የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 6/15 ገጽ 4-7
  • ብዙዎችን ለማዳን የተከፈለ ቤዛ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብዙዎችን ለማዳን የተከፈለ ቤዛ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መሸፈንና ነፃ ማውጣት
  • ተመጣጣኝ ቤዛ
  • አንድ ሰው ለብዙ ሰዎች ሊሞት የሚችለው እንዴት ነው?
  • የቤዛው ዝግጅትና አንተ
  • ለሁሉ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 6/15 ገጽ 4-7

ብዙዎችን ለማዳን የተከፈለ ቤዛ

መጋቢት 31, 1970 በጃፓን አገር በፉጂ ተራራ አጠገብ አንድ አውሮፕላን ተጠለፈ። የጃፓን ቀይ ሠራዊት ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባሎች የሆኑ ዘጠኝ ሰዎች በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩትን ከ120 በላይ የሚሆኑ ተሳፋሪዎችና የአይሮፕላን ሠራተኞች በምርኮኛነት ከያዙ በኋላ ወደ ሰሜን ኮሪያ ለመጓዝ እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ።

አውሮፕላኑ የኮሪያ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በሴኡል ከተማ ሲያርፍ የጃፓን ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት ሺንጂሮ ያማሙራ ለተጠላፊዎቹ ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣል ፈቃደኛ ሆኑ። ጠላፊዎቹ ሚኒስትሩን ለደህንነታቸው ዋስትና እንዲሆኑአቸው በመያዝ ከበረራ ሠራተኞች በስተቀር ሁሉንም ተጠላፊዎች ለቀቁ። ከዚያ በኋላ ወደ ፒዮንግያንግ በረሩና እጃቸውን ለሰሜን ኮሪያ ባለ ሥልጣኖች ሰጡ። ሚስተር ያማሙራና የአውሮፕላኑ አብራሪ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ጃፓን ተመለሱ።

በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከ120 በላይ ለሆኑ ተጠላፊዎች ልዋጭ ሆኖአል። ይህ ታሪክ አንድ ሰው እንዴት ለብዙ ሰዎች ራሱን ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ እንደሚችል ለመገንዘብ ሊረዳን ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤዛ የሚያስተምረውን ትምህርት በሚገባ እንድንረዳ ይህንን ትምህርት ጠለቅ ብለን መመርመር ይኖርብናል።

በመጀመሪያ ስለ ኃጢአት አመጣጥ በዝርዝር ማጥናት ያስፈልገናል። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሮሜ 5:12) ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሰው የመጀመሪያ ሰብአዊ ፍጡር የሆነው አዳም ነው። ስለ አዳም አፈጣጠርና ከአምላክ የጽድቅ ደረጃ ስላፈነገጠበት ሁኔታ የሚተርከውን ታሪካዊ መግለጫ ለማንበብ ትችላለህ። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች ሰፍሮ ይገኛል።

የዘፍጥረት ታሪክ አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ ከጀርባው ሆኖ በስውር የሚሠራ አንድ አሳሳች ኃይል እንደነበር ይገልጻል። ይህ አሳሳች ሥልጣን ለማግኘት የነበረውን ምኞት ለማርካት በአዳምና አዳም በሚወልዳቸው ልጆች ሁሉ ላይ ለመሠልጠን የሚያስችለውን ሤራ ጠነሰሰ። ይህ አሳሳች ሰይጣን ዲያብሎስ ነበር። አዳምን ለማሳሳት በእባብ ስለተጠቀመ “የቀደመው እባብ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:9) የሰው ልጆች አፍቃሪ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር የመወሰን መብቱን አዳም እንዲያከብርለት የነገረው ቢሆንም እባቡ የአዳምን ሚስት ሔዋንን አሳስቶ የአምላክን ትዕዛዝ እንድታፈርስ አደረገ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ባልዋ እንዲያምፅ ገፋፋችው። አዳም በዚህ በፈጸመው ድርጊት ራሱን ከአምላክ ለይቶ ነፃ አድርጎአል። ሆን ብሎ ኃጢአት ሠራ። ለልጆቹ ሊያወርስ የሚችለውም ይህን ዓይነቱን የኃጢአተኛነት ሕይወት ብቻ ነው።

እስከ ዛሬ ድረስ የዚህ ኃጢአት መዘዝ አለቀቀንም። እንዴት? ፈጣሪ አዳምና ሔዋን ሆን ብለው ያለመታዘዝን መንገድ ከመረጡ ውጤቱ ሞት እንደሚሆን ደንግጎ ነበር። ስለዚህ አዳም ኃጢአት በመሥራቱ የሰው ዘሮችን በሙሉ ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ሸጦአል።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-7

ታዲያ የሰው ልጅ ከዚህ ኃጢአት እንዴት ሊድን ይችላል? ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር በመምጣት “ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ በመስጠት” የሰው ልጆች የሚድኑበትን መንገድ ከፈተ።—ማቴዎስ 20:28

መሸፈንና ነፃ ማውጣት

የሰው ልጆች ደህንነት እንዲያገኙ ሁለት እርምጃዎች ማስፈለጋቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። (1) መልሶ መግዛትና (2) ነፃ ማውጣት። “ቤዛ” ተብሎ ስለተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ሊትሮን) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልበርት ባርነዝ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። “ቤዛ የሚለው ቃል ቃል በቃል ሲተረጎም አንድን ምርኮኛ ለማስለቀቅ የተከፈለ ዋጋ ማለት ነው። በጦርነት ጊዜ ወታደሮች በጠላት ተማርከው ሲወሰዱ ምርኮኞቹን ለማስፈታት የሚጠየቀው ዋጋ ቤዛ ተብሎ ይጠራል። ነፃ እንዲወጡ የሚያስችላቸው መንገድ ቤዛ ይባላል። ስለዚህ ማንኛውንም ሰው ከቅጣት፣ ከስቃይ፣ ወይም ከኃጢአት ነፃ የሚያስወጣው ነገር ሁሉ ቤዛ ተብሎ ይጠራል።”

አዎ፣ “ማንኛውንም ሰው ነፃ የሚያስወጣ ነገር” ሊትሮን ተብሎ ይጠራል። ስለዚህ ይህ የግሪክኛ ቃል ነፃ የማስወጣትን ድርጊት ወይም እርምጃን ያመለክታል።a

ሐዋርያው ጳውሎስ የተከፈለው ቤዛ የሚኖረውን ዋጋ ለማጉላት ከሊትሮን ጋር የሚዛመደውን አንቲሊትሮን የተባለ ቃል ተጠቅሞአል። በ1 ጢሞቴዎስ 2:6 ላይ “[ኢየሱስ] ራሱን ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ ለሁሉ ሰጠ” (አዓት) ይላል። የፓርክረስት የግሪክኛና የእንግሊዝኛ የአዲስ ኪዳን የቃላት መፍቻ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮኞች ከጠላቶች እጅ የሚቤዡበትንና የአንድ ሰው ሕይወት ለሌላው ሕይወት ልዋጭ ሆኖ የሚዋጅበትን ዋጋ ያመለክታል።” ቃሉ ትኩረት የሚያደርገው ቤዛው “የፍትሕ ሚዛን” የሚጠይቀውን ዋጋ ለማሟላት “ተመጣጣኝ” ወይም ችሎታ ያለው በመሆኑ ላይ ነው። ታዲያ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተመጣጣኝ ነበር ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

ተመጣጣኝ ቤዛ

አዳም የሰው ዘሮችን በሙሉ፣ እኛንም ጭምር ለኃጢአትና ለሞት ሸጦናል። አዳም የከፈለው ዋጋ ወይም ቅጣት ለዘላለም የመኖር ችሎታ የነበረውን ፍጹሙን ሰብዓዊ ሕይወቱን ነው። ይህን ለመሸፈን ተመጣጣኝ የሆነ ቤዛ፣ ማለትም ሌላ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት መከፈል ነበረበት። ይሁን እንጂ ፍጹም ካልሆኑ የሰው ዘሮች የተወለደ ማንኛውም ሰው ተፈላጊውን ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ሊከፍል አልቻለም። (ኢዮብ 14:4፤ መዝሙር 51:5) ይሁን እንጂ አምላክ በጥበቡ ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት የሚያስችለውን መንገድ አዘጋጀ። የአንድያ ልጁን ፍጹም ሕይወት ከሰማያት ወደ ድንግል ማርያም ማህፀን አዛወረና ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። (ሉቃስ 1:30-38፤ ዮሐንስ 3:16-18) ይህ ኢየሱስ ከድንግል ስለመወለዱ የሚገልጸው የአንድን ሃይማኖት መሪ ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተፈለሰፈ ታሪክ አይደለም። አምላክ ቤዛ ለማዘጋጀት የወሰደውን ምክንያታዊ እርምጃ የሚገልጽ ነው።

ኢየሱስ የመቤዠት ተግባሩን ለመፈጸም በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በንጽሕና መመላለስ ነበረበት። ይህንንም በሚገባ ፈጽሞአል። ከዚያም በኋላ መስዋዕታዊ ሞት ሞተ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሰው ዘሮችን ለማዳን ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ከፈለ። (1 ጴጥሮስ 1:19) በዚህም ምክንያት ‘አንድ ሰው ለብዙዎች ሞተ ለማለት እንችላለን።’ (2 ቆሮንቶስ 5:14) አዎ፣ “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ።”—1 ቆሮንቶስ 15:22

አንድ ሰው ለብዙ ሰዎች ሊሞት የሚችለው እንዴት ነው?

ቀደም ብሎ በተጠቀሰው የአውሮፕላኑ ጠለፋ ታሪክ ላይ ተጠላፊዎቹ ምንም ያህል ሀብት ቢኖራቸው ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የሚችሉበት መንገድ አልነበራቸውም። ግዴታ የውጪ እርዳታ አስፈልጎአቸው ነበር። በተጨማሪም ስለ እነርሱ የተያዘው ሰው አንዳንድ ሁኔታዎችን ማሟላት ነበረበት። የሰው ልጆችን ለመቤዠት በተከፈለው ቤዛ ረገድም ከዚህ በጣም በጠለቀ ሁኔታ ይሁን እንጂ ተመሳሳይ ነገር አስፈልጎአል። መዝሙራዊው “በሀብታቸው ብዛት የሚተማመኑ . . . ሰው ራሱን መቤዠትም ሆነ ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር መክፈል አይችልም። ለሰው ሕይወት የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ብዙ ነው። የቱንም ያህል ቢከፈል በቂ አይሆንም” ብሎአል። (መዝሙር 49:6-8 የ1980 ትርጉም) በእርግጥም የሰው ልጆች አንድ ውጪያዊ እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። የአምላክ የፍትሕ ሚዛን የሚጠይቀውን ሁሉ የሚያሟላ ከሆነ የሰው ልጆችን ሁሉ ለመቤዠት የአንድ ሰው ሕይወት በቂ ሊሆን ይችላል። ይህንን ብቃት ሊያሟላ የቻለው ፍጹም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በከፈለው ቤዛ አማካኝነት የሰው ልጅ ደህንነት የሚያገኝበትን መንግድ አዘጋጅቶአል። ይሁን እንጂ አምላክ በዚህ ብቻ አልተወሰነም። የሰው ዘሮችን ወደ ኃጢአት በመራው በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ የሞት ቅጣት በይኗል። (ራእይ 12:7-9) ይሖዋ በቅርቡ ይህን ወንጀለኛ ካሠረው በኋላ በመጨረሻም የዘላለም ጥፋት ምሳሌ በሆነው ‘በእሳትና ድኝ ባሕር ውስጥ ጥሎ’ የመጨረሻ ፍርዱን ይፈጽምበታል። (ራእይ 20:1-3, 7-10, 14) ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረት ሲወገድና የቤዛው ጥቅም ለሰው ልጆች ሁሉ ሲዳረስ የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት መዳፍ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ተጽእኖ ጭምር ይገላገላል። በዚህ መንገድ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ነፃነት አግኝተውና የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ ተጠቃሚዎች ሆነው ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ይደርሳሉ።

የቤዛው ዝግጅትና አንተ

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መስዋዕት ያወቁ ብዙ የሩቅ ምሥራቅ አገር ሰዎች አምላክ ላደረገላቸው ዝግጅት ከፍተኛ አድናቆት ተሰምቶአቸዋል። በዚህ ረገድ ካዙኦ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ሕይወቱ በጠቅላላ የቀለም መበጥበጫ ኬሚካል አሽትቶ በመስከር የተያዘ ነበር። ሰክሮ በሚነዳበት ወቅት በተደጋጋሚ በመኪናው ላይ የግጭት አደጋ አድርሶአል። ከጓደኞቹ መካከል ሦስቱ ጤንነታቸውን ካበላሹ በኋላ ራሳቸውን በራሳቸው ገድለዋል። ካዙኦም ራሱን ለመግደል ሙከራ አድርጎ ነበር። በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በተማራቸው ነገሮች ልቡ በመነካቱ ሕይወቱን ለማንጻት ወሰነ። የቀለም መበጥበጫ የማሽተት ሱሱን ለማሸነፍ ብዙ ትግል አስፈለገው። ልቡ የሥጋውን ፍላጎት በመፈጸምና ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ መካከል ለሁለት ተከፈለበት። አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ እንዲያደርግለት ለመጸለይ በመቻሉ ምን ያህል ደስ እንደተሰኘ መገመት ይቻላል። ካዙኦ በጸሎትና ከክርስቲያን ጓደኞቹ ባገኘው እርዳታ አማካይነት መጥፎ ልማዱን አሸንፎ አሁን በንጹሕ ሕሊና ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛል።

ባለፈው ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሰችውን ቺሳኮን ታስታውሳላችሁን? መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ስለ ቤዛው ፍቅራዊ ዝግጅት ለመረዳት ችላለች። አምላክ የሰው ዘሮችን ከኃጢአት ለማዳን ሲል አንድያ ልጁን እንደሰጠ ስትረዳ ልብዋ በጣም ተነካ። ቺሳኮ ራሷን ለይሖዋ ወሰነች። በአሁኑ ጊዜ 77 ዓመት አሮጊት ብትሆንም በየወሩ 90 ሰዓት ለሚያህል ጊዜ ለሰዎች ስለ ይሖዋ ታላቅ ፍቅርና የማይገባ ቸርነት ትናገራለች።

ለአንተም ቢሆን ቤዛው ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል። በቤዛው አማካይነት አምላክ የሰው ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚሆኑበትን የእውነተኛ ነፃነት መንገድ ይከፍታል። የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መስዋዕትነት የሚቀበሉ ሁሉ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ታላቅ ተስፋ ይጠብቃቸዋል። አንተም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተህ እንዴት በፍቅራዊው የቤዛ ዝግጅት አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ልትሆን እንደምትችል መርምር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ፓድሃ እና ከዚህ ቃል ጋር ዝምድና ያላቸው ቃላት “መቤዠት” ወይም “የቤዛ ዋጋ” ተብለው ተተርጉመዋል። ይህም ነፃ የማውጣት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አጉልቶ ያመለክታል።—ዘዳግም 9:26

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Courtesy of the Mainichi Shimbun

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ