ክፍል 1—በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ይሖዋ እንክብካቤ አድርጎልናል
የይሖዋ ምሥክሮች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በታገዱባቸው አገሮች ስለሚገኙት ወንድሞቻቸው ደህንነት ሲያስቡ ቆይተዋል። ምን አጋጥሟቸው እንደነበር በጥቂቱ ከሚያሳዩት ሦስት ጽሑፎች የመጀመሪያውን ስናቀርብ ደስ ይለናል። እነዚህ ጽሑፎች ምሥራቅ ጀርመን ተብሎ ይታወቅ በነበረው አገር በሚኖሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ላይ የደረሱ የግል ታሪኮች ናቸው።
በ1944 በስኮትላንድ፣ በአይር አቅራቢያ በሚገኘው በካምኖክ የጦር ሠፈር ውስጥ ረዳት ሐኪም ሆኜ የምሠራ የጦር እስረኛ ነበርኩ። ከአካባቢው ሰዎች ጋር መወዳጀት በጥብቅ የተከለከለ ቢሆንም ከጦር ሠፈሩ መውጣት ይፈቀድልኝ ነበር። አንድ እሁድ እለት በመንገድ እየተንሸራሸርኩ ሳለሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነገሮችን ለማስረዳት ቅን ፍላጎት ያለው አንድ ሰው አገኘሁ። ከዚያ በኋላ ሁል ጊዜ ለብቻችን ሆነን አብረን እንሸራሸር ነበር።
ከጊዜ በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ በሚደረግ ስብሰባ እንድገኝ ጋበዘኝ። እኔ የጠላት አገር ዜጋ ስለነበርኩ እኔን ወደ ስብሰባ መጋበዙ አደጋ ሊያስከትልበት ይችል ነበር። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን በዚያ ጊዜ አላወቅሁም ነበር። የተጋበዝኩት በአነስተኛ ቡድኖች ተከፋፍለው ከሚደረጉት የመጽሐፍ ጥናቶች በአንዱ እንድገኝ ነበር። የተጠናው ትምህርት በደንብ ባይገባኝም አንድ ነጭ ረዥም ልብስ የለበሰ ልጅ ከአንበሳና ከበግ ጠቦት ጋር ሆኖ የሚያሳይ ሥዕል ማየቴን በትክክል አስታውሳለሁ። ይህ በኢሳይያስ መጽሐፍ የተገለጸው የአዲስ ዓለም ሥዕል በጥልቅ ነካኝ።
በ1947 ከእሥር ቤት ተለቀቅሁ። ወደ አገሬ ወደ ጀርመን ተመለስኩና ከጦርነቱ በፊት የማውቃትን ማርጊትን አገባሁ። መኖሪያችንን ለፖላንድና ለቼኮስሎቫኪያ ድንበሮች ቅርብ በሆነችው በዚታው አደረግን። ከጥቂት ቀኖች በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ በራችንን አንኳኳ። “እነዚህ ሰዎች በእስኮትላንድ ካጋጠሙኝ ጋር አንድ ዓይነት ከሆኑ ከእነርሱ ጋር መተባበር አለብን” ብዬ ለባለቤቴ ነገርኳት። በዚያው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ከምሥክሮቹ ጋር ተሰበሰብን።
ወዲያውም በክርስቲያን ስብሰባዎች አዘውትረን የመገኘትንና በስብከቱ ሥራ የመካፈልን አስፈላጊነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርን። ምሥክሮቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለሚያስተምሩን ነገሮች በሕይወታችን በጣም ትልቅ ቦታ መስጠት ጀመርን። ከዚያ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን መምራት ጀመርኩ። ከዚያም በየካቲት ወር 1950 ሁለት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሆኑ ወንድሞች “ለመጠመቅ አትፈልጉም?” ብለው ጠየቁን። በዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ማርጊትና እኔ ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት አሳየን።
ችግሮች መከሰት ጀመሩ
ዚታው በሶቪየት ግዛት ክልል ውስጥ ባለው የጀርመን ክፍል ውስጥ ትገኝ ነበር። በ1949 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ችግር ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ተጀምሮ ነበር። ከብዙ ችግሮች በኋላ በባውትዘን አነስተኛ ስብሰባ የምናደርግበት አዳራሽ አገኘን። ከዚያም በኋላ በበጋው ወራት በበርሊን ወደሚደረገው ትልቅ የወረዳ ስብሰባ የሚወስዱን ልዩ የባቡር ጉዞዎች በድንገት ተሰረዙ። ይሁን እንጂ በሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር።
በተጨማሪም የጉባኤ ስብሰባዎች ይረበሹ ነበር። ሁከት ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ስብሰባውን በጩኸትና በፉጨት ለመረበሽ ሆነ ብለው በስብሰባ ይገኙ ነበር። በአንድ ወቅት ላይ የተጓዥ የበላይ ተመልካቹን ንግግር በኃይል ሊያስቆሙን ምንም ያህል አልቀራቸውም ነበር። ጋዜጦች “መዓት አውሪ ነብያት” ይሉን ነበር። አምዶቻቸውም በደመና እንነጠቃለን ብለን በማሰብ በኮረብቶች ጫፍ ላይ እንደተሰበሰብን የሚገልጹ ጽሑፎችን ያወጡ ነበር። ጋዜጦቹ የይሖዋ ምሥክሮች ከእኛ ጋር የጾታ ብልግና የመፈጸም ሙከራ አድርገዋል የሚሉ አንዳንድ ልጃገረዶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ‘ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ’ በማለት የምንሰጠው ትምህርት ተጠምዝዞ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የፆታ ግንኙነት የሚያደርጉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ብለን እንደምናስተምር ተደርጎ ተገለጸ።
በኋላም ጦርነት ቀስቃሾች ናቸው ተባልን። የአምላክ ጦርነት ስለሆነው ስለ አርማጌዶን የተናገርነው የጦር መሣሪያንና ጦርነትን እንደምናበረታታ ተደርጎ በስህተት ተተረጎመ። ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው ክስ ነበር። ሆኖም በነሐሴ ወር 1950 የማታ ሽፍት አታሚ ሆኜ ወደምሠራበት በአካባቢው የሚገኝ የጋዜጣ ማተሚያ ቤት ስደርስ እንዳልገባ ዘበኛው ከለከለኝ። ዘበኛው ከአንድ ፖሊስ ጋር ሆኖ “ከሥራ ተባርረሃል። እናንተ ጦርነት ደጋፊዎች ናችሁ” አለኝ።
ወደ ቤት ስመለስ ማርጊት ትልቅ እፎይታ አገኘች። “ከአሁን በኋላ የሚያስመሽህ ሥራ አይኖርም” አለች። በነገሩ አልተጨነቅንም፤ ወዲያው ሌላ ሥራ አገኘሁ። የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን ትምክህታችንን በአምላክ ላይ አደረግን፣ እሱም እንደተማመንንበት አደረገልን።
ሥራችን ታገደ
ነሐሴ 31, 1950 የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ታገደ። በየቦታው ወንድሞች ተይዘው ታሠሩ። ብዙ ምሥክሮች ተከስሰው ለፍርድ ቀረቡ። አንዳንዶቹም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው። በዚታው በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ስቃይ ደርሶባቸው የነበሩ ሁለት ወንድሞች በኮሚኒስቶች ታሠሩ። የጉባኤያችን የበላይ ተመልካች ከነባለቤቱ ከሁለት ትናንሽ ልጆቻቸው ተነጥለው ታሠሩ። ሁለቱ ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ብቻቸውን ተጣሉ። ዛሬ ሁለቱም ሴቶች ልጆች ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በቅንዓት ይናገራሉ።
የምሥራቅ ጀርመን ጉባኤ መልእክተኞች ጽሑፎችን ለማግኘት የምዕራብ ጀርመን ይዞታ ከነበረችው በርሊን ይመላለሱ ነበር። ከእነዚህ ደፋር መልእክተኞች መካከል ብዙዎቹ ተይዘው ወደ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ የእሥራት ፍርድ ተበይኖባቸዋል።
አንድ ቀን ባለሥልጣኖች ቤታችንን ለመፈተሽ በጧት ወደ ቤታችን መጡ። ይመጣሉ ብለን እንጠባበቅ ስለነበር የጉባኤውን ፋይሎች በሙሉ ከተርቦች ጎጆ ቀጥሎ ባለው የእህል ማስቀመጫችን ክፍል ውስጥ ደበቅሁት። ተርቦቹ እኔን አስቸግረውኝ አያውቁም ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎቹ አካባቢውን መበርበር ሲጀምሩ በድንገት በተርብ ደመና ተከበቡ። ሰዎቹ ራሳቸውን ለማዳን ከመሮጥ በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር።
ይሖዋ በ1949 በተደረጉት ስብሰባዎች አማካኝነት ለዕገዳው አዘጋጅቶን ነበር። የስብሰባው ፕሮግራም የግል ጥናታችንን፣ የጉባኤ ተሳትፎአችንንና የስብከት ሥራችንን እንድናጠናክር እንዲሁም አንዳችን ሌላውን የምናንጽና የምንደጋገፍ እንድንሆን አጥብቆ የሚያሳስብ ነበር። ይህም በእርግጥ ታማኞች ሆነን እንድንቆይ ረድቶናል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ሰዎች ቢነቅፉንና ቢረግሙንም ምንም ያህል አይሰማንም ነበር።
በዕገዳ ሥር ሆኖ ስብሰባዎችን ማካሄድ
የዕገዳው ማስታወቂያ እንደተነገረ ወዲያው እንዴት አድርገን የጉባኤ ስብሰባዎችን እንደምናካሂድ ለመወያየት ከሁለት ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። ስብሰባ ማድረግ የእስራት ፍርድ ያስከትል ስለነበር በስብሰባዎች ላይ መገኘት አደገኛ ነበር። በአካባቢያችን የሚገኙትን ምሥክሮች በየቤታቸው እየሄድን ጠየቅናቸው። አንዳንዶች ተጨንቀው ነበር። ሆኖም በስብሰባዎች የመገኘትን አስፈላጊነት ሁሉም ተገንዝበው ስለነበር በጣም ተጽናናን።
አንድ ጥሩ ፍላጎት ያለው ሰው የመሰብሰቢያ ቦታ አድርገን እንድንጠቀምበት የከብቶች ማደሪያ ቤት ሰጠን። ለማንኛውም ሰው ሊታይ በሚችል ግልጽ ቦታ የሚገኝ ቢሆንም በቁጥቋጦዎች ወደተሸፈነ መንገድ የሚያስወጣ የኋላ በር ነበረው። ስለዚህ ስንገባም ሆነ ስንወጣ አይታወቅም ነበር። በክረምት ወራት በሙሉ ይህ ያረጀ ቤት ወደ ሃያ የምንጠጋ ሰዎች በሻማ ብርሃን የምናደርገውን ስብሰባ ያስተናግድ ነበር። በየሳምንቱ ለመጠበቂያ ግንብ ጥናትና ለአገልግሎት ስብሰባ እንገናኝ ነበር። ፕሮግራሙ ከሁኔታችን ጋር የሚስማማና በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን እንድንቀጥል የሚያሳስብና የሚያበረታታ ነበር። ወዲያው ይህ ጥሩ ፍላጎት ያለው ሰው አዲስ ወንድማችን በመሆኑ ተደሰትን።
በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ የፍርድ ቤት ቅጣቶች እየቀለሉ ሄዱ። አንዳንድ ወንድሞችም ከእስራት ተፈቱ። ብዙዎቹ በግድ ምሥራቅ ጀርመንን ለቅቀው ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዲሄዱ ተደረጉ። ከምዕራብ ጀርመን ከመጣ ከአንድ ወንድም ጉብኝት በኋላ ወዲያውኑ በእኔም ላይ ያልተጠበቁ ነገሮች ተፈጸሙ።
የመጀመሪያው ትልቅ የሥራ ምድቤ
ራሱን ሐንስ ብሎ ከሚጠራ ወንድም ጋር ከተነጋገርን በኋላ በርሊን ሄጄ እንድጠይቅ አንድ አድራሻ ሰጠኝ። እኔም በዚሁ መሠረት ሄድኩና በበሩ ላይ የመጥሪያ ደወል ላይ የሚገኘውን የሚስጥር ስም አገኘሁና እንድገባ ተጋበዝኩ። ከሁለት ሰዎች ጋር አስደሳችና አጠቃላይ የሆነ ውይይት አደረግሁ። ከዚያም “አንድ ልዩ ሥራ ቢሰጥህ ትቀበላለህን?” ወደሚለው ጥያቄ አመሩ። መልሴም “አዎ” የሚል ነበር። “መልካም፣ ሁላችንም ለማወቅ የምንፈልገው ይህንን ነው፤ ወደ አገርህ በሰላም ተመለስ” አሉኝ።
ከሦስት ሳምንት በኋላ ወደ በርሊን እንድመለስ ተጠየቅሁና በዚያው ክፍል ውስጥ ተገኘሁ። ወንድሞች በዚታው አካባቢ ያለውን ቦታ የሚያሳይ ካርታ ሰጡኝና በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ በመግባት “በዚህ አካባቢ ከምሥክሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለንም። አንተ ይህን ግንኙነት ልታድስልን ትችላለህን?” አሉኝ። መልሴም “በእርግጥ እችላለሁ” የሚል ነበር። ከሪዛ እስከ ዚታው የሚደርስ 76 ኪሎሜትር ርዝመትና 48 ኪሎሜትር ስፋት ያለው ትልቅ አካባቢ ነው። ይህን ሁሉ አካባቢ የማዳርሰው በብስክሌት ነበር። ከእያንዳንዱ ምሥክር ጋር ግንኙነት ሲመሠረት በአካባቢው ከሚገኝ ጉባኤ ጋር እንዲቀናጅ ይደረግ ነበር። እያንዳንዱ ጉባኤ ደግሞ በርሊን ሄደው ጽሑፎችን የሚወስዱና መመሪያ የሚቀበሉ በቋሚነት የሚሠሩ ተወካዮችን ይልክ ነበር። የዚህ ዓይነቱ አሠራር ባለሥልጣኖች አንዱን ጉባኤ ቢያሳድዱ በሌሎች ጉባኤዎች ላይ ችግር እንዳይደርስ ተከላክሏል።
በይሖዋ መመካት
ስደት ቢኖርም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱሱን መመሪያ በመታዘዝ የአምላክን መንግሥት መልእክት ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ማድረሳችንን በፍጹም አቁመን አናውቅም ነበር። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 20:20) ቀደም ሲል የምናውቃቸውን ሰዎች እንድንጠይቃቸው በሚሰጡን አድራሻዎች መሠረት ጉብኝት ማድረግ ጀመርን። ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች አጋጥመውናል። አንዳንድ ጊዜ የምንሠራቸው ስህተቶች እንኳ ወደ በረከት ይለወጡ እንደነበር የሚከተሉት ምሳሌዎች ያሳያሉ። ባለቤቴና እኔ እንድንጎበኛቸው የሚፈልጉ ሰዎች አድራሻ ተሰጥቶን ነበር። ነገር ግን በስህተት ሌላ ቤት አንኳኳን። በሩ ሲከፈት በኮት መስቀያው ላይ የፖሊስ ዩኒፎርም ተሰቅሎ አየን። የማርጊት ፊት አመድ መሰለ። የእኔም ልብ በኃይል መምታት ጀመረ። ወዲያው የምንታሰር መስለን። አጭር ጸሎት አቀረብን። ሰውየው አጠር ባለ አነጋገር “እናንተ እነማን ናችሁ?” ብሎ ጠየቀን። ፀጥ ብለን ቆምን። “አንድ ቦታ እንዳየሁህ እርግጠኛ ነኝ። የት እንደሆነ ግን ማስታወስ አልቻልኩም” አለች ማርጊት። ደግማም “አዎ፣ ፖሊስ ነህ አይደል ተረኛ ሆነህ አይቼህ መሆን አለበት” አለች።
ይህ አነጋገር ቀዝቀዝ አደረገው። የወዳጅነት መንፈስ ባለው ድምጽ “እናንተ የይሖዋ ናችሁ አይደለም?” ብሎ ጠየቀን።
“አዎ፣ ነን። በርህን ማንኳኳታችን ምን ያህል ድፍረት እንደጠየቀብን ልትገነዘብ ትችላለህ። ስለ ደህንነትህ ስለምናስብ ነው” አልኩት።
ወደ ቤቱ እንድንገባ ጋበዘን። ብዙ ጊዜ ጉብኝት አደረግንለትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርንለት። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ክርስቲያን ወንድማችን ሆነ። ይህ ተሞክሮ በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት በጣም አጠናክሮልናል።
ብዙውን ጊዜ እህቶች እንደ መልእክተኞች ሆነው ይሠሩ ነበር። ይህም ሥራ ያለምንም ማወላወል ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ እንዲጥሉ ይጠይቅባቸው ነበር። ማርጊት ጽሑፎችን ለማምጣት ወደ በርሊን ስትሄድ ያጋጠማት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ከተጠበቀው በላይ ጽሑፎች ተጠራቅመው ነበር። ከመጠን በላይ ጽሑፎች የታጨቁበትን ሻንጣ በልብስ ማስጫ ገመድ ጥፍር አድርጋ ይዛ ነበር። ማርጊት ባቡሩ ውስጥ እስከገባችበት ጊዜ ድረስ ምንም ችግር አላጋጠማትም ነበር። ከዚያም በመንገድ ላይ እያሉ የድንበር ጠባቂ ሠራተኛ መጣ።
ወደ ሻንጣው እያመለከተ “ይህ የማን ነው? በውስጡስ ያለው ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ።
“የታጠቡ ልብሶች ናቸው” ብላ ማርጊት መለሰች። በመጠራጠር እንድትከፍተው አዘዛት። ማርጊት ሆነ ብላ በቀስታ አንዳንድ ቋጠሮ እየፈታች በሻንጣው ዙሪያ ያሉትን ገመዶች መፍታት ጀመረች። ሠራተኛው በባቡሩ ላይ መጓዝ የነበረበት እስከተወሰነ ርቀት ብቻ ነው። ከዚያም ወርዶ በሚመለስ በሌላ ባቡር ላይ መሣፈር ስለነበረበት መጣደፍ ጀመረ። በመጨረሻም ሦስት ቋጠሮዎች ሲቀራት ተስፋ ቆረጠ። “በቃ ጨርቅሽን ይዘሽ ሂጂ” በማለት ጮኸባት።
ይሖዋ በግል ያደረገልኝ እንክብካቤ
ብዙውን ጊዜ የጉባኤ ሥራዎችን የምሠራው ጨለማን ተገን በማድረግ ስለነበረ ከአራት ሰዓት የበለጠ አልተኛም ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ባለሥልጣኖች በራችንን ያንኳኩት እንዲህ ዓይነቱን የሌሊት ሥራ ከጨረስኩ በኋላ ነበር። የመጡት ፍተሻ ለማካሄድ ነበር። ምንም ነገር ለመደበቅ ጊዜ አልነበረም።
ባለሥልጣኖቹ የተደበቀ ነገር ይገኛል በማለት ሽንት ቤቱን ሳይቀር ሁሉንም ነገር ሲገለባብጡ አረፈዱ። ልብስ መስቀያው ላይ የተንጠለጠለውን ኮቴን ለመፈተሽ ያሰበ ሰው አልነበረም። የጉባኤ ሰነዶችን በፍጥነት በኮቴ ኪሶች ውስጥ ከትቼው ነበር። ኪሶቼ ፈታሾቹ በሚፈልጓቸው ነገሮች አብጠው ይታዩ ነበር። እነርሱ ግን ስላላዩአቸው ባዶ እጃቸውን ተመለሱ።
በሌላ ወቅት በነሐሴ 1961 በርሊን ነበርኩ። የበርሊን ግንብ ከመቆሙ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ጽሑፍ ለማምጣት መሄዴ ነበር። ወደ ዚታው ልመለስ ያሰብኩበት የበርሊን ባቡር ጣቢያ በሰዎች ተጨናንቆ ነበር። ባቡሩ ሲገባ ሁሉም ለመሣፈር በፍጥነት ወደ ውስጥ ሮጡ። እኔም ከሕዝቡ ጋር እየተጋፋሁ ሳላውቅ አንድ ባዶ ክፍል ውስጥ ገባሁ። ከመግባቴ ወዲያውኑ ዘበኛው በውጭ በኩል በሩን ዘጋው። ሌሎቹ ተሣፋሪዎች በሌላው የባቡሩ ክፍል ሲታጎሩ እኔ ግን ለብቻዬ በአንድ ክፍል ውስጥ ቆምኩ።
ወደ ዚታው ለመሄድ ጉዞ ጀመርን። ለተወሰነ ጊዜ በፉርጎው ውስጥ ብቻዬን ቆየሁ። ከዚያ በኋላ ባቡሩ ለጥቂት ጊዜ ቆም አለ፤ እኔ ያለሁበትም ክፍል ተከፈተ። ብዙ የሶቪየት ወታደሮች ገቡ። ከዚያ በኋላ ነበር እኔ የገባሁበት ክፍል ለሶቪየት ወታደሮች ብቻ የተፈቀደ ክፍል መሆኑ የገባኝ። መሬት አፏን ከፍታ ብትውጠኝ ደስ ባለኝ ነበር። ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ምንም አግባብ ያልሆነ ነገር የተደረገ አልመሰላቸውም ነበር።
ወደ ዚታው ጉዞአችንን ቀጠልን። እኛ ያለንበት ክፍል እንደተከፈተ ወታደሮቹ እየዘለሉ ወረዱ። በጣቢያው የነበሩትን ሁሉንም መንገደኞች መፈተሽ ጀመሩ። ካለምንም ችግር ባቡሩን ለቅቄ የወጣሁ እኔ ብቻ ነበርኩ። እንዲያውም አንዳንድ ወታደሮች ከፍተኛ መኮንን ስለመሰልኳቸው ሰላምታ ይሰጡኝ ነበር።
ጽሑፎች ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው የተረዳነው ከዚያ በኋላ ነበር። የበርሊን ግንብ በመሠራቱ ጽሑፍ የምናገኝበት መስመር ለጊዜው ተቋረጠ። ሆኖም አሁን ያገኘነው ጽሑፍ ለብዙ ወራት አገለገለን። በመሃሉ ግንኙነታችንን የምንቀጥልበት ዝግጅት ይፈጠራል።
በ1961 የበርሊን ግንብ መሠራቱ በምሥራቅ ጀርመን ለምንገኘው አዲስ ለውጥ አመጣ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ሁኔታ በቅድሚያ ተቆጣጥሮአል። በዕገዳ ሥር በነበርንበት ጊዜ ሁሉ ለእኛ የሚያደርገውን ጥበቃ አላጓደለም።—ሔርማን ለውብ እንደተናገረው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቦይትሰን በተደረገ ትንሽ ስብሰባ ላይ ተገኘን