ክፍል 3—በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ይሖዋ እንክብካቤ አድርጐልናል
ዕለቱ መጋቢት 14, 1990 ነበር። በዚህ ታላቅ ቀን በምሥራቅ በርሊን የሃይማኖት ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በዚያ ጊዜ የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ትባል በነበረችው በምሥራቅ ጀርመን ሕጋዊ እውቅና ያገኘ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ ሲሰጥ ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። በዚህ ቀን በተከናወነው ሥነ ስርዓት ላይ እንዳለሁ የይሖዋ ምሥክር በሆንኩበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታና ያሳለፍናቸውን የመከራ ጊዜያት ወደ ኋላ መለስ ብዬ አስታውስ ነበር።
በ1950ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ማርጋሬት የተባለችው የሥራ ጓደኛዬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ተመሠረተው እምነቷ በነገረችኝ ጊዜ በምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ይደርስ የነበረው ስደት በጣም ተባብሶ ነበር። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ማርጋሬት ወደሌላ ቦታ ሄዳ መሥራት ጀመረች። እኔም ከሌላ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። በ1956 ተጠመቅሁ። በዚሁ ዓመት ማርጋሬት እና እኔ ተጋባን። በበርሊን የሚገኘው የሊክትንበርግ ጉባኤ አባሎች ነበርን። በዚያ ጊዜ ይህ ጉባኤ በስብከቱ ሥራ የሚሳተፉ ወደ 60 የሚደርሱ የመንግሥት አስፋፊዎች ነበሩት።
ከተጠመቅሁ ከሁለት ዓመት በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጉባኤያችንን በግንባር ቀደምትነት ይመራ ወደነበረው ወንድም ቤት መጡ። አመጣጣቸው እርሱን ለማሰር ነበር። ነገር ግን ይሠራ የነበረው በምዕራብ በርሊን ስለነበር አላገኙትም። ቤተሰቦቹም እዚያው እንዲቆይ ነገሩት እና ከጥቂት ወራት በኋላ እነርሱም ወደ ምዕራብ ጀርመን ሄዱ። በዚያ ጊዜ የ24 ዓመት ወጣት ብሆንም በጉባኤው ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር። እነዚህን ኃላፊነቶቼን በጥንቃቄ እንድወጣ አስፈላጊውን ጥበብ እና ጥንካሬ ስለ ሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።—2 ቆሮንቶስ 4:7
መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ
የበርሊን ግንብ በነሐሴ ወር 1961 ሲቆም በምሥራቅ ጀርመን የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በምዕራብ ከሚገኙት ወንድሞቻቸው በድንገት ተለዩ። በዚያን ጊዜ ጽሑፎችን መጀመሪያ በታይፕ ጽፈን በማባዣ መሣሪያ እያባዛን የምናዘጋጅበት ጊዜ ጀመረ። ይህንን የሕትመት ሥራ በቤታችን ውስጥ በድብቅ ለማካሄድ የሚያስችለንን ቦታ ለማዘጋጀት ከ1963 ጀምሮ ሁለት ዓመት ፈጅቶብኛል። ቀኑን በሙሉ በብረታ ብረት ሥራ ስሠራ እውልና ሌሊቱን ከሌሎች ከሁለት ወንድሞች ጋር በመሆን የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን አዘጋጅ ነበር። ባለ ሥልጣኖች የማተሚያ ድርጅታችንን ምሥጢራዊ አሠራር ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በዚያን ጊዜ ምግባችን እያልን እንጠራው የነበረውን ጽሑፍ በጊዜው እንድናገኝ ይሖዋ ይረዳን ነበር።
መጽሔቶቻችንን በበቂ ቅጂዎች ለማዘጋጀት ብዛት ያለው ወረቀት ማግኘት ያስፈልገን ነበር። ብዙ ወረቀት ማግኘት ደግሞ ቀላል ነገር አልነበረም። በየጊዜው ብዛት ያለው ወረቀት ብንገዛ የባለ ሥልጣኖችን ትኩረት ሊስብብን ስለሚችል እያንዳንዱ ምሥክር አነስተኛ መጠን ያለው ወረቀት ይገዛና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደሚደረግባቸው ቦታዎች ያመጣ ነበር። ወረቀቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሚደረግባቸው ቦታዎች ተሰብስበው መጽሔቶቹ ወደሚዘጋጁበት ቦታ ይወሰዳሉ። ከዚያም የተዘጋጁት መጽሔቶች በሌሎች ወንድሞች ይከፋፈሉ ነበር።
ባለሥልጣኖች ጽሑፍ በማተም ሥራ ላይ ይሳተፋል ብለው ስለጠረጠሩኝ ጥብቅ ክትትል ሊያደርጉብኝ ጀመሩ። በ1965 መጨረሻ ላይ ከበፊቱ የበለጠ እንደሚከታተሉኝ እና አንድ ነገር ለማድረግ እንዳቀዱ ተገነዘብኩ። አንድ ቀን ማለዳ ላይ በድንገት መጡ።
ለትንሽ አመለጥሁ
በዚያ የክረምት ጠዋት ወደ ሥራ ለመሄድ ተነስቼ ነበር። ሌሊቱ ገና አልነጋም ነበር። በዚያ በሚጋረፍ የክረምት ቅዝቃዜ እንደምንም ተደፋፍሬ ተነሳሁ። መንገዴን እንደጀመርኩ አሻግሬ ስመለከት አራት ራሶች ከአጥሩ በላይ ታዩኝ። ሰዎቹም ታጠፉና ወደ እኔ አመሩ። ሰዎቹ የመንግሥት ባለስልጣኖች መሆናቸውን ሳውቅ በጣም ፈራሁ። ምን ማድረግ ነበረብኝ?
በረዶው ወደ አንድ ጎን ስለተቆለለ ቀጭን የመተላለፊያ መንገድ ብቻ ቀርቶአል። እኔም በቀጭኑ መንገድ መራመዴን ቀጠልኩ። ራሴን ዝቅ አድርጌ ዓይኔን ከመሬት ሳልነቅል እየሄድኩ አጭር ጸሎት አቀረብኩ። ሰዎቹ ወደ እኔ እየቀረቡ መጡ። አውቀውኝ ይሆን? በጠባቡ መንገድ ስንተላለፍ የሆነውን ነገር ማመን አቃተኝ። ፈጠን ፈጠን እያልኩ መራመዴን ቀጠልኩ። ከመካከላቸው አንዱ “እርሱ ነው!” ሲል ሰማሁት። “ስማ፣ ቁም!” ብሎ ጮኸ።
ባለኝ ኃይል ሁሉ ሮጬ ታጠፍኩና በጎረቤት አጥር ዘልዬ በጓሮ በኩል ባለው በር ወደ ቤቴ ገባሁና በሩን ዘግቼ ቀረቀርኩት። “ሁላችሁም ተነሱ! ሊይዙኝ መጥተዋል” ብዬ ጮህኩ።
ማርጋሬት ወዲያው ደረጃውን ወርዳ በበሩ አጠገብ ቆመች። ወደ ምድር ቤቱ በፍጥነት ሄድኩና ምድጃውን አያያዝኩ። በእጄ ይገኙ የነበሩትን የጉባኤ መዝገቦች በሙሉ እሳቱ ውስጥ ጨመርኳቸው።
ሰዎቹም “ክፈት! እኛ ሕግ አስከባሪዎች ነን በሩን ክፈት!” እያሉ በጩኸት አንቧረቁ።
ማርጋሬት ሁሉንም አቃጥዬ እስክጨርስ ድረስ ምንም እንዳልሰማ ሰው ዝም ብላ ቆመች። ከዚያም ወደ ማርጋሬት ሄድኩና በሩን እንድትከፍት ምልክት ሰጠኋት ሰዎቹም እየዘለሉ ገቡ።
“የሮጥከው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁኝ።
ወዲያው ተጨማሪ መርማሪዎች መጡና ቤቱ በሙሉ ተፈተሸ። በጣም አሳስቦኝ የነበረው የማተሚያ መሣሪያዎችንና 40,000 ወረቀቶች የተደበቁበትን ቦታ ፈልገው እንዳያገኙ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ማተሚያ ቤቱ የሚያስገባው ድብቅ በር ሳይታወቅ ቀረ። ምርመራው ለበርካታ ሰዓቶች ቢቆይም ይሖዋ በተረጋጋ መንፈስ ጸጥ እንድል ረዳኝ። ይህ ተሞክሮ ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ጋር የበለጠ እንድንቀራረብና ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ እንድናገኝ ረድቶናል።
እስረኞች ብንሆንም ነፃ ነበርን
በ1960ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ለውትድርና አገልግሎት እንድመዘገብ ተጠየቅኩ። እኔም ሕሊናዬ እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ለመፈጸም ስለማይፈቅድልኝ ከፍተኛ የጉልበት ሥራ በሚሠራበት የቅጣት ካምፕ ውስጥ ለሰባት ወራት ለመታሰር ተገደድኩ። ከበርሊን ደቡባዊ ምሥራቅ በሚገኘው በኮትበስ እስር ቤት ውስጥ 15 ምሥክሮች እንገኝ ነበር። ሁላችንም የታሰርነው በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችን ምክንያት ነበር። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 17:16) ለብዙ ሰዓቶች ከባድ የጉልበት ሥራ እንሠራ ነበር። ከሌሊቱ በ10:15 ተነስተን ከሠፈሩ ውጭ በሚገኙ የባቡር ሐዲድ መሥመሮች ላይ ለመሥራት እንወሰድ ነበር። እስረኞች በነበርንበት ጊዜ ስለ ይሖዋ መንግሥት ለሌሎች የምንናገርባቸው አጋጣሚዎች ነበሩን።
ለምሳሌ ያህል፦ ሁለት ጠንቋዮች ከእኛ ጋር በኮትበስ ነበሩ። አንድ ቀን አንደኛው ወጣት ጠንቋይ ከእኔ ጋር ለመነጋገር በጣም እንደሚፈልግ ነገረኝ። ምን ፈልጐ ይሆን? የልቡን አውጥቶ ነገረኝ፣ ሴት አያቱ ጠንቋይ እንደነበረችና የእርሷን መጽሐፎች ካነበበ በኋላ እርሱም ተመሳሳይ የሆነ የመጠንቆል ኃይል ሊያገኝ እንደቻለ ነገረኝ። ይህ ሰው ይቆጣጠረው ከነበረው ከዚህ ኃይል ለመላቀቅ ቢፈልግም ይህን በማድረጉ የሚደርስበትን ችግር ፈራ። ለብዙ ሰዓት አለቀሰ። ይህን ሁሉ የሚናገረው እኔ ምን እንዳደርግለት ይሆን?
ንግግራችንን እየቀጠልን ስንሄድ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ስለወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ የሚያስችለው ኃይል እንደሚለየው ገለጸልኝ። እኔም ክፉ የሆኑ መንፈሳውያን ፍጡሮች ማለትም አጋንንት እና ጻድቅ የሆኑ መላእክት መኖራቸውን አስረዳሁት። በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ አስማተኞች ወደ ክርስትና ሲመጡ የወሰዱትን እርምጃ ምሳሌ በማድረግ ለጥንቆላ ወይም ለሌሎች መናፍስታዊ ሥራዎች የሚገለገልባቸውን ዕቃዎች ሁሉ ማስወገድ የሚያስፈልገው መሆኑን ገለጽኩለት። (ሥራ 19:17-20) “ከዚያ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝ፣ በየትም ቦታ ታገኛቸዋለህ” አልኩት።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ወጣቱ ሰው ከእስር ቤት ወጣ። ከዚያ በኋላ ስለዚህ ሰው የሰማሁት ነገር የለም። ይሁንና ነፃነት ናፍቆት ሊጽናና እስከማይችል ድረስ በፍርሐት ከተዋጠው ከዚህ ወጣት ጋር ያሳለፍኩት ተሞክሮ ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር አጠነከረው። እኛ በዚያ ካምፕ እንገኝ የነበርነው 15 ምሥክሮች በእምነታችን ምክንያት በእስር ቤት ውስጥ የምንኖር ብንሆንም በመንፈሳዊ መንገድ ግን ነፃ ነበርን። ይህ ወጣት ሰው ከእሥር ቤት ቢወጣም አሁንም በጣም ያስፈራው ለነበረው “አምላኩ” ባሪያ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እኛ ምሥክሮች ያለንን መንፈሳዊ ነፃነት በጣም መንከባከብ ይገባናል።
የልጆቻችንም እምነት ተፈተነ
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው እምነታቸው የተፈተነባቸው ትላልቆች ብቻ ሳይሆኑ ትናንሽ ልጆች ጭምር ነበር። በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ እምነታቸውን እንዲተዉ ተጽእኖ ይደርስባቸው ነበር። አራቱም ልጆቻችን ለእምነታቸው ያላቸውን አቋም ለማረጋገጥ ተገድደዋል።
በትምህርት ቤት ሰኞ ሰኞ ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ የሚሰጥበት ስነ ሥርዓት ይደረጋል። ሰንደቅ ዓላማው በሚሰቀልበት ጊዜ ተማሪዎች ተሰልፈው የቴልማንን መዝሙር በመዘመር ለሰንደቅ ዓላማው ሰላምታ ይሰጣሉ። ኧርነስት ቴልማን በ1944 በናዚ ኤስ ኤስ ወታደሮች የተገደለ ጀርመናዊ ኮሚኒስት ነበር። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ቴልማን የምሥራቅ ጀርመን አርበኛ ሆነ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታችን መሠረት ቅዱስ አገልግሎት ሊቀርብ የሚገባው ለይሖዋ ብቻ በመሆኑ ባለቤቴና እኔ ልጆቻችን እንዲህ ባለው የሰንደቅ ዓላማ አከባበር ሥርዓት ሳይካፈሉ በአክብሮት ዝም ብለው እንዲቆሙ ነግረናቸው ነበር።
በተጨማሪም ልጆች በትምህርት ቤት ኮሚኒስታዊ መዝሙሮችን ይማሩ ነበር። ማርጋሬት እና እኔ ልጆቻችን ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት ሄደን ልጆቻችን ለምን እነዚህን የፖለቲካ መዝሙሮች እንደማይዘምሩ አስረዳን። ነገር ግን ሌላ ዓይነት መዝሙር ለመማር ፈቃደኞች መሆናቸውንም ጭምር ገለጽንላቸው። ስለዚህ ልጆቻችን ገና ከትንሽነታቸው ከእኩዮቻቸው የተለየ አቋም መውሰድን ተምረዋል።
ወደ 1970ዎቹ ዓመታት መጨረሻ አካባቢ ትልቋ ልጃችን የቢሮ ሥራ ልምምድ ለማድረግ ፈለገች። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰልጣኝ ሠራተኛ ልምምዱን ከመጀመሩ በፊት የ14 ቀናት የውትድርና ልምምድ የማድረግ ግዴታ ነበረበት። የሬናት ሕሊና በውትድርና ሥልጠና እንድትካፈል ስላልፈቀደላት ቆራጥ አቋም ወሰደች። ከዚያም የውትድርና ስልጠና የመውሰዱ ግዴታ ቀረላት።
ሬናት የቢሮ ሥራ ልምምድ እያደረገች ሳለ የተኩስ ልምምድ በሚደረግበት ክፍል ተገኝታ ነበር። አስተማሪውም “ሬናት፣ አንቺም የተኩስ ልምምድ ወደሚደረግበት መጣሽ?” አላት። የተኩስ ልምምድ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኗን አልተቃወመም። “አንቺ መተኮስ አያስፈልግሽም፣ በኋላ የምንወስደውን ምግብና መጠጥ ልታዘጋጂ ትችያለሽ” አላት።
በዚያው ቀን ምሽት ቤተሰባችን አንድ ላይ ተሰብስቦ ውይይት አደረገ። ሬናት በቀጥታ በልምምዱ ባትሳተፍም የተኩስ ትምህርት በሚሰጥበት ቦታ መገኘቷ ስህተት እንደሆነ ተሰማን። ሬናት ካደረግነው ውይይትና ጸሎት ድፍረትና ኃይል አግኝታ የጸና አቋም ወሰደች። ወጣቷ ልጃችን ለጽድቅ ሥርዓቶች ጥብቅ አቋም ስትወስድ መመልከት ምን ያህል የሚያበረታታ ነው!
የስብከት ሥራችንን ከፍ ማድረግ
በ1970ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ በሥራችን ላይ ይደርስ የነበረው ተቃውሞ በረድ ሲል ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ከምዕራብ በብዛት መምጣት ጀመረው ነበር። ጽሑፎችን ከምዕራብ ማምጣት በጣም አደገኛ ሥራ የነበረ ቢሆንም ደፋር ወንድሞቻችን በፈቃደኛነት ይሠሩ ነበር። የሚደርሱን ጽሑፎች ቁጥር መጨመሩንና ጽሑፎቹን ለማምጣት ወንድሞቻችን ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት በአድናቆት ተቀበልን። ዕገዳው በተጀመረበት አካባቢ ባሉት ኃይለኛ የስደት ዓመታት ከቤት ወደቤት እየሄዱ የመስበኩ ሥራ በእርግጥ ትልቅ ፈተና ሆኖ ነበር። አንዳንዶች ቢያዙ የሚደርስባቸውን ቅጣት በመፍራት የስብከት ሥራቸውን አቋርጠው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የስብከቱ ሥራ በአስደናቂ ሁኔታ ጨመረ። በ1960ዎቹ ዓመታት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አዘውትረው የሚካፈሉት ከጠቅላላዎቹ አስፋፊዎች 25 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ነበሩ። በ1980ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ግን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አዘውትረው የሚካፈሉት አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 60 በመቶ ከፍ ብሎአል። በዚህ ጊዜ ባለሥልጣኖች በስብከት ሥራችን ላይ ብዙም ትኩረት አያደርጉም ነበር።
አንድ ጊዜ ከእኔ ጋር አብሮ ያገለግል የነበረ አንድ ወንድም ትንሽ ሴት ልጁን ይዟት ስለመጣ ይዘናት ሄድን። እናነጋግራት የነበረችው አንዲት አሮጊት ሴት በትንሿ ልጅ መገኘት ስለተደሰተች ወደ ቤት እንድንገባ ጋበዘችን። የነገርናት ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት እንዳስደሰታትና እንደገና ተመልሰን እንድንጠይቃት እንደምትፈልግ ገለጸችልን። እኔም ተመላልሶ መጠየቁን ለባለቤቴ አስተላለፍኩና ከሴትዮዋ ጋር ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ይህች ሴት በእድሜዋ የገፋችና የተሟላ ጤንነት ያልነበራት ብትሆንም ክርስቲያን እህታችን ሆነች። ይሖዋን በማገልገሉ ሥራም በትጋት መሳተፏን ቀጥላለች።
ነፃነት እየቀረበ ሲመጣ የተደረጉ ማስተካከያዎች
ይሖዋ በበለጠ ነፃነት ለምንደሰትበት ጊዜ አዘጋጅቶናል። ለምሳሌ ያህል ዕገዳው ሊነሳልን ጥቂት ሲቀረው፣ በስብሰባ ቦታዎች እርስ በርሳችን የምንጠራራበትን ሁኔታ እንድንለውጥ ተመክረን። ከዚህ በፊት ለጥንቃቄ ተብሎ እርስ በርሳችን የምንጠራራው በመጀመሪያ ስሞቻችን ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ለብዙ ዓመታት አብረዋቸው የኖሩትን የእምነት ጓደኞቻቸውን ሁለተኛ ስም አያውቁም ነበር። አዳዲስ ሰዎች ወደ ስብሰባዎቻችን መምጣት ለሚጀምሩበት ጊዜ ዝግጅት ለማድረግ አንዳችን ሌላውን በቤተሰብ ስም እንድንጠራ ተመከርን። አንዳንዶች በቤተሰብ ስም መጥራት የመቀራረብን መንፈስ ያጠፋል በማለት ቅር ተሰኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ምክሩን የተከተሉት በኋላ ባገኘነው ነፃነት የመጡትን ለመቀበል ቀላል ሆኖላቸዋል።
በተጨማሪም ስብሰባዎችን በመዝሙር እንድንጀምር ተነግሮን ነበር። ይህን በማድረጋችንም በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ ጉባኤዎች የሚከተሉትን የስብሰባ ሥርዓት ለመለማመድ ችለናል። ሌላው ማስተካከያ የተደረገበት ጉዳይ በጥናት ቡድን ይገኙ የነበሩት ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ ከአራት ወደ ስምንት፣ በኋላም ወደ 10 በመጨረሻም ወደ 12 ከፍ ማለቱ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ የጥናት ቡድን በእያንዳንዱ ጉባኤ ለሚገኙ ለአብዛኛዎቹ ምሥክሮች አማካይ በሆነ ቦታ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ተደረገ።
አንዳንዴ የተደረጉትን ማስተካከያዎች ጠቃሚነት የምንረዳው ማስተካከያዎቹ ከተደረጉ በኋላ ነበር። ይህም ይሖዋ ምን ጊዜም ጥበበኛ እና አሳቢ አባት መሆኑን አስገንዝቦናል። ቀስ በቀስ ከምድራዊ ድርጅቱ አሠራር ጋር እንድንስማማ አደረገን። እኛም የዓለም አቀፉ የወንድማማቾች ማህበር ክፍሎች መሆናችን በይበልጥ እየተሰማን ሄደ። በእግጥም ይሖዋ አምላክ በምሥራቅ ጀርመን ለ40 ዓመታት ያህል በዕገዳ ሥር ለሠሩት ሕዝቦቹ ፍቅራዊ ጥበቃ አድርጐላቸዋል። አሁን ሕጋዊ እውቅና በማግኘታችን ምንኛ ተደስተናል!
ዛሬ፣ ምሥራቅ ጀርመን ተብሎ ይታወቅ በነበረው አገር 22,000 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። እነዚህ ወንድሞች ይሖዋ የሰጠንን ጥበብ የሞላበት መመሪያ እና በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ያደረገልንን እርዳታና ድጋፍ የሚያረጋግጡ ሕያው ምሥክሮች ናቸው። በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ያደረገልን እርዳታ እና ድጋፍ ማንኛውንም ሁኔታ ሊቆጣጠር የሚችል መሆኑን ያሳያል። በሕዝቦቹ ላይ የሚሠራ ማንኛውም ዓይነት የተንኮል መሣሪያ በምንም መንገድ አይሳካም። ይሖዋ በእርሱ የሚታመኑትን ሁልጊዜ ይንከባከባቸዋል።—ኢሳይያስ 54:17፤ ኤርምያስ 17:7, 8)—ሆርስት ሽሎይስነር እንደተናገረው
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሆርስትና ማርጋሬት ሽሎይስነር በምሥራቅ በርሊን በሚገኘው የማህበሩ ሕንፃ አጠገብ።