ጳውሎስና ፕላቶ ስለ ትንሣኤ የነበራቸው አመለካከት
ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:35-58 እና በ2 ቆሮንቶስ 5:1-10 ላይ ስለ ትንሣኤ ጽፎአል። ይህን በሚመለከት የተከተለው የግሪክ ፈላስፋ የነበረውን የፕላቶን ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት ነው ወይስ ኢየሱስና የተቀሩት ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያስተምሩትን ሐሳብ?
ኢሞርታሊቲ ኦቭ ዘ ሶል ኦር ሪዘሬክሽን ኦቭ ዘ ኢንዲቪጁዋል፦ ሴንት ፖልስ ቪው ዊዝ ስፔሻል ሪፈረንስ ቱ ፕላቶ (የማትሞት ነፍስ ወይም የግለሰብ ትንሣኤ፦ የቅዱስ ጳውሎስ አመለካከት ከፕላቶ ጋር ሲወዳደር) የሚለው በ1974 ላይ ታትሞ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሊቀ ጳጳሳት ድጋፍ ያገኘው ይህ መጽሐፍ ግልጽ የሆነ መልስ ይሰጣል። ከላይ በተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተገለጸውንና በጊዜው በነበረው የግሪካውያን ፍልስፍና ላይ የተመሠረተውን የትንሣኤ ባሕርይ ካብራሩ በኋላ ደራሲው በሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
“ፕላቶ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ከዘላለም እስከ ዘላለም ፍጻሜ ለሌለው ዘመን ትኖራለች ሲል አስተምሮአል። ፕላቶ እንደሚለው ነፍስ የዘላለማዊነትና ያለመሞት ባሕርይ አላት። . . . ቅዱስ ጳውሎስ ግን ይህን የመሰለ ትምህርት አላስተማረም ወይም አስተምሬአለሁ አላለም . . . ብለዋል።
“ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ነፍስ ወይም ስለ መንፈስ ዘላለማዊነት ከሥጋ የተለየ ሕልውና ያላት ስለመሆኗ የገለጸው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ትንሳኤ ምክንያት መላው ነፍስ፣ መንፈስና ሥጋ ተዋህዶት እንደሚነሳ ገልፆአል። ጳውሎስ ስለሰው ትንሳዔ የነበረው ግንዛቤ በመቃብር ውስጥ ያለ አስከሬን ትንፋሽ ገብቶበት ይነሳል ከሚለው እምነት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም።
“ጳውሎስ ስለ ሰው ትንሳኤ የነበረው ግንዛቤ መለወጥ፣ ዳግም መፈጠር በአምላክ ኃይል ወደ ሕልውና መመለስ ተብሎ ቢገለጽ የተሻለ ይሆናል። መላው ሰው ከነሙሉ ስብዕናው፣ ከነሙሉ ባሕርዩ፣ ከነሙሉ አእምሮአዊና ሥጋዊ አካሉ ይነሳል። ወደፊት የምናገኘው ትንሳኤ የሚፈጸመው በተፈጥሮ ባሕርያችን ወይም ችሎታችን ምክንያት ሳይሆን የአምላክ ንጉሣዊ ሥጦታ ስለሆነ ነው።”
አዎ፣ ከሞቱ በኋላ ሕያው ሆኖ መኖር የማንም ሰው የተፈጥሮ ባሕርይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለቅቡዓን የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች የሚሰጥ ክቡር የሆነ የይሖዋ ሥጦታ ነው—1 ቆሮንቶስ 15:20, 57፤ ፊልጵስዩስ 3:14
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግሪክ ፈላስፋ የነበረው ፕላቶ
[ምንጭ]
Vatican Museum photograph