ክፍል 2—በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ይሖዋ እንክብካቤ አድርጎልናል
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በናዚ የወታደር ደንብ ልብሴ መታጠቂያ ዘለበት ላይ “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ጽሑፍ ነበረው። ይህ ለእኔ አብያተ ክርስቲያናት በጦርነቱና ደም በማፍሰሱ ተግባር ተካፋይ መሆናቸውን የሚያሳየኝ ሌላው ማስረጃ ነበር። ይህ ነገር አስጠልቶኝ ነበር። ሃይማኖትን በመጥላት የአምላክን መኖር የምክድና በዝግመተ ለውጥ የማምን ሆኜ እያለሁ በምሥራቅ ጀርመን በሊምባክ-ኦበርፍሮህና ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አነጋገሩኝ።
ለሚያነጋግሩኝ ምሥክሮች “ክርስቲያን ይሆናል ብላችሁ አታስቡ” አልኳቸው። ይሁን እንጂ ያቀረቡልኝ የመከራከሪያ ነጥቦች በአምላክ መኖር እንዳምን አደረጉኝ። ለመመራመር ፍላጎት አደረብኝና መጽሐፍ ቅዱስ ገዛሁ። ከጊዜ በኋላ ከእነርሱ ጋር ማጥናት ጀመርኩ። ይህ የሆነው በ1953 የጸደይ ወራት ላይ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በምሥራቅ ጀርመን በኮሚኒስታዊ እገዳ ሥር ከሆነ ወደ ሦስት ዓመታት ያህል ሆኖት ነበር።
የነሐሴ 15, 1953 የመጠበቂያ ግንብ በዚያን ወቅት የነበረው የይሖዋ ምሥክሮችን ሁኔታ እንዲህ በማለት ገለጸ፦ “ምንም እንኳ ባለማቋረጥ ስለላ የተካሄደባቸውና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው ቢሆንም፣ የሚከታተላቸው ሰው አለመኖሩን ሳያረጋግጡ እርስ በርሳቸው መጠያየቅም ሆነ መነጋገር ባይችሉም፣ አንድ ሰው የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፍ ይዞ መገኘቱ ‘ጽሑፍ ያሰራጫል’ ተብሎ የሁለት ወይም የሦስት ዓመት እሥራት ቢያስፈርድበትም፣ ሥራውን የሚመሩ በመቶ የሚቆጠሩ የጐለመሱ ወንድሞች ቢታሰሩም በምሥራቅ ጀርመን የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች መስበካቸውን ቀጥለዋል።”
በ1955 ባለቤቴ ሬጂና እና እኔ በምዕራብ ጀርመን በናርምበርግ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተገኘን። ከአንድ ዓመት በኋላም ሁለታችንም በምዕራብ በርሊን ተጠመቅን። ይህ የሆነው ምሥራቅ ጀርመንን ከምዕራብ በርሊን የሚለየው የበርሊን ግምብ በ1961 ከመሠራቱ በፊት ነበር። ይሁን እንጂ ከመጠመቄ በፊትም እንኳን ቢሆን ለይሖዋ ያለኝ ታማኝነት ፈተና ላይ ወድቆ ነበር።
ሃላፊነት ተሰጠኝ
በሊምባክ ኦበርፍሮህና ለተጀመረው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የሚያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከምዕራብ በርሊን የሚያመጣ ሰው አስፈለገ። በዚያን ጊዜ ትንሽ የንግድ ሥራና ሁለት ታዳጊ ልጆች ነበሩን። ይሁን እንጂ ይሖዋን ማገልገል የሕይወታችን ዋናው ትኩረት ነበር። አሮጌ መኪናችንን ስድሳ መጻሕፍትን ደብቃ እንድትይዝ አድርገን ማሻሻያ አደረግንላት። መልእክትና ጽሑፍ አመላላሽ ሆኖ መሥራት አደገኛ ሥራ ነበር። ነገር ግን በይሖዋ እንድመካ አስተምሮኛል።
ከምሥራቅ በርሊን ወደ ምዕራቡ ክፍል በመኪና ማቋረጥ ቀላል አልነበረም። ብዙ ጊዜም እንዴት ይሳካልን እንደነበረ ይደንቀኛል። ነፃ በሆነው የጀርመን ክልል ከገባን በኋላ ጽሑፎችን እንሰበስብና ወደ ምሥራቅ ጀርመን የሚወስደውን ድንበር ከማለፋችን በፊት በመኪናዋ ውስጥ እንደብቀው ነበር።
በአንድ ወቅት ላይ መጽሐፎቹን ደብቀን እንደጨረስን ከአንድ አፓርታማ የወረደ አንድ የማናውቀው ሰው መጣ። “እናንተ” ብሎ ጮኸብን። ልቤ ለአንድ አፍታ ቆም አለች። ሲመለከተን ቆይቷል? “በሌላ ጊዜ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ይሻላችኋል። የምሥራቅ ጀርመን የፖሊስ መኪና እዚያ ጥግ ቆሟል፣ ሊይዟችሁ ይችላሉ” አለን። የእፎይታ ትንፋሽ ተነፈስኩ። ድንበር መሻገሩም በደህና ተሳካ። መኪናዋ ውስጥ የነበርነው አራታችንም እየዘመርን ወደ መኖሪያችን ተመለስን።
ተገልሎ ለመሥራት መዘጋጀት
በ1950ዎቹ ዓመታት የምሥራቅ ጀርመን ወንድሞች ጽሑፍና መመሪያ ያገኙ የነበሩት በምዕራብ ጀርመን ካሉት ወንድሞች ነበር። ነገር ግን በ1960 በምሥራቅ ጀርመን የሚኖር እያንዳንዱ ምሥክር በአካባቢው አብሮት ከሚኖረው ምሥክር ጋር የተቀራረበ ግንኙነት እንዲያደርግ ማስተካከያዎች ተደረጉ። ከዚያም በኋላ በሰኔ ወር 1961 የሽማግሌዎች የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ክፍል በበርሊን ተደረገ። ይህን የአራት ሣምንት የመጀመሪያ ኮርስ ተካፈልኩ። ስድስት ሣምንት ሳይሞላ የበርሊን ግንብ ሲቆም ከምዕራብ ጀርመን ጋር የነበረን ግንኙነት በድንገት ተቋረጠ። አሁን ሥራችን በድብቅ የሚካሄድ ብቻ ሳይሆን በግንኙነትም በኩል የተገለለ ሆነ።
በምሥራቅ ጀርመን የሚካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አለቀለት፣ ያቆማል ብለው አንዳንዶች ፈርተው ነበር። ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በፊት ቀደም ብሎ ተደርጎ የነበረው ድርጅታዊ ማስተካከያ መንፈሳዊ ጥንካሬአችንንና አንድነታችንን ይዘን እንድንቀጥል ረድቶናል። በተጨማሪም በመጀመሪያው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ስልጠና ያገኙ ሽማግሌ ወንድሞች ይህንን ማሰልጠኛ ለሌሎች ሽማግሌዎች ለማስተላለፍ የሚያስችላቸውን ትጥቅ አግኝተው ነበር። ስለዚህ ይሖዋ በ1950ዎቹ ለተደረገው ዕገዳ በ1949 በተደረጉት ወረዳ ስብሰባዎች እንዳዘጋጀን ሁሉ አሁንም ከፊታችን እንዲሁ ይጠብቀን ለነበረው መገለል አዘጋጀን።
ከምዕራብ ጋር የነበረን ግንኙነት መቋረጡ፣ ድርጅቱ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለብን ግልጽ አደረገው። በምዕራብ በርሊን ወደሚገኘው ክርስቲያን ወንድሞቻችን ደብዳቤ ጽፈን ከምዕራብ ለሚመጡ መንገደኞች ቅርብ በሆነው በአንድ የምሥራቅ አውራ ጐዳና ላይ እንድንገናኝ ሐሳብ አቀረብንላቸው። በቀጠሮው ቦታ የመኪና ብልሽት ያጋጠመን ለማስመሰል ሞከርን። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወንድሞች ጽሑፎች ይዘውልን በመኪና መጡ። ደስ የሚያሰኝ ሌላው ደግሞ ለጥንቃቄ ያህል በበርሊን ትቻቸው የነበሩትን የመንግሥት አገልግሎት የመማሪያ መጽሐፌን፣ ማስታወሻዬንና መጽሐፍ ቅዱሴንም ጭምር ይዘውልኝ መጡ። ጽሑፎቹን መልሼ ሳገኝ እንዴት ደስ አለኝ! እነዚህ ጽሑፎች በሚቀጥሉት ዓመታት ምን ያህል እንደሚያስፈልጉኝ አላወቅሁም ነበር።
በድብቅ የሚካሄድ ትምህርት ቤት
በሁሉም የምሥራቅ ጀርመን ክፍሎች የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል እንድናዘጋጅ ከጥቂት ቀናት በኋላ መመሪያ ደረሰን። እኔንም ጨምሮ አራት አስተማሪዎች ተሾምን። ይሁን እንጂ በዕገዳ ሥር እያለን ሁሉንም ሽማግሌዎች ማሰልጠን የማይቻል ሥራ መስሎ ተሰማኝ። ምን እንደምንሠራ እንዳይታወቅብን ኮርሶቹ በሽርሽር መልክ እንዲካሄዱ ወሰንኩ።
እያንዳንዱ ክፍል አራት ተማሪዎችን የያዘ ነበር። እኔ እንደ አስተማሪ ስድስተኛው ወንድም ደግሞ እንደ ወጥ ቤት ሆንን። ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም አብረው ይመጡ ነበር። ስለዚህ ቡድኑ ብዙውን ጊዜ ከ15 እስከ 20 ሰዎች ይይዝ ነበር። አንድ ቦታ ሁልጊዜ ለሽርሽር መሄድ ጥሩ መሆኑ አጠያያቂ መስሎ ስለተሰማኝ ቤተሰቤና እኔ ተስማሚ ሥፍራዎችን ለመፈለግ እንወጣ ነበር።
በአንድ ወቅት በአንድ ሠፈር ውስጥ እየተጓዝን ሳለ ከዋናው መንገድ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጫካ የሚያመራ ቀጭን የእግር መንገድ መኖሩን አስተዋልን። በጣም ተስማሚ ጥሩ ቦታ መስሎ ታየን። ስለዚህ የአካባቢውን ሹም ቀርቤ “ለአንድ ለሁለት ሣምንት ያህል ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ሆነን በመዝናናት የምናሳልፍበትን ቦታ እየፈለግን መሆናችንን አስረዳሁት። ልጆቻችንም በደንብ ለመጫወት እንዲችሉ ለብቻችን ለመሆን እንፈልጋለን፤ ያንን ጫካ ለዚህ ልንጠቀምበት እንችላለንን?” ብዬ ጠየቅሁት። እርሱም ስለተስማማ ዝግጅት አደረግን።
በቦታው በድንኳኖችና በተሳቢ መኪናዬ ተጠቅመን ከአካባቢው የተሰወረ ባለ አራት ማዕዘን ማዕከል ሠራን። ተሳቢ መኪናው እንደመማሪያ ክፍል ሆኖ አገለገለ። በየቀኑ ለ8 ሰዓት ያህል በጥንቃቄ ለሚደረግ ጥናት ለ14 ቀናት ያህል ተሰብስበንበታል። ያልተጠበቁ ሰዎች ቢመጡብን በማለት በዚህ በታጠረው ክፍል ወንበሮችና ጠረጴዛ አዘጋጅተን ነበር። ይህ ዓይነቱ ሁኔታም አጋጥሞን ነበር። እንደዚህ ባሉት ጊዜ ቤተሰቦቻችን ያደረጉልን ፍቅራዊ ድጋፍ በእውነት የሚደነቅ ነበር።
በትምህርቱ ክፍለ ጊዜ ቤተሰቦቻችን ቆመው ይጠብቁን ነበር። አንድ ጊዜ በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት የአካባቢው የኮሚኒስት ፓርቲ ጸሐፊ የነበረው የአካባቢው ሹም ወደ ጫካችን ሲያመራ ታየ። ጠባቂውም ከተሳቢ መኪናው ጋር በተያያዘ ሽቦ የማስጠንቀቂያ ምልክት ሰጠ። ወዲያውኑ ከመኪናው እየዘለልን ወጣንና አስቀድሞ ወደተዘጋጀው ጠረጴዛና ወንበሮች ሄደን ካርታ መጫወት ጀመርን። ነገሩን እውነተኛ ለማስመሰል የአልኮል መጠጥ በጠረጴዛው ላይ ነበር። ሹሙ በወዳጅነት መልክ ጠየቀንና ይካሄድ ስለነበረው ነገር ምንም ጥርጣሬ ሳያድርበት ተመልሶ ሄደ።
ከ1962 ጸደይ ወራት ጀምሮ እስከ 1965 መጨረሻ አካባቢ በመላው የአገሪቱ ክፍል የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ተደርጎ ነበር። በምሥራቅ ጀርመን ያለውን ሁኔታ መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ ማጥናትን የሚጨምረው ይህ ከፍተኛ ስልጠና ሽማግሌዎች የስብከቱን ሥራ በበላይነት እየተቆጣጠሩ እንዴት ማካሄድ እንደሚችሉ በማሰልጠን አዘጋጃቸው። በዚህ ትምህርት ቤት ለመሰልጠን ሽማግሌ ወንድሞች የዕረፍት ጊዜአቸውን መሰዋት ብቻ ሳይሆን የመታሠርን አደጋም ጭምር ተቀብለው ይመጡ ነበር።
ትምህርት ቤቱ ያስገኛቸው ጥቅሞች
ባለሥልጣኖች እንቅስቃሴዎቻችንን በጥንቃቄ ይከታተሉ ነበር። በ1965 መጨረሻ አካባቢ አብዛኛዎቹ ሽማግሌዎች በትምህርት ቤቱ ከሰለጠኑ በኋላ ድርጅታችንን ለማፍረስ አደገኛ ሙከራ አደረጉ። የሥራው መሪዎች ናቸው ብለው ያሰቧቸውን 15 ምሥክሮች አሰሩ። አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ያዳረሰ በደንብ ዝግጅት የተደረገበት እርምጃ ነበር። አሁንም የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ፣ ያቆማል፣ አለቀለት ብለው ብዙዎች አሰቡ። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ሁኔታዎችን አስተካከልንና ሥራችንን እንደበፊቱ ማካሄዳችንን ቀጠልን።
ይህን ማድረግ የተቻለው ሽማግሌዎቹ ከአገልግሎት ትምህርት ቤቱ ባገኙት ሥልጠናና በተለይ በእነዚህ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት አብረው በማሳለፍ ባዳበሩት መቀራረብና መተማመን የተነሳ ነው። በዚህ መንገድ ድርጅቱ ያለውን ጥንካሬ አሳየ። ድርጅታዊ መመሪያዎችን በታዛዥነት መከተላችን እንዴት ጠቀመን!—ኢሳይያስ 48:17
የመንግሥት ባለሥልጣኖች ያደረጉት ተጽእኖ በሥራችን ላይ ምንም ያህል ጉዳት እንዳላስከተለ በተከታዮቹ ወራት ግልጽ ሆነ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤቱን ሥልጠና እንደገና ለመጀመር ቻልን። ባለሥልጣኖቹ ሥራችንን እንደገና መጀመራችንን ሲያውቁ እነርሱም ዘዴዎቻቸውን ለመለወጥ ተገደዱ። ይህ ለይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ ድል ነበር!
በአገልግሎት ተግቶ መሥራት
በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ጥናት ተሳታፊዎች ብዛት አምስት ያህል ነበር። እያንዳንዳችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎቻችንን የምናገኘው በዚህ የመጽሐፍ ጥናት ዝግጅት በኩል ነበር። በዚያን ጊዜ የስብከቱን ሥራ የሚያስተባብሩት እነዚህ የጥናት ቡድኖች ነበሩ። ይሖዋ ገና ከመጀመሪያው ሬጂናን እና እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎችን እንድናገኝ በማድረግ ባረከን።
ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎትም እንዳይነቁብንና እንዳይዙን ሲባል ለወጥ ባለ ሁኔታ ይካሄድ ነበር። ወደ ተሰጠን አንድ አድራሻ እንሄድና ከዚያም ትንሽ አለፍ ብለን ወደ ሌላ ቤት እንሄድ ነበር። ወደ አንድ ቤት ስንደርስ አንዲት ሴት ሬጂናን እና እኔን ወደ ቤቷ እንድንገባ ጋበዘችን። ከእርሷ ጋር አጠቃላይ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት እየተነጋገርን ሳለን፣ ወንድ ልጅዋ ወደ ክፍሉ መጣ። የልጁ አነጋገር በጣም ቀጥተኛ ነበር።
“አምላካችሁን አይታችሁት ታውቃላችሁን?” ብሎ ጠየቀን። “እናንተ እናውቃለን ብትሉ፣ እኔ የማምነው የማየውን ብቻ እንደሆነ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ሌላው ነገር ሁሉ የማይረባ ነው” አለን።
“አንተ የምትለውን ላምን አልችልም። አንጐልህን አይተኸው ታውቃለህ? የምታከናውነው ማንኛውም ተግባር አንጐል ያለህ መሆኑን ያሳያል” አልኩት።
ሬጂና እና እኔ በዓይናችን ሳናያቸው መኖራቸውን የምንቀበለው ለምሳሌ እንደ ኤሌክትሪክ ያሉ ብዙ ነገሮች መኖራቸውን አስረዳነው። ወጣቱ ልጅ በጥሞና አዳመጠን፣ ለእርሱና ለእናቱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርንላቸው። ሁለቱም ምሥክሮች ሆኑ። እንዲያውም፣ እኔና ባለቤቴ ያስጠናናቸው 14 ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ግማሾቹ ከቤት ወደ ቤት ባደረግነው ጉብኝት ያገኘናቸው ሲሆኑ ግማሾቹ ደግሞ መደበኛ ባልሆነ ምሥክርነት የተገኙ ነበሩ።
አንድ ሰው በቋሚነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከተመራለትና ሰውዬውን ሊታመን ይችላል ብለን ካሰብን ወደ ስብሰባዎቻችን እንዲመጣ እንጋብዘው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ ተማሪው የአምላክን ሕዝቦች ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንዳይሆን ነበር። ስለዚህ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ከቆየ በኋላ ወደ ስብሰባ እንዲመጣ እንጋብዘው ነበር። በወቅቱ ትልቅ ቦታ የነበረውን አንድ ሰው አስታውሳለሁ። በኮሚኒስት ፓርቲ ከፍተኛ ሹሞች ዘንድ ስሙ በአንደኛ ደረጃ ከሚታወቁት አንዱ ነበር። ወደ ስብሰባዎች እንዲመጣ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ለዘጠኝ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን አጥንቷል። ዛሬ ይህ ሰው ክርስቲያን ወንድማችን ነው።
ባለሥልጣኖች አሁንም ይከታተሉን ነበር
በብዛት መታሰራችን ከ1965 በኋላ ቢቆምም ሙሉ በሙሉ ሰላምን አላገኘንም፤ ባለሥልጣኖች አሁንም ጥብቅ ክትትል ያደርጉብን ነበር። በዚህ ወቅት በድርጅታችን ውስጥ በይበልጥ እሳተፍ ነበር። ስለዚህ ባለሥልጣኖች ልዩ ትኩረት አደረጉብኝ። ስፍር ቁጥር ለሌለው ጊዜ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስጄ እመረመርና እጠየቅ ነበር። “ወህኒ ቤት መውረድህ ነው ነፃነትን ልትሰናበት ትችላለህ” ይሉኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ውሎ አድሮ ይለቁኝ ነበር።
በ1972 ሁለት ባለሥልጣኖች እኔን ለማነጋገር ወደ ቤቴ መጡ። ሳይታወቃቸው ድርጅታችንን የሚያሞግስ ቃል ተናገሩ። የጉባኤ የመጠበቂያ ግንብ ጥናታችንን ሲያዳምጡ ቆይተው ነበር። የርዕሰ ትምህርቱን ሐሳብ በጣም እንቃወማለን ብለው ሐሳባቸውን ገለፁ። ያሳሰባቸው ሌሎች ሰዎች ጽሑፉን ሲያነቡ ስለ ኮሚኒስት ርዕዮተ-ዓለም ምን ይሰማቸው ይሆን የሚለው ስጋት እንደሆነ ግልጽ ነው። የሆነው ሆኖ “የመጠበቂያ ግንብ በአምስት ወይም በስድስት ሚልዮን ቅጂ ይሠራጫል። በታዳጊ አገሮችም አንባብያን አሉት። ቀላልና ርካሽ የሆነ ጽሑፍ አይደለም” አሉ። በልቤም ‘ልክ ናችሁ’ አልኩ።
በ1972 በዕገዳ ሥር ከሆንን 22 ዓመት ሆኖ ነበር። ይሖዋ በፍቅርና በጥበብ ሲመራን ቆይቶ ነበር። መመሪያዎቹን በጥንቃቄ ተከትለናል። ነገር ግን በምሥራቅ ጀርመን የምንገኝ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ከማግኘታችን በፊት ተጨማሪ 18 ዓመታት ማለፍ ነበረባቸው። አምላካችን ይሖዋ እርሱን በማምለክ አሁን የምንደሰትበትን አስደናቂ ነፃነት ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን።—ሔልሙት ማርቲን እንደተናገረው።