የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 12/15 ገጽ 22-24
  • “ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቤተ ክርስቲያኗ የተቃወመቻቸው ትምህርቶች
  • የሳይንስ መጽሐፍ አይደለም
  • ጋሊሊዮ በመናፍቅነት ተፈረደበት
  • ጋሊልዮ
    ንቁ!—2015
  • የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት
    ንቁ!—2003
  • የተሳሳተ ግንዛቤ የተሰጠው መጽሐፍ
    ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ
  • በሳይንስና በሃይማኖት መካከል የተፈጠረ ግጭት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 12/15 ገጽ 22-24

“ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!”

በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ኢጣልያዊው የሳይንስ ሊቅና ፈላስፋ ጋሊሊዮ ጋሊሌ “መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ ስለመሄድ እንጂ ሰማያት እንዴት እንደሚሄዱ አያስተምርም” በማለት ተናግሯል። ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያጋጩትና ቤተክርስቲያኗም በእሥራትና በብዙ ሥቃይ እንደምትቀጣው እንድታስፈራራ ያደረጓት ይህን የመሳሰሉት እምነቶቹ ነበሩ። 350 ያህል ዓመታት ካለፉ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ ለጋሊሊዮ የነበራትን አመለካከት እንደገና መረመረች። በጋሊሊዮ ዘመን የተፈጸመው ነገር “በተግባር በሚታየው ሳይንስና በጭፍን መላ ምት መሃል የተፈጠረ ግጭት ነበር” ተብሎአል።

በዛሬው ጊዜ እውነትን ለማግኘት የሚመረምሩ ሰዎች ከጋሊሊዮ ገጠመኝ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ግጭት ለምን ደረሰ? በጋሊሊዮ ዘመን የነበረው ተቀባይነት ያገኘ ሳይንሳዊ አመለካከት መልሱን ይሰጣል።

በ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ምድር የአጽናፈ ዓለም እምብርት እንደሆነች ተደርጐ ይታሰብ ነበር። ፕላኔቶችም ፍጹም ክብ የሆነ ምሕዋር እንዳላቸው ይታሰብ ነበር። እነዚህ አስተሳሰቦች በሳይንሳዊ ዘዴ ያልተረጋገጡ የነበሩ ቢሆኑም እንደተረጋገጡ እውነቶች ተደርገው የእምነት ተቀባይነት አግኝተው ነበር። በእርግጥም ሳይንስ “ከምሥጢራዊና ከምትሐታዊ አስተሳሰቦች” ያልተቀላቀለ ስለነበረ ከሃይማኖት ተነጥሎ አይታይም ነበር።

ጋሊሊዮ በ1564 በፒሳ ከተማ ውስጥ ከተከበረ ቤተሰብ የተወለደው እንዲህ በመሰለው ዓለም ነበር። አባቱ ሕክምና እንዲያጠና ፈልጐ ነበር፤ ተመራማሪው ልጅ ግን በሂሳብ ትምህርት ተመሰጠ። ከጊዜ በኋላ የሳይንስ ፕሮፌሰር በመሆን አንዳንድ የኢኔርሺያ ሕጎችን አወጣ። ስለ ቀድሞዎቹ የዳች ቴሌስኮፖች (የሩቁን አቅርበው የሚያሳዩ መነፅሮች) አሠራር በሰማ ጊዜ ዲዛይኑን በጣም አሻሽሎ የራሱን መሣሪያ ሠራ። መሣሪያውንም ወደ ሰማይ አዙሮ በመመልከት ያገኘውን ዕውቀት ሲዴሪዩስ ኑንቺዩስ (ከዋክብታማው መልዕክተኛ) በተሰኘው የመጀመሪያ መጽሐፉ ላይ አትሞ አወጣ። በዚህ መጽሐፍም በዘመኑ ለነበረው ትውልድ ስል አራቱ የጁፒተር ጨረቃዎች አስተዋወቀ። በ1611 ወደ ሮም ተጠርቶ ሄደና ግኝቶቹን ለኢየሱሳዊው ኮሌጂዮ ሮማኖ (የሮማ ኮሌጅ) አቀረበ። እነሱም የጋሊሊዮ ቀን ተብሎ የሚከበር በዓል በማወጅ አከበሩት።

ቤተ ክርስቲያኗ የተቃወመቻቸው ትምህርቶች

በዚህ ጊዜ ጋሊሊዮ ከሮም ከመመለሱ በፊት ካርዲናል ቤላርሚን የሚባል አንድ ኃይለኛ ኢየሱሳዊ የጋሊሊዮ ትምህርቶች እንዲመረመሩ አነሣሣ። ጋሊሊዮ ፍጥረት የሚመራው ሰው በምርምርና ጥናት ሊደርስባቸው በሚችል ሕጎች አማካኝነት ነው ብሎ ያምን ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህን አመለካከት ተቃወመች።

አንዳንድ የከዋክብት ተመራማሪዎችም እንኳ ሳይቀሩ የጋሊሊዮን አስተያየት ተቃወሙ። ቴሌስኮፕ ያለውን ነባራዊ ነገር አጉልቶ ሊያሳይ አይችልም በማለት ግኝቱም የሐሰት ፈጠራ ነው ብለው አመኑ። እንዲያውም አንድ ቄስ በቴሌስኮፑ የሚታዩት ከዋክብት በሌንሱ ውስጥ የተተከሉ ነገሮች ናቸው የሚል ሐሳብ ሰጥቶ ነበር። ጋሊሊዮ በጨረቃ ላይ ተራሮች እንዳሉና ሰማያዊ አካላት ፍጹም ድቡልቡል ሳይሆኑ ወጣ ገባ ያለባቸው መሆናቸውን በተገነዘበ ጊዜ ክላቪየስ የተባለ ቄስ ጨረቃ መስተዋት በሚመስል ነገር የተከበበች ስለሆነ ተራሮች የሚመስሉ ነገሮች ብታይም መልኳ ፍጹም ኳስ ነው ብሎ ተከራከረው። ጋሊሊዮም መልስ ሲሰጥ “ውብ በሆነ የሐሳብ በረራ ላይ የተመሠረተ እምነት ነው” አለው።

ጋሊሊዮ “የተፈጥሮ መጽሐፍ” ብሎ ከሚጠራው የፍጥረት ጥናት ለማንበብ ያለው ጠንካራ ምኞቱ ኒኮላውስ ኮፐርኒከስ ወደሚባል አንድ የፖላንድ የከዋክብት ተመራማሪ ሥራ ዞር እንዲል አድርጐታል። ኮፐርኒከስ በ1543 ምድር በፀሐይ ዙሪያ እንደምትዞር የሚያስረዳ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር። ጋሊሊዮ ይህ እውነት መሆኑን አረጋገጠ። ይሁን እንጂ ይህ ጋሊሊዮን በዘመኑ ከነበረው ሳይንሳዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተቋሞች ጋር አጋጨው።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኮፐርኒከስን የከዋክብት ጥናት እንደ ፋሲካ የመሳሰሉት ዕለቶች የሚውሉበትን የቀን መቁጠሪያ ለመወሰን ብትጠቀምበትም የኮፐርኒከስ ሐሳቦች በይፋ ተቀባይነት አላገኙም ነበር። የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣኖች ምድር የጽንፈ ዓለም እምብርት ነች የሚለውን የአርስቶትልን ንድፈ ሐሳብ ይደግፉ ነበር። ይሁን እንጂ የጋሊሊዮ አዳዲስ ሐሳቦች ስማቸውን፣ ዝናቸውንና ሥልጣናቸውን ጥርጣሬ ላይ ጣለው።

በአውሮፓ በሙሉ የነበሩ ሳይንቲስቶች የኮፐርኒከስን ሐሳብ ለማረጋገጥ በተናጠል ቢሠሩም በምሁራን ዓለም ውስጥ ብቻ ስለ ጉዳዩ ከመወያየት አላለፉም ነበር። በዚህም ምክንያት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አላስቸገረቻቸውም። ጋሊሊዮ ግን በላቲን ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የተራው ሰው ቋንቋ በነበረው በጣሊያንኛም ጭምር ጽፎ ግኝቶቹን በሕዝብ ዘንድ አሳውቋቸው ነበር። ቀሳውስቱ ጋሊሊዮ ጥርጣሬ ላይ የጣለው እነሱን ብቻ ሳይሆን የአምላክን ቃልም ጭምር እንደሆነ ተሰማቸው።

የሳይንስ መጽሐፍ አይደለም

በእርግጥ ስለ አጽናፈ ዓለም እውነቱን መርምሮ ማግኘት የአምላክን ቃል ጥርጣሬ ላይ የሚጥል አይደለም። የአምላክ ቃል ተማሪዎች ወይም ተመራማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በሚነካበት ጊዜ ትክክል ቢሆንም የሳይንስ መምሪያ መጽሐፍ አለመሆኑን ይገነዘባሉ። መጽሐፉ የተጻፈው ፊዚክስ ወይም ሌላ የተፈጥሮ ሳይንስ ለማስተማር ሳይሆን የአማኞችን መንፈሳዊነት እንዲያሳድግ ተብሎ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ጋሊሊዮም ከዚህ ጋር ተስማምቷል። ሁለት ዓይነት አነጋገሮች ማለትም ትክክለኛ የሳይንስ ቃላትና በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ የየዕለቱ መነጋገሪያ ቃላት እንዳሉ አመልክቶ ነበር። “በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ . . . እነዚህን የሳይንስ ቃላት ከተራው ሰው የመረዳት ችሎታ ማለትም ፍጹም ከሆነው እውነት ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል” በማለት ጽፎ ነበር።

ለዚህ አባባል ምሳሌ የሚሆኑ አነጋገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ጥቅሶች ላይ ይገኛሉ። አንዱ ምድር “መሠረት” እና “የማዕዘን ድንጋይ” እንዳላት አድርጐ የሚናገረው ኢዮብ 38:6 ነው። አንዳንዶች ይህን ጥቅስ ምድር አንድ ቦታ የተቸከለች ለመሆኗ እንደ ማስረጃ አድርገው ያላግባብ ይጠቀሙበታል። እንዲህ ዓይነቶቹ አገላለጾች ስለ ምድር የሚናገሩ ሳይንሳዊ ገለጻዎች ሳይሆኑ የሕንፃ ሊቅ የሆነውን የይሖዋን የመሬት አፈጣጠር ከሕንፃ አሠራር ጋር በቅኔያዊ አነጋገር ማመሳሰላቸው ብቻ ነበር።

ኤል ጌይምነት የተባለ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ጋሊሊዮ ጋሊሌ በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ “ሳይንስን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ መሠረት ለመገደብ የሚፈልጉ ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው የሃይማኖት ሊቃውንት በመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ላይ ውርደት ከማምጣት በቀር ምንም አይፈይዱም” በማለት አስገንዝቧል። ሐሳበ ግትር የሆኑ ሰዎች በራስ ወዳድነት ምክንያት ያደረጉት ከዚህ የተለየ አይደለም። ጋሊሊዮ እንዲመረመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ወደ ቅዱሱ ቢሮ ተልኮ ነበር።

የካቲት 19, 1616 የካቶሊክ የሃይማኖት ሊቃውንት ሁለት ሐሳቦች ቀረቡላቸው። እነሱም (1) ፀሐይ የአጽናፈ ዓለም እምብርት መሆኗ (2) መሬት የአጽናፈ ዓለም እምብርት ያለመሆኗ ነበሩ። የካቲት 24 ሐሳቦቹ የቂሎችና የመናፍቃን ሐሳቦች ናቸው በማለት አወገዟቸው። ጋሊሊዮም በእነዚህ ሐሳቦች እንዳይጸናና እንዳያስተምር ታዘዘ። የእርሱና የሌሎችም በርካታ መጻሕፍት ታገዱ።

ጋሊሊዮ ድምፁ ጠፋ። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከመሰደዱም በላይ ወዳጆቹም የነበሩ ሰዎች እርሱን ለመርዳት ሳይችሉ ቀሩ። ራሱን በምርምርና ጥናት ሥራ ላይ አሰማራ። በ1623 የጳጳስ ለውጥ ባይደረግ ኖሮ ስለ እርሱ ዳግመኛ አንሰማም ነበር። ይሁንና አዲሱ ጳጳስ ኦርባን ስምንተኛ ምሁርና የጋሊሊዮም ደጋፊ ነበሩ። ጳጳሱ አዲሱን መጽሐፉን እንደማይቃወሙ ወሬው ለጋሊሊዮ ደረሰው። እንዲያውም ጳጳሱ አድማጮች ባሉበት በመጽሐፉ ላይ ክርክር እንዲደረግ ሐሳብ አቀረቡ። ይህን የሚያበረታታ የሚመስል ሁኔታ ስላገኘ ጋሊሊዮ ሥራውን ቀጠለ።

ምንም እንኳ የጋሊሊዮ ሁለቱን ዋና የዓለም ሥርዓቶች የሚመለከት ውይይት የተሰኘው መጽሐፍ በ1632 ለመጀመሪያ ጊዜ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፈቃድ ቢታተምም የጳጳሱ ስሜት ወዲያውኑ ቀዘቀዘ። ጋሊሊዮ በ70 ዓመት ዕድሜው ኢንኩዚሽን በተሰኘው የወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመናፍቃውያን ፍርድ ቤት ፊት ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቀርብ ተጠራ። ቤተክርስቲያንዋ በመናፍቅነት ሳትከስሰው በመጀመሪያ መጽሐፉ እንዲታተም የፈቀደችበትን ምክንያት መግለጽ ስለነበረባት ጋሊሊዮ ከዚያ በፊት የኮፐርኒከስን ትምህርት እንዳያስተምር ተደርጎበት የነበረውን እገዳ በማጭበርበር ደብቆአል ተባለ። ዳያሎግ የተባለው መጽሐፍ የከዋክብትን ሥርዓት፣ የኮፐርኒከስን ጭምር የሚያወዳድር ስለሆነ እገዳውን የሚጻረር ነው የሚል ክስ ቀረበበት።

ጋሊሊዮ የእርሱ መጽሐፍ ኮፐርኒከስን የሚነቅፍ እንደሆነ መልስ ሰጠ። በመጽሐፉ ውስጥ ኮፐርኒከስን የሚደግፍ ብዙ ሐሳብ ተሰጥቶ ስለነበረ ይህ የሰጠው የመከላከያ መልስ ደካማ ነበር። በተጨማሪም የጳጳሱ ቃላት ከመጽሐፉ ገጸ ባሕርያት በጣም ደደብ በነበረው ሲምፕሊችዮ የሚባል ገጸ ባሕርይ እንዲነገሩ ተደርገው ስለነበረ ጳጳስ ኦርባን ስምንተኛን የሚያስቀይም ነበር።

ጋሊሊዮ በመናፍቅነት ተፈረደበት

ጋሊሊዮ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ። ታሞ ስለነበረና ቃሉን ካላነሳ በግርፊያ እንደሚሠቃይ አስፈራርተውት ስለነበረ ቃሉን አጠፈ። በጉልበቱ ተንበርክኮ “. . . የተባሉትን ስሕተቶችና የመናፍቅነት ትምህርቶች . . . ዳግመኛ አልናገራቸውም። . . . በዚህ ወንጀል እንድጠረጠር የሚያደርጉኝን ትምህርቶች ሁሉ . . . ክጃቸዋለሁ።” ከተንበረከከበት ሲነሣ ግን ምድሪቱን መታ አድርጎ “ኢፑር ሲ ሙዋቬ! [ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!]” በማለት እንደተናገረ የሚገልጽ አፈ ታሪክ አለ።

ፍርዱ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በእስራት መቀጣት ሆነ። ከዘጠኝ ዓመት እስራት በኋላ ሞተ። በ1634 የጻፈው ደብዳቤ “ጠቡን ያነሣው የኔ አስተያየት ወይም እምነት ሳይሆን በኢየሱሳውያን ዘንድ መጠላቴ ነው” ብሏል።

በ 1822 በሥራው ላይ የተጣለው እገዳ ተነሣ። ይሁን እንጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄው እንደገና በዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ተነሥቶ ጋሊሊዮ “በቤተ ክርስቲያኗ ሰዎችና ድርጅቶች . . . እንዲሠቃይ” የተደረገ ስለመሆኑ የእምነት ቃል የሰጠው በ1979 ነበር። ላ ኦስር ቫቶሬ ሮማኖ በተባለው የቫቲካን ጋዜጣ ላይ የጋሊሊዮን የ1633 ፍርድ እንደገና የሚመረምር በዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የተቋቋመው ልዩ ኮሚሽን ዕውቅ አባል የሆኑት ማሪዮ ዳዲዮ “ጋሊሊዮ መናፍቅ መባሉ በሃይማኖታዊ ትምህርትም ይሁን በቤተ ክርስቲያን አንጻር ምንም ዓይነት መሠረት ያለው አይመስልም” ብለዋል። ዳ አዲዮ ባሉት መሠረት የኢንኩዚሽን ፍርድ ቤት ሥልጣኑን ተላልፏል። የጋሊሊዮ ንድፈ ሐሳቦች የእምነት ደንቦችን አይጥሱም ነበር። የቫቲካኑ ጋዜጣ በጋሊሊዮ ላይ በመናፍቅነት የተሰጠው ብይን መሠረተቢስ እንደነበረ አምኗል።

ከጋሊሊዮ ተሞክሮ ምን እንማራለን? አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። በመጽሐፍ ቅዱስና በሳይንስ መሃል ግጭት ያለ ሲመስል እያንዳንዱን “ልዩነት” ለማስታረቅ መሞከር አያስፈልገውም። ከሁሉ በላይ የክርስትና እምነት የተመሠረተው በሳይንስ ላይ ሳይሆን “ስለ ክርስቶስ በሚነገረው ትምህርት” ላይ ነው። (ሮሜ 10:17 የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም ሳይንስ ዘወትር የሚለወጥ ነው። ዛሬ በጣም ታዋቂ የሆነና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ የሚመስል ንድፈ ሐሳብ ነገ ስሕተት እንደሆነ ይደረስበትና ተቀባይነት ያጣል።

ሆኖም ሃይማኖት በሳይንስ ላይ የሚያደርገውን ጭቆና ለማሳየት ሳይንቲስቶች የጋሊሊዮን ጉዳይ ሲያነሡ ማስታወስ ያለባቸው የጋሊሊዮ ግኝት በዘመኑ በነበረው የምርምር ተቋምም ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ እንደነበረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዘመኑ ከነበረው አስተሳሰብ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ከዚያ እውነት ጋር የሚጋጭ አልነበረም። የአምላክ ቃል ምንም ዓይነት ክለሳ አላስፈለገውም። ችግር የፈጠረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የነበራት የተሳሳተ አተረጓጐም ነበር።

ማንኛውም ሰው በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ባለው በጣም የሚደነቅ ስምምነትና የተፈጥሮ ሕግ ፈጣሪው የሆነውን ይሖዋ አምላክን በእጅጉ ለማድነቅ መገፋፋት ይኖርበታል። ጋሊሊዮ “ሥራው ከቃሉ ያነሰ ክብር የሚሰጠው ነውን?” በማለት ጠይቆ ነበር። ሐዋርያውም “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጽ ሆኖ ይታያልና” በማለት መልስ ሰጥቷል።​—ሮሜ 1:20

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ