የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 6/1 ገጽ 20-23
  • አምላክን ለማገልገል የገባሁትን ቃል መጠበቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክን ለማገልገል የገባሁትን ቃል መጠበቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያደግኩባት ሊትዌኒያ
  • የገባሁትን ቃል ማክበር
  • ብዙም ሳልቆይ የገጠሙኝ የእምነት ፈተናዎች
  • እገዳና በድጋሚ መታሰር
  • በእስር ቤት ውስጥ በእምነት መጽናት
  • ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ
  • አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች ማድረግ
  • ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቄያለሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን ለመቀጠል ያደረግነው ትግል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • አምላክ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ‘ይሖዋን በተስፋ የሚጠባበቁ ደስተኞች ናቸው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 6/1 ገጽ 20-23

አምላክን ለማገልገል የገባሁትን ቃል መጠበቅ

ፍራንትስ ጉድሊኪስ እንደተናገረው

እኔ ባለሁበት ጓድ ውስጥ ከሚገኙት ከመቶ ከሚበልጡ ወታደሮች መካከል በሕይወት የተረፉት አራት ብቻ ነበሩ። ከሞት ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጬ ስለነበረ ተንበረከኩና ‘ከዚህ ጦርነት በሕይወት ከተረፍኩ ለዘላለም አገለግልሃለሁ’ ስል ለአምላክ ቃል ገባሁ።

ይህን ቃል የገባሁት ከዛሬ 54 ዓመት በፊት በሚያዝያ 1945 በጀርመን ጦር ሠራዊት ውስጥ በወታደርነት በማገለግልበት ጊዜ ነበር። ይህ የሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሲሆን የሶቪየት ጦር ባለ በሌለ ኃይሉ ወደ በርሊን እየገፋ በመምጣት ላይ ነበር። የእኛ ወታደሮች ከበርሊን 65 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት በኦደር ወንዝ ላይ በምትገኘው በዜሎ መንደር አቅራቢያ መሽገው ነበር። በዚያም እያለን ሌት ተቀን በከባድ መሣሪያ እንደበደብ የነበረ ሲሆን እኔ ያለሁበት ጓድ ክፉኛ ጉዳት ደረሰበት።

በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርር ብዬ በማልቀስ ወደ አምላክ የጸለይኩት የዚያን ጊዜ ነበር። ፈሪሃ አምላክ የነበራት እናቴ ብዙ ጊዜ ትጠቅሰው የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትዝ አለኝ:- “በመከራ ቀን ጥራኝ፣ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ።” (መዝሙር 50:​15) ለሕይወቴ በጣም ስለፈራሁ እዚያው ምሽግ ውስጥ ሆኜ ከላይ እንደገለጽኩት በማለት ለአምላክ ቃል ገባሁ። ቃሌን ልጠብቅ የምችለው እንዴት ነው? ለመሆኑ የጀርመን ሠራዊት አባል ልሆን የቻልኩትስ እንዴት ነበር?

ያደግኩባት ሊትዌኒያ

በ1918 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሊትዌኒያ ነፃነቷን በማወጅ ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግሥት አቋቋመች። የተወለድኩት በ1925 በባልቲክ ባህር አቅራቢያ በምትገኘው በሜሜል (ክላይፔዳ) አውራጃ ነበር። አውራጃዋ ከሊትዌኒያ ጋር የተቀላቀለችው እኔ ከመወለዴ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።

እኔና አምስት እህቶቼ ደስ የሚል የልጅነት ጊዜ አሳልፈናል። አባባ ልክ እንደ ቅርብ ጓደኛችን የነበረ ሲሆን የተለያዩ ነገሮችንም አብሮን ይሠራ ነበር። ወላጆቻችን የኤቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን አባላት ቢሆኑም እናቴ በቄሱ ግብዝነት በመበሳጨቷ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አቁመው ነበር። ሆኖም ለአምላክና በጉጉት ታነበው ለነበረው ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ነበራት።

በ1939 ጀርመን እኛ የምንኖርበትን የሊትዌኒያ ክፍል በቁጥጥር ሥር አዋለ። ከዚያም በ1943 መጀመሪያ ላይ በጀርመን ሠራዊት ውስጥ ገብቼ በውትድርና እንዳገለግል ተጠራሁ። በአንድ ውጊያ ላይ እንዳለሁ ቆሰልሁ፤ ሆኖም ካገገምሁ በኋላ ወደ ምሥራቅ ግምባር ተመለስኩ። በዚህ ጊዜ ጦርነቱ አቅጣጫውን ቀይሮ የነበረ ሲሆን ጀርመኖችም የሶቪየትን ጦር በመሸሽ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ ነበር። በመግቢያው ላይ እንደ ተጠቀሰው ከመገደል ለጥቂት ያመለጥኩት በዚያን ጊዜ ነበር።

የገባሁትን ቃል ማክበር

በጦርነቱ ወቅት ወላጆቼ በጀርመን አገር ከላይፕሲግ ደቡብ ምሥራቅ ወደምትገኘው የኦሻትስ ከተማ ተዛውረው ነበር። ልክ ከጦርነቱ ማግሥት ወላጆቼ የት እንዳሉ ማወቅ አስቸጋሪ ነበር። ይሁንና በመጨረሻ ለመገናኘት በመቻላችን ምንኛ ተደሰትን! ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሚያዝያ 1947 ማክስ ሹቤርት የሚባል የይሖዋ ምሥክር የሚሰጠውን የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ ከእናቴ ጋር ንግግሩ ወደሚሰጥበት ቦታ ሄድኩ። እናቴ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘች ታምን የነበረ ሲሆን እኔም ጥቂት ስብሰባዎችን ከተካፈልኩ በኋላ እምነቷን ለመጋራት በቃሁ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቴ ከመሰላል በመውደቋ ምክንያት በደረሰባት ጉዳት ለጥቂት ወራት ከታመመች በኋላ ሞተች። ከመሞቷ በፊት ሆስፒታል እያለች እንደሚከተለው በማለት ሞቅ ባለ ስሜት አበረታታችኝ:- “ከልጆቼ መካከል ቢያንስ አንዱ እንኳ ወደ አምላክ የሚወስደውን መንገድ እንዲይዝ አዘውትሬ እጸልይ ነበር። አሁን ጸሎቴ መልስ ስላገኘ በሰላም ላንቀላፋ እችላለሁ።” እናቴ ከሞት ተነሥታ ጸሎቷ ሙሉ በሙሉ መፈጸሙን የምትመለከትበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ!​—⁠ዮሐንስ 5:​28

በነሐሴ 8, 1947 የወንድም ሹቤርትን ንግግር በሰማሁ ልክ በአራተኛው ወር ለይሖዋ አምላክ ራሴን በመወሰን በላይፕሲግ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። በመጨረሻ ለአምላክ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም የሚያስችሉኝን እርምጃዎች እየወሰድኩ ነበር። ወዲያውኑ አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወይም ምሥራቅ ጀርመን ተብሎ መጠራት በጀመረው አገር ውስጥ በወቅቱ ወደ 400 የሚጠጉ አቅኚዎች ነበሩ።

ብዙም ሳልቆይ የገጠሙኝ የእምነት ፈተናዎች

በኦሻትስ የሚኖር አንድ ጎረቤቴ የጀርመን ሶሻሊስት አንድነት ፓርቲ (ኤስ ኢ ዲ) አባል ከሆንኩ በመንግሥት ድጎማ የሚሰጥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ልከታተል እንደምችል በመንገር ስለ ማርክሲዝም ሊሰብከኝ ሞክሮ ነበር። ኢየሱስ የሰይጣንን ግብዣ እንዳልተቀበለ ሁሉ እኔም የቀረበልኝን ግብዣ አልተቀበልኩም።​—⁠ማቴዎስ 4:​8-10

ሚያዝያ 1949 አንድ ቀን ላይ ሁለት ፖሊሶች እምሠራበት ቦታ መጥተው አብሬያቸው እንድሄድ ጠየቁኝ። በአካባቢው ወደሚገኘው የሶቪየት የመረጃ ወኪል ከተወሰድኩ በኋላ በምዕራቡ ለሚገኙ ካፒታሊስቶች ትሰልላለህ የሚል ክስ ቀረበብኝ። ታማኝነቴን ማስመስከር የምችለው ከቤት ወደ ቤት መሥራቴን በመቀጠልና ስለ ሶቪየት ኅብረት ወይም ስለ ኤስ ኢ ዲ አፍራሽ የሆነ ነገር ስለሚናገር ሰው ወይም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ስለሚመጣ ስለ ማንኛውም ሰው ሪፖርት በማድረግ መሆኑን ነገሩኝ። ይህን እንደማላደርግ ስገልጽ እስር ቤት ከተቱኝ። በኋላም ወደ አንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ወሰዱኝ። ለ15 ዓመታት በሳይቤሪያ ከባድ ሥራ እንድሠራ ተፈረደብኝ!

ምንም የስሜት መረበሽ ሳይታይብኝ በመቅረቱ መኮንኖቹ ተገረሙ። ከዚያም የተፈረደብኝ ፍርድ የሚጸና ሲሆን ከእነሱ ጋር ለመተባበር ዝግጁ እስከምሆን ድረስ ግን በሳምንት አንድ ጊዜ እየመጣሁ ሪፖርት እንዳደርግ ነገሩኝ። ከጎለመሱ ወንድሞች ምክር ለማግኘት ስል በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ይገኝበት ወደነበረው ወደ ማግደቡርግ ሄድኩ። ይከታተሉኝ ስለነበር ጉዞው ቀላል አልነበረም። ማግደቡርግ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በሕግ ክፍል ውስጥ የሚያገለግለው ኧርንስት ቮ እንዲህ አለኝ:- “በትግልህ ግፋበት ታሸንፋለህ። አቋምህን ብታላላ ትሸነፋለህ። በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያገኘነው ትምህርት ይህ ነው።”a ይህ ምክር አምላክን ለማገልገል የገባሁትን ቃል እንድጠብቅ ረድቶኛል።

እገዳና በድጋሚ መታሰር

በሐምሌ 1950 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ታስቦ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ነሐሴ 30 ላይ ፖሊስ በማግደቡርግ የሚገኘውን ይዞታችንን ቀማ፤ የስብከት ሥራችንም ታገደ። ስለዚህ የሥራ ምድቤ ተቀየረ። ፖል ሂርሽቤርገ እና እኔ 50 በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች በእገዳው ሥር አገልግሎታቸውን በተደራጀ ሁኔታ ለመቀጠል እንዲችሉ በመርዳት ከእያንዳንዱ ጉባኤ ጋር ሁለት ወይም ሦስት ቀናት እንቆይ ነበር። በቀጣዮቹ ወራት ስድስት ጊዜ በፖሊስ ከመታሰር አመለጥኩ!

በአንድ ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ሰው ሽታዚ ለሚባሉት የመንግሥት የጸጥታ ሠራተኞች አሳልፎ ሰጠን። ይህም በመሆኑ በሐምሌ 1951 ፖልና እኔ በመንገድ ላይ እንዳለን ጠመንጃቸውን በደገኑ አምስት ሰዎች ተይዘን ታሰርን። መለስ ብለን ስናስበው እንደሚገባን ያህል በይሖዋ ድርጅት ላይ ትምክህታችንን እንዳልጣልን ለመገንዘብ ችለናል። በእድሜ የገፉ ወንድሞቻችን ለየብቻ እንድንጓዝ መክረውን ነበር። ከመጠን በላይ በራስ መተማመን ነፃነታችንን አሳጥቶናል! ከዚህም በላይ በምንታሰርበት ጊዜ ምን እንደምንል አስቀድመን አልተወያየንም ነበር።

በታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ሆኜ ወንድሞቼን አሳልፌ እንዳልሰጥ ወይም እምነቴን እንዳልክድ እንዲረዳኝ ይሖዋን እያለቀስኩ ለመንኩት። ተኝቼ እያለሁ የጓደኛዬ የፖል ድምፅ በድንገት ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። በሽታዚ የምርመራ ጥያቄ ይቀርብለት የነበረው እኔ ከታሰርኩበት ክፍል በላይ ነበር። ምሽቱ ስለሚሞቅና ስለሚወብቅ የባልኮኒው በር ተከፍቶ ስለነበር የሚነጋገሩት ነገር ትንሽ ትንሽ ይሰማኝ ነበር። በኋላ ላይ እኔም የምርመራ ጥያቄ ሲቀርብልኝ ተመሳሳይ የሆኑ መልሶች ሰጠሁ፤ በዚህም ኃላፊዎቹ ተገረሙ። እናቴ ትወደው የነበረው “በመከራ ቀን ጥራኝ፣ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደጋግሞ ወደ አእምሮዬ ይመጣ የነበረ ሲሆን ከፍተኛም ብርታት ሰጥቶኛል።​—⁠መዝሙር 50:​15

የምርመራ ጥያቄ ከቀረበልን በኋላ ፖልና እኔ ለፍርድ ከመቅረባችን በፊት በሃል ከጊዜ በኋላ ደግሞ በማግደቡርግ በሚገኘው የሽታዚ እስር ቤት ውስጥ ለአምስት ወራት ታሰርን። በማግደቡርግ እያለን በወቅቱ ተዘግተው የነበሩትን የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎቻችንን አንዳንድ ጊዜ ከሩቁ አያቸው ነበር። በእስር ቤት ከመሆን ይልቅ በዚያ ሆኜ ለመሥራት እመኝ ነበር! የካቲት 1952 ላይ “የ10 ዓመት እስራትና የ20 ዓመት የዜግነት መብት ማጣት” እንደተፈረደብን ተነገረን።

በእስር ቤት ውስጥ በእምነት መጽናት

ቢያንስ ለአሥር ዓመት እንዲታሰሩ የተፈረደባቸው የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ልዩ የሆነ ምልክት ያደርጉ ነበር። በሱሪያችን አንደኛው እግር ላይ እና በጃኬታችን አንደኛው ክንድ ላይ ቀይ ሪባን ይሰፋ ነበር። በተጨማሪም በክፍላችን በር በውጪ በኩል ትንሽ፣ ቀይ ክብ ካርድ ይለጠፍ የነበረ ሲሆን ይህም አደገኛ ወንጀለኞች መሆናችንን ለጠባቂዎቹ የሚያሳውቅ ነበር።

በእርግጥም ባለ ሥልጣናቱ በጣም አደገኛ ወንጀለኞች አድርገው ያዩን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይኖረን ተከልክለን ነበር፤ ምክንያቱም አንድ ጠባቂ እንዳለው “መጽሐፍ ቅዱስ የያዘ የይሖዋ ምሥክር ጠመንጃ ከያዘ ወንጀለኛ ጋር አንድ ነው።” የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ ስንል ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ይጠቅስ የነበረውን የሩሲያዊውን ጸሐፊ የሊዎ ቶልስቶይን መጽሐፎች እናነብ ነበር። እነዚህን ጥቅሶች በቃላችን አጥንተናቸው ነበር።

በ1951 ከመታሰሬ በፊት ከኤልዛ ሪመ ጋር ተጫጭተን ነበር። አዘውትራ እስር ቤት በመምጣት ትጠይቀኝ የነበረ ሲሆን በወር አንዴ ደግሞ ስንቅ ትልክልኝ ነበር። በተጨማሪም በስንቁ ውስጥ መንፈሳዊ ምግብ ሸሽጋ ትልክልኝ ነበር። አንድ ጊዜ ጥቂት የመጠበቂያ ግንብ ገጾች በቋሊማ ውስጥ ከትታ ላከችልኝ። አብዛኛውን ጊዜ ጠባቂዎቹ በቋሊማው ውስጥ የተደበቀ ነገር እንዳለ ለመፈተሽ ሲሉ ቋሊማውን ቆርጠው ይመለከቱት ነበር፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ ስንቁ የደረሰው የሥራ ቀኑ ሊጠናቀቅ ትንሽ ሲቀረው ስለነበረ ቋሊማው ሳይፈተሽ አለፈ።

በወቅቱ ካርል ሃይንትስ ክሌበና እኔ ምሥክሮች ካልሆኑ ሌሎች ሦስት እስረኞች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ነበርን። ታዲያ ያንን መጠበቂያ ግንብ ማንም ሳያየን ማንበብ የምንችለው እንዴት ነበር? አንድ መጽሐፍ የምናነብ አስመስለን በውስጡ ግን የመጠበቂያ ግንብ እትሞቹን ከተን እናነብ ነበር። ይህን ውድ መንፈሳዊ ምግብ ደግሞ በእስር ቤቱ ውስጥ ለነበሩ ሌሎች መሰል ምሥክሮች እናስተላልፍ ነበር።

በእስር ቤት በነበርንበት ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች ለመንገር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ተጠቅመንባቸዋል። በዚህ ምክንያት አብረውኝ ከታሰሩት ውስጥ አንዱ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ለመመልከት በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ

ወደ ስድስት ለሚጠጉ ዓመታት በእስር ካሳለፍኩ በኋላ ሚያዝያ 1, 1957 ላይ ተለቀቅሁ። ከሁለት ሳምንታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከኤልዛ ጋር ተጋባን። ሽታዚ ከእስር መለቀቄን ሲሰሙ ተመልሼ እንድታሰር ለማድረግ ሰበብ አስባብ መፈላለግ ጀመሩ። ከዚህ ለመሸሽ ስል ከኤልዛ ጋር ድንበር አቋርጠን ወደ ምዕራብ በርሊን ሄድን።

ምዕራብ በርሊን ስንደርስ ማኅበሩ እቅዳችን ምን እንደሆነ ጠየቀን። አንዳችን አቅኚ ሆነን ለማገልገል አንዳችን ደግሞ ሥራ ለመሥራት እንዳሰብን ገለጽን።

“ሁለታችሁም አቅኚ ሆናችሁ ብታገለግሉ ምን ይመስላችኋል?” ተብለን ተጠየቅን።

“የሚቻል ከሆነማ አሁኑኑ እንጀምራለን” ስንል መለስን።

በመሆኑም በየወሩ ራሳችንን ለመደገፍ የሚያስችል የተወሰነ ገንዘብ ተቆራጭ ተደርጎልን በ1958 ልዩ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። መጽሐፍ ቅዱስን እናስጠናቸው የነበሩ ግለሰቦች ሕይወታቸውን ለውጠው የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ መመልከት እጅግ ያስደስተን ነበር! በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የልዩ አቅኚነት አገልግሎት ባልና ሚስት እንደመሆናችን መጠን ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቦናል። ኤልዛ መኪናችንን ስጠግን እንኳን ሳይቀር ከጎኔ አትጠፋም ነበር። በተጨማሪም አንድ ላይ ሆነን እናነብ፣ እናጠናና እንጸልይ ነበር።

በ1969 የተጓዥነት ሥራ እንድንሠራ የተመደብን ሲሆን በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን እየጎበኘን ለአባላቱ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እናደርግ ነበር። በተጓዥነት ሥራ ተሞክሮ ያለው ዮዜፍ ባርት “በምድብ ሥራህ ላይ ስኬታማ ለመሆን ከፈለግህ ወንድሞችን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ቅረባቸው” የሚል ምክር ለገሰኝ። ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሬአለሁ። በዚህ ምክንያት ከመሰል ምሥክሮች ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ግንኙነት የነበረን ሲሆን ይህ ደግሞ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በቀላሉ ምክር እንድንሰጣቸው አስችሎናል።

በ1972 ኤልዛ ሐኪም ቤት ተመርምራ ካንሰር እንዳለባት ስለተነገራት ቀዶ ሕክምና አደረገች። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የቁርጥማት በሽታ ያዛት። ሕመሙ ቢያሰቃያትም በየሳምንቱ አብራኝ በመሆን ጉባኤዎችን ማገልገሏንና ከእህቶች ጋር በአገልግሎት በመሰማራት የምትችለውን ሁሉ ማድረጓን አላቋረጠችም።

አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች ማድረግ

በ1984 አማቶቼ ያልተቋረጠ እንክብካቤ ስላስፈለጋቸው የተጓዥነት ሥራችንን አቁመን ከአራት ዓመታት በኋላ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ እንክብካቤ ስናደርግላቸው ቆየን። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ከዚያም በ1989 ኤልዛ በጠና ታመመች። በመጠኑም ቢሆን ስለ ተሻላት ደስ ቢለኝም የቤት ውስጥ ሥራዎችን በሙሉ የምሠራው እኔ ነኝ። የማያቋርጥ የሕመም ስሜት የሚሰማውን ሰው እንዴት በእንክብካቤ መያዝ እንዳለብኝ አሁንም እየተማርኩ ነው። ውጥረትና ጭንቀት ቢኖርብንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር አልቀነሰም።

ደስ የሚለው ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአቅኚነት በማገልገል ላይ እንገኛለን። ይሁንና አስፈላጊ የሆነው ነገር ያለን የኃላፊነት ቦታ ወይም ለማከናወን የቻልነው መጠን ሳይሆን የታመንን ሆነን መቆየታችን መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል። አምላካችንን ይሖዋን ለማገልገል የምንፈልገው ለጥቂት ዓመታት ሳይሆን ለዘላለም ነው። ያሳለፍነው ተሞክሮ ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን ግሩም ስልጠና ሰጥቶናል። ይሖዋም እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እሱን እንድናወድሰው የሚያስችለንን ጥንካሬ ሰጥቶናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የኧርንስት ቮ የሕይወት ተሞክሮ በነሐሴ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25 እስከ 29 ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ በማግደቡርግ ታስሬ ነበር

[ምንጭ]

Gedenkstätte Moritzplatz Magdeburg für die Opfer politischer Gewalt; ፎቶ:- Fredi Fröschki, Magdeburg

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1957 ስንጋባ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከኤልዛ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ