የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 4/15 ገጽ 3-4
  • የወደፊት ዕጣችን አስቀድሞ ተጽፏልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የወደፊት ዕጣችን አስቀድሞ ተጽፏልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አምላክ ዕድላችንን አስቀድሞ ወስኖታልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ዕድልህ አስቀድሞ ተወስኗል?
    ንቁ!—2007
  • አደጋዎች የሚያጋጥሙት በዕድል ነው ወይስ በአጋጣሚ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ዕድል ተወስኗል የሚለው እምነት ከአምላክ ፍቅር ጋር ሊስማማ ይችላልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 4/15 ገጽ 3-4

የወደፊት ዕጣችን አስቀድሞ ተጽፏልን?

ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ አይሁዶች፣ የሂንዱ እምነት ተከታዮች ወይም በማንኛውም እምነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል።

ለምሳሌ ያህል በታኅሣሥ 6, 1997 የሳይቤሪያ ከተማ በሆነችው በኢርኩትስክ አንድ አሠቃቂ አደጋ ደርሶ ነበር። አንድ ግዙፍ የዕቃ ማጓጓዣ AN-124 አውሮፕላን ገና መብረር ከመጀመሩ ሁለቱ ሞተሮቹ መሥራታቸውን አቆሙ። ነዳጅ ጢም ተደርጎ የተሞላው ይህ አውሮፕላን በአንድ የመኖሪያ ሰፈር ላይ ወድቆ ተከሰከሰ። በርካታ የመኖሪያ አፓርታማዎች በእሳት ተያያዙ። አደጋው ልጆችን ጨምሮ ራሳቸውን ሊከላከሉ በማይችሉ ብዙ ነዋሪዎች ላይ ሞትና ጉዳት አስከተለ።

አደጋው በደረሰበት በዚያ የሳይቤሪያ አካባቢ የተለያየ ዓይነት ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች እንደሚኖሩ እሙን ነው። አንዳንዶች ክርስቲያኖች እንደሆኑ ቢናገሩም አደጋው የደረሰው በዕድል ምክንያት ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። እነሱም ሆኑ ሌሎች ‘የአምላክ ፈቃድ ነበር፤ እነዚያ በአደጋው የሞቱ ሰዎች በዚህ ሁኔታ ባይሞቱ ኖሮ እንኳ በሌላ መንገድ መሞታቸው የማይቀር ነበር። ምክንያቱም ይህ ዕድላቸው ነው’ ብለው ያስቡ ይሆናል።

ሰዎች አፋቸውን ሞልተው ይናገሩም አይናገሩ ዕድል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ብዙ ሃይማኖቶች ዘንድ ቦታ ያገኘ ፅንሰ ሐሳብ መሆኑን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ያንጸባርቃል። ብዙ ሰዎች የወደፊቱ ዕጣችን ማለትም ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ እስከ ምንሞትበት ቀን ድረስ ያለው ጊዜ አስቀድሞ የተጻፈ ነው ብለው ያምናሉ።

ሰዎች ስለ ዕድል የሚያምኑት በተለያየ መልኩ ስለሆነ ለቃሉ ጠቅለል ያለ ፍቺ ለመስጠት ያዳግታል። ዕድል በዓለማችን ላይ የሚፈጸሙት ነገሮች ሁሉ፣ እያንዳንዱ ድርጊትና እያንዳንዱ ክንውን፣ መልካምም ይሁን መጥፎ ሊቀር የማይችል፤ ከሰው ቁጥጥር በላይ በሆነ ከፍተኛ ኃይል ቀደም ሲል የተወሰነ በመሆኑ መፈጸሙ የማይቀር የሚል መሠረታዊ ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህን የመሰለው አመለካከት በኮከብ ቆጠራ፣ በሂንዱዎችና በቡዲሂስቶች ካርማ እንዲሁም ሕዝበ ክርስትና በምታስተምረው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል በሚለው እምነት ውስጥ ይገኛል። ወደ ጥንቷ ባቢሎን መለስ ስንል አማልክት በአንድ በተጻፈ ሰነድ አማካኝነት ዕድልንና የወደፊት ጊዜን ይቆጣጠራሉ ብለው ሰዎች ያምኑ ነበር። እነዚህን “የዕድል ሰሌዳዎች” የሚቆጣጠር አምላክ የሰዎችን፣ የመንግሥታትንና የአማልክትን የወደፊት ዕጣ እንኳ ሳይቀር ለመወሰን ይችላል ተብሎ ይታመን ነበር።

ብዙ አማኞች በመለኮታዊ ውሳኔ መሠረት ሰዎች ከመወለዳቸው በፊት በእነርሱ ላይ የሚደርሰውን ሁሉ ማለትም የሕይወታቸውን ርዝማኔ ጨምሮ ወንድ ወይም ሴት፣ ሃብታም ወይም ድሃ፣ ችግረኛ ወይም ደስተኛ መሆናቸውን የሚወስነው አምላክ ነው የሚል እምነት አላቸው። ይህ ሁሉ ነገር ከመፈጸሙ በፊት በአምላክ አእምሮ ውስጥ ወይም በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የሚገኝ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ አንድ አማኝ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ “ሜክቱብ” ማለትም አስቀድሞ ተጽፏል ብሎ መናገሩ የተለመደ ነው! አምላክ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ እስካለው ድረስ ማን እንደሚታዘዘው ወይም ማን እንደማይታዘዘው የሚወስነው እሱ መሆን አለበት ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች አንድ ሰው ከመወለዱ በፊት እንኳን ሳይቀር የወደፊት ዕጣው የዘላለም ሕይወት ይሁን ወይም የዘላለም ጥፋት አምላክ አስቀድሞ ወስኖበታል ብለው ያምናሉ።

ይህ በአንዳንድ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚሰጠውና ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል ከሚለው ትምህርት ጋር ሳይመሳሰልብህ አይቀርም። በ16ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊው የተሃድሶ አራማጅ ጆን ካልቪን ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ትምህርት ዋነኛ ደጋፊ ነበር። ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል ለሚለው እምነት ፍቺ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “አምላክ በእያንዳንዱ ሰው ላይ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር የወሰነበት ዘላለማዊ ዕቅድ ነው። ሁሉንም ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ስላልፈጠረ አንዳንዶቹን ለዘላለም ሕይወት ሌሎቹን ደግሞ ለዘላለም ኩነኔ አስቀድሞ ወስኗቸዋል።” ካልቪን አክሎ ሲናገር “አምላክ የመጀመሪያው ሰው እንደሚሳሳትና ዘሮቹ የሚያጋጥማቸውን ውድቀት አስቀድሞ ለማየት ከመቻሉም በላይ ራሱ ፈልጎ ያደረገው ነገር ነው” ብሏል።

ሆኖም ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን ትምህርት በግል የሚያምኑበት ሁሉም የሃይማኖት አባላት አይደሉም። ሰው የመምረጥ ነፃነት ያለው መሆኑን ሃይማኖታዊ ጽሑፎች እንደሚጠቅሱ አንዳንዶች በትክክል ይናገራሉ። በእርግጥ ሰብዓዊ ድርጊቶች የነፃ ምርጫ ውጤቶች ናቸው በሚለውና አምላክ አስቀድሞ የወሰናቸው ናቸው በሚሉት ሐሳቦች መካከል ከፍተኛ ክርክር ሲካሄድ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ፍትሐዊ የሆነው አምላክ ሰው ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች በሙሉ በኃላፊነት እስከጠየቀ ድረስ ሰው ለመምረጥና የመረጠውን ለማድረግ ነፃነት ሊኖረው ይገባል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች የሚፈጥረው አምላክ ነው፤ ይሁን እንጂ ሰው እነዚህን ድርጊቶች በሆነ መንገድ “የራሱ በማድረግ” በኃላፊነት ተጠያቂ ይሆንባቸዋል ይላሉ። ጠቅለል ባለ አነጋገር በዕለት ተለት ሕይወታችን ውስጥ የሚፈጸመው እያንዳንዱ ክንውን፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ በአምላክ አስቀድሞ የተወሰነ ነው ብለው ብዙዎች ያምናሉ።

አንተስ ምን ብለህ ታምናለህ? አምላክ የወደፊት ዕጣህ ምን እንደሚሆን አስቀድሞ ወስኖታልን? ሰዎች ስለ ወደፊት ዕጣቸው ምርጫ የማድረግ እውነተኛ ነፃነት በእርግጥ አላቸውን? የወደፊት ዕጣችን በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ የተመካው እስከ ምን ድረስ ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

SEL/Sipa Press

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ