የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
አንድ የውኃ ጉድጓድ ማግኘት ሕይወት እንደ ማግኘት የሚቆጠርባት ቤርሳቤህ
“ከዳን እስከ ቤርሳቤህ።“ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዘንድ የተለመደ አባባል ነው። በሰሜናዊ ድንበር ዳርቻ አቅራቢያ ከምትገኘው ዳን በደቡብ እስካለችው ቤርሳቤህ ድረስ ያለውን መላውን እስራኤልን ያጠቃልላል። በሰሎሞን ግዛት ስለነበረው ሰላም እንዲህ ተገልጿል፦ “በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑ እና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።“—1 ነገሥት 4:25፤ መሳፍንት 20:1
በዳንና በቤርሳቤህ መካከል የነበረው ልዩነት የቦታ መራራቅ ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ዳን በቂ ዝናብ ያላት ስትሆን በስተቀኝ ባለው ፎቶግራፍ እንደሚታየው ከዮርዳኖስ ወንዝ ምንጮች ለአንደኛው የሚገብሩ ወንዞችም ከምድሪቱ ይፈሳሉ። ቤርሳቤህ ግን በባሕር አካባቢ የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ከዚህ በጣም የተለየች ነበረች።
በቤርሳቤህ አካባቢ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ከ150 እስከ 200 ሚሊ ሜትር ብቻ ነበር። ይህንን በአእምሮህ ይዘህ ከላይ ያለውን የቤርሳቤህን ጉብታ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ተመልከት።a የምታየው ልምላሜ በቤርሳቤህ አካባቢ ያሉ ሜዳዎች ለአጭር ጊዜ ለምለም በሚሆኑበትና የተወሰነ መጠን ካለው የክረምት ዝናብ በኋላ የተነሣ ፎቶግራፍ መሆኑን ይጠቁማል። በአቅራቢያው ያሉ ሜዳዎች ለጥራጥሬ እህሎች ተስማሚ ነበሩ፤ አሁንም ቢሆን እንደዚያ ናቸው።
አካባቢው ደረቅ በመሆኑ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤርሳቤህ የሚሰጣቸው ዘገባዎች ሁሉ የውኃ ጉድጓድንና የውኃ ባለቤትነትን አጉልተው የሚገልጹ ናቸው። ከተማዋ የምትገኘው በረሃውን አቋርጠው ወደ ደቡብ በሚወስዱ የግመሎች ቅፍለት መጓጓዣ በሆኑ መንገዶች አጠገብ ነበር። በዚያ የሚያልፉት ተጓዦችም ሆኑ እዚያ የሚያርፉት ለእነርሱ እና ለከብቶቻቸው ውኃ እንደሚያስፈልጋቸው መገመት ትችላለህ። ይህ ውኃ ደግሞ በዳን እንደሚታየው ከመሬት ውስጥ እየተፍለቀለቀ የሚወጣ ሳይሆን ከውኃ ጉድጓዶች የሚገኝ ነበር። እንዲያውም ’ቤር’ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ከመሬት በታች ያለን ውኃ ለማውጣት የተቆፈረን አንድ ጉድጓድ ያመለክታል። ቤርሳቤህ ማለት “የመሀላውን የውኃ ጉድጓድ“ ወይም “የሰባቱ የውኃ ጉድጓድ“ ማለት ነው።
አብርሃም እና ቤተሰቡ በቤርሳቤህ ውስጥ እና በአካባቢዋ ለረጅም ጊዜ ኖረዋል። ስለዚህ የውኃ ጉድጓዶችን ጠቀሜታ ያውቁ ነበር። የሣራ አገልጋይ የነበረችው አጋር ወደ በረሃ ስትኮበልል ከውኃ ጉድጓዶች ወይም በጉድጓዶቹ ከሚጠቀሙት የበድዊን ዘላኖች ውኃ አገኛለሁ ብላ አቅዳ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በሚቀጥለው ገጽ ላይ ከላይ ባለው ሥዕል በሲና ልሳነ ምድር ከሚገኝ የውኃ ጉድጓድ አንዲት የበድዊን ዘላን ውኃ ስትቀዳ ትታያለች። አብርሃም አጋርን ከተሳዳቢ ልጅዋ ጋር ማባረር ግድ በሆነበት ጊዜ በደግነት ለመንገድ የሚሆናትን ውኃ ሰጣት። ያ ሲያልቅ ምን አጋጠማት? “እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፣ የውኃ ጉድጓድም አየች፤ ሄዱም አቁማዳዋን በውኃ ሞላች፣ ብላቴናውንም አጠጣች።“—ዘፍጥረት 21:19
አብርሃም የአጋርን አቁማዳ ለመሙላት ውኃ ከየት አገኘ? ምናልባት የታማሪስክ ዛፍ ከተከለበት ቦታ አጠገብ ከቆፈረው የውኃ ጉድጓድ ይሆናል። (ዘፍጥረት 21:25-33) አሁን ሳይንቲስቶች አብርሃም የታማሪስክ ዛፍን ለመትከል ያደረገው ምርጫ ተገቢ መሆኑን ይስማማሉ ሊባል ይችላል። ምክንያቱም ይህ ዛፍ ቀጫጭን ቅጠሎች ያሉትና ብዙ እርጥበት የማያባክን ስለሆነ ምንም እንኳ አካባቢው ደረቅ ቢሆንም ሊፋፋ ይችላል።- ከታች ያለውን ሥዕል ተመልከት።
በአብርሃምና በአንድ ፍልስጤማዊ ንጉሥ መካከል ከነበረው ክርክር ጋር በተያያዘ መንገድ አብርሃም የውኃ ጉድጓድ መቆፈሩ ተጠቅሷል። ከፍተኛ የውኃ እጥረት ስለነበረና ጥልቀት ያለው የውኃ ጉድጓድ ለመቆፈር ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ የውኃ ጉድጓድ በጣም ውድ ሀብት ነበር። እንዲያውም በዚያን ወቅት ሳያስፈቅዱ የጉድጓዶችን ውኃ መጠቀም የባለቤትነትንም መብት መዳፈር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።—ከዘኁልቁ 20:17, 19 ጋር አወዳድር።
የቤርሳቤህን ጉብታ ብትጎበኝ በስተደቡብ ምሥራቅ ካለው ተዳፋት ላይ በጥልቀት የተቆፈረ ጉድጓድ ታያለህ። አንድ ወጥ አለት በመቦርቦርና ላይኛውን ክፍል በግንብ በማጠናከር የተዘጋጀው ይህ ጉድጓድ (ከታች የሚታየው) መቼ እንደተቆፈረ የሚያውቅ የለም። ዘመናዊ በቁፋሮ የጥንት ታሪክ ተመራማሪዎች ወደታች ከሠላሳ ሜትር በላይ ካጸዱ በኋላ እንኳ መጨረሻውን አላገኙትም። ከእነርሱም መካከል አንዳቸው ’ይህ የውኃ ጉድጓድ አብርሃም እና አቢሜሌክ ቃል ኪዳን ያደረጉበት ’የመሀላው የውኃ ጉድጓድ’ ነው ለማለት ፈታኝ ነው“ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።—ቢብሊካል አርኪዎሎጂ ሪቪው
ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ቤርሳቤህ በኋላኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ተስፋፍታ ታላቅ በር ያላት የተመሸገች ከተማ ሆና ነበር። ለከተማዋ ሕልውናና እድገት መሠረት የነበረው ከጥልቅ ጉድጓዶቿ የሚገኘው ሕይወት አድን ውኃዋ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a For a larger view of Tell Beer-sheba, see the 1993 Calendar of Jehovah’s Witnesses.
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.