በሳይንስና በሃይማኖት መካከል የተፈጠረ ግጭት
በሞት አፋፍ ላይ የነበረው የ70 ዓመቱ የከዋክብት ተመራማሪ ለግኝቱ ማስረጃ የሆነውንና ለኅትመት የተዘጋጀውን ጽሑፍ ለማንበብ ይታገላል። እርሱ አወቀውም አላወቀው ጽሑፉ የሰው ልጅ ስለ ጽንፈ ዓለም ባለው አመለካከት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፤ እንዲሁም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እስከ ዘመናችን ድረስ የዘለቀ ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሏል።
ይህ የሆነው በ1543 ሲሆን አዛውንቱ ሰው ደግሞ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነው ፖላንዳዊው ኒኮላውስ ኮፐርኒከስ ነው። ኮፐርኒከስ፣ ኦን ዘ ሪቮሉሽንስ ኦቭ ዘ ሄቨንሊ ስፊርስ የሚል ርዕስ ባለው መጽሐፉ ላይ የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ፀሐይ እንጂ ምድር እንዳልሆነች ገልጿል። ይህ ሰው በዚህ መጽሐፉ ብቻ፣ የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ምድር ናት የሚለውን እጅግ በጣም ውስብስብ አስተሳሰብ የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ፀሐይ ናት በሚለው ቀላልና ግልጽ ጽንሰ ሐሳብ ተክቶታል።
መጀመሪያ ላይ ወደፊት ውዝግብ እንደሚነሳ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ አልነበረም። ይህ የሆነበት አንደኛው ምክንያት ኮፐርኒከስ ሐሳቡን በዘዴ ያቀርብ ስለነበረ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ምድር የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ናት በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ታምን የነበረችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ለሳይንሳዊ መላ ምቶች ተቃውሞ የነበራት አይመስልም። እንዲያውም ሊቀ ጳጳሱ ራሳቸው መጽሐፉን እንዲያሳትም ኮፐርኒከስን አደፋፍረውታል። ኮፐርኒከስ ጽሑፉን ባሳተመበት ጊዜ በፍርሃት ተውጦ የነበረው አዘጋጅ ፀሐይ እምብርት ናት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ፣ የሒሳብ ቀመር እንጂ ትክክለኛ የከዋክብት ምርምር ውጤት ነው ለማለት እንደማይቻል ራሱ ባዘጋጀው መቅድም ላይ ገልጿል።
ግጭቱ ተፋፋመ
ቀጥሎ በግጭቱ ውስጥ የገባው ሰው ጣሊያናዊው የከዋክብት ተመራማሪ እንዲሁም የሒሳብና የፊዚክስ ሊቅ የሆነው ጋሊሊዮ ጋሊሌ (1564-1642) ነው፤ ይህም ሰው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። ጋሊሊዮ በወቅቱ በተፈለሰፈው ሌንስ ተጠቅሞ በሠራው ቴሌስኮፕ አማካኝነት ከዚያ በፊት ታይተው የማያውቁ የሰማይ አካላትን በደንብ ተመለከተ። ይህም የኮፐርኒከስ ግንዛቤ ትክክል እንደነበር ለማወቅ አስቻለው። ከዚህም በተጨማሪ ጋሊሊዮ በአሁኑ ወቅት ነቁጠ ፀሐይ (ሰንስፖትስ) በመባል የሚታወቁትን በፀሐይ አካል ላይ የሚገኙትን ነጠብጣቦች ተመለከተ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ከነበረው ፀሐይ አትለወጥም ወይም አትበላሽም ከሚለው የፍልስፍናና የሃይማኖት ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚቃረን ነበር።
ጋሊሊዮ ከኮፐርኒከስ በተቃራኒ በድፍረትና በቅንዓት ስላወቀው ነገር ይከራከር ነበር። ይህንንም ያደረገው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኮፐርኒከስን ንድፈ ሐሳብ በግልጽ በማውገዟ ምክንያት ሃይማኖታዊ ተቃውሞ አይሎ በነበረበት ጊዜ ነው። ጋሊሊዮ ይከራከር የነበረው ፀሐይ እምብርት ነች ስለሚለው ሐሳብ ትክክለኝነት ብቻ ሳይሆን ይህ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል በማለት ስለነበር ቤተ ክርስቲያኒቱ በመናፍቅነት ትጠረጥረው ጀመር።a
ጋሊሊዮ ስለ ጉዳዩ ለመከራከር ወደ ሮም ቢሄድም አልተሳካለትም። በ1616 ቤተ ክርስቲያኒቱ ጋሊሊዮ፣ ኮፐርኒከስን ደግፎ መናገሩን እንዲያቆም ስላዘዘችው ለጥቂት ጊዜ ሐሳቡን ከመግለጽ ታቅቦ ነበር። በ1632 ላይ ግን የኮፐርኒከስን ሐሳብ የሚደግፍ ሌላ ጽሑፍ አሳተመ። በቀጣዩ ዓመት የካቶሊክ የፍርድ ሸንጎ በጋሊሊዮ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት በየነበት። ይሁን እንጂ የዕድሜውን መግፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ብያኔው በፍጥነት ወደ ቁም እስር እንዲለወጥ ተደረገ።
ብዙዎች በጋሊሊዮ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ ሳይንስ በሃይማኖት ላይ ይበልጥ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ድል መቀዳጀቱን እንደሚያሳይ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የተሳሳተ መደምደሚያ ከግንዛቤ ያላስገባቸውን በርካታ ሐቆች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጋሊሊዮ በንዴት መልስ ይሰጥና በሽሙጥ ይናገር ስለነበር ሳያስፈልግ ኃይለኛ ጠላቶችን አፍርቷል። እንዲሁም ፀሐይ እምብርት ነች የሚለውን ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፋል ብሎ በመከራከር ራሱን ሃይማኖታዊ እውቀት እንዳለው አድርጎ አቅርቧል፤ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ይበልጥ አስቆጣት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮፐርኒከስ
[ምንጭ]
ጆርዳኖ ብሩኖ ኤንድ ጋሊሌ ከተባለ ጽሑፍ ላይ የተወሰደ (ጀርመንኛ)
[በገጽ ላይ የሚገኝ ሥዕል3]
ጋሊሊዮ በሮም በሚገኘው የካቶሊክ ፍርድ ሸንጎ ፊት ቀርቦ ተከራክሯል
[ምንጭ]
ዘ ሂስቶሪያንስ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ ከተባለው መጽሐፍ ጥራዝ IX, (1904) ላይ የተወሰደ
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከበስተ ኋላ ያለው ሥዕል:- ኮፐርኒከስ ስለ ሥርዓተ ፀሐይ የነበረውን አመለካከት የሚያሳይ ካርታ