የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 9/1 ገጽ 4-7
  • መጽሐፍ ቅዱስ በዕድል ማመንን ይደግፋልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ በዕድል ማመንን ይደግፋልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተወቃሹ ማን ነው?
  • “ጊዜና አጋጣሚ”
  • አለፍጽምና ያስከተላቸው አስከፊ ውጤቶች
  • በዕድል ማመን የሚያስከትለው ጎጂ ውጤት
  • ከአምላክ ጋር ለሚኖረን ዝምድና እንቅፋት ነውን?
  • ከዕድል ማነቆ መላቀቅ
  • ሕይወትህን የሚቆጣጠረው ዕድል ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • አደጋዎች የሚያጋጥሙት በዕድል ነው ወይስ በአጋጣሚ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የወደፊት ሕይወትህ በዕድል የተወሰነ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 9/1 ገጽ 4-7

መጽሐፍ ቅዱስ በዕድል ማመንን ይደግፋልን?

ስም ማጥፋት! የሐሰት ክስ! በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከበረ ቦታ ያለው አንድ ግለሰብ በሐሰት ወሬ ስሙ እንደጠፋ ካመነበት ነገሮችን የግድ ማስተካከል እንዳለበት ይሰማዋል። ስሙን ባጠፉት ሰዎች ላይም ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል።

በዕድል ማመንም ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ስም ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም። ይህ ፅንሰ ሐሳብ በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሱት አሳዛኝ ሁኔታዎችና አደጋዎች ሁሉ አምላክን በግል ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። በዕድል የምታምን ከሆነ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደሚከተለው የሚል ነገር የሠፈረበት ዶሴ አዘጋጅቷል ብለህ ታምናለህ ማለት ነው፦ ‘ዛሬ ጆን የመኪና አደጋ ይገጥመዋል፣ ፋቱ በወባ በሽታ ትለከፋለች፣ የማማዱ ቤት በዓውሎ ንፋስ ይፈራርሳል’! በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን አምላክ ለማምለክ ትገፋፋለህን?

በዕድል የሚያምኑ ሰዎች ‘ለሚደርሱብን ችግሮች ተጠያቂው አምላክ ካልሆነ ታዲያ ሌላ ማን ይሆናል?’ ብለው ይጠይቃሉ። በፊተኛው ርዕስ የተጠቀሰውን ወጣት ዑስማንን ያሳሰበው ይህ ነበር። ይሁን እንጂ እውነቱን ለማወቅ መገመት ወይም የራሱን መላምት መፍጠር አላስፈለገውም። አምላክ በመንፈሱ በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሠፈራቸው ትምህርቶች አማካኝነት ከዚህ የሐሰት ክስ ራሱን ነፃ እንዳደረገ አወቀ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንመርምር።

ተወቃሹ ማን ነው?

ብዙውን ጊዜ እንደ ጎርፍ ማጥለቅለቅ፣ ዓውሎ ነፋስ እና ርዕደ መሬት ያሉት ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትሉ አደጋዎች የአምላክ ቁጣ ተብለው ይጠራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን አደጋዎች የሚያመጣው አምላክ ነው አይልም። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጸመውን አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ እልቂት ለወሬ ነጋሪ የተረፈው አንድ ሰው እንዲህ ሲል ሪፖርት እንዳደረገ ይነግረናል፦ “የእግዚአብሔር እሳት [እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያስተላልፈው ትርጉም መብረቅ የሚል ነው] ከሰማይ ወደቀች፣ በጎቹንም አቃጠለች፣ ጠባቂዎችንም በላች።”—ኢዮብ 1:16

ይህ ፍርሃት ያራደው ሰው መብረቁን ያወረደው አምላክ እንደሆነ አድርጎ ሳያስብ አይቀርም፤ ይሁን እንጂ ተወቃሹ አምላክ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። ኢዮብ 1:7-12ን ብታነብ ይህን መዓት ያወረደው አምላክ ሳይሆን የእርሱ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ትረዳለህ! ሁሉም አደጋዎች በቀጥታ ሰይጣን የሚያመጣቸው ናቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ አምላከ ተጠያቂ የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ግልጽ ነው።

እንደሚታወቀው ሰዎች አንድ መጥፎ ነገር ሲደርስ ብዙውን ጊዜ ወቀሳ መሰንዘር ይቀናቸዋል። ጥረት ካለማድረግ፣ ጥሩ ሥልጠና ካለማግኘት ወይም ደግሞ ለሌሎች አሳቢ ካለመሆን የተነሣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ረገድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በተመሳሳይም ቸልተኝነት ለጤና መታወክ፣ ለአደጋዎችና ለሕልፈተ ሕይወት ሳይቀር ሊዳርገን ይችላል። በቀላሉ አንድ ሰው መኪና በሚያሽከረክርበት ጊዜ የወንበሩን ቀበቶ መጠቀሙ ግለሰቡ በመኪና አደጋ የመሞቱን አጋጣሚ በእጅጉ ይቀንሰዋል። ፈጽሞ ሊለወጥ የማይችል “ዕድል” ቢኖር ኖሮ ቀበቶው አንዳችም ለውጥ አያመጣም ነበር። በተጨማሪም ተገቢውን የሕክምና ክትትል ማድረግና ንጽሕናን መጠበቅ በለጋ ዕድሜያቸው በሞት የሚቀጩትን ሰዎች ቁጥር በጣም ይቀንሳል። እንዲያውም እንዲሁ በተለምዶ “የአምላክ ቁጣዎች” ናቸው የሚባሉት አንዳንዶቹ አደጋዎች ሰዎች ራሳቸው የሚያመጧቸው ናቸው፤ በሌላ አባባል የሰው ልጅ በምድር ላይ የዘረጋው የተዛባ አስተዳደር ያፈራቸው አሳዛኝ ውጤቶች ናቸው።—ከራእይ 11:18 ጋር አወዳድር።

“ጊዜና አጋጣሚ”

ምክንያታቸው በግልጽ የማይታወቅ ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞች መኖራቸው አይካድም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 9:11 [አዓት] ላይ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና አጋጣሚ ሁሉን ይገናኛቸዋል።” እንግዲያውስ ከሚደርሱት አደጋዎች በስተጀርባ ያለው ወይም የአደጋው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች የቀጣቸው ፈጣሪ ነው ለማለት የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት የለንም።

ኢየሱስ ክርስቶስም በዕድል በማመን ላይ የተመሠረቱ ሐሳቦችን ተቃውሟል። ኢየሱስ አድማጮቹ ሁሉ ጠንቅቀው ያውቁት የነበረውን አንድ አሳዛኝ ሁኔታ በመጥቀስ እንዲህ አለ፦ “በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፣ እላችኋለሁ።” (ሉቃስ 13:4, 5) ኢየሱስ አደጋውን ያያያዘው ከአምላክ ጣልቃ ገብነት ጋር ሳይሆን ‘ከጊዜና አጋጣሚ’ ጋር ነበር።

አለፍጽምና ያስከተላቸው አስከፊ ውጤቶች

ይሁንና በማይታወቅ ምክንያት ስለሚያጋጥመው ሞትና ሕመምስ ምን ማለት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉ በአዳም ይሞታሉ’ በማለት ስለ ሰው ልጅ ሁኔታ ቀጥተኛ መግለጫ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) አባታችን አዳም የአለመታዘዝን ጎዳና ከተከተለበት ጊዜ አንስቶ ሞት የሰው ልጆችን ሲያጠቃ ኖሯል። አምላክ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው አዳም ለዘሮቹ የሞትን ቅርስ አውርሷል። (ዘፍጥረት 2:17፤ ሮሜ 5:12) በመሆኑም ለሁሉም ዓይነት ሕመም ምክንያት የሆነው የሁላችን አባት የሆነው አዳም ነው። በወረስነው ድካም ምክንያት በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ነገሮች እንደጠበቅነው ሳይሆኑ ወይም ሳይሳኩ ሊቀሩ ይችላሉ።—መዝሙር 51:5

ለምሳሌ ያህል ድህነትን ተመልከት። ብዙውን ጊዜ በዕድል ማመን በችግር የሚቆራመዱ ሰዎች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አሜን ብለው እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል። ‘ዕድሌ ነው’ ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ነገር ምክንያት ሰብዓዊ አለፍጽምና እንጂ ዕድል እንዳልሆነ ይገልጻል። አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ስንፍና ወይም ያላቸውን ገንዘብ በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ምክንያት ድሀ ይሆናሉ፣ በሌላ አባባል ‘የዘሩትን ያጭዳሉ።’ (ገላትያ 6:7፤ ምሳሌ 6:10, 11) በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሥልጣን ላይ ባሉ ስግብግብ ሰዎች ብዝበዛ ምክንያት የድህነት ኑሮ ይገፋሉ። (ከያዕቆብ 2:6 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ይላል። (መክብብ 8:9 አዓት) ድህነትን ሁሉ ያመጣው አምላክ ወይም ዕድል ነው ለማለት የሚያስችል ምንም ማስረጃ የለንም።

በዕድል ማመን የሚያስከትለው ጎጂ ውጤት

በዕድል ማመን እንደሌለብን የሚያሳየው ሌላው አሳማኝ ምክንያት ደግሞ ይህን ትምህርት በተቀበሉት ሰዎች ላይ የሚያስከትለው ውጤት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።” (ማቴዎስ 7:17) በዕድል ማመን ከሚያፈራቸው ‘ፍሬዎች’ መካከል አንዱን ይኸውም ሰዎች ለኃላፊነት ባላቸው አመለካከት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንመልከት።

በግል ላሉብን ኃላፊነቶች ተገቢውን አመለካከት መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው። ወላጆች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር እንዲያሟሉ፣ ሠራተኞች ተግባራቸውን በትጋት እንዲያከናውኑ፣ አምራቾች ጥራት ያለው የምርት ውጤት እንዲያቀርቡ ከሚያነሳሷቸው ነገሮች መካከል አንዱ ይህ ነው። በዕድል ማመን ይህን የኃላፊነት ስሜት ሊያጠፋው ይችላል። ለምሳሌ ያህል የመኪናው መሪ የተበላሸበት አንድ ሰው አለ እንበል። ከልቡ የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው ከሆነ ለራሱ ሕይወትም ሆነ ላሳፈራቸው ሰዎች ሕይወት ባለው አሳቢነት ተነሳስቶ መሪውን ያስጠግነዋል። በአንፃሩ ደግሞ አንድ በዕድል የሚያምን ሰው ችግር የሚፈጠረው ‘አምላክ ካዘዘ’ ብቻ ነው ብሎ በማሰብ አደገኛ የሆነውን ሁኔታ በቸልታ ሊያልፍ ይችላል!

አዎን፣ በዕድል ማመን ግዴለሽነትን፣ ስንፍናን፣ ለተከሰተው ነገር ኃላፊነቱን ከመውሰድ መሸሽንና ሌሎችንም በርካታ አሉታዊ ባሕርያት በቀላሉ ሊያስፋፋ ይችላል።

ከአምላክ ጋር ለሚኖረን ዝምድና እንቅፋት ነውን?

ከዚህ ሁሉ በላይ ጎጂ የሆነው ደግሞ በዕድል ማመን አንድ ሰው በአምላክ ፊት ላለበት ኃላፊነት ወይም ግዴታ በሚኖረው ስሜት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ነው። (መክብብ 12:13) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ቸር [“ጥሩ፣” አዓት] እንደሆነ ቅመሱ እዩም” በማለት የሰው ልጆችን ሁሉ አጥብቆ መክሯል። (መዝሙር 34:8) አምላክ ከጥሩነቱ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነገሮችን ገልጿል።—መዝሙር 15:1-5

ከእነዚህ መካከል አንዱ ንስሐ መግባት ነው። (ሥራ 3:19፤ 17:30) ይህም ስህተትን አምኖ መቀበልንና አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል። ሁላችንም ፍጹማን ሰዎች ባለመሆናችን ንስሐ መግባት የሚጠይቁ ስህተቶች እንሠራለን። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በዕድል ቁጥጥር ሥር እንዳለና እርሱ ሊያደርገው የሚችል ነገር እንደሌላ የሚሰማው ከሆነ ንስሐ መግባት ያስፈልገኛል ብሎ ለማመን ወይም ለሠራው ስሕተት ኃላፊነቱን ለመውሰድ ይከብደዋል።

መዝሙራዊው “ምሕረትህ [“ፍቅራዊ ደግነትህ፣” አዓት] ከሕይወት ይሻላል” በማለት ስለ አምላክ ተናግሯል። (መዝሙር 63:3) ይሁንና በዕድል ማመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሰቆቃቸው ሁሉ ምንጭ አምላክ እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ይህም ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ እንዳይቀርቡ ስላደረጋቸው ከፈጣሪያቸው ጋር እውነተኛና ልባዊ ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ መንገዱን አጥሮባቸዋል። ድሮውንስ የሚደርሱብህ ችግሮችና ፈተናዎች ሁሉ ምንጭ አድርገህ ለምታየው አካል እንዴት ፍቅር ሊያድርብህ ይችላል? በመሆኑም በዕድል ማመን በአምላክና በሰዎች መካከል አንድ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል።

ከዕድል ማነቆ መላቀቅ

በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ወጣቱ ዑስማን በአንድ ወቅት የዕድል እምነት ተገዢ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን አማካኝነት አስተሳሰቡን እንዲመረምር ስለረዱት ዑስማን በዕድል ላይ የነበረውን እምነት ለመተው ተገፋፍቷል። በዚህም ምክንያት ታላቅ እፎይታ ከማግኘቱም በላይ ሕይወትን አዎንታዊ በሆነ መንገድ መመልከት ችሏል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን አውቋል።—ዘጸአት 34:6

አምላክ እያንዳንዱን የሕይወታችንን ዝርዝር ባይቀይስም እንኳ ስለወደፊቱ ጊዜ ግን ዓላማ እንዳለው ዑስማን መገንዘብ ችሏል።a 2 ጴጥሮስ 3:13 እንዲህ ይላል፦ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” የይሖዋ ምሥክሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ የተሰጠበት የዚህ “አዲስ ምድር” ክፍል ሆነው ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲይዙ መርዳት ችለዋል። አንተንም ቢሆን ሊረዱህ ይፈልጋሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት እያደግህ ስትሄድ የወደፊት ሕይወትህ የተመካው አንተ ምንም ልትቆጣጠረው በማትችለው አስቀድሞ በተወሰነ ዕድል ላይ እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። ሙሴ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የተናገራቸው ቃላት በዚህም ረገድ ይሠራሉ፦ “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን [አስቀምጫለሁ]፤ . . . እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ . . . አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉን ትሰማ ዘንድ ምረጥ።” (ዘዳግም 30:19, 20) አዎን፣ የወደፊት ሁኔታን በሚመለከት መምረጥ ትችላለህ። ይህ ለዕድል የተተወ ነገር አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አምላክ ስላለው አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ሰፊ ትንታኔ ለማግኘት የሐምሌ 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 3-7ን ተመልከት።

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

እነዚህ አደጋዎች ‘የአምላክ ቁጣ’ አልነበሩም

[ምንጭ]

U.S. Coast Guard photo

WHO

UN PHOTO 186208 /M. Grafman

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ