አደጋዎች የሚያጋጥሙት በዕድል ነው ወይስ በአጋጣሚ?
አንዲት ክርስቲና የምትባል የምታምር ወጣት ልጅ በብራዚል አገር ሳኦ ፓውሎ ከተማ የኖቬ ዴ ጁልሆን ጎዳና ስታቋርጥ አውቶቡስ እንደደረሰባት አላየችም ነበር። ሾፌሩ መኪናውን ለማቆም ታግሎ ነበር፤ ግን አልቻለም። ክርስቲና ተዳጠችና ሞተች።
የዚህ አሳዛኝ አደጋ ዜና ኦ ኤስታዶ ዴ ኤስ ፓውሎ (ሐምሌ 29,1990)በተባለው የብራዚል ጋዜጣ ላይ በፊት ለፊቱ ገጽ ላይ ተዘግቦ ነበር። ሆኖም ይህ በብራዚል በያመቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ከሚደርሱት 50,000 ሞቶች መካከል አንዱ ብቻ ነበር። ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በእንዲህ አይነቶቹ አደጋዎች ምክንያት አካለ ስንኩላን ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ይተርፋሉ። ታዲያ ይህች ወጣት ልጃገረድ ያልተረፈችው ለምንድን ነው? በዚያ ቀን እንድትሞት ዕድልዋ ተወስኖ ነበርን?
ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች አዎ፣ ተወስኖ ነበር ብለው ይከራከራሉ። ሰው የሚሞትበትን ቀን የመሳሰሉት ትላልቅ ሁኔታዎች በዕድል አስቀድመው የተወሰኑ ናቸው ብለው ያምናሉ። ይህም እምነት “ዕድልን ሊዋጋ የሚችል የለም፤” “ቀኑ ደርሶ ነው” ወይም “የሚሆነው ይሆናል ወይም መሆን ያለበት ሳይሆን አይቀርም” ለሚሉትና ለመሳሰሉት አባባሎች ምክንያት ሆኗል። እንዲህ የመሳሰሉት የተለመዱ አባባሎች እውነትነት አላቸውን? ከዕድል መዳፍ ልንወጣ የማንችል የዕድል ምርኮኞች ነን ማለት ነውን?
ሁሉም ነገር አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው የዕድል እምነት በጥንት ግሪካውያንና ሮማውያን ዘንድ በጣም ተስፋፍቶ ነበር። ዛሬም ሳይቀር ይህ አስተሳሰብ የብዙ ሃይማኖቶች ጠንካራ የእምነት ክፍል ሆኖ ቀርቷል። ለምሳሌ እስልምና “አላህ ካልፈቀደውና የተወሰነው ጊዜ ካልደረሰ በቀር ማንም ነፍሱ አይሞትም”የሚሉትን የቁርዓን ቃላት አጥብቆ ይዟል። በዕድል ማመን በሕዝበ ክርስትናም ውስጥ የተለመደ ሲሆን በተለይ ጆን ካልቪን ባስተማረው የአርባ ቀን ዕድል ይበልጥ ሊስፋፋ ችሏል። ስለዚህ ቀሳውስት የደረሰው አደጋ “የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ነው” ብለው ላዘኑ ቤተሰቦች መናገራቸው የተለመደ ነው።
አደጋዎች የዕድል ውጤቶች ናቸው ብሎ ማመን ግን ከተፈጥሮአዊ የፍርድ ሚዛን፤ ከተሞክሮና ከትክክለኛ አስተሳሰብ ጋር ይጋጫል ወይም ይቃረናል። መጀመሪያ ነገር የመኪና አደጋዎች የመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ውጤት ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም ጠለቅ ተብሎ ሲመረመር አብዛኛውን ጊዜ አደጋ የሚደርሰው በታወቁ ምክንያቶች እንደሆነ ይደረስበታል። በተጨማሪም የመቀመጫ ቀበቶ ማሰር የመሳሰሉትን ምክንያታዊ ጥንቃቄዎች ማድረግ ሞት የሚያስከትል አደጋ የመድረሱን አጋጣሚ በእጅጉ እንደሚቀንስ የእስታትስቲክስ ማስረጃ አለ። ከአደጋ የሚያድኑ ጥንቃቄዎችን ማድረግ አስቀድሞ የተወሰነውን የአምላክ ፈቃድ ሊለውጥ ይችላልን?
በዕድል ማመን አማኙን ሰው በጥልቅ ይነካዋል። የፍጥነት ገደቡንና የትራፊክ ምልክቶችን እንዲጥስ ወይም የሚያሰክር መጠጥ ወይም የሚያደነዝዝ ዕጽ ወስዶ መኪና ማሽከርከርንና የመሳሰሉትን አጉል ተግባሮች እንዲፈጽም አያበረታታውምን? ከዚህም በላይ በዕድል ማመን አንዳንድ ሰዎች አደጋ ሲደርስባቸው አምላክን እንዲያማርሩ አነሳስቷቸዋል። በመናደድና መድረሻ በማጣት፣ እንዲሁም አምላክ ምንም ደንታ እንደሌለው በማመን ጭራሹኑ እምነታቸው ሊጠፋ ይችላል። ኢመርሰን የተባለ ግጥም ጸሐፊ “በሕይወት ውስጥ በጣም መራራና አሳዛኝ የሆነው ነገር በጭፍን ዕድል ማመን ነው” ብሎ መናገሩ ትክክል ነበር።
ነገር ግን ስለ አደጋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? በእርግጥ እነዚህ ሁሉ የዕድል ሥራዎች ናቸው ብሎ ያስተምራልን? በተጨማሪም ስለወደፊቱ የመዳን ዕድላችን ምን ይላል? የግል ምርጫችን በዚህ ጉዳይ ላይ ውጤት ይኖረዋል?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሕይወት ውስጥ መራራና አሳዛኝ የሆነው ነገር በጭፍን ዕድል ማመን ነው።”—ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን