? በቦትስዋና የምትገኝ አንዲት እህት ልክ እንደዚህ አደረገች። በፊት እውነትን ትቃወም ነበር፤ ሆኖም ባሏ ከመጽሔቶቹ ያነብላት ነበር። ከጊዜ በኋላ ልቧ ተለወጠና ምሥክር ሆነች። ምንም እንኳን ማንበብ ባትችልም መጽሔት በማበርከት በኩል የተሳካ ውጤት ታገኛለች። በምታበረክትበት ጊዜ እንዲህ ትላለች፦ “ማንበብ አልችልም፤ ሆኖም ባሌ እነዚህን መጽሔቶች ያነብልኛል። ደስ ይሉኛል፤ እርስዎም እንደሚደሰቱባቸው እርግጠኛ ነኝ።”

ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ ለምን ዘወትር አትሳተፍም? መንፈሣዊ ብቃቶቹን እንዳሟላህ ክርስቲያናዊው ጉባኤ ይህን ሥራ ለመጀመር በደስታ ይረዳሃል። ይሁን እንጂ መጽሔት ማበርከት የአገልግሎቱ አንድ ዘርፍ ብቻ ነው። በምሥራቹ ሥራ በሃይል በመትጋት ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው አገልግሎቱን ሚዛናዊ ለማድረግ ይጥራል። ለምሳሌ ያህል የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በሚልዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት ያወጣል። እነዚህ መጻሕፍት ለሕዝብ ቋሚ የመንፈሣዊ ምግብ ምንጭ እንዲሆኑ ሲባል ይበረከታሉ። በአገልግሎትህ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ እንደተባለው ያሉትን መጻሕፍት በማበርከት በኩል ጥሩ ልምድ መስርተሃልን?

ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በማሰብ ስምና አድራሻቸውን በደንብ ትይዛለህን? ሰዎቹን በዚህ መንገድ ተመላልሶ መጠየቁ ከሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆነውን የአገልግሎት ዘርፍ ወደ ማግኘት ሊመራ ይችላል፤ እርሱም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራ ነው። በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ኢየሱስ ‘ደቀ መዛሙርት እንድናደርግና እንድናጠምቃቸው’ የመከረን መሆኑን አስታውስ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ልናስጠናቸው ያስፈልጋል ማለት ነው። እርግጥ ጥናት ለማግኘት ሳይሰለቹ መሥራትን ይጠይቃል። አንድ ምሥክር አረጋውያን የሆኑ ባልና ሚስት አገኘና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ከልብ ተስማሙ። ይሁን እንጂ ሊያስጠናቸው ሲመጣ ለሦስት ተከታታይ ሣምንታት ለሚቀጥለው እያሉ ቀጠሮ ሰጡት። በመጨረሻው ጥናቱ ተጀመረላቸው። ከዚያም ባልና ሚስቱ አንድ አንድ ሣምንት እያሳለፉ ጥናቱን ይሰርዙታል። በመጨረሻው ግን ሚስቲቱ ዕድገት እያደረጉ ሄዱና ተጠመቁ። ወንድም እንዲህ ይላል፦ “ከተጠመቁ በኋላ ዐይኖቻቸው የደስታ ዕንባ አቀረሩ፤ ይህም የእኔና የሚስቴ ዐይኖች የደስታ ዕንባ እንዲያቀሩ አደረገ።” አዎ፤ በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት መሳተፍ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታ ያመጣል!

ራስህን አቅርብ!

ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያው ጳውሎስ እኛ ልንከተለው የሚገባንን ጥሩ የቅንዓት ምሳሌ ትተውልናል። በዘመናችንም ቢሆን ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ታላላቅ ምሳሌዎች አሉን። ምሥራቹን የሚያውቁ ሁሉ ሌሎች ይህን ምሥራች እንዲያውቁ ሙሉ ትጋት የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን ነው። ይህ ሁሉ ድካም “ከንቱ” እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።​—1 ቆሮንቶስ 15:58

አብዛኞቻችን ልክ እንደ ጳውሎስ የገንዘብ ወጪን የሚጠይቁ ግዴታዎች አሉን። በዚህ ምክንያት ብዙዎች አቅኚ ለመሆን አይችሉ ይሆናል። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ሁላችንም በሮሜ 12:11 ላይ የተሰጠውን ምክር ለመከተል እንችላለን፦ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ።” ሁኔታችሁ ቢለወጥና በይሖዋ አገልግሎት ማሳለፍ የምትችሉት ተጨማሪ ጊዜ ብታገኙ ጳውሎስ ያደረገውን በመከተል አጋጣሚውን አትልቀቁት። በምሥራቹ ሥራ በከፍተኛ ትጋት ተሳተፉ! ይህን ማድረጋችሁ አሁን ብዙ በረከት ከማምጣቱም በላይ ወደፊት ፍጻሜ ከሌለው ደስታ ጋር የዘላለም ሕይወት ያመጣላችኋል!​—ማቴዎስ 19:28, 29

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ