የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ይሖዋ ለእሥራኤል በሲና ምድረ በዳ የሚያስፈልገውን ሰጠ
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ‘እባብና ጊንጥ ጥማትም ወዳለባት ውኃ ወደሌለባት ወደ ታላቂቱና ወደምታስፈራው ምድረ በዳ’ ሲያመሩ እስቲ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! እነዚህ በዘዳግም 8:15 ላይ የሚገኙት የአምላክ ቃላት እሥራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ በሲና ምድረ በዳ በፊታቸው አስፈሪ መስሎ የሚታየውን ረዥም ጉዞ እንዳደረጉ በግልጽ ያሳዩናል። አንዱ ከፍተኛ ችግር በቂ ምግብና ውኃ ማን ይሰጣቸዋል? የሚለው ጥያቄ ነበር።
እሥራኤላውያን በአባይ ወንዝ ዳርቻ ባለው ደለል ላይ ሠፍረው በባርነት ይኖሩ ነበር። ነገር ግን ምንም ነገር አላጡም ነበር። ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች ወይን፣ በጢህና ሌሎች አዝርእት እንዲሁም የተመጣጠነ የምግብ ዓይነት አሣና ዶሮ ይመገቡ እንደነበረ በጥንት መቃብሮች ላይ ያሉ የግድግዳ ስዕሎች ያሳያሉ። በምድረ በዳ ሳሉ እንደሚከተለው በማለት ማጉረምረማቸው እንዴት ትክክል ነበር! “የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፣ ዱባውንም፣ በጢኹንም፣ ኩራቱንም፣ ቀዩንም ሽንኩርት፣ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን።”—ዘኁልቁ 11:4, 5፤ 20:5
እሥራኤላውያን ቀይ ባህርን ከተሻገሩ በኋላ የሲና ምንነት ወዲያውኑ ግልጽ ሆነላቸው። ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚወስደውን የእግር መንገድ ተዉና ሾጠጥ ወዳለው የባህር ሰላጤ ጫፍ አመሩ። በምድረ በዳ 80 ኪ.ሜ. ያህል እንደተጓዙ የሚጠጡት ውኃ የማግኘታቸው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ሆነ። በዚያ አካባቢ የነበረው ውኃ ስለሚመርና ምናልባትም በሽታ ሊኖረው ስለሚችል ያገኙትን ውኃ መጠጣት አይችሉም ነበር። “ምን እንጠጣለን?” ብለው ጮኹ። አምላክ ውኃውን ወደ ጣፋጭነት በመለወጥ ጣልቃ ገባ።—ዘጸአት 15:22-25
ከላይ ያለው የግመሎች ቅፍለት ምን እንደሚመስል ልብ በል። እሥራኤላውያን ያን በረሃ አቋርጠው ወደ ሲና ተራራ እንዴት ለመዝለቅ ይችሉ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ትክክለኛነት ልትገነዘብ ትችላለህ። እራሳቸውን እንዲሁም መንጐቻቸውን በሕይወት ለማቆየት የሚያስችላቸውን በቂ ምግብና ውኃ በማግኘት መቀጠል የሚችሉት እንዴት ይሆን?—ዘጸአት 12:38
ወደ ደቡብ አቅጣጫ ትንሽ እንደተጓዙ ወዲያው በኤሊም አጠገብ ጥማቸውን የሚያረካላቸውን ውኃና ጉልበታቸውን የሚያጠናክርላቸው ምግብ አገኙ። (ዘጸአት 15:27) ይሁን እንጂ ይህ የጉዞአቸው መጨረሻ አልነበረም። “ወደ [እውነተኛው (አዓት)] አምላክ ተራራ” ወደ ሲና እያመሩ ነበር። (ዘጸአት 3:1፤ 18:5፤ 19:2፤ 24:12-18) ይህም 120 ኪ.ሜ. ርቀት ያለው ወጣ ገባ የሆነ ደረቅ ምድር ነበር።
ይህ ትልቁ ቡድን ወደ ሲና ተራራ አጠገብ እንደደረሱ ፋራን በሚባል የበረሃ ገነት አጠገብ አረፉ። ይህም ቦታ በስተግራ ባለው ፎቶ ግራፍ ላይ በከፊል ይታያል።a ይህ ቦታ በረሃውን አቋርጦ እስከ ቀይ ባሕር (ስዊዝ ባህረ ሰላጤ) ይደርሳል። እሥራኤላውያን በዚያ ቦታ እንዴት ያለ ግሩም ዕረፍት ማግኘት ይችላሉ!
‘ታላቂቱና የምታስፈራው ምድረ በዳ’ የሚለው አገላለጽ በአጠቃላይ ለሲና ምድረ በዳ ተስማሚ ቢሆንም እሥራኤላውያን በፋራን የበረሃ ገነት ባሉበት ግርማ ሞገስ ባላቸው የዘንባባ ዛፎችና በሌሎች ዛፎች ጥላ መደሰት ችለው ነበር። ወዲያው ለሚበሉትም ሆነ ይዘውት ለሚሄዱት በቂ ጣፋጭ ተምር አግኝተው ነበር።
ይህ ሁሉ ሊገኝ የቻለው በፋራን አካባቢ ውኃው በመሬቱ ላይ ተንጣሎ ይገኝ ስለ ነበር ነው። በዚያ በረሃ እየተንከራተትክ (እየተጓዝክ) ያለኸው አንተ ብትሆንና የሚጠጣ ውኃ በድንገት ብታገኝ እንዴት እንደሚሰማህ እስቲ አስበው! እንግዲህ ይህ ሁሉ በሲናም እንኳ ቢሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ውኃ ሊገኝ እንደሚችል ያሳያል። አንዳንድ ጊዜም ጠለቅ አድርጎ ጉድጓድ መቆፈር ግድ ይሆናል። ከዚያ በኋላም ቢሆን ከጉድጓዱ ባልዲ ወይም እንሥራ አጥልቆ ውኃ ሞልቶ በማውጣት መንጐችን ማጠጣት ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። እስከ ዛሬ ድረስ ያሉ የሲና አረብ በረኸኞችም ለራሳቸውም ሆነ ለግመሎቻቸው ውኃ ለማግኘት ሲሉ የውኃ ጉድጓዶችን ይፈልጋሉ።—ከዘፍጥረት 24:11-20፤ 26:18-22 ጋር አወዳድር
እርግጥ ነው እሥራኤላውያን ሊወጡት የማይችሉት የሚመስላቸው ችግር ሲያጋጥማቸው ያንጎራጎሩባቸው ጊዜያቶች ቢኖሩም ምግብና ውኃ አግኝተው ነበር። አንዳንድ ጊዜ አምላክ በተአምር ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር። (ዘፀአት 16:11-18, 31፤ 17:2-6) በሌላ ጊዜም በጣም የሚያስፈልጋቸውን ተፈጥሮ ባስገኘቻቸው ነገሮች ለማርካት “እረፍት ወደሚገኝበት ቦታ” በቀጥታ ይመራቸው ነበር። (ዘኁልቁ 10:33-36 አዓት) ምንጊዜም ታማኝ ለሆኑት በተስፋይቱ ምድር የሚጠብቃቸው የተትረፈረፈ ምግብ ከፊታቸው አስቀምጦላቸው ነበር።—ዘዳግም 11:10-15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፎቶ ግራፉ በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ በትልቁ ይገኛል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 24 , 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.