ታስታውሳለህን?
በቅርብ ጊዜ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በጥሞና ተመልክተሃልን? ከሆነ የሚከተሉትን ማስታወስ ትችላለህ።
◻ ይሖዋ ስላደረጋቸው ጦርነቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ታሪክ “ታላቁን መከራ” ለመጋፈጥ ትምክህት የሚሰጠን እንዴት ነው? (ማቴዎስ 24:21)
ሁሌ በተጠንቀቅ የሚጠባበቀው ይሖዋ ጠላቶቹን ሊያስትና ሁኔታዎችን ሕዝቡን ለማዳን በሚያስችል ሁኔታ መቀየስ እንደሚችል አሳይቷል።—8/15 ገጽ 27
◻ ወላጆች በራሳቸውና በልጆቻቸው መሃል ያለውን ግንኙነት ለመጠበቅ ምን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋቸዋል?
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው። እንዲሁም ለልጆቻቸው አእምሮአዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ እድገት ሲሉ አንዳንድ ነገሮችን መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለባቸው።—9/1 ገጽ 22
◻ የኢየሱስ መለወጥ በአሁኑ ጊዜ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል? (ማርቆስ 9:2-4)
መለወጡ በይሖዋ ትንቢታዊ ቃል ያለንን እምነት ሊገነባልንና ኢየሱስ ክርስቶስም የአምላክ ልጅና ተስፋ የተገባው መሲሕ ለመሆኑ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ሕይወት ትንሣኤ ለማግኘቱ ያለንን እምነት ያጠነክረዋል። በአምላክ መንግሥት ያለንን እምነትም ይጨምርልናል።—9/15 ገጽ 23
◻ በኢሳይያስ 11:6 ላይ “ለጊዜው” (አዓት) የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
ይህ ጥቅስ በጥንቃቄ ሲተረጎም የበግ ጠቦትና ተኩላ በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ ለዘወትር አንድ ላይ እንደማይሆኑ ያሳያል። እነዚህ እንስሳት ያኔም የተለያዩ መኖሪያዎች ሳይኖሩአቸው አይቀርም። ስለዚህ በመጀመሪያዋ ገነት እንደነበረው “ለማዳ እንስሳትና የዱር አራዊት” በመባል ሊከፋፈሉ ይችላሉ። (ዘፍጥረት 1:24) ይሁን እንጂ እንስሳት ያላንዳች ስጋት በአንድ አካባቢ ሊሆኑ ስለሚችሉ እርስ በርሳቸው በሰላም ይኖራሉ።—9/15 ገጽ 31
◻ ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ምንድን ነው?
ለእውነተኛ ክርስትና ቁልፉ ፍቅር ነው። እምነት፣ ሥራና ተስማሚ ባልንጀርነት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ፍቅር ከሌለ ግን ዋጋ አይኖራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት ይሖዋ በላቀ ሁኔታ የፍቅር አምላክ ስለሆነ ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:1-3፤ 1 ዮሐንስ 4:8)—10/1 ገጽ 20
◻ “ለመወለድ ጊዜ አለው። ለመሞትም ጊዜ አለው” የሚለው በመክብብ 3:2 ላይ ያለው አባባል አምላክ የመሞቻችንን ጊዜ አስቀድሞ ወስኖታል የሚለውን ሐሳብ ይደግፋልን?
አይደግፍም። ሰለሞን ፍጹማን ያልሆኑትን የሰው ልጆች የሚያጠቃቸውን የሕይወትና የሞት የማያቋርጥ ዑደት መግለጹ ብቻ ነበር። መክብብ 7:17 እንዲህ ይላል፦ “እጅግ ክፉ አትሁን እልከኛም አትሁን፤ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት።” የአንድ ሰው ዕለተ ሞት አስቀድሞ የተወሰነ ቢሆን ኖሮ ይህ ምክር ምን ትርጉም ይኖረው ነበር?—10/15 ገጽ 5-6
◻ ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮማ ጳጳስ መሆኑን የሚቃረነው ምንድን ነው?
ጴጥሮስ የሮማን ከተማ መጐብኘቱን እንኳ የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም። ጴጥሮስ ከክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ከመሆኑ በቀር ስለራሱ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም። (2 ጴጥሮስ 1:1)—10/15 ገጽ 8
◻ ክርስቲያኖች ወደ ቀብር ስነ ሥርዓት አበባ ቢልኩ ተገቢ ነውን?
ልማዱ (ወይም የአበባው ቅርጽ እንደ መስቀል ዓይነት ሆኖ) በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው የሚሰጠው ትርጉም ሃይማኖታዊ ከሆነ መወገድ ይኖርበታል። ስለዚህ ክርስቲያኖች በመስቀል ቅርጽ የተሠሩ አበባዎችን አይልኩም ወይም በእርግጥ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትርጉም ያላቸውን ነገሮች በማንኛውም ዓይነት መደበኛ መንገድ አይጠቀሙባቸውም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት በሌለው መንገድ አበባዎችን የመስጠት ልማድ ተስፋፍቷል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ያዘኑ ሰዎችን ለማጽናናትና የኀዘኑ ተካፋይነታቸውንና አሳቢነታቸውን ለማሳየት አበባዎችን ልከዋል።—10/15, ገጽ 31
◻ ይፋ የሆኑ ስለ ሥላሴ የሚሰጡ ፍቺዎች ግልጽ የሚያደርጉት ነገር ምንድን ነው?
ግልጽ የሚያደርጉት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለመረዳት ቀላል የሆነ ሐሳብ ያለመሆኑን ነው። ከዚህ ይልቅ በአያሌ መቶ ዘመናት ውስጥ የተሰባሰበና እርስ በርሱ የተቆላለፈ ውስብስብ የሆነ የሐሳቦች ስብስብ ነው። የሥላሴ አማኞችን ጨምሮ ብዙ ምሁራን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ያምናሉ።—11/1 ገጽ 21-2
◻ 29 እዘአ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ዋነኛ ቦታ የያዘው ለምንድን ነው?
ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትክክለኛ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን የጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ስለጀመረበት ዓመት ዓለማዊ ታሪክ ከሚሰጠው ማስረጃ ጋር በማዋሃድ የዮሐንስ አገልግሎት በ29 እዘአ ፀደይ ወራት እንደጀመረና ከ6 ወራት በኋላ በዚያው ዓመት በመከር ወራት ኢየሱስ እንደተጠመቀ ሊያሰሉ ስለሚችሉ ነው።—11/15 ገጽ 31
◻ ዕብራይስጥ ተናጋሪ ለሆኑ ሕዝቦች “አምልኮ” ማለት ምን ማለት ነበር? ይህስ ዛሬ ላሉት የይሖዋ ምስክሮች የሚሠራው ለምንድን ነው?
“አምልኮ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ተመሳሳይ “አገልግሎት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ስለዚህ በዕብራውያን ሐሳብ አምልኮ ማለት አገልግሎት ማለት ነው። ዛሬም ቢሆን ቃሉ ለይሖዋ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጉም ይኸው ነው። ስለዚህ የእውነተኛ ሃይማኖት አንዱና በጣም አስፈላጊ የሆነ ምልክት አምላካዊው የስብከት ሥራ ነው።—12/1 ገጽ 19