ሃይማኖት በእርግጥ አስፈላጊ ነውን?
ለሃይማኖት ትልቅ ቦታ ትሰጣለህን? የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ወይም ቤተክርስቲያን አባል ነህን? ከሆንክ 1844 ጀርመናዊው ፈላስፋ ካርል ማርክስ “ሃይማኖት . . . የሕዝብ መርዝ ነው” በጻፈበት ጊዜ ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ጋር በብዙ መንገድ አንድ ነህ ማለት ነው። በዚያ ዘመን ወደ ቤተክርስቲያን የማይሄድ ሰው እምብዛም አልነበረም። ሃይማኖትም በማንኛውም የሕብረተሰብ ደረጃ ላይ ኃይለኛ ተጽዕኖ ነበረው። ዛሬ ግን ያ ሁኔታ ባስደንጋጭ ሁኔታ ተለውጧል። ሃይማኖትም በመቶ ሚልዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ቦታ የለውም። ቢኖረውም የተሰጠው ቦታ በጣም ጥቂት ነው። ቤተክርስቲያን የምትሄድ ከሆነ በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ በቁጥር አነስተኛ ከሆነው ክፍል ሳትቆጠር አትቀርም።
እንዲህ ያለውን ለውጥ ያስከተለው ምንድን ነው? መጀመሪያ ነገር ካርል ማርክስ ከፍተኛ ተደማጭነት ያገኘ ፀረ ሃይማኖት ፍልስፍና አስፋፍቷል። በግልጽ እንደሚታየው ካርል ማርክስ ሃይማኖት ለሰዎች መሻሻል ወይም ዕድገት እንቅፋት እንደሆነ ቆጥሯል። የሰው ልጆች ፍላጎት ሊሟላ የሚችለው ለአምላክም ሆነ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጡ ሃይማኖቶች ቦታ በማይሰጠው የቁስ አካላዊነት ፍልስፍና አማካኝነት ነው አለ። “ለሕዝቦች ደስታ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር የሃይማኖት መጥፋት ነው” እስከማለት ደርሷል።
የማርክስ የቁስ አካላዊነት ፍልስፍና በጀርመኑ ሶሻሊስት በፍሬዴሪክ ኤንግልስና በሩሲያዊው የኮሙኒስት መሪ ቭላድሚር ሌኒን አማካኝነት ይበልጥ ተስፋፍቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲሶው የሰው ዘር የኖረው ይብዛም ይነስ ይህን አምላክ የለሽ ፍልስፍና በሚከተሉ ፖለቲካዊ መንግሥታት ሥር ነው። እስከ አሁንም ብዙ ወንዶችና ሴቶች እንዲህ ባለው መንግሥት ሥር እየኖሩ ነው።
የዓለማዊነት ዕድገት
ነገር ግን ሃይማኖት በሰው ልጅ ላይ ያለውን ተጽዕኖ ያዳከመው የኮሙኒስት ፍልስፍና መስፋፋት ብቻ አልነበረም። በሳይንስ ዘርፍ የተደረገው ዕድገትም ድርሻ አበርክቷል። ለምሳሌ ያህል የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በሕዝብ ዘንድ ያገኘው ታዋቂነት ብዙ ሰዎች የፈጣሪን ሕልውና እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ።
ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ “ቀደም ብሎ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንደፈጠራቸው ተደርገው ይታሰቡ ለነበሩ ክስተቶች ሳይንሳዊ ማብራሪያ መገኘቱ” እና “የተደራጀ ሃይማኖት ተጽዕኖ እንደ ሕክምና፣ ትምህርትና ኪነጥበብ ከመሳሰሉት ተግባሮች ላይ መወገዱ” ሰዎች የፈጣሪን ሕልውና እንዲጠራጠሩ ካደረጓቸው ምክንያቶች መሃል መሆናቸውን ይጠቅሳል። እንደዚህ የመሰሉ ሁኔታዎች ዓለማዊነት እንዲስፋፋ አድርገዋል። ዓለማዊነት ምንድን ነው? “ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ችላ መባል አለባቸው ወይም ሆን ተብሎ ከግምት ውጭ መደረግ አለባቸው በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ. . . የሕይወት አመለካከት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ዓለማዊነት በኮሙኒስትና ኮሙኒስት ባልሆኑ አገሮች ተቀባይነት አግኝቷል።
ነገር ግን የሃይማኖትን ተጽዕኖ ያዳከሙት ዓለማዊነትና ማርክሲዝም-ሌኒንዝም ብቻ አልነበሩም። የሕዝበ ክርስትና አብያተክርስቲያናትም ተወቃሾች ናቸው። ለምን? ምክንያቱም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመውበታል። እንደዚሁም መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ፋንታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎችንና የሰው ፍልስፍናዎችን አስተምረዋል። በመሆኑም መንጎቻቸው ወይም ምዕመናኖቻቸው የዓለማዊነትን ኃይለኛ ጥቃት ለመቋቋም እስኪሳናቸው ድረስ በመንፈሳዊነታቸው በጣም ተዳክመዋል።
በተጨማሪም በስተመጨረሻው አብያተክርስቲያናቱ ራሳቸው በአብዛኛው ለዓለማዊነት ተሸንፈዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ምሁራን ለብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት ያጠፋባቸውን ከፍተኛ ትችት የሚባል የምርምር ዘይቤ አቀረቡ። አብያተ ክርስቲያናት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ተቀበሉ። ያም ሆኖ በፍጥረት እናምናለን ይላሉ። ነገር ግን የሰው አካል በዝግመተ ለውጥ ከመጣ በኋላ አምላክ የፈጠረው ነፍስን ብቻ ሊሆን ይችላል በማለት ለዚህ ፍልስፍና መንገድ ከፈቱ። በ1960ዎቹ ዓመታት የፕሮቴስታንት ሃይማኖታውያን “አምላክ ሞቷል” የሚል ሃይማኖታዊ ትምህርት አመጡ። ብዙ የፕሮቴስታንት ቀሳውስት ቁሳዊ ነገሮችን የማሳደድን አኗኗር ፈቀዱ። ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ማድረግንና ግብረ ሰዶማዊነትን ሳይቀር መፍቀድ ጀመሩ። አንዳንድ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት የካቶሊክን እምነት ከአብዮታዊው የማርክሲዝም ፍልስፍና ጋር በመቀላቀል በነፃ አውጪነት ላይ የተመሠረተ ሃይማኖታዊ ትምህርት አስፋፍተዋል።
የዓለማዊነት መሸነፍ
በእነዚህ ምክንያት የተነሣ ዓለማዊነት በተለይ ከ1960ዎቹ ዓመታት እስከ 1970ዎቹ ዓመታት የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ተስፋፍቶ ቆየ። ከዚያ በኋላ ነገሮች መለወጥ ጀመሩና ዋና ዋናዎቹ አብያት ክርስቲያናት በአብዛኛው እንደገና ማንሰራራት የጀመሩ መሰለ። በዓለም ዙሪያ በሙሉ በ1970ዎቹ የመጨረሻ አጋማሽና በ1980ዎቹ ዓመታት የአዳዲስ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መስፋፋት ጀመሩ።
ሃይማኖት ያንሰራራው ለምንድን ነው? ስለኅብረተሰብና ስለሰው ባሕርይ ጥናት የሚያደርጉት ፈረንሳዊው ሶሺዮሎጅስት ጊልስ ኬፐል “ዓለማዊው ትምህርት የተማሩ ተራ ምዕመናን . . . ዓለማዊው ባሕል መንገዳቸውን እንደዘጋባቸውና ከአምላክ ነፃ ወጥተናል ሲሉ በትዕቢታቸውና በከንቱነታቸው የዘሩትን ፍሬ ማለትም ብልግናን፣ መፋታትን፣ ኤድስን፣ በዕጾች ያለአግባብ መጠቀምንና ራስን መግደልን እንዳጨዱ ያምናሉ” ብለዋል።
የዓለማዊነት ሽሽት የተፋጠነው በተለይ ማርክሲዝም ሌኒንዝም የተንኮታኮተ ከመሰለበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። ይህ ማርክሲዝም ሌኒንዝም አምላክ የለሽ ፍልስፍና ለብዙ ሰዎች የታወቀ ሃይማኖት ሆኖ ቆይቶ ነበር። እምነታቸውን በሱ ላይ ጥለው የነበሩ ሰዎች ያጋጠማቸውን ግራ መጋባት ገምቱ! ከመስኮብ የተላከ የዋሽንግተን ፖስት የዜና መልእክት የኮሙኒስት ፓርቲ ከፍተኛ ትምህርት ቤት የቀድሞ ሥራ መሪ የነበሩት እንደሚከተለው እንደተናገሩ ጠቅሶ ዘግቧል፦ “አንድ አገር የሚኖረው በኢኮኖሚውና በተቋሞቹ ብቻ ሳይሆን በአፈታሪኮቹና በመሥራች አባቶች ላይ ጭምር ነው። ማንኛውም ህብረተሰብ ታላላቅ አፈታሪኮቹ የተመሠረቱት በእውነት ላይ ሳይሆን በፕሮፓጋንዳና በቅዥት ላይ መሆኑን ሲገነዘብ በጣም ይጎዳል። በሌኒንና በአብዮቱ ረገድ እያጋጠመን ያለው ይህን የመሰለ ሁኔታ ነው።”
የፈረንሳይ ሶሺዮሎጂስትና ፈላስፋ የሆኑት አድጋርድ ሞሪን ስለኮሙኒስቱና ስለካፒታሊስቱ ዓለም ሲናገሩ እንደሚከተለው በማለት የእምነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፦ “ሲንኮታኮት ያየነው ለወዛደሩ የተዘረጋለት ብሩህ ተስፋ ብቻ ሳይሆን ሳይንስ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብና ዲሞክራሲ ሊሰፍኑበት ይገባ የነበረው የዓለማዊ ሕብረተሰብ ልማዳዊና ባሕሪያዊ ዕድገት ጭምር ነው።. . . . ባሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት መሻሻል ዋስትና ያለው አልሆነም። ተስፋ ያደረግንበት የወደፊቱ ሕይወታችን ተንኮታኩቷል።” ሰው አለአምላክ እርዳታ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት ላይ እምነታቸውን ጥለው የነበሩ ብዙ ሰዎች የወደቀባቸው የባዶነት ስሜት ይህን የሚመስል ነው።
በሃይማኖት ላይ የተቀሰቀሰ አዲስ ስሜት
በዓለም አቀፍ ደረጃ ነገሮች እንደታሰበው ሳይሆኑ በመቅረታቸው ምክንያት የተፈጠረው ግራ መጋባት ግለሰቦች ለሕይወታቸው መንፈሳዊ አለኝታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። የሃይማኖትን አስፈላጊነት ተረድተዋል። ይሁን እንጂ በዋና ዋናዎቹ አብያተክርስቲያናት ደስ አይሰኙም። አንዳንዶቻቸውም ስለፈውስ አምልኮቶች፣ ልዩ ስጦታና ልዩ ዕውቀት አለን ስለሚሉትና ሰይጣን አምላኪ ስለሆኑ ቡድኖችና ስለሌሎቹ አዳዲስ ሃይማኖቶች ጥርጣሬ አላቸው። ሃይማኖታዊ አክራሪነትም አስቀያሚ ገጹን ብቅ ማድረግ ጀምሯል። አዎን፣ ስለዚህ ሃይማኖት የመመለስ መልክ እያሳየ ቢሆንም ይህ የሃይማኖት እንደገና ማንሰራራት ለሰው ልጅ ጥሩ ነገር ነውን? በእርግጥ ማንኛውም ሃይማኖት የሰው ልጆችን መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟላልን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሃይማኖት የጭቁኑ ፍጥረት ትካዜ፣ የግፈኛው ዓለም ስሜትና የነፍስ የለሹ ሁኔታ ነፍስ ነው፥ ሃይማኖት የሕዝብ መርዝ (ማደንዘዣ) ነው።”
[ምንጭ]
Photo: New York Times, Berlin—33225115
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካርል ማርክስና ቭላድሚር ሌኒን ሃይማኖት የሰው ልጆች ዕድገት እንቅፋት መሆኑን ተረድተው ነበር
[ምንጭ]
Musée d’Histoire Contemporaine—BDIC (Universitiés de Paris)
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማርክሲስት ሌኒንስት ፍልስፍና በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ልብ ውስጥ ታላላቅ ተስፋዎችን ኣሳድሮ ነበር
[ምንጭ]
Musée d’Histoire Contemporaine—BDIC (Universitiés de Paris)
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Cover photo: Garo Nalbandian