የሰው ልጅ ከኃጢአት ቀንበር የሚላቀቅበት መንገድ ይኖራልን?
ቺሳኮ ከአራት ወጣት ልጆችዋ ጋር ሆና ከመኖሪያ ቤቷ 600 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ አንድ ከተማ የሕዝብ መፀዳጃ ቤት ታጸዳ ነበር። ሥራዋን በምትሠራበት ጊዜ ትርጉሙን የማታውቀውን ስለ ቡድሂስቶች እምነት የሚተርክ ዜማ ታዜማለች። ሁሉም ሃይማኖቶች ያላቸውን ማዕከላዊ ባሕርይ ለመረዳት የሚፈልግ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አባሎች ከሚፈጽሙአቸው ሃይማኖታዊ ልማዶች አንዱ ይህን ዜማ ማዜም ነው።
“ራሴን አዘውትሬ በጾምና በጸሎት ባስጨንቅም ባሕርዬን መለወጥ አልቻልኩም። ሌሎች ሰዎችን ከልቤ ይቅር ለማለትም ሆነ በቀና መንፈስ ተነሳስቼ ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት አልቻልኩም” በማለት ቺሳኮ ታስታውሳለች።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት የሚያስተምረው ትምህርት በማይታወቅባቸው የሩቅ ምሥራቅ አገሮች እንኳን ብዙ ሰዎች ልክ እንደ ቺሳኮ የኃጢአት ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑ ሕሊናቸው ይወቅሳቸዋል። (ሮሜ 2:14, 15) በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ለሚገኝ ሰው ርኅራኄ ሳያሳይ በመቅረቱ ወይም መባል የማይገባው ነገር በመናገሩ በጣም አዝኖና ተጸጽቶ የማያውቅ ሰው ይኖራልን? (ያዕቆብ 4:17) አስቀያሚ የሆነው የምቀኝነት ባሕርይ በወጣቶችም ሆነ በሽማግሌዎች ላይ የሚታይ አይደለምን?
ታዲያ ሰዎች እንደነዚህ ባሉት ባሕርያት የሚረበሹት ለምንድን ነው? ቢረዱትም ባይረዱትም ውስጣዊ የሆነ የበደለኛነት ወይም የኃጢአተኛነት ስሜት ስላላቸው ነው። በእርግጥም ሰዎች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት የሚናገረውን አወቁም አላወቁ በኃጢአተኛነት ዝንባሌ ተነክተዋል። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የተመራመረ አንድ ሰው “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ብሎአል።—ሮሜ 3:23
ኃጢአት ሊሻር ይችላልን?
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በተለይም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ የኃጢአተኛነትና የበደለኛነት ስሜታቸውን ከሕሊናቸው ለመፋቅ ሲሞክሩ ይታያሉ። ዶክተር መኒንገር ዎትኤቨር ቢኬም ኦቭ ሲን (ኃጢአት ምን ደረሰበት?) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “‘ኃጢአት’ የሚለው ቃል . . . ፈጽሞ ጠፍቶአል ለማለት ይቻላል” ብለዋል። ይሁን እንጂ አንድ ያረጀ ሰው “እርጅና” የሚለውን ቃል ማስወገዱ እርጅናውን ሊያቆምለት እንደማይችል ሁሉ “ኃጢአት” የሚለውን ቃል ማስወገድም ቢሆን ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። የኃጢአት ዝንባሌ ያለን ከመሆናችን ሐቅ ልንሸሽ አንችልም። ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታም የሚያድነን ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ ማን ያድነናል?
ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እየፈለገ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ የሚያስቸግረው መሆኑን ካመነ በኋላ “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” ሲል ጠይቆአል። ጳውሎስ ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ፦ “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” አለ። ጳውሎስ ለምን እንደዚህ አለ? አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መስዋዕት አማካኝነት የኃጢአት ስርየት ስላዘጋጀ ነው።—ሮሜ 7:14-25
ይሁን እንጂ 3,500,000,000 ከሚሆኑት (ቁጥራቸው ክርስቲያን ነን ከሚሉት በእጥፍ ይበልጣል) ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ስለ ቤዛ መረዳት በጣም ያዳግታቸዋል። ለምሳሌ ያህል በጃፓን ውስጥ ለሚኖር እና ለጥቂት ጊዜ ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ላጠና አንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው ትልቅ እንቅፋት የሆነበት የቤዛ መሠረተ ትምህርት ነበር። በሩቅ ምስራቅ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አንድ ሰው ለሁሉም ሊሞት ይችላል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እንግዳ ነገር ይሆንባቸዋል።
ይህ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ምክንያቱም በክርስትና ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች እንኳን ይህንን መሠረታዊ ትምህርት መረዳት ያስቸግራቸዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ “ስለ ስርየት ግልጽ የሆነ ትምህርት መስጠት አልተቻለም። በአንዳንድ ክፍሎችም ትልቅ የሃይማኖታዊ ትምህርት ችግር ፈጥሮአል” ይላል።
በዚህ ትምህርት ላይ የተፈጠረው ግራ መጋባት ምን ያህል የሰፋ መሆኑን ሃይማኖታዊ ጸሐፊ የሆኑት ኤን ኤች ባርቡር ከጻፉአቸው ቃላት መረዳት ይቻላል፦ “አንድ ምድራዊ ወላጅ አንድን ዝንብ በመርፌ እየወጉ አሰቃይቶ መግደል ልጁ ለፈጸመው መጥፎ ድርጊት ማካካሻ ይሆናል ብሎ እንደማያስብ ሁሉ የክርስቶስም ሞት ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት የመጣውን ፍርድ ሊሽር አይችልም” ብሏል። ከባርቡር ጋር አብሮ ይሠራ የነበረው ቻርለስ ቲ ራስል በቤዛ ትምህርት ላይ የተነሳውን ተቃውሞ መከላከል አጣዳፊና በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘበ። ራሱን ከባርቡር ለየና በ1978 አዲስ መጽሔት አዘጋጅቶ ማውጣት ጀመረ። ይህም መጽሔት ይህ አሁን አንተ የምታነበው መጽሔት ነው። መጠበቂያ ግንብ መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የክርስቶስ ቤዛዊ መስዋዕት ጽኑ ጠበቃ ሆኖ ቆይቶአል።
ይሁን እንጂ ይህ ትምህርት “ክርስቲያን” ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላልን? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት አንድ ሰው ለሰው ልጅ በሙሉ ስለመሞቱ የሚገልጸውን ይህን ትምህርት ቀረብ ብለን እንመርምር።